>
5:16 pm - Friday May 23, 6769

ካልሞትክ አይገሉህም!!! ( ዳንኤል ክብረት)

ካልሞትክ አይገሉህም!!!
  ዳንኤል ክብረት
አንድ ገስግስ የሚባል ፈረስ የነበረው ሰው ነበር፡፡ ሰውዬው ይህንን ፈረስ ለብዙ አመታት ሲገለገልበት ኖሯል፡፡ በብዙ ቦታዎች ብዙ አስደናቂ ነገሮችን አብረው አይተዋል፤ ሰርተዋልም፡፡ በብዙ አውደ ውጊያዎች ውለዋል፡፡ አያሌ ውድድሮችን አሸንፈዋል፡፡ ከልጆቹ እኩል ይወደው ነበር፡፡ እንደ ራሱ አድርጎም ይጠነቀቅለት ነበር፡፡
አንድ ቀን የገስግስ ጌታ ከሌሎች ጓደኞቹ ጋር መንገድ ሲሄዱ ዋሉና ደክሟቸው ሜዳ ላይ አረፍ አሉ፡፡ ሁሉም ፈረሶቻቸውን ሳር እንዲግጡ ለቀቋቸው፡፡ ገስግስ ሳር እየጋጠ እያለ የቆመበት ቦታ ከዳውና መሬቱ ተንሸራቶ ወደ ገደል ውስጥ ገባ፡፡ ገደሉ በጣም ሩቅ እና መግቢያ የሌለው ነበር፡፡ እዚያ ቦታ ሆኖ የሚያሰማውን ጩኸት ሰምተው ጌታውና ጓደኞቹ መጡ፡፡ ሲያዩት ገስግስ እጅግ በጣም ጥልቅ ከሆነ ጉድጓድ ውስጥ ወድቋል፡፡ እርሱን ለማውጣት የሚያስችል ነገር እንዳለ ብለው ጥቂት አሰቡ፤ ግን ለጊዜው አልመጣላቸውም ፡፡ ባለቤቱ አዘነ፡፡
ጓደኞቹም ከሀዘኑ አፅናኑትና ‹‹ ምንም ማድረግ አይቻልም ፡፡ ከዚህ በኋላ ገስግስም አርጅቷል፤ አሁን ደግሞ እዚህ ገደል ውስጥ በመውደቁ ምክንያት እጅግ ይጎዳል፤ ከዚህ በኋላ ምንም አይጠቅምህም፡፡ እኛም ካሉን ትርፍ ፈረሶች አንዱን ይዘህ መንገዳችንን እንቀጥል ›› አሉት፡፡ ባለቤቱ እጅግ አዘነ ፡፡ የእነርሱን ንግግር የሚሰማው ገስግስም በጣም አዘነ፡፡ የነበረውን አገልግሎት፤ የዋለበትን ቦታ፤ ያሳለፈውን ጊዜና ሁኔታ ዛሬ የደረሰበትን ጉዳት እና ድካም እያሰበ በጣም ተሰማው፡፡ ይበልጥ ደግሞ የጌታውን እና የጓደኞቹን ተስፋ የመቁረጥ ንግግር ሲሰማ እርሱም ተስፋ ቆረጠ፡፡ ባለቤቱ አንድ ሀሳብ ለጓደኞቹ አቀረበ፡፡‹‹ ከዚህ በኋላ ገስግስን ለማውጣት መሞከር ከንቱ ድካም ነው፡፡ ነገር ግን በዚህ ሁኔታ ጥሎ መሄድም ህሊናን እረፍት የሚነሳ ነው፡፡ ባይሆን ባለበት ጉድጓድ በሰላም እንዲሞት አፈር እናልብሰው››አላቸው፡፡ ሁሉም በሀሳቡ ተስማሙ፡፡ ገስግስ ግን ይበልጥ አዘነ፤ ይበልጥ ተስፋ ቆረጠ፡፡ ከዚህ በኋላ ምንም ዋጋ እንደሌለው የመኖር ተስፋውም እንደመነመነ ልጡ የተራሰ ጉድጓዱ የተማሰ እንደ ሆነ ተሰማው፡፡ ሞቱን እያየው ሊሞት ነው፡፡
ከዚህ ጉድጓድ በተአምር መውጣት ተመኘ፡፡ ግን ምንም መንገድ ሊታየው አልቻለም፡፡ ቀድሞ እርሱ ሞተ ሞትን የሚያመልጥበት አንዳች ብልሀት አጣ፡፡ ቀድመህ ስትሞት እንደዚህ ነው፡፡ የማምለጫው መንገድ አይታይህም፡፡ የማይታይህ ስለሌለ አይደለም፤ ከእያንዳንዱ ችግር የመውጫ መንገድ አለ፡፡ ያንን የምታየው ግን ቀድመህ ካልሞትክ ብቻ ነው፡፡
የመጀመሪያዎቹ ኮረቶች እና አፈር ገስግስ ላይ ወደቁ፡፡ ከወደቁበት ድንጋዮች እና አፈር ይልቅ ሞትን ማሰቡ ገስግስን ጎዳው፡፡ ‹‹ እየሞትኩ ነው ማለት ነው›› ብሎ ማሰቡ ይበልጥ አመመው፡፡ መጀመሪያ የወደቀበትን ድንጋዮችና አፈሩን ጀርባውን በማነቃነቅ ከላዩ ላይ አራገፈ፡፡ ከዚያ ከላዩ ላይ የነበሩት ድንጋዩችና አፈር ከጀርባው ሲያራግፋቸው ከእግሩ ስር አረፉ፡፡ ይሄኔ ገስግስ አንድ ሀሳብ ብልጭ አለለት፡፡‹‹ ለምን ቀድሜ እሞታለሁ፤ ያለችኝን ጥቂት እድልም ብትሆን ለምን አልጠቀምባትም ፡፡›› አለና ከላዩ ላይ የሚወርደውን ድንጋይ እና ማራገፉን ቀጠለ፡፡ ድንጋዩና አፈሩ ያመዋል፤ ነገር ግን ለመኖር እየታገለ ለማሸነፍም እየጣረ ስለነበረ ህመሙን የሚያስችል ብርታት አገኘ፡፡
‹‹ የሚያልቅልህ አለቀልኝ ያልክ ቀን ነው፤ የምትሞተው ሞትኩ ብለህ የተቀበልከው እለት ነው፤ የምትሸነፈው ልብህ የተረታ እለት ነው፡፡ አፈር ስለጨመሩብህ ብቻ ልትቀበር አትችልምኮ አፈሩን ማራገፍ ካልቻልክ እንጂ፡፡ አሁን ያደረጉህን ተውና የሆንከውን አስብ፤ ያጋጠመህን ተውና የወሰንከውን አስብ፤ ያውልህ የመውጫ መንገዱ፤ ግን ለህያዋን እንጂ ለሙታን አይታይምና ቀድመህ አለመሞትህን እርግጠኛ ሁን››
Filed in: Amharic