>

ሕገ መንግስተ ህወሓት በስታሊናዊ መመሪያው ብሄሮችንና ዜጎችን ጠፍንጎ የሚቆጣጠርበት ሰነድ ነው!!! (ጌታቸው ስሜ)

ሕገ መንግስተ ህወሓት በስታሊናዊ መመሪያው ብሄሮችንና ዜጎችን ጠፍንጎ የሚቆጣጠርበት ሰነድ ነው!!!
ጌታቸው ስሜ
* በህገ መንግስቱ ላይ ውይይት አሁን!
ላለፉት 27 ዓመታት አይነኬ የሆነውና አሁንም በአይነኬነቱ እየተጓዘ ያለው ህገ መንግስት ላይ በይፋ ውይይት መጀመር አለበት፡፡ ‹‹ይህን ህገ መንግስት ለመቀየርና ለማሻሻል ጊዜው አሁን አይደለም›› የሚሉ የመኖራቸውን ያህል ‹‹በሚቀየርበትና በሚሻሻልበት መንገድ ላይ ቶሎ ወደ ውይይት መግባት አለብን የሚሉ የህበረተሰብ ክፍሎች ቁጥራቸው ቀላል አይደለም፡፡ ምንም እነኳ ‹‹ጭራሽ መሻሻል የለበትም፤ አንድም አንቀፅ መቀነስ የለበትም›› የሚሉ ብሄረተኛ ፖለቲካኞችም መኖራቸውን ባንዘነጋም፡፡
ይህ ህገ መንግስት የኢትዮጵያን ህዝብ ቤተ መከራ አድርጓል፡፡ በዓለም ላይ በየትኞውም አገር መገንጠልን በይፋ ያሰፈረ ህገ መንግስት የለም፡፡ ለብሄሮች፣ ብሄረሰቦች እውቅና የሚሰጠው ህገ መንግስት ለዜጎች እውቅና ነፍጓል፡፡ በሌላ አገላለፅ ለዜግነት ጭራሽ እውቅና አይሰጥም፡፡ ለብሄሮች ብቻ እውቅና የሚሰጥና ዜግነትን ወይም ግለሰቦችን የማያውቅ የቃል ኪዳን ሰነድ ወይም ህገ መንግስት ሊባል አይችልም፡፡ የፖለቲካ ፕሮግራም እንጂ፡፡
በህገ መንግስቱ ሰብዓዊ መብትና ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት የተካተተበት ክፍል ቅሬታ የማያስነሳ ቢሆንም፤ አብዛኞው ክፍል አንድ የህገ መንግስት ሰነድ ሊያሟላ የሚችለውን ድንጋጌዎች አላካተተም፡፡ ለምሳሌ ያሀል የህገ መንግስት ፍርድ ቤት (Constitutional Court) ስልጣንን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውስዶታል፡፡ ይህ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው ህገ መንግስታዊ ና የህግ ጥያቄዎች ሲነሱ ምላሽ የሚሰጠው፡፡ የህገ መንግስት አማካሪ ምክር ቤት የሚባለውም የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ያማክራል እንጂ ውሳኔ ሰጪ አይደለም፡፡ ብሄር ብሄረሰቦች የሚወከሉበት ይህ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የፍርቤ ቶችን ህግ የመተርጎም ስልጣን ሁሉ ጠቅልሎ ይዟል፡፡
የህገ መንግስት ባለሙያዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ህገ መንግስትም ህገ መንግታዊነትም (Constitution and Constitutionalism) የለም ሲሉ ይናገራሉ፡፡ ስለዚህም ህዝብ በተወካዮቹ አማካይነት ተወያይቶ መክሮና ዘክሮ የሚያፀድቀው ህገ መንግስት ያስፈልገናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከወዲሁ ማለትም ይቀየር፣ ይከለስ፣ ይሻሻል፣ አይሻሻልም የሚሉትን ሁሉ የሚያካትት ውይይት በአስቸኳይ መጀመር አለበት፡፡
ህወሓትና ኦነግ ተስማምተው ህዝብ ሳያወያዩ ያቀበሉን የአሁኑን ህገ መንግስት ህገ መንግስት ብሎ መጥራት ያዳግታል፡፡ ህወሓት ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት በሚለው ስታሊናዊ መመሪያው ብሄሮችንና ዜጎችን ጠፍንጎ የሚቆጣጠርበት ሰነድ ነው፡፡ ያገባናል የሚሉ የፖለቲካ ልሂቃን ውይይቱን ባገኙት ሚዲያም ሆነ መገናኛ ዘዴ እየተወያዩ ቢያዳብሩት ከወዲሁ ትልቅ መሰረት መጣል ይቻላል፡፡
Filed in: Amharic