>

ትግራይን ለመቅጣት - ክፉ ማድረግ አይጠበቅብህም "መርሣት" ብቻ!!! (አሰፋ ሀይሉ)

ትግራይን ለመቅጣት – ክፉ ማድረግ አይጠበቅብህም “መርሣት” ብቻ!!!
አሰፋ ሀይሉ
ይህ የ1977 ዓ.ም. የሀገራችን ድርቅ ወቅት ነው። ድርቅ አልነው እንጂ ድርቅ ብቻ አይደለም። ረሃብ ነው። ያውም የሰው ነፍስ የሚቀጥፍ ረሃብ። “ፋሚን” ብቻ አይደለም ይሄ። “ስታርቬሽን” ነው። ረሃብ በአካሉ። ረሃብ በአምሣሉ።
ይህ በፎቶው የሚታየው የየትኛው ኢትዮጵያዊ ረሃብ ነው? – የትግራይ ረሃብ ነው። ትግራይ፤ እና ትግሬ፤ የኢትዮጵያችን ሥር መሠረት የተጣለበት ሥፍራ፥ እና የኢትዮጵያዊነትን መሠረት የጣለ ሕዝብ ነው። የድሮ አክሱማውያን ነገሥታት የወርቅ ሣንቲሞች ላይ – ከሺ አምስት መቶ ዓመታት በፊት – የሚገርም የስንዴ ዛላዎችን የያዙ ሣንቲሞች – አሁን ድረስ በቁፋሮ ይገኛሉ። እና ስገምት – የትግራይ ምድር የደረቀው በጊዜ ሂደት በመጣ የተፈጥሮ መራቆት የተነሣ ነው። ረሃቡም፣ መከራውም ያን ተከትሎ የመጣ ዘመን-አመጣሽ ክስተት ይመስለኛል።
ግን ኸጊዜ በኋላም ይምጣ ቀደም ብሎ – ከትግራይ የበቀለ ኢትዮጵያዊ – ደመ-መራር ስለመሆኑ ነው የታሪክ ድርሣናት የሚያወሱት። የሩቆቹን “ክብረ-ነክ” ስለሆኑ ብተዋቸው – በሀገራችን የመጀመሪያውን የዘመናዊ አርት ት/ት አውሮፓ ሄደው የቀሰሙት – ደጃች አፈወርቅ ገ/የሱስ ለምሣሌ – ስለአፄ ዮሐንሥ ሲያሄሱ፦ “ባሩድ የሸተተው አውሬ፤ ረሃብ ያሣደደው ትግሬ፤ አንድ ነው እንዲሉ” – በማለት – በተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ለትግራዮች ያደረውን የዘመኑን አስተሣሰብ – በ1901 ዓ.ም. በሮም ባሳተሙት መጽሐፋቸው – ግልጽልጽ አድርገው አስቀምጠውታል።
አዎ። ከጊዜ በኋላም ይሁን ከጊዜ በፊት – የትግራይ ምድር – በተፈጥሮ ሥጦታው የታደለ ምድር አይደለም። ጓድ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ራሳቸው፦ “እህል አይታፈስበት፣ ወርቅ አይታፈስበት፣ አልማዝ አይገኝበት፣ it’s nothing!” እያለ ስለ ትግራይ ምድር የቸፈጥሮ መካንነት እያነሱ ሲያስተባብሉ የሚታዩበት የቴሌቪዥን መግለጫ አላቸው። አዎ። ትግራይን ተፈጥሮ አላደለውም። ስለዚህ ተፈጥሮ ያደላቸውን በከፍተኛ ጦረኝነት ማስገበር ወይም ከመረቃቸው መቃመስ – ለዘመናት – የእያንዳንዱ የትግራይ ነዋሪ – ያልታወጀ ተፈጥሮ-ወለድ መርህ ነው።
ለዚህ ይመስላል – በቁጥር የበዙ የኢትዮጵያ ገዢዎች – ትግራይን ለመቅጣት ሲያስቡ የሚጠበቅባቸው ቀላል ተግባር – በቃ – ትግራይን “መርሣት!”ን በቂ ቅጣት አድርገው ነበር የሚወስዱት። በ1965 ዓ.ም. ላይ ግርማዊ ጃንሆይ በወሊድ የሞተችባቸውን ትንሺቱን ልጃቸውን ቂም ለመወጣት እስኪባልባቸው ድረስ ትግራይን – ረስተዋት ነበር።
ከታሪክ ማህደሮች ባሻገር – የነበሩ እማኞች እንዳወሱኝ – ጃንሆይ በእርግጥም – ወደ መጨረሻው – ትግሬን ረስተውት ነበር። ትግራይ የሚሠሩ የመንግሥት ሠራተኞች፣ መምህራን፣ ወዘተ የሚከፈላቸው ደመወዝ ራሱ ተረሣ። ት/ቤቶች ተዘጉ። ሆስፒታሎች ያለሃኪም፣ ሆቴሎች ያለተመጋቢ – ሁሉም ኦና ቀሩ። ረሃቡ ጠና። የመሐል ሀገር ሰው ወደ ከረጢቱ አፈገፈገ።
እና ምን ልልህ ነው? – ትግራይን ለመቅጣት – ክፉ ማድረግ አይጠበቅብህም። መርሣት ብቻ። ከረሣሀቸው ይራባሉ። ከረሣሀቸው ይጠማሉ። ከረሣሀቸው ይሰደዳሉ። እና ትግራዮች ሁሌም – የኢትዮጵያ አንድነት አቀንቃኞች ነበሩ። ባህረነጋሲያውያን (ኤርትራውያን) እስኪጀነጅኑአቸው ድረስ። ወይ በሆነ ፀበል እስኪያጠምቁዋቸው ድረስ።
ትግራዮች ሁሌም ለመረሣት የሚሰጡት መልስ አላቸው። በኃይል መነሣት። ማመፅ። አድባሩ እስኪደነግጥ ድረስ መሸመቅ። መዋጋት። እና ማሸነፍ። ብቻ።
አሁን ይህ ዘግናኝ ረሃብ በትግራይ ምድር የለም። ማንም ኢትዮጵያዊ ትግሬዎችን አይረሣቸውም። የውድቀቱ ሁሉ ምንጭ የማድረግ ዝንባሌ አለው። የትግራይ መንግሥት ጥጋብ ካሣየ እንደሚረሣ ግልፅ ነው። ሲረሣ ደሞ ባሩድ እንደሸተተው አውሬ ሆኖ ይነሣል። ይህ የታሪክ ሃቅ ነው። ኢትዮጵያ ፈጣሪዋን ትግራይን አትረሣም!። የትግራይ እናት ኢትዮጵያዊ እናት ናት። የትግሬ ፅንስ የታላቋ ኢትዮጵያ ፅንስ ነው።
ጥቂት ትግሬዎች – የኢትዮጵያን ሕዝብ – እንደ ወገን ሣይሆን እንደ ጠላት አይተው – በደል አድርሰውበታል። እነዚያ የትግራይን ሕዝብ ሁሉ አይወክሉም። የትግራይ ሕዝብ በኢትዮጵያዊነቱ ተደራድሮ አያውቅም። ኢትዮጵያ ስትጎመራ ይጎመራል። ኢትዮጵያ ስትከስም ይስማል። ወገናችን ነው። ሕመሙ ያመናል። ደስታው ፍታታችን ነው።
አምላክ ኢትዮጵያን ክፉ አየሠስነካት። እምዬ ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር። አምላክ እምዬ ኢትዮጵያን አብዝቶ ይባርክ። አሜን።
Filed in: Amharic