>

ለእርቃችሁ ደም መፍሰስ ካለበት የኔን ደም አፍሱና ታርቃችሁ ኦሮሞን አስታርቁልን!!! (ኦቦ ሃይሌ ገብሬ)

ለእርቃችሁ ደም መፍሰስ ካለበት የኔን ደም አፍሱና ታርቃችሁ ኦሮሞን አስታርቁልን!!!

ኦቦ ሃይሌ ገብሬ

 

በመላኩ አላምረው

“እባካችሁ ታረቁ። ለእርቅ የሚሆን ከብት እንገዛለን። አይ ከብት አይደለም ሰው ይታረድልን የምትሉም ከሆነ ይኸው የኔን ደም አፍሱና ታርቃችሁ ኦሮሞን አስታርቁልን። (የሰው ደም ካላፈሰሳችሁ እሺ የማትሉ ከሆነ በእናንተ ጠብ ንፁሃን በየቀኑ ከሚሞቱ እኔን ሽማግሌውን እረዱኝና ታረቁ፤)”
(እኝህ ኦቦ ሃይሌ ገብሬ የተባሉ የኦሮሞ ሽማግሌ ዛሬ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ባለው የኦዴፓ እና ኦነግ የእርቅ ስነ ስርአት ላይ እንባ እያፈሰሱና እየተማፀኑ የተናገሩት ነው።)
በእውነት የእኝህን አዛውንት ተማፅኖ ረግጦ ሳይታረቅ የሚወጣ ይኖር ይሆን???
.
“ሰማይ ተቀደደ ቢሉት፣ ሽማግሌ ካለ ይሰፋል” አለ፤ “ሽማግሌ ከሌለስ? ቢሉት፣ ሽማግሌ ከሌለማ እንደተቀደደ ሲያፈስ ይኖራል” አለ ይባላል። ጥሩ አባባል ነው። እውነተኛ ሽማግሎች ካሉ የተጣሉ ኃይሎች ይታረቃሉ።
በሀገራችን ታሪክ ሽምግልና ከመንግሥት በላይ የሰላምና የእርቅ፣ የስምምነትና የአብሮነት ሚና ተጫውቷል ማለት ይቻላል። የተጋደሉ ባለደም ወገኖችን ይቅር አባብሎ የሚያስማማውና አጋብቶ አዋልዶ የሚያኖረው ሽምግልና ነው። ይህን እሴት ልንጠብቀው ይገባል።
እውነተኛ ሽማግሎች ካሉና ሽማግሌን የሚያከብር መንግሥት ከተፈጠረ ሀገር ሰላም ይሆናል። ችግሩ ሽማግሌን የማያከብር አባቱን የሚንቅ ወፍ ዘራሽ ሥርዓት ካለና ከቀጠለ ነው። አሁን ሀገራችን የደረሰችበት ዝቅታና የገባችበት የችግር አዙሪት ከመንግሥታዊ ሥርዓት ዝቅጠት የመጣ ነው። የተጋደለን የሚያስታርቁ ሽማግሎችን ቦታ በተገቢው መልኩ ስላልጠበቅንና ለትውልዱ አቅልለን በማሳየት ትጥቅና ፖሊስ ሲብስም ወታደር ብቻ እያሳየን ያሳደግነው ትውልድ በሽማግሌ ለመታረቅ እምቢ ቢል አይገርምም።
ከሽማግሌም ባለፈ ጦርነትን በቃልና በመስቀል ገዝተው የሚያቆሙ የእምነት አባቶችን አይታ የኖረች ሀገር ናት ኢትዮጵያችን። ይሁንና የሀገርን ትውፊት ወደ ጎን ብሎ ዘመን አመጣሽ ሳይንስ ላይ ብቻ የሚያተኩር ሥርዓት ካለና ከቀጠለ፣ ለእምነት ተቋማት ተገቢውን ክብር ባለመስጠት አባቶች እንዳይከበሩና ፍጹም እምነት አልባና ሥርዓት የለሽ ትውልድ ሊፈጠር ይችላል። ይህ ደግሞ ሀገርን ብዙ ዋጋ ያስከፍላል። ይህ እንዳይፈጠር ካሁኑ በደንብ ሊሰራበት ይገባል።
ልቡ ያልተገዛ ሕዝብ አካሉን መሳሪያ አይገዛውም። ልብን የሚገዛው ደግሞ በፍቅር የሆነ የእምነት አባቶችና የተከበሩ ሽማግሎች ቃል እንጅ ጦር መሳሪያ አይደለም።
የሕግ የበላይነት በመንግስት መከበሩና ግድ ቢሆንም ያለ ሽምግልና እና እምነታዊም ባህላዊም ስርዓት አጋዥነት ግን ሊረጋገጥ አይችልም።
የጦሩን ጉዳይ ለአባ ገዳዎች ሰጥቻለሁ!!!
አቶ ዳውድ ኢብሳ 
በዛሬው እለት የኦሮሞ አባ ገዳዎች ህብረት ባዘጋጁት መድረክ ላይ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ኦነግ ጦር ጉዳይን ለአባ ገዳዎች ሰጥቻለሁ›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የኦነግ ሊቀመንበሩ አቶ ዳውድ በመድረኩ እኛ ከኤርትራ የመጣነው በሰላማዊ መንገድ ለመታገል በመስማማት ነው፤ ለሰላም ሌት ተቀን እንሰራለን ብለዋል።ከመንግስት ጋር እያጋጨን ያለው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ኦነግ ጦር ጉዳይ ነው ያሉት አቶ ዳውድ ከዚህ በኋላ የጦሩን ጉዳይ ለአባ ገዳዎች ሰጥቻለሁ ብለዋል።
Filed in: Amharic