>

የዶ/ር አብይን  ሸክም የተረዳን ለት በስሙ የምናቆምለት ዘመን ተሻጋሪ ኃውልት!!! (አሰፋ ሀይሉ)

የዶ/ር አብይን  ሸክም የተረዳን ለት በስሙ የምናቆምለት ዘመን ተሻጋሪ ኃውልት!!!
አሰፋ ሀይሉ
 
እኔ ግን ሣስበው – ምናልባት አንድ ቀን – ይህ ሰው – በጫንቃው ላይ ተሸክሞ የሚዞረውን – የሀገሪቱን የችግር ሸክም ክብደቱ –  የቱን ያህል እንደሆነ – ሁላችን በትክክል የተገነዘብን ቀን – የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆ ብሎ ወጥቶ – ለዚህ ዶ/ር አብይ ለሚሉት ጠይም ሰው – እንዲህ የመሠለ ዘመን ተሻጋሪ ኃውልት በስሙ የሚያቆምለት ይመስለኛል። አንድዬ የኢትዮጵያ አምላክ ይርዳው እና ያዝልቅለት ማለት ነው።
የዚህን ሰው አስገራሚ ቀናነት እና የሀገሪቱን ነገር ለመሸከም ያለውን ፍፁም ፈቃደኝነትና ቀናነት፣ እና ከሁለመናው ላይ የምትመለከተውን አስገራሚ እምነት – ፈጣሪ የኢትዮጵያ አምላክ በዚሁ ያዝልቅለት ማለት ነው ዛሬ። ምናልባት እዝጌሩ ብሎልን ዛሬን ከተሻገርናት – ነገ ላይ የሚደርሱ ትውልዶች – በዚያ በቀደመው ዘመን – ይህ ኢትዮጵያን ከአፉ የማይነጥል ሰው – በአንድ ወቅት – የዚህችን ሀገር ተቃርኖዎች ሁሉ በጫንቃው ተሸክሞ ጎብጦላት ነበር – ለማለት ይበቁ እንደሆነ።
ሁላችንን የኢትዮጵያ ልጆች የዚያ ሰው ይበለን።
ለማንኛውም አንድዬ ሸክማችንን ያቅልልልን። በየታሪኩ ምዕራፍ የተጋረጡባትን ሸክሞቿን በዜጎቿ የተባበረ የጋራ ጥረት ያቀለለች – የበለፀገች ነፃ አፍሪካዊት ሀገር – ነፃ ዜጎች ነበርን። አሁንም – ወደፊትም – በዜጎቿ ልባዊ መረዳዳት እና የተባበረ ክንድ – እነሆ ዳግም ወደታላቅ አፍሪካዊ ብልፅግናዋ የተመለሰች – የአንዲቱ የኢትዮጵያ ኩሩ ዜጎች እንሆን ዘንድ አምላክ ይርዳን!
ኢትዮጵያዬ – ብለን ሁላችንም የኢትዮጵያ ዜጎች – አፋችንን ሞልተን በየልሣናችን የምንናገርላት – እና የምንናገርባት – የአንዲት ታላቅ የፍቅር ሀገር ውድ ዜጎች ሆነን – ባንድ ወገናዊ ልብ ተገናኝተን ለትውልድ ብልፅግና ባንድ ላይ ቆመን ለምንዘምርበት አይቀሬ ዘመን ሁላችንን ያብቃን ፈጣሪ አምላክ።
አምላካችን ከማንወጣው ችግር ይታደገን። በችግራችን ያፅናን። ችግራችን የቱን ያህል የተቆለለ ቢመስል – ለችግራችን መፍትሔ አያሣጣን። ፍቅር ካለ ተራራም ይገፋልና – ፍቅር በምድራችን ማዕዘናት ሁሉ ይስፈፍ። ታላላቆቻችንን ይባርክ። ታናናሾቻችንን ያበርታ። የነገዪቱ ኢትዮጵያ ሰው ይበለን።
እና ይህን ሰው የፈጣሪ ቀናዒነት በሸክሞቹ ሁሉ ይራዳው።
እምዬ ኢትዮጵያ – ለዘለዓለም – በፍቅር – በብልፅግና – ለዘለዓለም – ትኑር ! ! ! !
ቸር ይግጠመን።
Filed in: Amharic