>

ዘጠና ደቂቃዎች ከጓድ ሊቀ መንበሩ ጋር !!! (ውብሸት ታዬ)

ዘጠናደቂቃዎች ከጓድ ሊቀ መንበሩ ጋር !!!
ውብሸት ታዬ
   ስማቸው ከማንኛውም ማዕረግ በፊት ሲጠራ ‘ብርሃኑ ነጋ ቦንገር’ ይባላል። ከሰውየው ጋር ዳግም ቁጭ ብለን ሃሳብ ለመለዋወጥ በትንሹ 13 ዓመት ፈጅቶብናል።  በሕይወት ዘመናቸው ሁለት ጊዜ ዱሩ ጥራኝ ብለው በረሃ ወርደዋል። በሕይወታቸው ሁለቴ ሞት ተፈርዶባቸዋል።
   የመጀመርያው ዓላማህ ዓላማዬ ባሉት ድርጅት አሲምባ ላይ፤ ሁለተኛው በዓላማ ተቀናቃኞቻቸው እዚሁ በመዲናችን። ሶስት ጊዜ ያህል ታስረዋል። በኢሕአፓ፣ በኢሕአዴግ እና በኢሕአዴግ(አቤት…!በማሰር የተካነ ድርጅት)።
   በ1969 ዓ.ም ኢሕአፓ ያሰረቻቸው በትግሉ ላይ የዲሲፕሊን ጥፋት በተገኘባቸው ላይ ይወሰድ የነበረውን ርሸና በመቃወማቸው ሲሆን በዚህ ‘ጥፋታቸውም’ ታስረው የተቃወሙት እርምጃ በሳቸውም ተፈጻሚ ሊሆን… ጫፍ ደርሶ … ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ስለነበር ተረፉ(ማርያም አወጣቻቸው!)::
   እናም በማለዳው ለሌሎች ለመትረፍ ነፃነት ብለው ከወጡለት የፋኖ ትግል ወደስደት አመሩ። በሱዳንም ለሁለት ዓመታት የዘመኑ ስደተኛ የሚሆነውን እየሆኑ ኖሩ። አሜሪካ ገቡ፤ ተማሩ። ‘እምቢልታ’ የተሰኘች ተወዳጅ መጽሔት አቋቁመው ነበር(አንድ ሰሞን እንደኛ አድርጓቸው ነበር ማለት ነው)። ስርዓት ሲቀየር ተመለሱ።
   ሁለተኛው እስር ሚያዝያ 1ቀን 1993 ዓ.ም በብሔራዊ ሎተሪ አዳራሽ ከፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም(የሥርዓቶች ሁሉ ጎንታይ) ጋር በመሆን በአካዳሚክ ነፃነት ዙርያ  ያደረጉትን የፓናል ውይይት ተከትሎ የአአዩ ተማሪዎች ላሄዱት አመጽ በእርሾነት ተጠርጥረው ለወራት ታሠሩ። ክሱ ተማሪዎቹን ‘አትፍሩ’ ብላችኋል የሚል ነበር። ፕ/ር መስፍን ‘ታዲያ ተማሪዎችን ፍሩ ብዬ ላስተምር ነበር?’ ማለታቸው ይታወሳል።
   ሶስተኛው በእስር የተካኑት ባለጊዜዎች ከታሪካዊው የ1997 ዓ.ም ማግስት የታሰሩበት የጥቅምት 22/1998 ዓ.ም እስር ነው(በዚያው ቀን እኔም እከትብባት ከነበረችው ጋዜጣ መላ ባልደረቦች ጋር ታስሬ ነበር)። ያም አለፈ።
ከእስር እንደወጡ ለሥርዓቱ መሪዎች “ከዚህ በኋላ አምስት ዓመት ከቆያችሁ፤ ምክንያቱ የእናንተ ጥንካሬ ሳይሆን የእኛ ድክመት ነው!”የምትል ዝነኛ ንግግር አደረጉ።
   ከዝነኛ የአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰርነት ወደአማጺ ጦር መሪነት ተቀየሩ። ድርጅቱም መሪ አድርጎ መረጣቸው። ጓድ ሊቀ መንበር !
ከውዱ ኢትዮጵያዊ ወንድሜ ከፕሮፌሰር ብርሃኑ ጋር በጎ ቆይታ ነበረኝ። የ30 ደቂቃ ቀጠሮ አስይዤ 1:30 ሰዓት ወስጄባቸዋለሁ። ሁለታችንም የሰዓቱን መንጎድ የደረስንበት በመጨረሻ ነበር።
   ከፕሮፌሰሩ  ጋር ስትሆኑ ከላይ የጠቃቀስኩላችሁን፤ ሰውየው ያለፉባቸውን ለውጭ ተመልካች አድቬንቸር የሚመስሉ ዝክሮች እያሰባችሁ ፈገግ እያላችሁ ነው። ፊት ለፊታችሁ ፖለቲከኛ፣ ምሁር፣ አክቲቪስት እና የአማጽያን መሪ ተደባልቆ በአንድ ሰው ውስጥ ይታያችኋል። እና የምትማሩት ነገር አታጡም፤ ቢያንስ የምትጎዱት ነገር የለም።
   የእኔ የሁልጊዜ ዋና መልዕክት፤ አገራችን እንደሳቸው ሁሉ ባለ ብዙ ዘርፍ ልሂቃን ሞልተው የተረፏት ቢሆንም በተለያየ መስመር መጓዛቸው የቅርቡን ግብ እንዳንደርስበት አድርጎናልና አማራጮቻችን ይብዙ፥ መዳረሻችን ግን ለአንዲቷ አገራችን ልዕልና የተለመ ይሁን የሚል ነው። መልካም ሰንበታት እመኝላችኋለሁ።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ያስብ፤ ሕዝቧን ይባርክ!
Filed in: Amharic