>
7:22 am - Wednesday December 7, 2022

የማትረሳ ድንቅ ምሽት (ሠርፀ ፍሬ ስብሐት)

የማትረሳ ድንቅ ምሽት
             በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ!!
የሙዚቃ ባለሙያ ሠርፀ ፍሬ ስብሐት
ግርማዊነታቸው፥ “የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴአትር ቤትን” (የዛሬው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትርን) በስማቸው ካሠሩ እና መርቀው ከከፈቱ በኋላ፣ ታላላቅ ቴአትሮችን እና የሙዚቃ ኮንሠርቶችን በቴአትር ቤቱ በመገኘት በክብር ተመልክተዋል፣ ባለሙያዎችን ሸልመዋል፣ ጥበብን አድንቀዋል።
ከግርማዊነታቸው በኋላ፣ ኮለኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያምም ይህንኑ “የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴአትር ቤት”፤ ስያሜውን “ብሔራዊ ቴአትር” ከማሰኘታቸው በቀር፣ በቀደመ ክብሩ ልክ፣ በተለያዩ ጊዜያት የቴአትር እና የሙዚቃ ዝግጅቶችን ተመልክተውበታል፣ የኪነት ቡድኖችን አበረታትተውበታል፣ ሶሻሊስታዊውን የሥነ ጥበብ ዐተያይ ተግብረውበታል።
ከደርግ የሥልጣን ዘመን በኋላ ግን፣ ግርማዊነታቸው እና ኮለኔል መንግሥቱ በየተራ ተቀምጠውበት በነበረው የንጉሠ ነገሥቱ መቀመጫ ላይ ተቀምጦ፣ የጥበብ ዝግጅት የተከታተለ የሀገር መሪ አልነበረንም።
እንደማስታውሰው፥ ይኸው ጉዳይ የጥበብ ባለሙያዎችን አሳስቧቸው ከአቶ መለስ ዜናዊ ጋር ግንቦት ፳፱ ቀን ፳፻፫ ዓ.ም. በነበረው የውይይት መድረክ ላይ በጥያቄ መልክ፣ “መቼ ነው ቴአትራችንን፣ ሙዚቃችንን፣ ሥነ ጥበባችንን ብሔራዊ ቴአትር ተገኝተው የሚመለከቱልን? ከተማሪነት ጊዜዎ በኋላስ ቴአትር ቤቱን ዐይተዉት ያውቃሉን?” ተብለው ተጠይቀው ነበር። በጊዜው ጥያቄውን አብጠልጥለው “አይመለከተኝም” በሚል ዓይነት የሰጡትን ምላሽ፣ ብዙ የሥነ ጥበብ ሰዎች እስከዛሬ በትልቅ ቅሬታ ያስታውሱታል።
ይህንን ኹሉ እንዳነሳ ምክንያት የኾነኝ፣ ማናችንም ባልገመትነው እና ባልጠረጠርነው ድንገተኛ ክስተት፣ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዛሬ ምሽት (ጥር ፳ ቀን ፳፻፲፩ ዓ.ም.) በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ላይ ተገኝተው ከፍ ያለ ትምህርት ያለው ንግግር ማድረጋቸው በፈጠረብኝ ግርምት ነው።
 
የኾነው እንዲህ ነው፦
“ምስክር የሻነው ሚዲያ እና ፕሮሞሽን ድርጅት” በየሦስት ወራት  (እያሠለሰ) በሚያዘጋጀው መርኀ ግብር ላይ የዛሬው ተረኛ ርዕስ “ስንዋደድ” ተሰኝቶ የሚቀርብበት መድረክ ነበር የተሠናዳው። ረ.ፕሮፌሰር ነቢዩ ባዬ፣ ዶ/ር ሰሎሞን ተሾመ ባዬ፣ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በዕለቱ ዐቢይ ጭብጥ ላይ ድንቅ ንግግሮችን አድርገዋል።
የመድረኩ የመጨረሻ ተናጋሪ የነበሩት ሙሐዘ ጥበባት ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፤ ባልተለመደ ኹኔታ ከመድረኩ ጀርባ መጥተው፣ “የዛሬውን የእኔን ንግግር፣ አንድ ዘወትር በዚህ መድረክ ላይ ለመገኘት ፍላጎት ላለው፣ በቅርቡ ከውጪ ለመጣ ወዳጄ አስቀድሜ ዕድል ልስጥና ከእርሱ ንግግር በኋላ እመለሳለሁ።” ብለው፣ ገና ከመድረኩ አትሮንስ ኹለት እርምጃ ሳይራመዱ፣ የቴአትር ቤቱን ታዳሚ ልብ ቀጥ የሚያደርግ እንግዳ ወደ መድረኩ ፈገግታ በተመላ ትሁት የዕጅ ሰላምታ ዕጁን እያውለበለበ በታዳሚው ኹሉ ፊት ድቅን አለ።
የሌሎችን ባላውቅም፣ እኔ ለተወሰኑ ደቂቃዎች የማየውን ነገር ማመን አልቻልኩም። የታዳሚው ጭብጨባ፣ ጩኸት እና መውደዱን የገለጸበትን መንገድ፣ እንደ ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ ያለው “የቃል አንጥረኛ” ደራሲ በሥዕል መልክ የሚጽፈው እንጂ እኔ የምገልጸው ዓይነት አይደለም።
መሪዎች ቆመውበት የማያውቁትን የጥበብ መድረክ ይህ በኹሉ ነገሩ ማስደነቅ የየዕለት ግብሩ የኾነለት ወጣት ጠቅላይ ሚኒስትር ተሠየመበት። [ደራሲ ስለኾነ ይኹን እንጃ] ብቻ፣ ያ ግዙፍ የቴአትር ቤቱ መድረክ ከእግሩ በታች ኾነለት፣ ተገዛለት፣ ተሸነፈለት፣ መድረኩን በእርጋታ ነገሠበት።
“…ተፈጥሮ ንፉግ እና ጨካኝ አይደለችም። ስንሰጥ በእጥፍ የምትሰጠን፣ ስንነፍግ የምትነፍገን ነች እንጂ። ታላቁ የጥበብ ሰው ጥላሁን ገሠሠን ገና ስሙን ሲጠራ ብዙ ነገር ይታወሰናል። ይህ የኾነበት ምክንያት፣ የተሠጠውን ውድ ስጦታ መልሶ በብዙ እጥፍ አትርፎ ስለሰጠ ነው። ሎሬት ጸጋዬ ገብረ መድኅን በሰጡን የጥበብ በረከት ልክ እናከብራቸዋለን፣ አትሌት ደራርቱ ቱሉ የተሰጣትን ስጦታ አውቃ ባትሰጠን ኖሮ፣ አርሲ እንዳሉ አንዲት እናት ከመንደሯ የማይሻገር ስም ይዛ ትቀር ነበር።…” በሚል፣ መሳጭ ንግግር የታዳሚውን ቀልብ ቀጥ አድርጎ የያዘ አጠር ያለ ንግግር አድርገው፣ በዚያው ትሁት የመድረክ እና የሕዝብ አክብሮት፣ የብዙዎች የአድናቆት ጭብጨባ እና ጩኸት እንዳጀባቸው – መድረኩን ተሰናብተው ወጡ፥ ጠ.ሚ. ዐቢይ አሕመድ።
በዚህ ግዙፍ የጥበብ መድረክ ላይ በመቆም የመጀመሪያው የሀገር መሪ እንደኾኑ ሲታሰበኝ፣ ያየሁት ነገር እውን የኾነ አልመስል አለኝ።
እሺ፥ ለዚህስ ምን ይባል ይኾን?*እናመሰግናለን ከማለት በላይ ለጊዜው የመጣልኝ ቃል የለም።
  እናመሰግናለን
Filed in: Amharic