>

የሕዝብና ቤቶች ቆጠራን በተመለከተ ቅድመ ማስጠንቀቂያ! (ቹቹ አለባቸው)

የሕዝብና ቤቶች ቆጠራን በተመለከተ ቅድመ ማስጠንቀቂያ!
ቹ አለባቸው
1. ሌላ አማራጭ ካለ ንገሩኝ! 
አንዳንድ ወዳጆቸ አዴፓ እንዲህ ቢያደርግ፤እንዲህ ደግሞ ባያደርግ እያልኩ ምክር አዘል ሃሳብ ስሰጥ፤ አዴፓ አለ ወይ? በአዴፓ ተስፋ አለመቁረጥህ ይገርመናል! አዴፓን ለማጀገን ትሞክራለህ! ሹመት ፈልገሀል መሰል ! ወዘተ…የመሳሰሉትን ሃሳቦች በመሰንዘር፤አዴፓን እንድረሳው ይመክሩኛል፡፡ የእነዚህ ወንድም/ እህቶቸ ሃሳብ ይገባኛል፤ በአዴፓ ላይ ተስፋ በመቁረጣቸው ነው፡፡ ነገር ግን እኔም አንድ ጥያቄ አለኝ፤ይሄውም በአሁኑ ወቅት ሌላ ምን ምርጫ አለ? በአሁኑ ወቅት አዴፓን ከመግፋት ውጭ ያለውን ሌላ አማራጭ እስኪ ጠቁሙኝና እኔም ወደናንተ ሃሳብ ልደመር? አዴፓን እንርሳው ማለት ብቻውን መፍትሄ ይሆናል? ከአጭር ጊዜ አኳያስ የአማራን አጀንዳዎች በህጋዊ መድረኮች አንስቶ ሊያሰማ የሚችልና አቅምና እድሉ ያለው፤ ከአዴፓ ሌላ አማራጭ አለን? ካለ ጠቁሙኝ፡፡
ለሁሉም በእኔ እምነት፤አዴፓን በህጋዊ መንገድ በሌሎች አማራዊ ኋይሎች መተካት እስካልተቻለ ድረስ፤በአሁኑ ወቅት የአማራን አጀንዳ በህጋዊ መንገድ አንስቶ የመሞገትም ሆነ በቸልታ የማለፍ አቅምና እድል በአዴፓ እጅ ናት፡፡ ስለሆነም በዚህ ሁኔታ ውስጥ እስካለን ድረስ አዴፓን ከመግፋት ወደኋላ ማለት ለሌላ ጥፋት መዳረግ ነው ብየ አምናለሁ፡፡ አዴፓን በመጥላት፤ በማጣጣል፤ በድርጅቱ ላይ ተስፋ ቆርጦ ቁጭ በማለት መፍትሄ የሚመጣ ቢሆን ኖሮ፤እኔን ቀዳሚ ባልተገኘ ነበር፡፡ ግን አይሆንም፡፡ ስለሆነም ሌላ ተኪ ኋይል እስካልመጣ ድረስ፤ ዛሬም አዴፓ ከእንቅልፉ ነቅቶ፤ ከዘገምተኛ ጉዞው ተላቆ፤ከተላላኪነት ታሪኩ ወጥቶ የአማራን  ህዝብ ጥቅም እንዲያስከብር መወትወቴን እቀጥላለሁ! ለዛሬው ደግሞ በቅርቡ የሚካሄደውን የህዝብና ቤቶች ቆጠራና አዴፓ ሊያተኩርባቸው በሚገቡ ነጥቦች ዙሪያ የግሌን አስተያየት  እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡
2. የ 2007 (1999 ዓ.ም ) የህዝብና ቤት ቆጠራ ብልሽት ከአማራ አንጻር!
መቸም  በ2007 ዓ.ም የተካሄደውን የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ውጤትና በአማራ ህዝብ ላይ አስከትሎት ያለፈውን ጦስ የሚረሳ አማራ ይኖራል ብየ አልገምትመ፤ካለ እሱ ገልቱና ነገር አይገባሽ ነው፡፡ ለማስታወስ ያክል ብቻ፤በራሱ መንግስት ባመነው ሪፖርት ብቻ፤ በዚህ ወቅት ከ2.4 ሚሊየን በላይ አማራ ጠፍቷል፡፡ ስለዚህ ሁኔታ የጉዳዩ ባለቤት የመንግስቱ መ/ቤት እንዲህ ገልጾታል”… During the tabulation and consistency checks of the census data, it was found that the counted population for the Amhara Region was relatively lower than the projected population size by a large number, 2.4 million (CSA, April 2012, P. 83).
አሁን ጥያቄው ይሄ ቁጥር እንዴት በዚህ መጠን ሊቀንስ ቻለ? የሚለው ነው፡፡ ለዚህ ጥያቄ በርካታ ምክንያቶችን መደርደር እንችላለን፡፡ለምሳሌ ሆን ተብሎ  የተሰራ ስራ ነው፤ህዝቡ በትክክል ባለመቆጠሩ ነው፤ ወዘተ…የመሳሰሉትን፡፡ በእኔ እምነት ደግሞ፤ እነዚህ ምክንያቶች እንዳሉ ሆኖ፤ ዋነኛው ምከንያት፤ ሆን ተብሎ የአማራ ህዝብ የእድገት ምጣኔ ዘገምተኛ እንዲሆን ታስቦ ሲሰራ በመክረሙ ስራ የመጣ ውጤት ነው እላለሁ፡፡ በአገሪቱ ሲካሄድ የከረመው የቤተሰብ ምጣኔ ልማት የአማራን ህዝብ ቁጥር ብቻ እንዴት እንደቀነሰው ጥናት ያስፈልገዋል፡፡ በዚህ በኩል የዚሁ ጉዳኛ መ/ቤት በ2008 ዓ.ም ባወጣው የማጠቃለያ ሪ‹ርት ( Summary and Statistical Report of the 2007 Population and Housing Census Results: A population size by age and sex ( December, 2008፣ ገጽ 11)) አማራን ህዝብ አመታዊ የእድገት ምጣኔ፤ከሁሉም ክልሎች ባነሰ ሁኔታ በ1.7 % አስቀምጦታል፡፡ ግን እንዴት? ብአዴንስ በወቅቱ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን አቋም ነበረው? .
Table 1.3 Annual Population Growth Rate by Region between 1994-2007( ለበለጠ መረጃ  ገጽ 11ን ይመልከቱ)
3. የአማራ ብሄር ቁጥር በአሳሰቢ ደረጃ እየቀነሰ መምጣት፤
ሌላው አሳሳቢ እየሆነ የመጣው አንዱ ችግር፤ የአማራ ህዝብ ድርሻ/ሬሽዮ በትልቅ ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ነው፡፡ ለምሳሌ ከሚከተለው ሰንጠረዥ መመልከት እንደሚቻለው፤ እ.ኤ.አ. በ1994 ዓ.ም በተደረገው የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ወቅት፤የኦሮሞ ህዝብ 17 ሚሊየን፤የአማራ ደግሞ 16 ሚየን ነበር( ኦሮሞ 32.1 %፤አማራ 30.1 %) ፡፡ ነገር ግን ከ10 አመት በኋላ( 2007) በተካሄደ ቆጠራ፤ በሁለቱ ህዝቦች መካከል የታው የህዝብ እድገት ቁጥር እጅግ ገራሚ ነው፡፡ ይሄውም የኦሮሞ ህዝብ ቁጥር ከ25 ሚሊየን በላይ( 34.5%) ሲደርስ ፤የአማራ ህዝብ ቁጥር ደግሞ በ19 ሚሊየን( 26.9%) ገደማ ብቻ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ይህ ትልቅ ልዩነት ነው፡፡ግን ይሄ ጉዳይስ እንዴት ሊከሰት ቻለ? በዚህ ጉዳይ ዙሪያስ አዴፓ ምን አቋም ወስዶ ነበር? ስማኝ አዴፓ! ጥያቄ እያቀረብኩ ነው? ይሄን ሁሉ የምደክመው፤ጊዜ ኖሮኝ፤ገንዘብ ደልቶኝ አይደለም፤ጥያቄ ስላለኝ ነው፡፡
Table 2.2 Percentage Distribution of Major Ethnic Groups: 2007( ለበለጠ መረጃ ገጽ 16ን  ይመልከቱ)::
በዚህ ሁኔታ ከተቀጠለ የአማራ እጣ ፋንታ ምን ሊሆን ይችላል? አማራ በአጭር አመታት ውስጥ አነስተኛ ቁጥር ካላቸው ህዝቦች ተርታ ሊመደብ የማይችልበት እድል አይኖርም ብላችሁ ታስቡ ይሆን ?ለዚህ ሁሉ ክፍተት፤ በተለይም በሁለቱ ህዝቦች ( ኦሮሞና አማራ) መካል ለተከሰተው የቁጥር ልዩነት እነ “ብሄር የለንም”  ባይ አማራዎች ምን ያክሉን አስተዋጽኦ አበርክተው ይሆን? እስኪ ፈትሹት? ብቻ ነገሩ አሳሳቢ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ አማራ አንድ ሆኖ መነሳት አለበት ፤ ያለበለዝያ ሕወሀት በተራዘመ ሂደት “አማራን ወደ አናሳ ብሄርነት” መቀየር ይቻላል ብላ አስባ የሰራችው ስራ ፍሬ ማፍራቱን እያንዳንዱ አማራ ማወቅ አለበት፡፡
——————////——–———
4. የአማራ ህዝብ ቁጥር በትግራይ ክልል በተለየ ሁኔታ መቀነሱና የ ብአዴንና የፕላን ኮሚሽን ቢሮው  ነገር!
አንዳንዴ የኛ አማራዎች ነገር ይገርመኛል፡፡ አጀንዳችን ውስንነት ያለበት፤ወቅታዊሞቅ ሞቅ ሞቅ ይበዛበታል፡፡ ካነሳሁት አጀንዳ አንጻር ስነሳ፤ስለ አማራ ህዝብ ቁጥር መቀነስ ስናወራ፤በዋነኛነት ትኩረታችን ክልሉ ላይ ማድረግ ይታያል፡፡ ይህ ልክ አይደለም፤ መስተካከል አለበት፡፡ ስለ አማራ ህዝብ ቁጥር እንዲሁም የእድገት ምጣኔው ስናሰላ፤በክልሉ ውስጥ ስላለው አማራ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ክልሎች ስላለው አማራ ጭምር መሆን አለበት፡፡ ለምሳሌ ትግራይ/ኦሮሚያ ውስጥ የሚኖር አማራ ቁጥሩ እንዴት እያደገ ነው? የአማራው የእድገት ምጣኔ የትግሬው/ የኦሮሞው ህዝብ በሚያድግበት የእድገት ምጣኔ ልክ እያደገ ነው ወይ? ወዘተ… የሚሉትን ሁኔታዎች ጭምር መመልከት አለብን፡፡ ያለበለዝያ እይታችን ሸውራራ መሆኑ ነው፡፡ ለሁሉም አሁንም ይሄንን ጉዳይ የመከታተል አቅሙና እድሉ ያለህ አዴፓ ነህና ነቃ ብትል ጥሩ ነው፡፡
በዚህ ጉዳይ ዙሪያ አንድ የገጠመኝን አስደንጋጭ ነገር ላካፍላችሁ፡፡ በቅድምያ፡ እ. ኤ. አ. በ1994 እና በ2007 ዓ.ም የተካሄዱትን የህዝብና ቤት ቆጠራ ውጤቶች፤ከብሄር ስብጥር አንጻር በንጽጽር መመልከት ሊኖርብን ነው፡፡
በዚህም መሰረት በ1987/1994 ዓ.ም በተካሄደው የህዝብ ቆጠራ ሪፖርት መሰረት፤በትግራይ ክልል ውስጥ( በወልቃይት ብቻ) ይኖር የነበረው የአማራ ህዝብ ቁጥር 81, 279 እንደነበር ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡ ነገር ግን በ1999/2007 ዓ.ም በተካሄደው ቆጠራ ይህ የአማራ ህዝብ ቁጥር፤የትግራይ ህዝብ ባደገባት የእድገት ምጣኔ ብናሰላው እንኳን (በ 2.5%)፤ 81, 279*2.5*10 = 2,031:: ይህ ማለት በ2007 ዓ.ም በተካሄደ ቆጠራ ትግራይ ውስጥ በወልቃይት ብቻ ይኖር የነበረው አማራ ህዝብ ቁጥር  በ 2,031 ጨምሮ ከ83, 000 በላይ በሆነ ነበር፡፡ ነገር ግን የአማራ ቁጥር መጨመሩ ቀርቶ፤ በ1987 ዓ.ም ከነበረበት 81,279፤ ከ10 አመት በኋላ በትልቁ ቀንሶ 70,561 ሆኖ ተገኘ፡፡ ይህ ማለት ቢያንስ ከ13, 000 በላይ አማራ አድራሻው አልታወቀም ማለት ነው፡፡ አዴፓና የአብክመ ፕላን ኮሚሽን መ/ቤት እየሰማችሁኝ ይሆን?
 ይህ ጉዳይ ፡ እንዴትና ለምን እንደ ተከሰተ ጥልቅ ጥናት ያስፈልገዋል፡፡ ለጊዜው ግን በወቅቱ አንድ መቀሌ ዩንቨርሲቲ ውስጥ ይማር የነበረ የዐማራ ልጅ ስለ ጉዳዩ የነገረኝን ነገር ላንሳለችሁ፡፡ ይሄው የዐማራ ልጅ ትግራይ መቀሌ ዩንቨርሲቲ እያለ ከትግሬ ጓደኞቹ ጋር በትግራይ ስለ ዐማራ ሕዝብ ቁጥር እየቀነሰ መምጣት ሲጫወቱ፤ አንዱ ጓደኛው እንዳለው፣ ለቁጥሩ መቀነስ ምክንያቱ “ድሮ ዐማራ ነን ሲሉ የነበሩት ሰዎች አሁን ደግሞ ትግሬ ነን ብለው ስለተመዘገቡ ለዐማራው ቁጥር መቀነስ አንዱ ምክንያት ሊሆን ይችላል” ብሎ እንደነገረው አጫውቶኛል፡፡ በርግጥ ይህ ጉዳይ አንዱ ምክንያት ሊሆን ቢችልም፣ሌሎች ምክንያቶችም ይኖሩ እንደሆን ግን ሊታይ ይገባዋል፡፡ ለምሳሌ የወልቃይትና ጠገዴ፣የሁመራና የጠለምት አካባቢ ነዋሪዎች እየተፈናቀሉና እየተሰደዱ ወደ ዐማራና ሌሎች ክልሎች መምጣት ለቁጥሩ መቀነስ አንዱ ምክንያት ሆኖ ሊታይ ይችላል፡፡ ሌላም ምክንያት ሊኖር ይችላል፡፡
በነገራችን ላይ የዐማራ ሕዝብ ቁጥር በትግራይ ክልል ውስጥ ለምን እንደሚቀንስ ምክንያቱን ለማወቅ ፈልጌ፣ በ2008 ዓ.ም. ወደ ዐማራ ክልል ፕላን ኮሚሽን መ/ቤት ሂጄ ነበር፡፡ በወቅቱም የቢሮውን ኃላፊ (አቶ በድሉ) እና ሌሎቹን ባለሙያዎችን አግኝቼ ስለሁኔታው ስጠይቃቸው፤በወቅቱ ሁሉም ግንዛቤው እንዳልነበራቸው ነገሩኝ፡፡ በቀጣይ ግን ነገሩን እንደሚያጣሩት፣የደረሱበትን መረጃም እንደሚያሳውቁኝ ተነጋግረን ነበር የተለያየነው፤ ከዚያ በኋላ ምን እንደሠሩ መረጃ የለኝም፡፡ ስገምት ግን…..፡፡ ለሁሉም ትግራይ ውስጥ የሚገኝ የዐማራ ቁጥር ለምን እየቀነሰ እንደሚያድር፤ የትግራይ ሕዝብ በሚያድግበት ዓመታዊ የሕዝብ እድገት ምጣኔ ልክ ለምን አማራ ማደግ እንዳልቻለ መረጃ ያስፈልገናል፡፡ይሄን ጥያቄ መልስ ለመስጠት አቅምና እድሉ ያለው አሁንም አዴፓ ነው፡፡
——–///——-
5. ማጠቃለያ፡-
ከላይ ያነሳኃቸውን ነጥቦች በጥንቃቄ ልንመለከታቸው ይገባል፡፡ የዘንድሮ ህዝብ ቆጠራ ከነዚህ እንከኖች በጸዳ መልክ ስለመካሄዱ መከታተል ይገባል፡፡ ትኩረታችን መሆን ያለበት አማራ ክልል ውስጥ ስለሚካሄደው ቆጠራ ብቻ ሳይሆን፤ በመላ ኢትዮጵያ ያለውን አማራ ጭምር በማሰብ መሆን አለበት፤የአማራ መኖሪያው አማራ ክልል ብቻ አይደለም፤ሁሉም ክልሎች ናቸውና፡፡
በዚህ ጉዳይ መላው የአማራ ህዝብ በተለይም ወጣቱ እንቅልፉን ትቶ በመረጃ መደጋገፍ አለበት፡፡ አዴፓ ደግሞ መንግስታዊ ስልጣኑን ተጠቅሞ ስራውን ቢሰራ ጥሩ ነው፡፡ እኛ በአንድነት እንጅ በብሄር አናምንም “ብሄር የለንም” የምትሉ አማራ ወንድም/እህቶቸም ልብ ግዙ፤እንዳታስበሉን! ሁሉ እንደናንተ ቢያስብ ጥሩ ነበር፤ግን ሌላው ስለአንድነት የሚሰብከው እንደናንተ ብሄሩን ትቶ ሳይሆን፤ በብሄሩ ስም እየተመዘገበ ነው፡፡ ስለሆነም በአንድነት ፖለቲካ ማመናችሁን ባልቃወማችሁም፤በህዝብ ቆጠራ ወቅት ግን ይሄን “ብሄር የለኝም” የሚል ዘመኑን ያልዋጀ አባበል እንዳትጠቀሙበት፤ አደራ እንዳታስበሉን! ወቅቱ እንንተ እንደምታስቡት የቅንነት ወቅት አይደለም፤የብልጠትና ጥሎ የማለፍ ወቅት እንጅ፡፡ ስለሆነም ሌለው ብልጥ ሲሆን፤አማራ የሚጃጀልበት ነገር አይታየኝም፤ በተለይም የአዲስ አማራ ነቃ በሉ፤እንዳታስበሉን! አዴፓም በዚህ ዙሪያ ብትሰራ ጥሩ ነው፤ይሄ “ብሄር የለኝም” የሚል አባባል፤ ከአጭርም ሆነ ከረዥም ጊዜ አኳያ፤ በአማራ ህዝብ ላይ ሊያስከትል የሚችለውን፤ታሪካዊ፤ፖለቲካዊ፤ኢኮነሚያዊ፤ማህበራዊና ስነ-ልቦናዊ አደጋ አሳይ፤ አስተምር፤ሚዲያህንም ለዚህ ስራ ተጠቀምበት፡፡
ወቅቱ እንቅልፍ የምንተኛበት ወቅት አይደለም!!
Filed in: Amharic