>

የምነቅፍብህ ነገር አለኝ (ከይኄይስ  እውነቱ)

የምነቅፍብህ ነገር አለኝ

ከይኄይስ  እውነቱ

ከኢትዮጵያዊነት ጋር የተጣላው ወያኔ ትግሬ/ሕወሓት በብቸኝነት ሠልጥኖበትና ‹ግንባር› በሚለው አሸባሪ ድርጅት ሽፋን የተሰባሰቡ ቅጥረኛ አሽከሮቹ በኢትዮጵያ ምድር የባለጉበትን የአገዛዝ ዘመን ባንድ በቀደመ ጽሑፌ የዕብደትና ድንቁርና ዘመን ማለቴን አስታውሳለሁ፡፡ አሁንም ከዕብደትና ድንቁርናው ዘመን የወጣን አይመስለኝም፡፡ ምን ተይዞ ጉዞ! የአገዛዙ ሥርዓት፣ የሚመራበት ፍልስፍናና ርዕዮት (ካለው ማለቴ ነው – ለእኔ በጽሑፍ ያስቀመጡትም ሆነ በንግግር ሲያደነቁሩን የኖሩት ተራ ማጭበርበር አድርጌ ነው የምቆጥረው)፣ አስተሳሰቡና የአሠራሩ መንገድ ባልተለወጠበት ተጀምሯል የሚባለው ‹ለውጥ› ከአያያዙ ሳስተውል የእውር ድንብር ጉዞ ይመስላል፡፡ አገራችን አሁንም ዐቢይ በሚመራው የወያኔ ድርጅት በቆመ የማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥት› እና በዚሁ አማካኝነት በተፈጠረ የሐሰት ጐሣ ፌዴራሊዝም በሁከት፣ በሽብር፣ በድንቁርና ጭምር ከዳር እስከ ዳር እየተናጠች ትገኛለች፡፡ ማንም አመዛዛኝ አእምሮና ኅሊና ያለው ኢትዮጵያዊ ወያኔ ሕወሓትና አሽከሮቹ ባገራችን የተከሉት ነቀርሳ ባንድ ዓመት ወይም ባጭር ጊዜ ይወገዳል የሚል እምነት የለውም፡፡ ሆኖም አንዳንዶቹ የፀጥታና የደኅንነት ችግሮች ከቊጥጥር ውጭ መሆን የዐቢይ አገዛዝ ሕግና ሥርዓትን የማስከበር ዳተኝነትና ድክመት ውጤቶች መሆናቸው አያጠያይቅም፡፡

ባለፈው ‹ሕዝብ ለሕዝብ እንወቃቀስ› በሚል አስተያየቴ ራሴንም ጨምሬ በሕዝብ በኩል ያለውን ድክመት በመጠኑ በመግለጽ፣ የአገር ህልውና እንዲቀጥል እና ከዘመናት የአገዛዞች ፍርርቅ ወጥተን ነፃነት፣ እኩልነትና ፍትሕ የሠፈነበት የተሻለ ሥርዓት የምንፈልግ ከሆነ ለንግግራችንም ሆነ ለድርጊታችን በደቦ ሳይሆን በየግላችን ተጠያቂ መሆናችን ዐውቀን ፣ በጐሣ ውስጥ ሳንወሸቅ በኃላፊነት ስሜት እንቀሳቀስ፤ከድንቁርናና ዕብደቱ ወጥተን ‹ሰው› እንሁን በሚል (አስተዋይ ከተገኘ) የተሰማኝን አካፍዬአለሁ፡፡

ዛሬ ወደ አገዛዙ እመለሳለሁ፡፡ የ‹ፖለቲካ ትክክለኝነት› የሚባለውን ማሽሞንሞን ለፖለቲከኞችና ላገራችን ብዙኃን መገናኛዎች በመተው እንደ ወትሮው ያመንኩበትንና አእምሮዬን እናገራለሁ፡፡ ‹የምነቅፍብህ ነገር አለኝ› እያልኩ የማትታቸው አስተያየቶች ባንድ ርእሰ ጉዳይ ላይ ያነጣጠሩ ሳይሆኑ ‹ለውጥ› በተባለው ጉዞ ውስጥ ግራ ያጋቡኝን አገራዊ ፈትለ ነገሮችን ለማንሳት ያለመ ነው፡፡

  • ለዘመናት አገዛዞች በእጃቸው ጭብጥ በእግራቸው ርግጥ አድርገው በባርነት ሲያንገላቱት የኖረው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲህ ይላል፡፡ የምትመራው ድርጅት በወንጀል የተተበተበ ቢሆንም ከወንድምህ ለማ ጋር አገርን ለማዳን ያሳየህውን ቆራጥነትና ቅንነት፣ የፈጸምከውን ሥራህን ድካምህን ትዕግሥትህንም ዐውቃለሁ፡፡ ቀድሞውንም አላግባብ የታሰሩ እስረኞችን በመልቀቅ፣ በውጭ የሚገኙና  አሸባሪው ‹በአሸባሪነት› የፈረጃቸውን የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ወደ አገር ውስጥ ገብተው ዓላማቸውን በሰላም እንዲያራምዱ ማድረግህ (በኦነግ ረገድ ስህተት የፈጸምክ ቢሆንም)፣ ብዙኃን መገናኛዎች ባንፃራዊነት በነፃነት እንዲቀሳቀሱ መደረጉ፣ ባጠቃላይ አንፃራዊ የመናገርና የመጻፍ መብት መከበሩ፣ ገና ሥርዓት ባይዝም ከኤርትራ ጋር የጠብ ግንኙነት አቁሞ የሰላም ምዕራፍ መጀመሩ ወዘተ. ሕዝብ በአኮቴት ተቀብሎታል፡፡ ወያኔ ‹ግንባር› ብሎ በፈጠረውና አሁን አንተ በምትመራው ሽብርተኛ ድርጅት ውስጥ ቊጥራቸው ቀላል የማይባሉ አመራሮችና ካድሬዎች በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት መፈጸማቸውን እና በተደራጀ ዝርፊያ የፈጸሙትን ቅጥ ያጣ ሌብነትና ሌሎችም ነውሮች ታውቃለህ፤ ታግሠህማል፡፡ ዳሩ ግን የምነቅፍብህ ነገር አለኝ፡፡ ባይመርጥህም አብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ድጋፉንና አመኔታውን ቸሮህ፣ ተሰሚነት ያላቸው የውጭ መንግሥታትም ከጎንህ እንደሚሆኑ ቃል ገብተውልህ፣ ገና ከማለዳው ማስተዋል የተሞላበት የማያዳግሙ ርምጃዎችን እንደትወሰድ ተመክረህ ሳለ ለእውነተኛ የሥርዓት ለውጥ ቀዳሚ ተግባር የሆነውን፣ ላለፉት 27 ዓመታትና አሁንም አገራችን ለምትገኝበት ሁለንተናዊ ምስቅልቅል በዐቢይ ምክንያትነት የሚጠቀሰውን የወያኔ የይስሙላ ‹ሕገ መንግሥት› ሲሆን በሕዝብ ተሳትፎ እንዲቀየር፣ ቢያንስ በመሠረታዊ መልኩ ማሻሻል ሲገባ እስካሁን በዝምታ አልፈሀል፡፡ ሕዝብ ያመጣውን ለውጥ፣ ሥርዓትና መልክ አስይዞ አንኳር አገራዊ ጥያቄዎችን በመመለስ ሽግግሩን ለመምራት ያሰበ መሪ ነውረኛ ድርጅቱንና በግዙፍ ወንጀሎች ሊጠየቁ የሚችሉ አባላቱን የሚያስታምም ከሆነ በሕዝብ ዘንድ የመከዳት ስሜት አልፎም ትግሉና የከፈለው መሥዋዕትነት ከንቱ የመቅረት ስሜት ሊፈጥር እንደሚችል መገመት ያስፈልጋል፡፡

ቅድሚያ ለሰውነት፣ ቅድሚያ ለኢትዮጵያ ህልውና፣ ቅድሚያ ለሕዝባችን ደኅንነትና ለማይከፋፈል ግዛታዊ አንድነት፣ ቅድሚያ ለሕግ ልዕልና/ለፍትሕ የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ፡፡

  • ለዘመናት የተገፋውና በመንደርተኞች የገዛ አገሩን ባለቤትነት የተነጠቀው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲህ ይላል፡፡ ሥልጣንን ተገን አድርገው የኢትዮጵያን ሕዝብ ደም መጥጠው አጥንቱን ያስቀሩትን በአመዛኙ ከአንድ መንደር የተገኙ የተደራጁ ቱባ ሌቦችን በቊጥጥር ሥር የማዋል ጅምሩ በጎ ርምጃ እንደሆነ ተመልክተናል፣ በርትተህ እስመጨረሻውም ዝለቅበት ብለናል፡፡ ይሁን እንጂ ሌቦቹ ከተሸሸጉበት ሆነው ሲንጫጩ ዋናዎቹን ነውረኞች ወደ ዳኝነት የማቅረቡ ጅምር በመቋረጡ አዝነንብሃል፡፡ ስለዚህም የምነቅፍብህ ነገር አለኝ፡፡ ከሚጠረጠሩበት ግዙፍ የሰብአዊ መብት ጥሰትም ሆነ የአገርና ሕዝብ ሀብት ዝርፊያ ተጠያቂነት ለመሸሽ ‹ተደምረናል› የሚሉ አያሌ ግለሰቦች ባንተ አገዛዝ ዙሪያ ሹመት ተሰጥቷቸው ተከማችተዋልና እነዚህንም ሆነ በምትመራው ‹ግንባር› ውስጥ ባሉ ድርጅቶች በሙሉ እንዲሁም ‹አጋር› ባልካቸው ውስጥ የሚገኙ አውራና ግልገል የወንጀል ተጠርጣሪዎችን ወደ ፍርድ መድረክ እንዲመጡ ባለማድረግህ አስቆጥተህኛል፡፡ ጅምር ለውጡ ለመንግሥተ ሕዝብ፣ ለሕግ የበላይነትና እኩልነት ከሆነ በወንጀለኞችና በአእምሮ ድኩማኖች ሊመራ አይችልም፡፡ ወያኔ ሕወሓት ጠፍጥፎ በሠራቸው የጐሣ ድርጅቶች በወል እና በግለሰብ አባላት ደረጃ በተናጥል በሕዝብና አገር ላይ የተፈጸሙ ወንጀሎችን እንደ ሁኔታው በፍርድና ተበዳዩ ሕዝብ የሚስማማበትን በይቅርታና በዕርቅ ሥርዓት እንዲታይ ማድረግ ይቻላል፡፡ ሆኖም አንተ የምትመራው ‹ግንባርና› በውስጡ የሚገኙ አባል የጐሣ ድርጅቶች (አጋሮች የምትሏቸውን) ጨምሮ እስከ ግለሰብ አባላት በተለያየ ደረጃ በወንጀል ተጠርጣሪዎች በመሆናቸው ባንተ የሚቋቋም የዕርቅ ኮሚሽን በየትኛውም መመዘኛ አስከፊውን የታሪክ ምዕራፍ ይዘጋል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ምክንያቱም ማንኛውም ሰው በራሱ ጉዳይ ዳኛ ሊሆን አይችልም የሚል ዓለም አቀፍ የሕግ መርህ አለና፡፡ ተጠያቂው ዳኛ ሆኖ ከተሰየመ ወይም ሰያሚ ከሆነ ‹ዕርቁም› የለበጣ ነው የሚሆነው፡፡

ቅድሚያ ለሰውነት፣ ቅድሚያ ለኢትዮጵያ ህልውና፣ ቅድሚያ ለሕዝባችን ደኅንነትና ለማይከፋፈል ግዛታዊ አንድነት፣ ቅድሚያ ለሕግ ልዕልና/ለፍትሕ የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ፡፡

 

  • በኑሮ ውድነትና ከቤት ንብረቱ በመፈናቀል የበዪ ተመልካች በመሆን የድህነት ጥግ ውስጥ የሚገኘው ኢትዮጵያዊ ዜጋ እንዲህ ይላል፡፡

ንቅዘትን ÷ ሌብነትን መጸየፍህን እወድልሀለሁ፤ አገር ተረጋግቶ የሕዝብህ ኑሮ እንዲሻሻል እንደምትፈልግም ዐውቃለሁ፡፡ ዳሩ ግን የምነቅፍብህ ነገር አለኝ፡፡ ከውጭ መንግሥታት በዕርጥባን እና በብድር የመጣ ገንዘብ ባብዛኛው ባመራር ላይ ይገኙ የነበሩ አንዳንዶቹም አሁንም በሥልጣን ላይ ያሉ አመራሮች ለከት የሌለው ስግብግብነት ከአገር እንደሸሸና ለቤተዘመዶቻቸው መጠቀሚያ እንዳደረጉት ካንተ የተሠወረ አይደለም፡፡ በተለይም ሕወሓት የሚባለው ድርጅት በግንባር ቀደምትነት፣  ከዚያም በምትመራው ‹ግንባር› ውስጥ በሚገኙ 3 ድርጅቶች የሕዝብ ሀብት ተዘርፎ የተቋቋሙትን የወንጀል ፍሬዎች፣ ሕዝብ ለፍቶ በባንክ ያስቀመጠውን ጥሪት ፈቃጅ÷ተበዳሪና ብድር ሠራዥ በመሆን ሕዝብ በባንኮች ላይ እምነት እንዲያጣ ምክንያት የሆኑትን የፓርቲ የንግድ ተቋማት በሚገባ እያወቅኽ ዝም ብለሀል፡፡ የነዚህም በወንጀል የተቋቋሙ የንግድ ድርጅቶች ገቢ የግለሰቦችንና ቤተዘመዶቻቸውን ኪስ ከማዳበር አልፎ ሽብር ለመፍጠርና ለማከፋፈል እየዋለ እንደሆኑ የዐደባባይ ምሥጢር ሆኗል፡፡ ስለሆነም መናጢ ሆኖ በችጋር የሚጠበሰው ሕዝብ በዓይነ ቁራኛ እየተከታተለህ ነው፡፡ የወንጀል ፍሬ የሆኑት የፓርቲ የንግድ ተቋማት የሂሳብ ምርመራ ተደርጎ ከተቋቋሙበት ጊዜ ጀምሮ የሚጠበቅባቸውን ግብር ከነ ቅጣቱ፣ የባንክ ዕዳ ከነወለዱ ከከፈሉ በኋላ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የኢትዮጵያ ሕዝብ ንብረት ሆነው በሥራ እጦት የሚናጠው ወጣት የሚሠማራባቸው ድርጅቶች ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ችግሩ ውስብስብ ፈተናውም ከበድ ያለ ቢሆንም ባገርም በውጭም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሊረዱህ ዝግጁ ናቸውና ካንተ የሚፈለገው በዕቅድ÷በሕግና በሥርዓት ለማከናውን ያለህን ቁርጠኝነት ማሳየት ብቻ ነው፡፡ ይህ እንደሚደረግ ቃል ባልተገባበት፣ ዛሬም በንቅዘትና በሌሎች ነውሮች የተተበተቡና ከፊደል የተጣሉ የፓርቲ ሰዎች በየኤምባሲው እየተሾሙ ባለበት ሁኔታ በስደት የሚኖረው ኢትዮጵያዊ አንድ ብር እንዲያዋጣ የመጠየቁ ሞራል ከየት ይመጣል? በባዕድ አገር ደም ተፍቶ ሠርቶ ለሚያዋጣው ገንዘብ ምን ዋስትና አለው?

ቅድሚያ ለሰውነት፣ ቅድሚያ ለኢትዮጵያ ህልውና፣ ቅድሚያ ለሕዝባችን ደኅንነትና ለማይከፋፈል ግዛታዊ አንድነት፣ ቅድሚያ ለሕግ ልዕልና/ለፍትሕ የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ፡፡

 

  • የጐሣ ፓርቲ መዋቅሮች እንጂ ‹መንግሥት› በሌለበት፣ ከቀበሌ ካድሬ እስከ ወያኔ ሸንጎ የጐሣ ‹ባላባቶች› ሠልጥነውበት በፍትሕ እጦትና ተወዳዳሪ በሌለው የአስተዳደር በደል የተማረረው ኢትዮጵያዊው ወገን እንዲህ ይላል፡፡

 

በተበታተነም መልኩ ቢሆን አንዳንድ ተቋማትን እና አፋኝና ለአሠራር አመቺ ያልሆኑ ሕጎችን ለማሻሻል ፤ አንዳንድ ሲንከባለሉ የመጡ በዋናነት ፖለቲካ/ሥርዓት-ወለድ አገራዊ ችግሮችን ለመፍታት በማለም ኮሚሽኖችን፣ በርካታ ግብረ ኃይሎችንና ኮሚቴዎችን በሕግም ያለሕግም በማቋቋም የጀመርካቸው ውጥኖች እንዳሉ ዐውቃለሁ፡፡ ጅምሩ በጎ እንደሆነም እረዳለሁ፡፡ ዳሩ ግን በዚህም ረገድ የምነቅፍብህ ነገር አለኝ፡፡ እነዚህ ርምጃዎች ጥገናዊና የቅብ ይዘትና ቅርፅ ያላቸው መምሰል ባንድ በኩል፤ በሌላ ወገን ጎን ለጎን በየደረጃው የሚታዩና መናበብ ጭርሱኑ ያልጎበኛቸው ድርጊቶች መስተዋል፤ ስትጀመር የነበረህን ቅንነትና መሠረታዊ የሥርዓት ለውጥ ለማምጣት እየሠራህ መሆንህን እንድጠራጠር አድርገውኛል፡፡ ስለዚህ የምነቅፍብህ አለኝ፡፡ የሽግግር ጊዜ መሪም ብትሆን፣ የሽግግሩ ጊዜ አጭርም ይሁን ረጅም፣ ሁሉንም የኅብረተሰብ  ክፍሎች ባሳተፈ አገራዊ ጉባኤ ባጭር÷በመካከለኛና በረጅም ጊዜ የሚከናወኑ አንኳር አገራዊ አጀንዳዎችን ቅደም ተከተል በማስያዝ ሽግግሩ በኅብረተሰቡ ወሳኝ ተሳትፎ በሥርዓት መመራት እንዳለበት አገርን አጥርተው በሚያውቁ አንጋፋ ምሁራንና የአገር ባለውለታዎች ብተወተወትም በራስህ መንገድ ገፍተህበታል ፡፡ ጉዞአችንን የምናውቅበት ፍኖተ ካርታ ለማዘጋጀትና የቁርሾ ምዕራፍ ለመዝጋት እንዲህ ዓይነቱ ጉባኤ አስፈላጊ መሆኑን በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ይታመንበታል፡፡ በደፈናው ‹እኔ አሸጋግራችኋለሁ› የሚለው አዋጪ አይመስልም፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሞተው፣ ዘግናኝ ስቃያትን የተቀበለው፣ የተሰደደው፣ ከሰው በታች ሆኖ የተዋረደው፣ ለአገር ጥፋት ለሕዝብ እልቂት ምክንያት የሆነው ድርጅት (‹ግንባር›) ፈቃድ እንዲፈጸም አይደለም፡፡ የወያኔ ጐሣ ድርጅቶች እየተፈራረቁ እንዲገዙትም አይደለም፡፡ ከወያኔም ውጭ ያለ ለአንድ ጐሣ/ነገድ ጥብቅና የቆመ ድርጅትም እንዲገዛው አይደለም፡፡ ባለወር ተረኛ ዘረኛ/ጐሠኛ ከላይ እስከ ታች እንደ ንግድ ባንካችን እንዲሠለጥንበትም አይደለም፡፡ (ከዚህ ቀደም ባቀረብኩት አስተያየት እንደገለጽኩት ጥያቄው ለምን ካንድ ነገድ ሆኑ አይደለም፤ በየትኛውም መመዘኛ ብቃት ስለሌላቸው እንጂ፤ በወያኔ ሕወሓት በመንደርተኝነት ምክንያት በንግድ ባንክና በልማት ባንክ የተፈጸመውን ከፍተኛ ዝርፊያና የተአማኒነት ችግር ልብ ይሏል፡፡ በዚህ አያያዝስ ለፍቶ ጥቂት ጥሪት የያዘው ነጋዴም ሆነ ሠራተኛው ሕዝብ ገንዘቡን በባንክ እንዲያስቀምጥ የሚገፋፋውም ሁኔታ የለም፡፡ የቁጠባ ክምችት ዝቅተኛ ነው ብሎ ኅብረተሰቡንም መቀስቀስ ትርጕም አልባ ይሆናል)፡፡

የዐቢይ አገዛዝ ይህንን ቢያውቅም በቢሮክራሲው፣ በፀጥታው መ/ቤትና በሠራዊቱ የሚያደርጋቸው የኃላፊዎች ምደባ፣ ኃላፊዎቹም የሚሰበስቧቸው የበታች ኃላፊዎች ድርጅታዊ መሆኑ፤ አልፎ ተርፎም በወንጀል ተጠርጣሪ ነውረኞችን ባደባባይ ማወደሱ (አርከበንና ተወልደን ለአብነት ይጠቅሷል) ይህ ወንድማችን ምን ነካው በማለት ብዙዎችን አስደንግጧል፡፡ በተለይም ኦሕዴድ (አዴፓ) የተባለውና በሕወሓት ቦታ የ‹ግንባሩን› አመራር የተረከበው ድርጅት ጥቂት የማይባሉ አባላት በየተመደቡበት የሚያሳዩትን የወር ተረኝነት/ባለጊዜነት ጠባይ እንዲሁም የመንደርተኝነት አድራጎት በዝምታ ከማየትም አልፈህ በአዲስ አበባ ከተማ ከሕግ ውጭ ያስቀመጥከው የድርጅትህ ሹም እየፈጠረ ያለውን ምስቅልቅል እንዳለየህ መሆንህ ከፍተኛ ትዝብት ውስጥ ከቶሀል፡፡ ይህም በተዘዋዋሪ ዘረኝነትን/ጐሠኝነትን ማፅደቅ ካልሆነ ሌላ ምን ትርጕም ሊሰጠው ይችላል? ባገሪቱ የመጨረሻው የሕግ ባለሥልጣን አድርገህ ያስቀመጥከው ግለሰብ በብቃትም ሆነ በሞራል ልዕልና ረገድ በጭራሽ ለቦታው የሚመጥን አለመሆኑንም አጥተህው አይደለም፡፡ በድሬደዋ ከተማና ሕዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለውም ሕወሓት-ሠራሽ በደል መቀጠሉ የሽግግር አመራርህ የጎላ ሳንካ ነው፡፡

አገርን በማረጋጋቱና ሰላም በማስፈን ተግባር እንደተወጠርክ በሚገባ እናውቃለን፡፡ ያም ሆኖ ጅምር ለውጡ መንገዱን ሳይስት ለማስቀጠል የሚፈልጉ ብቃት ያላቸው በርካታ ኢትዮጵያውያን ከምትመራው ‹ግንባር› ውጭ መኖራቸውን በሚገባ እያወቅህ ወይም (ምክር በመጠየቅ) ማወቅ ሲገባህ የአገዛዞች የአፈና መዋቅር ሆነው ሕዝብ ሲያንገላቱ የነበሩ የወረዳ (የቀበሌ) እና የክ/ከተማ መዋቅሮች ባንዳንድ ቦታዎች ለውጥ እየተካሄደ መሆኑን እስክንጠራጠር ድረስ በለመዱት የድንቁርናና የንቅዘት መንገድ ቀጥለዋል፡፡ በዘመነ ሕወሓት የወጡ ኢፍትሐዊ የሆኑ ሕጎችን (እሱኑም ቢሆን ይዘቱና ትርጕሙ ሳይገባቸው) ተግባራዊ ለማድረግ በተለይም ከግል የመኖሪያ ቤቶች ጋር በተያያዘ እየፈጸሙ ያሉት ነውር ሕዝቡን እያማረረ ነው፡፡ ከመጥሪያ ወረቀት አቅም እንኳን በማስፈራሪያ የተሞሉና የንብረት ዋስትና የሌለበት አገር ለማስመሰል በሕገ ወጥ ቃላት የታጀሉ መሆናቸውን እየታዘብን ነው፡፡

አሁንም የምነቅፍብህ ሌላ ነገር አለኝ፡፡ አገዛዝህ በቢሮክራሲው ውስጥ በአመዛኙ የድርጅት ሰዎች ከመመደብ ባለፈ ቢሮክራሲውን የለውጥ መንፈስ ጭርስኑ የጎበኘው አይመስልም፡፡ በለመደው አሠራር ቀጥሏል፡፡  እዚህም እዚያም የየተቋማቱን ሕጎች ለመከለስ የተቋቋሙ ጊዜያዊ ኮሚቴዎች እንዳሉ ብንሰማም ባንዳንድ ቦታዎች ከአባላት ምደባ ጀምሮ ከብቃት ይልቅ በትውውቅ የሚፈጸምበትና ግልጽነት የሌለው አሠራር ነግሦ ይታያል፡፡ ሥራው ባጠቃላይ የዘመቻና የውክቢያ ጠባይ ዐይሎበት ይታያል፡፡ ለአብነት ያህል (ባንድ ወቅት የመስተንግዶ ጊዜን በማሳጠር ‹ምስጉን› ተብሎ የተሸለመው) የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ የተቋቋመበት ሕግ የተሻሻለው በቅርብ ጊዜ ቢሆንም በተለይ በየቅርንጫፉ ያሉ ሠራተኞች (ዋናውን ጽ/ቤትም ጨምሮ) በአመዛኙ በጐሣ መጓተትና በፖለቲካ ታማኝነት የተመለመሉ በመሆናቸው፣ አንዳንዶቹ የወረቀት ማስረጃ ቢይዙም በተግባር ዕውቀቱ የሌላቸው፣ ማሰብ ያቆሙ የሚመስሉና ሕጉንም ሆነ በባለ ጉዳይ የሚቀርቡ ፈርጀ ብዙ ጉዳዮችን በዘፈቀደና ያለአሳብ በ‹ቼክ ሊስት› ብቻ የሚስተናገድ (mechanical) ማድረጋቸው፣  ከሁሉም በላይ ባለጉዳይን ከፍ ዝቅ አድርገው የሚናገሩና ከማስረዳት ይልቅ ዘለፋ የሚቀናቸው፣ ሠንሠለታዊ ከሆነ የንቅዘት አሠራር ያልፀዱ፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በሕግ ከተፈቀዱና የመንግሥት አስተዳደር መ/ቤቶች ተፈጻሚ ከሚያደርጓቸው ጥቂት ስታንዳርድ ውሎች (adhesive contracts) በስተቀር በሕግ የተሰጠ የመዋዋል ነፃነትን የሚያሳጡ አስገዳጅ ውሎችን ያለበቂ ጥናት በማዘጋጀት (በነገራችን ላይ “templates/samples” መሠረታዊ ይዘትን ለማሳየት በአማራጭነት የሚዘጋጁ እንጂ አስገዳጅ አይደሉም) ባለጉዳዮችን እያጉላሉ ይገኛሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል የቤት ሽያጭና ኪራይ ውሎችን በሚመለከት፡፡

ወደ ቀደመ ነገራችን ስንመለስ ዕውቀትና ልምድን ከሠናይ ሥነምግባር ጋር የየዙና የበሰሉ ዜጎች ወደ ጎን የተገፉበት ሁኔታ በስፋት ይስተዋላል፡፡  በተለይም በቢሮክራሲው ውስጥ እንደኔ ‹‹ጐሣ/ነገድ አልባ›› የሆኑ÷ የኢትዮጵያ ሉዐላዊ ግዛት በሙሉ ባለቤት ነኝ ብለው የሚያስቡ ዜጎች ቦታ የላቸውም፡፡ ምንም እንኳን አብዛኛው የሕዝባችን ክፍል ወጣት ቢሆንም ባለፉት 27 ዓመታት በነበረው ከፋፋይና ጐሣን መሠረት ያደረገ የፖለቲካ ሥርዓት ምክንያት (በግልና በቤተሰብ ጥረት ጥቂት የተረፉ ከሌሉ በቀር) አብዛኛው ትውልድ ገዳይ በሆነ የትምህርት ሥርዓት የጠፋ (በየትምህርት መስኩ ማወቅ የሚገባውን መሠረታውያን የሳተ)፣ አገራዊ ስሜቱ የደከመ፣ በሞራል የተንኮታኮተ፣ በሥራ አጥነት ተስፋ የቆረጠ መሆኑ አገዛዝህ የተረከበው መራር እውነት መሆኑን መዘንጋት የለበትም፡፡ ስለሆነም ከገባንበት ማጥ ለመውጣት ከፈለግን ባገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ዐዋቂዎችን መጠቀምና ወጣቶችም በሥራቸው ሆነው ዕውቀት፣ ልምድና ክህሎት እንዲያዳብሩ ማድረጉ፣የባከነውንም ጊዜ የሚያካክሱበት የሥልጠና መርሐግብር ነድፎ መንቀሳቀሱ  ሁሉንም አትራፊ ያደርጋል፡፡

በዳኝነቱም ረገድ ማሻሻያ ለማድረግ የተደራጀ ግብረ ኃይል እንዳለ ሰምተናል፡፡ ጅምሩንና አሳቡን በበጎነት እንመለከተዋለን፡፡ ይሁን እንጂ በዚህም ረገድ የምነቅፍብህ ነገር አለኝ፡፡ ለመሆኑ መዓዛም ሆነች አገዛዝህ (የዳኝነት ጉዳይ በመሆኑ ጣልቃ አልገባሁም ቢባል እንኳን ስለተመደቡት ግለሰቦች ዕውቀቱ የለህም ተብሎ አይታሰብም) ለዚህ ታላቅ ተግባር የተመረጡትን አንዳንድ ሰዎች ብቃትም ሆነ በሞራል ልዕልና ረገድ ያላቸውን ስብእና ዐውቃችሁ ነው ቡራኬ ሰጥታችሁ የተሠማሩት? ነገሩ ታጥቦ ጭቃ እንዳይሆን ኧረ ባካችሁ እናስተውል፡፡ በፖለቲካው ረገድ አገር ሲያምሱ የነበሩ ሆድ አደር የግፍ ተባባሪዎች እንዲሁም የዳኝነቱን ሥርዓት ለፖለቲካ ዓላማና ለአስፈጻሚው አካል ምርኮኛ በማድረግ በሕዝብ ሕይወት፣ ነፃነትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ደባ ሲፈጽሙ የቆዩ እንዳሉበት አጥታችሁት ነው? ወይስ ‹ተደምረው› ነው ብለን መራር ቀልድ እንናገር? ባጠቃላይ (ምክንያቱ ማናቸውም ይሁን) ኢትዮጵያ ከወያኔ ድርጅት ውጭ ሰው የላትም ወይ? ክፉ ልማድ ሆኖ ይሆን የአሠራራ መንገዳችን/ዘዴአችን እና ቋንቋችን ኹሉ ከወያኔያዊ ቅኝት ያልወጣው? እግረ መንገዴን ሳላነሳ የማላልፈው ደግሞ በዓፄ ኃ/ሥላሴና በደርግ አገዛዞች ወቅት ነፍስ ያወቁ ሰዎች የወያኔ የጐሣ ሥርዓት የፈጠራቸውን መርዘኛ ቃላት (ለምሳሌ፤ ‹ብሔር÷ብሔረሰቦችና ሕዝቦች›፣ ‹ክልል›፣ ‹አቅጣጫ ማስቀመጥ› ወዘተ.) ሳይጎረብጣቸው መጠቀማቸው በእጅጉ ይገርመኛል፡፡  

በመጨረሻም ባንድ ወገን ሕዝብን ለማስደሰት በሌላ በኩል ነውረኞችንም ላለማስከፋት የሚደረገው በሁለት ልብ የማነከስ ጉዳይ÷ በራድ ወይም ትኩስ ሳይሆኑ ለብ ማለት ከሕዝብ አፍ መተፋትን ያስከትላልና ከሁለት ያጣ ሆኖ እንዳያስከፍል ብርቱ ጥንቃቄና አስተውሎት ያሻል፡፡ ባሮጌ አቁማዳ አዲስ ወይን ማኖሩ ከቀጠለ ድካምህን ሁሉ ከንቱ እንዳያደርገው ሥጋት አለኝ፡፡ አሁንም ከ‹ልጆች› ጋር ሳይሆን አገርን ከሚያውቁ ከበሰሉ ኢትዮጵያውያን ጋር መምከር÷ደጋግሞ መምከር ያስፈልጋል፡፡

ቅድሚያ ለሰውነት፣ ቅድሚያ ለኢትዮጵያ ህልውና፣ ቅድሚያ ለሕዝባችን ደኅንነትና ለማይከፋፈል ግዛታዊ አንድነት፣ ቅድሚያ ለሕግ ልዕልና/ለፍትሕ የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ፡፡

Filed in: Amharic