>
5:36 pm - Wednesday November 30, 2022

የእነ በረከት ስምኦን የጠበቃ ማቆም ጉዳይ (ውብሸት ሙላት)

የእነ በረከት ስምኦን የጠበቃ ማቆም ጉዳይ

ውብሸት ሙላት

አቶ በረከት በወንጀል ድርጊት ተጠርጥረዉ በቁጥጥር ሥር ይገኛሉ፡፡ ተጠርጥረዉ ምርመራ እየተከናወነባቸዉ ባሉትም ሆነ ገና ምርመራ ባልተጀመረባቸዉ የወንጀል ድርጊቶች የፖሊስ ምርመራ ይቀጥላል፡፡ ክስም ይቀርባል፡፡ የፍርድ ሒደቱም ይቀጥላል፡፡

ይህ በሚሆንበት ጊዜ

በአቶ በረከት ዘመን በራሳቸዉ ትእዛዝና በግል ዉሳኔ ያደርጉት እንደነበረዉ ዓይነት የፍርድ ሒደት መቀጠል የለበትም፤ይሆናል የሚል ጥርጣሬም የለኝም፡፡

በምርመራ ወቅትም ምንም ዓይነት ኢ-ሰብኣዊ ድርጊት ሊፈጸም አይገባም፤ይፈጸምባቸዋል የሚል ጥርጣሬም የለኝም፡፡

አቶ ታደሰ ካሳ በዋናነት የአማራ ሕዝብንና (አገዉንም ቅማንትም ጨምሮ) ክልሉ በድለዋል፤ወንጅል ፈጽመዋል፡፡ አቶ በረከትም ቢሆኑ ፍጹም ጭካኔና ጥላቻ በተሞላበት ሁኔታ የአማራን ሕዝብ በድለዋል፡፡ ሁለቱም ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ዉለዉ ምርመራ እየተደረገባቸዉ ያሉት ጉዳዮች በዋናነት ጥረት ጋር የተያያዙ ናቸዉ፡፡ ጥረት ደግሞ ምንም እንኳን እንዳሻቸዉ ሲመዘብሩት ቢኖሩም፣ የይስሙላም ቢሆን ለአማራ ክልል ሕዝብ ሲባል የተቋቋመ ነዉ፡፡ ብዙዎቹ ድርጅቶችም ክልሉ ዉስጥ ያሉ ስለሆነ ወንጀላቸዉን መርምሮ፣ ከስሶ፣ ዳኝነት የመሥጠት በሕግ ችሎታና ሥልጣን አለዉ ክልሉ፡፡

ለበረከትም ሆነ ለታደሰ ካሳ ተከላካይ ጠበቃ የክልሉ መንግሥት የመቅጠር ሃላፊነት አይኖርበትም፡፡ የዘረፉት ገንዝብ እንኳን ጠበቃ ለመቅጠር ይቅርና የግል አዉሮፕላን፣ መርከብ፣ ደሴት ወዘተ ለመግዛት በቂ ነዉ፡፡

ለበረከትና ለታደሰ ካሳ ጥብቅና ለመቆም ወይም ላለመቆም መወሰን ያቃታቸዉ ጠበቆች በስልክ የግል ምክር እንድለግሳቸዉ ጠይቀዉኝ ነበር፡፡ በአንድ በኩል እነዚህ ጠበቆች እኔን ስለሚያዉቁኝ፣ በሌላ በኩል ለአቶ በረከትም ይሁን ለአቶ ታደሰ ያለኝን ጥላቻ (ለአማራ ሕዝብ ያላቸዉ ጥላቻና ያደረሰቡት በደል ምናልባትም ከፋሽስት ኢጣሊያ በባሰ ዉስብስብና ጥልቅ ስለሆነ፣ ያደረሱት በደል በገንዘብም ይሁን በሌላ ነገር ሊለካና ሊሰላ ስለማይችል) ስለሚያዉቁ ይሆናል፡፡ በወንጀል መጠየቅ እንዳለባቸዉም በይፋ መግለጼን ስለሚያዉቁ ይሆናል፡፡

የእኔ አስተያየትም በጠበቃ ሥነ ምግባር የሚጠይቀውም የሚያስገድደዉም አንድን ወንጀል ሰቅጣጭ፣አስነዋሪ፣ቀፋፊ ወዘተ ነዉ በማለት ጥብቅና አልቆምም ስለማይባል፣የጥብቅና ፈቃድም ስለሚያስነጥቅ ለሙያቸዉ ክብር በመስጠት አገልግሎት እንዲሰጡ ነዉ፡፡

ይሁን እንጂ፣አቶ በረከትም ሆኑ አቶ ታደሰ በግል እጅግ አስነዋሪ ወንጀሎችን የፈጸሙባቸዉ ግለሰቦች ስላሉ እንዲሁም የአማራን ሕዝብ ያልፈጸሙበት ወንጀል ስለሌለ ከሙያዊ ግዴታ ባለፈ ምንም ዓይነት ተግባር እንዳይፈጽሙ እንዲሁም በደላቸዉ አስነዋሪም ስለሆነ ሕዝብ ጋር እልህ ዉስጥ የሚከት ተግባር እንዳይገቡ ነዉ በማሳሰቢያነት የጠቆምኩት፡፡

ለአቶ በረከትም ሆነ ለታደሰ ጥብቅና መቆም የሚችሉት በአማራ ክልል በማናቸዉም ፍርድ ቤት ጥብቅና ለመቆም የሚያስችል ፈቃድ ያላቸዉ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ ማለት ከአማራ ክልል ፍትሕ ቢሮ (ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ) የአንደኛ ደራጃ የጥብቅና ፈቃድ ያላቸዉ መሆን አለባቸዉ ማለት ነዉ፡፡ በአማራ ክልል የጥብቅና አገልግሎት መሥጠት የሚያስችለዉ የጥብቅና ፈቃድ የሌለዉ ሰዉ ጠበቃቸዉ ሊሆን አይችልም ማለት ነዉ፡፡ በመሆኑም ከፌደራል፣ከመቀሌ ወዘተ ጠበቃ እየፈለጉ ነዉ መባሉ፣ ፈልገዉ ቢያገኙም ከአማራ ክልል ያወጡት ፈቃድ ከሌላቸዉ የጥብቅና አገልግሎት መስጠት አይችሉም፡፡ ክልክል ነዉ፡፡

ሌላዉ አቶ በረከት ኢንተርኔት የለም ኢንተርኔት መጠቀም እንደሚፈልጉ ለፍርድ ቤት መጠየቃቸዉን በተለያዩ ሚዲያዎች እየተዘገበ ነዉ፡፡ እንኳን ኢንተርኔት መጽሐፍ እንዳይገባ ሲያስከለክሉ አልነበር፡ መታሰር ማለት ምን እንደሆነ የማያዉቅ ለ27 ዓመታት አገር ሲመራ/ሲያፈር ነበር? አሳዛኝ ነዉ! መረጃ ወደ ማረሚያ ቤት እንዴት እንደሚገባ እና እንደሚወጣ የማያውቅ ሰዉ አገር ጭንቅላት ላይ ተቀምጦ ኖረ:: ያሳዝናል!

ለማንኛዉም ጠበቃቸዉ መሆን የሚፈልግ ወይም እነ አቶ በረከት የሚፈልጉት ጠበቃ (ዎች) ጥብቅና ይቁሙላቸዉ፡፡ የአማራ ሕዝብ ፍትሕ እንዲዛባ አይፈልግም፡፡ ፍትሕ እንዲሰፍን እንጂ! እሥራትም ይሁን የገንዘብ ቅጣት፣የሞት ፍርድም ይሁን የጉልበት ሥራ… ብቻ ሕጉ የሚፈቅደዉን እንዲፈረድባቸዉና እንዲቀጡ ነዉ ፍላጎቱ፡፡ ሕዝቡ እንደ በረከትና ታደሰ ያለ ፍርድ ቤት ዉሳኔ፣ ያለ ፍትሐዊ ሥርዓት እርምጃ እንዲወሰድ አይሻም፡፡ በረከትና ታደሰ የመማሪ ዕድሜ ባይኖራቸዉም ሌሎቹ ይማሩበት፡፡

Filed in: Amharic