>

አጼ ኅይለሥላሴ የአፍሪካ አባት የጥቁር ሕዝቦች ንጉስ! (ሀይለገብርኤል አያሌው)

አጼ ኅይለሥላሴ የአፍሪካ አባት የጥቁር ሕዝቦች ንጉስ!

ሀይለገብርኤል አያሌው

ከአመት በፊት  ወደ አሜሪካዋ እሩቅ ደሴት ሃዋይ ሄደን ነበር:: እዛም ቢግ አይስላንድ በተባለ ለብቻው ተነጥሎ ባለ ደሴት የጥቁር ዘር ማየት ብርቅ ነው:: አብዛኛው ነጭ እና የጃፓንና የቻይና መልክ ያላቸው የሃገሬው ሰው የሚብዛበት ነው:: በዚያ ጥቁር ማየት ብርቅ በሆነበት ውብ ደሴት ገበያ ውስጥ ስንዞር የኢትዮጵያ ባንዲራ አንብሳው ያለበትና በተለያየ ግዜ የተነሳ ፎቶና በሰዓሊዎች ቀለማት በሕብር የተንቆጠቆጠ የጃንሆይ ስዕላት ደምቀው የሚታዩበት ሱቁ ደረስን::

ለባለሱቁ ራስተፈራውያን ኢትዮጵያዊ እንደሆንን ሃይለስላሴም ንጉሳችን እንደሆኑ በኩራት ለልጆቻች እየገለጽን እያለ የሱቁ ባለቤት በቁጣና በንቀት ለዛ ባለው አማርኛ እናንተ ኢትዮጵያውያን ንጉሳችንን የት ታውቁትና ታሪክ አጥፍታችሁ ታሪክ ታወራላችሁ በሚል ሃይለቃል ተቆጣን:: እናንተ እኮ ቅዱስ መሬት ላይ መቆማችሁን የማታውቁ መሃይሞች : ባህር ላይ ቆማችሁ ውሃ የምትጠሙ ሰነፎች ናችሁ:: አያችሁ ለኛ ለካሪቢያን ሕዝቦችና ለአፍሪካውያን ኢትዮጵያን ቅዱስ ምድር ጃ  ደግሞ ከአምላክ የተላከ ነብይ ነበር :: እናንተ ግን ይህን አታውቁም :: ስለዚህም ሰድባችሁ ገደላችሁት :: ሻሸመኔ ኖሬያለሁ ኢትዮጵያን በሙሉ አይቻለሁ :: ንጉሳችንን በመግደላችሁ ገና ብዙ ትቀጣላችሁ:: እኛ ግን ይህው በታሪኩ እየኮራን በጸሎትም እያሰብነው እንኖራለን:: በማለት እስከ ዶቃ ማሰሪያችን ነግሮ ለልጆቹም እንዲረዱት በእንግሊዝኛ የሃይለስላሴን ታላቅነት የጥቁር ሕዝብ ንጉስነትና የአምላክ መልዕክተኛ መሆን ዘርዝሮ በማስረዳት ወደፊት ሲያድጉ ይህንን እውነት እንዲፈትሹ መክሮ የሃይለስላሴ ፎቶ ያለበት የደረት ባጅ ሸልሞ ተለያየን::

እንደዛን ግዜ በራሴ ያፈርኩበት ግዜ የለም:: የምንመልሰው መልስ የምንሰጠው ሃሳብ እስኪጠፋ ድረስ የራስን ታሪክ በሌላ የሩቅ ሰው ሲነገርና የወቀሳ መአት ሲወርድ የሚፈጥረው መሸማቀቀ ቃላት ሊገልጸው አይችልም:: ያ ሰው ያን ሁሉ ውርጅብኝ ሲያወርድብን ንዴትና ብሽቀት ቢሰማኝም ንግግሩና ቁጣውን ግን በቅጡ ለመረዳት እረጅም ግዜ ወስዶብኛል::

እውነት ነው ባለፈው ግማሽ ክፍለዘመን እኛ ኢትዮጵያውያን የቁልቁለት ጉዞ ውጪ እንኳን ሌሌች ሕዝቦች የሚዘክሩት የኛ የምንለው በጎ ነገር ምን አለን:: ንጉሱን ከቀበርን ጀግኖችን ካዋረድን አዋቂዎችን ከዘረጠጥን  በሗላ የት ደረስን:: ሞት እረሃብ ስደትና ውርደት የኛ መገለጫ አልሆኑምን? ጃንሆይን አይተው የአድዋ ድል የነጻነት ችቦ ብርሃን ሆኖቸው ከባርነት እስር ቤት የወጡ : እንደ ሰንጋ ከብት ከመሸጥና መለወጥ ትላንት የዳኑት : ብዙዎቹ የአፍሪካ ሃገሮች በስልጣኔ በኢኮኖሚና በዲሞክራሲ አልፈውን ሲሄዱ እኛ ግን የት ነው ያለነው?

እግዚአብሔር መርቆ የሰጥንን ሃገር ታሪክና የክብር መክሊት አክብረን መያዝ ባለመቻላችን ሌሎች ከበሩበት የኛ አባቶች በከፈቱት የነጻነት መንገድ ሌሎች ወደ ለምለም   መስክ ተጏዙበት:: እኛ ግን ወደ ቆንጥርና ወደ ቁልቅለት  የኮረኮንች መንገድ ወረድን:: ከዛሬም ይልቅ የነገው ከባድ እየሆነብን ነው:: ለዚህ ሁሉ ቀውስ ደግሞ ምክንያት የትላንት አባቶችን ማድረጋችን ችግራችንን ውስብስብ መፍትሄውንም እሩቅ አድርጎታል::

ታሪክ የለሽ ታሪክ አውሪ ትውልድ ትላንት ሌኒን ለተባለ ባዕድ ሃውልት ስናቆም ከዛም የጥላቻ ግንብ የሃሰት ሃውልት ጀግኖችን ማቆሸሻ የሻጋታ ፖለቲካ የትንሽነት መግለጫ የድንቁርና ማሳያ አኖሌ የተባለ በሃሰት ድርስት ላይ ቆመን ድንጋይ ስናቆም በጎውና መልካሙ ተረሳ::

ለሃይለስላሴ ለሚኒሊክ አይደለም ለሁሉም የሃገራችን ጀግኖች ለነደጃች ባልቻ  ለነእራስ አሉላ ለሌሎቹም መታሰቢያ ለኛም ኩራትና ክብር እንዲሆን አይደለም በሃገራችን በሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ከተሞች ሃውልት እንዲቆምላቸው ባደረግን ነበር:: የኢትዮጵያ የትላንት ጀግኖች ክብራቸው ሃገራዊ ብቻ ሳይሆን እህጉራዊም ጭምር ነው::

የታላቁ ንጉስ የቀዳማዊ ሃይለስላሴ ሃውልት ዛሬ በዶር አብይ በጎ ጥረት በአፍሪካ ሕብረት ጽ/ቤት ቅጥር ግቢ መቆሙ መልካም ነው:: በእራሳችን ሗላ ቀር የፖለታካ ሽኩቻ ይህ ሃውልት መቆም ከነበረበት እጅግ ዘግይቷል :: ሃውልቱ ቆመ አልቆመ የሃይለላሴን ታሪክ አያስቀርም:: ማንም ወደደም ጠላው ክብርና ሞገስ የነበረው የሃይለስላሴን የአፍሪካ የነጻነት አባትነትና የጥቁር ሕዝቦች ንጉስ የመሆን ታሪክ መለወጥ አይቻልም::

ክብር ለጀግኖች አባቶቻችን!

Filed in: Amharic