>
2:10 am - Wednesday February 1, 2023

በተቃዋሚ ድርጅቶች ላይ የሚደረገው ማዋከብ ይቁም፣ የፖለቲካ እስረኞች በሙሉ አሁኑኑ ይፈቱ! ሸንጎ

ኅምሌ 2፣ 20006

Abrha Desta, Yeshiwas Assefa, Daneil Shibeshi & Habtamu Ayalewማክሰኞ ኅምሌ 1፣ 2006 ( July 8፣ 2014) የህወሓት/ኢህአዴግ መንግስት በሀገሪቱ ውስጥ በህጋዊነትና በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች አመራር አባላት ከሆኑት ውስጥ አቶ ሀብታሙ አያሌውንና አቶ ዳንኤል ሽበሽን ከአንድነት ፓርቲ፣ አቶ የሽዋስ አሰፋን ከሰማያዊ ፓርቲ እንዲሁም አቶ አብረሀም ደስታን ከአረና ፓርቲ ማሰሩን ተረድተናል።
የተጠቀሱት ግለሰቦች በሀገራችን ውስጥ ያለው የመብት መረገጥ፣ የፍትህ መጥፋት፣ የህግ የበላይነት አለመኖር ፣ ግፍ ስቃይና መከራ እንዲያበቃ ምሳሌ የሆነ ትግል በሰላማዊ መንገድ ሲያካሂዱ የቆዩ ለመሆናቸው እጅግ ብዙ መረጃ መጥቀስ ይቻላል።

በተደጋጋሚ እንደገለጽነው እነዚህን ታጋዮች ከቆራጥ የትግል ሰሜታቸው ለማደናቀፍ ከቶውንም አይቻልም። ዛሬ ሃብታሙ አያሌውን፣ ዳንኤል ሽበሽን፤ የሽዋስ አሰፋንና አብረሀም ደስታን ስቃይ በበዛበት እስርቤት ውስጥ አፍኖ ማሰቃየት ይቻላል፤ እነዚህን ግለሰቦች፣ ከወዳጅ ዘመዶቻቸውና ከህጻናት ልጆቻቸው መለየት ተችሏል። ሆኖም ግን የነሱን አስተሳሰብ፣ የነሱን ራዕይና እምነት ማሰር ከቶውንም አይቻልም። ወደ እስር ቤት በመወርወር ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር መለያየት ቢቻልም፣ በሚሊዮኖች ከሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው ጋር ግን ያለውን ያስተሳሰብ አንድነትና የራዕይ መቆራኘት ከቶውንም መበጣጠስ የሚችል ምንም ሀይል የለም።
ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ብቻ የታየውን ሁኔታ ብናገናዝብ ፣ የህወሓት/ ኢህአዴግ እርምጃዎች ከልበ ሙሉነትና ከጥንካሬ የመነጩ ሳይሆን፣ ከመርበትበትና የሚይዝ የሚጨብጠውን ከማጣት የተነሱ እንደሆነ እንገነዘባላን። በራሱ የሚተማመንና የህዝብ ድጋፍ አለኝ የሚል መንግስት ምርጫ በመጣ ቁጥር የተቃዋሚ ድርጅት መሪዎችን ወደ አስር ለመወርወር አይጣደፍምና። ሕዝባዊ ድጋፍ ያለው መንግሥት ቢሆን ኖሮ፣ ከተቃዋሚ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት አላቸው በሚባሉ መገናኛብዙኃን ቃለመጠይቅ አካሂደዋል በሚል ተልካሻና ጸረ ዴሞክራሲ ሰበብ፣ ሰላማዊ ታጋዮችን ለማሰር ባልተጣደፈ ነበር። እውነቱን ለመናገር፣ በተጠቀሱት የተቃዋሚ ድርጅቶች መገናኛ ብዙሀን የራሱ የገዥው ቡድን አባላት ሳይቀሩ ቀርበው ቃለመጠይቅ አድርገው እንደነበር (ለምሳሌ ስብሀት ነጋ) የሚታወሰው ነው። ይህ ሆኖ እያለ በዚህ አይነት ሰበብ የተቃዋሚ ድርጅት መሪዎች ለእስር መዳረጋቸው የሚያሳየው መንግስታዊ ሽብርን ያለ መአቀብ ለማካሄድ እንዲያስችለው ያወጣውን “የፀረ አሸባሪ አዋጅ” አገዛዙ ምን ያክል ሕዝብን ለማፈንና ሰላማዊውን ትግል ለማዳከም እንደፈለገው እንደሚጠቀምበት ነው። ይሁን እንጂ፣ እየጠነከረ የመጣው የህዝብ ቁጣ የተቃዋሚ ድርጅት መሪዎችን በማሰር የሚገታ አይደለም። የህዝብ ቁጣ መሰረቱ የፍትህ መዛባት፣ ተስፋ ሰጭ ኢኮኖሚ አለመኖር፣ የአድሎና በደል መስፋፋት፣ የመብት መረገጥ…. ወዘተ እንደመሆኑ መጠን፣ እነዚህ ሁሉ መፍትሄ ባላገኙበት ሁኔታ ህዝብን ሰጥ-ለጥ ማሰኘት ከቶውንም እንደማይቻል ህወሓት/ኢህአዴግ ሊገነዘበው ይገባል።በተደጋጋሚ እንደገለጽነው፣ የህወሓት/ ኢህአዴግ መሪዎች ለሚወስዱት እያንዳንዱ እርምጃ የሚከተለውን ውጤት ደግመው ደጋግመው ሊያስቡበት ይገባል። ከህዝብ ተነጥለው በህዝብ ተጠልተው እንደበረገጉ መኖር አንዱ አማራጫቸው ነው። ሌላው ደግሞ ለ23 ዓመታት ያካሄዱት የግፍና የጭቆና ስርዓት ውጤት እንደሌለው ተገንዝበው ከቀጣይ ጥፋት መቆጠብና ያጥፊና ጠፊ ፖለቲካ አዙሪት ከሀገራችን ውስጥ እንዲጠፋ ሁሉንም አሳታፊ የሆነ ብሄራዊ መግባባትና እርቅ እውን ሊሆን የሚችልበትን መንገድ ማመቻቸትና እውን ማድረግ ነው። ይህ አማራጭ ለሁሉም የሚበጅና የወደፊቱን ትውልድም በአመጽ ከተሞላ የፖለቲካ አዙሪት የሚያድን ነው። ይህ ሂደት የሚጀመረው የፖለቲካ እስረኞችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በመፍታት ነው።
በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር የሚገኘውም ኢትዮጵያዊ በሰሜታዊ ጉዳዮች ሳይምታታ የህዝቡ የነጻነት ራዕይ እውን የሚሆንበትን ትግል በመደገፍ የነጻነት ቀን ባስቸኳይ እውን እንዲሆን ጥረቱን እንዲቀጥል ጥሪያችንን በድጋሚ እናሰማለን። ሀብታሙ አያሌው፣ ዳንኤል ሽበሽ፣ የሽዋስ አሰፋና አብረሀም ደስታ ባስቸኳይ ይፈቱ። የፖለቲካ እስረኞች በሙሉ ባስቸኳይ ይፈቱ።
ድል ለኢትዮጽያ ህዝብ

የኢትዮጵያ ህዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ

Filed in: Amharic