>
5:01 pm - Wednesday December 3, 8719

ይድረስ ለአዲስአበቤ ውዲቷ ወዳጄ! (ኤርሚያስ ለገሰ) 

ይድረስ ለአዲስአበቤ ውዲቷ ወዳጄ!
ኤርሚያስ ለገሰ 
 
ውዲቷ ወዳጄ!
ከተለያየንበት ጊዜ አንስቶ ለጤናሽ እንደምን ከርመሻል። ከእግር ጥፍሯ እስከ ራስ ፀጉሯ የታመመችው መዲናችን ሰሞኑን እንዴት ከረመች? በሽታዋን መርምሮ ካንሰሯን የሚመነግል፣ ጋንግሪኗን ቆርጦ የሚጥል የፓለቲካ ዶክተር አገኘች ወይ? ወይንስ አሁንም አቤ ጉበኛ እንዳለው በጉጉት የሚጠበቀው የፓለቲካ ዶክተር “አልወለድም!” ብሎ አስቸገረ ወይ? አዲስአበቤ ” ቆንጆዎቹ ገና አልተወለዱም!” ከሚለው ቅኝት መውጣት አልቻለም?
ውዲቷ ወዳጄ! 
ሰሞኑን የአዱገነት አየር በእነዛ አጉራ ዘለሎች ፀያፍ አንደበት ተበክሎ እንደነበር ከሰደድሽልኝ መልዕክት መገንዘብ ችያለሁ። በአዲስ አበባ መርከብ የተሳፈረው አዲስአበቤ ሲነጋገር የከረመው በእነዚህ ሃሳብ የሚፈሩ ከአፍንጫቸው ርቀው የማያዩ ትናንሾች መሆኑን ተገንዝቤያለሁ። ሁኔታው አዲስ አበባ መልሕቋን የምትጥልበት ስፍራ እንዳልደረሰች አመላክቶኛል።
 ለካስ የአዲስአበቤ የጨለማ ዘመን ገና አልተገፈፈም? ለካስ ገና ነው? እንደው መከራ ጠሪና ሟርተኛ እንዳትይኝ እንጂ ስለ አዲስ አበባና አዲስአበቤ ሳስብ በከፍተኛ ሁኔታ የሚያሳስበኝ ነገር አለ። ይኸውም ከትላንት እና ከዛሬው በላይ የወደፊት የአዲስአበቤ ሁኔታ ፈጽሞ አደገኛ እንደሆነ እነግርሻለሁ። ለአዲስ አበባ መጪው ጊዜ ከትላንቱ በማይተናነስ ከባድ ነው። መራሩን ሃቅ ለመጋፈጥ በቂ የማታገያ ሃሳብ መያዝ ይጠይቃል።ይሄን የምገልጥልሽ አንቺና አዲስአበቤ በፍርሃት ቆፈን እንድትሸበሩ አይደለም።
 አስቀድመሽ እንደምታውቂው እኔ በቀቢፀ ተስፋ የምኖር ሰው አይደለሁም። እንዲያም ሆኖ ይህ ወቅት ለአዲስአበቤ መልካም ወቅት አለመሆኑ ይሰማኛል። ወትሮም እንደምልሽ ዘመኑ ” የተረሳችው አዲስ አበባ፣ ኖሮ የሌለው አዲስአበቤ” የሚለው አገላለጥ አሁንም አልተቀየረም። የሀሳብ ትግሉ እስኪጀመር ድረስም የሚለወጥ አይደለም።
 እርግጥ ሰሞኑን በተፈጠረው ሁኔታ በመጠኑም ቢሆን ማዘኔን አልደብቅሽም። ነገር ግን ሙሉ ለሙሉ ቅሬታ አልተሰማኝም። ምክንያትም አለኝ። ደጋግሜ እንደገነገርኩሽ  እኔ የምከተለው “የሌውንስ የለውጥ ሞዴል” ( Lewins 3 step change model) ነው። በዚህ አይነት የለውጥ ሞዴል የመጀመሪያ ምዕራፍ ላይ እንዲህ አይነት መጥፎ አጋጣሚዎች እንደሚከሰቱ በሰፊው ይዘረዝራል። አሁን በአዲስ አበባ እየሆነ ያለው ይሄ ነው።  በዚህ የመጀመሪያ ምእራፍ ሽብርን፣ እልቂትንና የመንፈስ ጭንቀትን አልፎ ሄዶም የአገር ጥፋትን የሚያስከስቱ የሀሳብ ጐልያዶች እንደ አሸን የሚፈሉበት ነው።
ውዲቷ ወዳጄ!
ከዚህ በፊት እንደገለጥኩልሽ አዲስአበቤ “የፀጉራም ውሻ” ጩኸት በተነሳ ቁጥር ስፍራውን መልቀቅ የለበትም። ታላቁ መጽሐፍ የአጉራ ዘለሎች ዛቻ የተነሳብህ እንደሆነ ስፍራህን አትልቀቅ ይላል። ቦታውን የለቀቀ ማረፊያ ጣቢያውን ለሌላ ባይተዋር የሚለቅበት ሁኔታ ይፈጥራል። አካባቢውን የለቀቀ በቦታውና በስፍራው አዲስ መወለድ አይችልም። ቦታን መልቀቅ እነዚህ የጥፋት መልዕክተኞችን፣ በጥላቻና በመከፋፈል በሽታ አእምሮአቸው የታመሙትን የልብ ልብ መስጠት ነው። ቦታን መልቀቅ ማለት ለፓለቲካ ነጋዴዎችና ቁማርተኞች መዲናይቱ ባለቤት የሌላት ከሚያስመስሉ የእለት ተእለት ትርኢቶች መጋበዝ ይሆናል።
ውዲቷ ወዳጄ!
መቼም ለአንቺ ያለኝ ስስትና አክብሮት የተለየ ነው። አዲስአበቤ ከታሰረበት የአካልና የመንፈስ ባርነት ነፃ እንዲወጣ የምታደርጊው ትግል በታሪክ የሚታወስ ነው። አዲስአበቤ ተስፋ የራቀው መስሎ በታየበት ፣ የአዲስአበቤን እውነተኛ ፍላጐት በድፍረት የሚመራ ሐይል የውሀ ሽታ በሆነበት ወቅት ግንባር ቀደም በመሆንሽ አከብርሻለሁ።በዚህ ትጋትሽ ከጥቂቶች አንዷ በመሆንሽ እሳሳልሻለሁ።
 እርግጥም አዲስአበቤ ከአንቺ ብዙ ትምህርት ቀስሟል። በመዲናይቱ ላይ አደጋ መጣሁ መጣሁ እያለና በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ በዝምታ መቆየት የሚጸጽት ነው።  እውነቱን ንገሪኝ ካልሽኝ እነዚህ ፀጉራሞች መዲናይቱን ወደ አደገኛ አቅጣጫ ሲመሯት ያውም በአዱገነት እምብርት ላይ ተቀምጠው በምንተዳኤና በመሐል ሰፋሪነት መኖር ወንጀል ነው። አዲስአበቤ ላይ ካራና ሜጫ መዘው እልቂትና ብጥብጥ ሲደግሱ በምንቸገረኝነት መመልከት ሐጢያት ነው። እደግመዋለሁ ስርዬት የሌለው ምድራዊ ሐጢያት ነው። መንግስትስ ቢሆን ከዜሮ ተነስቶ በሃያ ሚሊዮን ብሮች የግል መኖሪያ ቤት ሲገዛ ከየት መጣ ብሎ አይጠይቅም? የአዲስ አበባ አስተዳደር አይጠይቅም? በመንግስት ስልጣን ላይ ያላችሁ ግለሰቦች በበለፀገችው አሜሪካ ከ10ሺህ በላይ ትራንዛክሽን ሲካሄድ የአሜሪካ ደህንነት ቢሮ እንዲያውቅ ይደረጋል ብላችሁ ዲስኩር ስታሰሙ አልነበረም? ለምን የተናገርነውን መኖር አቃተን? ግለሰቦቹ የገንዘብ ላውንደሪ እየሰሩ መሆኑ በደህንነቱ እየታወቀ ለምን ዝም ተባለ? ኸረ ለመሆኑ የተዘረፈው የ18 ባንኮች ከ10 ሚሊዮን ያላነሰ የደሃ ገንዘብ የት ገባ? አዲስ አበባ ላይ ቪላ ተገዛበት? ዘረፋውን አዲሳአባ ቁጭ ብሎ የመራው እና ዘራፊው ተጠየቀ? ያሳፍራል። ማፈሪያዎች!!
 ያም ሆነ ይህ አዲስአበቤ ለሃሳብ ካራ አልፎ ከሄደም በጉልበት ለመከላከል መደራጀት ይኖርበታል።
ውዲቷ ወዳጄ፣
ሰሞኑን በሰደድሽልኝ መልዕክት ላይ አዲስአበቤ የኢትዮጵያ ሕዝብ አይንና ጆሮ የሆነውን ኢሳት ለመቀበል ሽር ጉዱን አጠናክሮ ቀጥሏል። ወትሮም ቢሆን ውለታውን የማይረሳው አዲስአበቤ ለኢሳት አክብሮቱን ለመግለፁ በነቂስ እንደሚወጣ ሳይታለም የተፈታ እንደሚሆን አውቃለሁ። ይህም ሆኖ በመዲናይቱ ነዋሪዎች መኩራቴን ልሸሽግሽ አልፈልግም። እርግጥም ላለፉት ክፍለ -ዘመናት በጠላቶቿ እንደ አሮጌ ቁና የተወረወረው አዲስአበቤ ያንዣበበትን ስጋት መተንፈስ የቻለው የራሱ ሚዲያ በሆነው ኢሳት ነበር። ሙት ወቃሽ አታድርጊኝና የአራዳ ልጆች መለስ ዜናዊ የሚባል ትልቁ ዳቦ ሊጥ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ የተመለከቱት በኢሳት አማካኝነት ነው። አዲስ አበባ ባለቤት አልባ፣ አዲስአበቤ ደግሞ ” ኢትዮጵያዊ አልቢኖ” ሆኖ በጠራራ ፀሀይ አጥንቱ ሲጋጥ ከፊት የደረሰለት ኢሳት ነው። የህውሓት አገዛዝ አዲስአበቤን ሲያፈናቅል፣ መሬት ወረራውና ነጠቃው የተደራጀ መንግስታዊ ሌብነት እና ዝርፊያ መሆኑን ኢሳት ሲወተውት ሌሎች እንደ መዓት ጠሪ ይቆጥሩት ነበር። አልፎ ሄዶም እነዚህ የሚዲያ ተቋማትና ጋዜጠኞች ከህውሓት ጋር በመጃመል አዲስአበቤን በመዝናኛ ፕሮግራም ሲያዘናጉት ነበር። ዛሬ የኢሳትን አጀንዳ ተቀብለው በማስተናገዳቸው ከፍተኛ ደስታ ይሰማናል። ከሽሽት እና ሀሜት ተላቀው የጨለማውን ግርዶሽ ለማሳየት ሲሽቀዳደሙ ስናይ ድካማችን ፍሬ ማፍራቱን እንመለከታለን። የኢሳት አንዱ ስኬት ምንአልባትም ዋነኛው የድል ውጤት ይኸኛው ነው። የኤሌክትሮኒክስ ነፃ ሚዲያ ማኃፀን ከፋች በመሆናችን ልንኮራ ይገባል።  ኢሳት እና የኢሳት ባልደረቦች የከፈሉት መስዋእትነት እንደተጠበቀ ሆኖ!
 
ውዲቷ ወዳጄ፣
አዲስአበቤ በቀጣዩ ቅዳሜ ” መንገዶች ሁሉ ወደ ሚሌኒየም አዳራሽ ያመራሉ!” በማለት የሚተመው ለትላንትናው ውለታ ብቻ አይደለም ያልሽው ትክክለኛ አባባል ነው። እዚህ ላይ በተጨማሪነት የማቀርበው ወሳኝ ነጥብ አለ። ኢሳት በስምንት አመት ጉዞው ያስተናገዳቸው አያሌ ጉዳዮች አሉት። የአገዛዙ ጠንቅ በመሆን በሽብርተኝነት ተፈርጆም ነበር። ከደሃው በተሰበሰበ ገንዘብም ከ28 ጊዜ በላይ ከሳተላይት እንዲወርድ ተደርጓል። ምንአልባት በኢትዮጵያ የሚዲያ ታሪክ ውስጥ ለዚህ ያህል ጊዜ እየወጣና እየወረደ የቀጠለ ሚዲያ በብቸኝነት ሊጠቀስ የሚችለው ኢሳት እና ኢሳት ብቻ ነው። ይሄ ብቻ አይደለም። የጨለማውን ስርአት ለማጋለጥ በኢሳት የቀረቡ ኢትዮጵያውያንም መከራ ደርሶባቸዋል። አገዛዙ ” እኔን ያየህ ተቀጣ” በሚል ጨካኝ እርምጃው የስቃይ ብትሩን አሳርፎባቸዋል። ኢሳት ስምንተኛ አመቱን ሲያከብር ብቻውን ሳይሆን ከእነዚህ የመስዋእትነት ቀንዲሎች ጋር በመጣመር ነው። እነሱ ባይኖሩ ኖሮ ጨለማው በብርሃን አይሸነፍም ነበር።
ውዲቷ ወዳጄ!
ከላይ በመልእክትሽ እንዳሳሰብሽኝ የአዲስአበባ የነፃነት ትግል ከሄደበት ያልሄደበት ይበልጣል። ሰላማዊው የሃሳብ ትግሉ ተጀመረ እንጂ አልተጠናቀቀም። ለሃሳብ ትግሉ ደግሞ እንደ ኢሳት ያሉ የሚዲያ ውጤቶች የማይተካ ሚና አላቸው። በኢትዮጵያችን ብሎም በመዲናችን ዲሞክራሲ ያሸንፍ ዘንድ ኢሳት የበላይነቱን መቀዳጀት አለበት። በአጭሩ   በምንወዳት አገራችን በምንሳሳላት ከተማችን ፍትሕ፣ ዲሞክራሲ፣ እኩልነት እና የአገር ባለቤትነት እንዲረጋገጥ የኢሳት መጠናከር ወሳኝነት አለው። ኢሳት ካልተጠናከረ የአዲስአበቤን የሰላማዊ ትግል ራዕይ ተርጉሞ ማስተጋባት አይችልም። ኢሳት ካልተጠናከረ የዘር ፓለቲካ ነጋዴዎች የሀይል ሚዛኑን አዛብተው እና የሚዲያ ድባቡን ተቆጣጥረው አዲስአበቤ ራሱን በራሱ ለማስተዳደር እንዲያስችለው የመደራጀት ፍላጐቱ ሊመክን ይችላል። እናም የቀጣዩ ቅዳሜ አዲስአበቤ ወደ ሚሌኒየም አዳራሽ የሚያደርገው ጉዞ የህልውናው መረጋገጥ ነው።
ዘረኞቹ ሰባት መቶ እና ስምንት መቶ ኪሎሜትር ተጉዘው በአይሱዙ ደጋፊዎቻቸውን ያመላለሱት ወደ ኢትዮጵያ የመጣውን ሀይል ለመቀበል ብቻ አልነበረም። እንደውም የአቀባበሉ ፊታውራሪዎች ለመጪው ሃይል የመረረ ጥላቻ ያላቸው ናቸው። በአደባባይም መጪው ሃይል ከሞተ ቆይቷል ብለው እስከ መፃፍ የደረሱ ናቸው። ይሁን እንጂ አጋፋሪዎቹ ዛሬም ድረስ የሆዳቸውን በሆዳቸው ይዘው ያደረጉት እንቅስቃሴ ያጋጠማቸውን የህልውና አደጋ በጊዜያዊነት ለመሻገር በማሰብ ነበር። ለዚህም ነበር የገነቡት የእምቧይ ካብ ሲናድ ” ከምርጫ በኃላ እንገናኝ” በሚል የአጉራ ዘለሎች ድንፋታ የተሞሉት። ስለዚህም የቅዳሜው የአዲስአበቤ በነቂስ ወደ ሚሌኒየም አዳራሽ መትመም አጉራዘለሎችን ዳግም የመቅበር እርምጃ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። ከዚህ አንፃር ካየነው አዲስአበቤ በመጪው ቅዳሜ የሚያሳየው ንቅናቄ አላማ ከኢሳትም በላይ ነው። የመጪውን የአዲስ አበባ እጣ ፈንታ የሚወስን ይሆናል። መለወጥ ወይም መሞት!
ውዲቷ ወዳጄ፣
ለዛሬ ዘለግ ያለ መጣጥፌን የሰደድኩልሽ አበይት ጉዳይ ስላጋጠመኝ ነው። አንቺም ለነፃነትሽ የምታደርጊው ትግል አጠናክረሽ እንድትቀጥይ የሃሳብ ድጋፍ ለማድረግ በማሰብ ነው። ለሌላ ጊዜ እጥር ምጥን አደርገዋለሁ። ከዛሬው በዚሁ ይብቃኝ። ከቻልሽ ቅዳሜ ከሚሊኒየም አዳራሽ በቢልቢላ ልታገኝኝ ሞክሪ። ሰላም።
       ……//……
ማሳሰቢያ:  ” አዲስአበቤ” ሌላ ትርጉም እስካልተሰጠው ድረስ አዲስ አበባ በመወለድ የሚገኝ ማንነት አይደለም።
Filed in: Amharic