>
5:18 pm - Saturday June 15, 1213

ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የከተሞች ቀን ክብረ በዓል አስመልክቶ ያስተላለፉት መልዕክት!!! (ኢ.ፕ.ድ)

ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የከተሞች ቀን ክብረ በዓል አስመልክቶ ያስተላለፉት መልዕክት!!!
ኢ.ፕ.ድ
አንድ አካላችን ታሞ ሙሉ ጤና ሆኖ ውሎ ማደር ይቻል ይሆናል። መክረም ግን አዳጋች ነው። የታመመ አካላችንን ማከም የምንችለው ደግሞ የተባበርን የተደመርን እንደሆነ ነው!!
የዘንድሮ የኢትዮጵያ ከተሞች ቀን በጅግጅጋ ከተማ ይከበራል። ከተሞች የደረሱበትን ደረጃ የሚመዝኑበት፣ ልምድ  የሚለዋወጡበት፣  የላቀ  ልማትና  የሥራ  ውጤት፣  የተሻለም  አስተዳደር  ያስመዘገቡ  የሚመሰገኑበትና የሚሸለሙበት  መድረክ  ነው።
የዘንድሮው  በዓል  በተለይም  የኢትዮጵያዊነትን  ቀለምና  ውበት  የምንዘክርበት፤ መደመር ለከተሞች ሰላምና ብልጽግና መሠረት መሆኑን የምናጠናክርበት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
በሀገራችን    በየጊዜው    እየጨመረ    የመጣውን    ከገጠር    ወደ    ከተማ    ፍልሰት    በብልሐትና    በብቃት የሚያስተናግዱ፣  ለነዋሪያቸውም  ሆነ  ለአድሮ  ሂያጅ  ምቹ  የሆኑ፣  የኅብረ  ብሔራዊነታችን  ማሳያና  ከራስ አልፎ በሌሎች የሚወደዱ፣ ለሀገር ሰላምና ልማትም አስተዋጽዖ የሚያደርጉ ከተሞችን ለመፍጠር መትጋት  የክብረ  በዓል  ብቻ  ሥራ  አይደለም፡፡  እንድናስታውስና  እርስ  በእርሳችን  እንድንማማር  መድረክ ይከፈታል እንጂ።
በመሆኑም ይህን በዓል ስናከብር የተሠራውን እያደነቅን፣ እየተማማርን፣ የቤት ሥራችንንም እየለየን የምንንደረደርበት ይሆናል።
ባለፉት   ጥቂት   ወራት   ኢትዮጵያ   እያስመዘገበች   ካለቺው   ለውጥ   አንፃር   ከተሞቻችን   የመደመር መናኸሪያዎች፣   የትሥሥርና   የአንድነታችን   መገመጃዎች   እንዲሆኑ   መሥራት   ያለብን   ወቅት   ላይ እንገኛለን። በመደመር እሳቤ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የትም ሄዶ መሥራት፣ መኖር፣መበልጸግና ከሌሎች የሀገሩ ልጆች ጋር እኩል ሀብት የመጋራት ሕገ መንግሥታዊ መብቱን መጠቀም እንዲችል ከተሞች የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት መዘጋጀት አለባቸው።
የከተሞች ለነዋሪዎቻቸው ምቹ፣ በቂና ጥራት ያለው መሠረተ ልማትና አገልግሎት ለመስጠት አስተዳደርን ማቀላጠፍ፣ ሥራ አጥነትን መቀነስ፣ የመሬት አስተዳደርን ማሻሻል፣ አረንጓዴነትን ማስፋፋትና ቴክኖሎጂና ፈጠራን ተጠቅሞ መሠልጠን ዋና ተግባራቸው ነው።
የለውጥ አቅጣጫችንም በሁሉም የአሠራር መዋቅሮች ይህንኑ ሕዝብ ተኮር የሆነ የአገልግሎትና የተቋማት ግንባታን ይሁነኝ ብሎ እስከ ታች  ድረስ  ለማዳረስ፤  የሰው  ኃይልና  የፋይናንስ  ዐቅሙን  በማደራጀት  ተጨባጭ  ተቋማዊ  ማሻሻያዎች አድርጓል።
ይህም በአንድ ጀምበር ሳይሆን በሂደት በሁሉም ከተሞች የሚታይ ለውጥን እንደሚያመጣ አያጠራጥርም።  ከዚህ  አንጻር  የከተማ  ነዋሪዎች  የሚያነሡዋቸው  ፍትሐዊና  ምክንያታዊ  የመኖሪያ  ቤት፣ የውኃ፣ የኤሌክትሪክ፣ የትራንስፖርት፣ የመንገድ፣ የጤና፣ የፍሳሽና ቆሻሻ አወጋገድ ወዘተ ጥያቄዎችን ለመመለስ እነዚሁ የመንግሥት መዋቅሮች ተግተው ይሠራሉ።
የከተሞች ቀንን ስናከብር ሌላው ማሰብ ያለብን ስለ ከተሞቻችን የእርስ በእርስ ትብብር፣ መማማርና መረዳዳት ነው። ይህ ሲሆን አንዳችን ከአንዳችን ስኬትም ሆነ ስሕተት ትምህርት እየወሰድን ሀገራዊ ዕድገታችንን የበለጠ ለመደገፍ መንገድ እንከፍታለን። የሀገራችን ለውጥ እየበሰለ፣ እየጎመራ፣ ሁሉም ዓይኑን ወደ እኛ እየጣለና “ምን እናግዛችሁ፣ እንዴትስ የዚህ ታሪካዊ ክስተት አካል እንሁን?” የሚልበት ወርቃማ ጊዜ ላይ እንገኛለን።
ወርቃማው ጊዜ ዋጋ እንዲኖረው የውጭም ሆነ የሀገር ውስጥ ሙዓለ ንዋይን ለመሳብ የማንተኛ፣ ለመማር የምንፈጥን፣ ለመተባበር የማንለግም፣ ለመለወጥ የምንጓጓ መሆንን ይጠይቃል። ሌሎች ከኛ ለመጠቀም ሲችሉ እኛ እራሳችንን እንዴት እንጥቀም የሚል አስተሳሰብን ሰንቀን መጓዝም የግድ ይለናል።
ኢትዮጵያውያንም በኢትዮጵያ ውስጥ እስካለን እኩል ተጠቅመን ለመበልጸግና ሀገር ለማልማት ኢትዮጵያዊ መተባበርን መገንዘብ፣ በመደመር መገናዘብን ይጠበቅብናል።
አንድ አካላችን ታሞ ሙሉ ጤና ሆኖ ውሎ ማደር ይቻል ይሆናል። መክረም ግን አዳጋች ነው። የታመመ አካላችንን ማከም የምንችለው ደግሞ የተባበርን የተደመርን እንደሆነ ነው።
ይህንኑ እሳቤ ይዘን ነገ ማየት ለምንፈልጋት የልጆቻችን ኢትዮጵያ፣ ዛሬ   ተባብረን   መሠረት   መጣል   አለብን፡፡   ለዚህ   ደግሞ   ከተሞቻችንን   የኅብረት   ዐውድማ   ማድረግ ይጠበቅብናል።
ከተሞች  በዜጎችና  በብሔሮች  ስብጥር  የኢትዮጵያ  ናሙና  ናቸው፡፡  ከተሞችን  የኅብረት ዐውድማ ስናደርግ የምርት፤ የጉልበትና የአገልግሎት ግብይቱ ለሁሉም ትሩፋት ያመጣል፤ ከተሞችን የኅብረት  አውድማ  ስናደር  የሁሉም  ድምጽ  ተሰምቶ  ፍትሕና  ርትዕ  አካል  ይነሣል፡፡  ከተሞችን  የኅብረት ዐውድማ ስናደርግ ብዝኃነት ያላቸው ማንነቶች የተደመረ ጥበብ አፍልቀው ፈጠራ ይበልጥ ይመጥቃል፤ ይጠልቃል፡፡
የዘንድሮን የከተሞች ቀን ስናከብር ከተሞች የቁሳዊ ልማታቸው ደረጃ የት እንደደረሰ ከመፈተሽ ባሻገር በከተሞች   ውስጥ   በቋሚነት   የሚኖሩ   ኢትዮጵያውያን   ዜግነታቸው   እንዲከበር፣   ፍላጎትና   ጥቅማቸው እንዲጠበቅ፣ ፈጠራቸው እንዲያብብ የሚያስችል በመደመር መንፈስ ልምድና ሐሳብ የምንለዋወጥበት፤ ስኬትን የምናወድስበት፤ ከውደቀትም ትምህርት የምንወስድበት ሊሆን ይገባል፡፡ ከተሞቻችንን የሥልጣኔ ማዕከላት   ለማድረግ   ከነዋሪዎች፣   ከአልሚዎች   እና   ከመላው   ኢትዮጵያውያን   ቅን   ልቦናና   ተጨባጭ እንቅስቃሴ  ይጠበቃል፡፡
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ፣ ተከብራና በልጽጋ ለዘላለም ትኑር!” ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
የካቲት 8፣ 2011  ዓ.ም
Filed in: Amharic