>
8:21 am - Saturday November 26, 2022

ብዕር ፣ ክላሽኒኮቭ እና ሥልጣን . . . ! (አሰፋ ሀይሉ)

ብዕር ፣ ክላሽኒኮቭ እና ሥልጣን . . . !
አሰፋ ሀይሉ
አንድ ሰሞን – በምርጫ 97 ማግሥት – አቶ በረከት ሥምዖን በሚቆጣጠረው የመንግሥት የኮሙኒኬሽን ቢሮ አማካይነት በየቤታችን በየ30 ደቂቃው በየፕሮግራሞች ጣልቃ ቋቅ እስኪለን ድረስ እየተደጋገመ እንዲለቀቅልን የተደረገ አንድ መንግሥታዊ መልዕክት ነበረ። እንዲህ የሚል ፦
<<ሕጋዊነትን እና ኢሕጋዊነትን እያጣቀሱ፤
በመንታ መንገድ ላይ መጓዝ አይቻልም!!>> የሚል።
መልዕክቱ ለዚያኔዎቹ የቅንጅት ለአንድነትና ለዲሞክራሲ መሪዎች የሚተላለፍ ሾርኔ ነበረ መሠለኝ። የምን ሾርኔ?! ለምን ይዋሻል?!! ሙ ጅ ር  ያለ ግልፅ ያደባባይ ማስጠንቀቂያ ይባል እንጂ።
እና ግን አሁን አቶ በረከት ኢንተርኔት ባይኖራቸውም ይኸው የያኔ ቃላቸውን አንስቼ በድረ-ገፅ አኑሬያለሁ። ያኔስ ይሄ ለማን ነበረ የሚገባው? አሁንስ ላይ??? ስለዚህ ነገር እርስዎ ምን ይላሉ??፦ <<ሕጋዊነትን እና ኢሕጋዊነትን እያጣቀሱ በመንታ መንገድ ላይ መጓዝ አይቻልም!!>> (ወይ??!!!)
ነገሩማ.. ያኔ… የአብዬን ወደ እምዬ ነገር ነበረ ነገሩ። “በሌባ ጣትህ በሌላው ላይ ስትጠቁም ሶስቱ ጣቶችህ ደሞ መልሰው በራስህ ላይ የሚጠቁሙብህ” ዓይነቱ እውነታም ነበረው። ወይም አለው። ይሄንኑ እውነት – በወቅቱ – በአንድ ሳምንታዊ ጋዜጣ ላይ – “ሕገመንግሥቱን እየገደሉ ማዳን” በሚል ርዕስ – በብዕር ስሜ አውጥቼው ነበረ። የዚያ ሳምንቱ ዕትም የጋዜጣው የመጨረሻ ዕትም ሆኖ ቀረ። የእኔም። አሁን ያኔን እና ያንን እንተወው። እና ይቅር ጥያቄው። ይቆየን መልሱም። አሁን ወደ ፎቶግራፉ እንሸጋገር እስቲ በሠላም።
ይሄን ፎቶ… አንዴ… በአንድ ምሽት ላይ… እንደ ነርቭ አድርጎ ሲነሽጠኝ… ከአላሚ ስቶክ ፒክቸርስ… በውድ ዋጋ ገዝቼ ለእውነት መታሰቢያ እንዲሆነኝ በብቻዊ ዶሴዬ ቆልፌ ያኖርኩት ተለቅ ያለ ፎቶ ነው። ኦሪጂናሉን ለአላሚ አርካይቭስ እንካችሁ ያላቸው በበርካታ የፎቶ ስብስቦቹ የታወቀው ኔይል ኩፐር ነው።
በፎቶው የሚታየው የያኔዋ የህወኀት የተማረ ተጋዳላይ – በወቅቱ ህወኀት በምትቆጣጠረው የአድዋ አንድ ቀበሌ ውስጥ ባለች እንደ ቢሮ በሚገለገሉባት አ
ጠባብ የድንጋይ ቤት ተቀምጦ – የኢትዮጵያ መንግሥት በሚያስተዳድረው ሌላ ከተማ ላሉ ቤተሰቦቹ ደብዳቤ እየፃፈ ነው። የተማረ ታጋይ – ከአድዋ – ዓይነት መሆኑ ነው። /አይ ፈረንጂ…!! /
በጣም የሚገርመኝ ታዲያ – የቤተሰብ የዓመታት ናፍቆት እንባውን እያስነባው እና በናፍቆት ሰቀቀን ለሚወዳቸው ቤተሰቦቹ እየፃፈም እንኳ – ይህም እንኳን ሆኖ – ሀሳቡም የሠላምና የፍቅር ሆኖ ራሱ – ይህ የወየነ ታጋይ – ከብዕሩ ጎን – የጦር መሣሪያውን እንደ መድፍ ደግኖታል። ብዕርና ታጣፊ ክላሽ – በአንድ ላይ!!!!!!
አዎ። ብዕርና ታጣፊ ክላሽ። ይህ ነው ከመነሻው እስከ አሁኗ ደቂቃም ድረስ የማይለያየው የህወኀት መንታ ሰብዕና!! ከ67 እስከ 83። ከ83 እስከ 2011። እና ምናልባትም ለወደፊትም።
ብዕርና ክላሽኒኮቭ። ይህ ነው የህወኀታውያን የማይነጣጠል፣ የተቆራኘ፣ የተጋዳይ ነፍስና ሥጋ!! ላለፉት 27 ዓመታት ደግሞ – በላዩ ላይ – “ሥልጣን” የሚባል የአድራጊነት መንፈስ ሲጨምርበት – የምሥጢረ ህወኀት ሕላዌ – ይሄ ኾነ ፦ ብዕር ፣ ክላሽኒኮቭ እና ሥልጣን።
ለኢትዮጵያችን እንደ ሀገር – አሳዛኙ ነገር – ይህ በሶስት ፈርጅ የተሳለ (ወይም የተሞረደ) ምሥጢረ ህወኀት –  ኢትዮጵያን ለድፍን 27 ዓመታት በስሙ እየባረከ በሥልጣን ደቁኖ መኖሩ ብቻ አይደለም።
ህወኀት በቆይታው ይሄንን የህላዌ ወንጌሉን ለሌሎቹም አስተምሮብን – ሀገሪቱን ከጫፍ እጫፍ – ይኸው ነግቶ በጠባ ቁጥር እንደምናየውና እንደምንሰማው – በያቅጣጫው – ምኞትና ህልማቸው ሁሉ – ኃይልና ሥልጣን ፣ ብዕርና ክላሽኒኮቭ – ‘ባሩድና ብርጉድ’ – ካልኩሌተርና ቡል-ዶዘር ብቻ በሆኑ – ህልቆ ወ መሣፍርት በሌላቸው ጭፍራ ደቀ መዝሙሮቹ አጥለቅልቆን ሄደ።
እና ቢሄድም አልሄደም ህወሃት። ያኔ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ (አሊያም ወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሳ) – “ቅንጅት መንፈሥ ነው!” እንዳሉት – ይኸው – “ውሻ በቀደደው ጅብ ይገባል” ሆነና ነገሩ – አሁን ላይ – በቃ – “ህወኀት መንፈስ ነው!”። (እንበል አሥራ ሁለት ጊዜ።)
አሁን አሁን የምንሰማቸውን አንዳንድ ክስተቶች ሳስተውል – ለካንስ – እላለሁ – ለካንስ – የማናውቀው ጌታቸው አሰፋ የተባለ እንደ ካርሎስ ቀበሮ ፎቶ-አልባ የምሥጢረ-ህወኀት ጠባቂ ግለሰብ ብቻ ሳይሆን – በቃ – አሳምረን የምናውቀው ህወኀትም ራሱ – አለ አይደለ? በቃ – ወደ መንፈስነት እየተለወጠብኝ ነው። ምክንያቱም – ህወኀትን ሄደ ስል መጣም እየሆነብኝ ነዋ።
ኧረ አለ ጎበዝ። በአካል ቢያልፍም በመንፈስ ይኖራል። በመንፈስ ባይኖርም በግብሩ (በሥራው) ይኖራል። ብቻ ግን አለ። መኖሩንማ አለ – ይኖራልም – ሁሉ የማይሳነው አንድዬ ፈጣሪ አምላክ – ህወኀት በኢትዮጵያ ላይ የዘራውን የምሥጢረ ሕላዊ ጋኔን – ከትውልዳችን ላይ ሰንኮፉን ነቅሎ እስኪገላግለን ድረስ።
ቀደም ብዬ ቃል በገባሁት መሠረት – የህወኀት የኩርፊያ ፖለቲካና 6ቱ ወቅታዊ ሀገራዊ ሥጋቶች – በሚል ርዕስ ባዘጋጀሁት ፅሁፌ – ተመልሼ ወደ ፌ.ቡ. ፊቴን አቃንቼ እስከምመጣ ድረስ – ሠላም ያቆየን። ኬር ሁኑልኝ። ለዛሬ አበቃሁ።
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ።
Filed in: Amharic