>

"ያ የመጠላላት ዘመን ይብቃ፤ ለትውልዱ ኢትዮጵያዊነት በስፋት ይነገረው!!!" (ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ)

«ገጣሚ ጸሐፊ ተውኔት ከፖለቲካ በላይ ስለሆነ ለፖለቲካ አያጎነብስም»ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ

 
ተወልደው ያደጉት በድሬዳዋ ከተማ ነው። በሙያቸው ፀሐፊ-ተውኔትና የሥነ ጽሁፍ ምሁር ናቸው። በኢትዮጵያ

ታሪክ ላይ ጥልቅ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ ይታወቃሉ። በአሁኑ ወቅት የ70 ዓመት እድሜ ባለፀጋ ናቸው።

«ጓደኛሞቹ»፣ «ፍቅር በአሜሪካ» እና ሌሎችንም ቴአትሮችን ለመድረክ አብቅተዋል። በርካታ ግጥሞችንና
መጽሐፎችን ለህትመት አብቅተዋል። «የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ» በተሰኘው አነጋጋሪ መጽሐፋቸው ስማቸው ጎልቶ ይነሳል።
በአሁኑ ወቅት ኑሮአቸውን በአሜሪካ ያደረጉት ታዋቂው የሥነ ጽሑፍ ምሁር ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ፤ በሊንከን
ዩኒቨርሲቲ በሂዩማኒቲስ የትምህርት ዘርፍ በማስተማር ላይ ይገኛሉ። ከዚህ ቀደም «Heaven to Eden» እና
«The Hidden and untold History of the Jewish People and Ethiopians» የሚሉ መጽሐፍትን በእንግሊዝኛ ቋንቋ አሳትመዋል። ሁለቱም (አማዞን) በተባለ የመጽሐፍ መሸጫ ድረ ገፅ ላይ ከተፈላጊ መጻሕፍት ተርታ ተሰልፎላቸዋል። በቅርቡም «ላሟ» የተሰኘ ባለ ሁለት ገቢር ቴአትር ጽፈው አጠናቀዋል። የዛሬው የዘመን እንግዳችን ናቸው። ከእርሳቸው ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው ይቀርባል።

አዲስ ዘመን፡- አንዳንዶች ‹‹የፍቅር አባት›› ሌሎችም ‹‹የታሪክ አባት›› ይሉዎታል። የትኛው ይስማማዎታል?

ፕሮፌሰር ፍቅሬ፡-እኔ ራሴን የማየው እንደ ገጣሚና ጸሐፊ ተውኔት አድርጌ ነው። ነገር ግን ተማሪ ሆኜ ታሪክ እወድ ስለነበር በታሪክ በጣም ጥሩ ውጤት አመጣ ነበር። እናም ጸሐፊ ተውኔትና ገጣሚ ባልሆን የታሪክ ጸሐፊ እሆን ነበር ብዬ አስባለሁ። ደግሞም ታሪኩን ብቻ ሳይሆን የምወደው አጻጻፋቸውንም ጭምር ስለነበር ለቋንቋም ልዩ ፍቅር አድሮብኛል። አንቺ እንዳልሺው የአማራና የኦሮሞው እውነተኛው የዘር ምንጭ የሚለውን መጽሐፍ ከጻፍኩ በኋላ የታሪክ አባትና የፍቅር አባት የሚሉ ቅጽሎች ሰጥተውኛል። እንግዲህ ይህ የህዝብ አስተያየት ነው።

አዲስ ዘመን፡- በሌላ በኩል ደግሞ አነጋገሪና አከራካሪ ግለሰብ ናቸው ይባላል። እርስዎ አከራካሪ ሰው ነኝ ብለው ያምናሉ? ከሆነስ ለምን?

ፕሮፌሰር ፍቅሬ፦ እኔ የማቀርባቸው ሃሳቦች ለክርክር ወይም ራሴን አነጋጋሪ ሰው ለማድረግ አይደለም። አንድ የሚታየኝና የመሰለኝን ነገር ለሌሎች እናገራለሁ፤ እጽፋለሁ። ከዚያ በኋላ ሰዎች ያከራክራል፤ አያከራክርም ብለው ይፈርጁታል። ይሁን እንጂ እኔ እስቲ የሚያከራክር ነገር ልጻፍ ብዬ ተነስቼ አላውቅም።

አዲስ ዘመን፡- ለእርስዎ የአገር አንድነትና ኢትዮጵያዊነት ማለት ምን ማለት ነው? በተለያዩ አካባቢዎችና መድረኮች ስለአገር አንድነትና ሕብረት የሚያስተምሩትስ ከምን መነሻ ነው?

ፕሮፌሰር ፍቅሬ፡- እንግዲህ በእኔ እምነት በእኩልነት ላይ እስከተገነባና በፍትህ ርትዕ ላይ እስከተቀመጠ ድረስ የአገር አንድነትን ማስጠበቅ ለማንኛውም አገር ጠቃሚ ነው። ሁሉም አገር ተበታትኖ ሳለ አንድ ያደረጉት ሰዎች አሉ። ለምሣሌ ከአውሮፓ ጣሊያን ተበታትና ሳለች «ጋሪ ባልዲ» የተባለ ሰው በግድም በውድም አገሪቱን አንድ አድርጎ ዛሬ ትልቅ አገር ለመሆን በቅታለች። ጀርመንም እንዲሁ ተበትኖ እያለ «ቢስማርከ» የሚባል ሰው «ዘ አይረን ቻንስለር» እያሉ የሚጠሩት ግለሰብ አስተባብሮ አገሩን አንድ በማድረጉ ዛሬ ጀርመን ከዓለም ሀብታም ከሆኑት አገራት መካከል በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች። ግን ይህ ሲሆን በቀላሉ ተሳክቶለታል ማለት አይደለም። አንዳንድ ትንንሾቹ አገሮች ጀርመን አንድ ከሆነች እነርሱ ስለሚዋጡ ቢስማርክን በከፍተኛ ደረጃ ተቃውመውት እንደነበር ይታወሳል። አሜሪካም እንከፈል ብለው ደቡቦቹ ብዙ ጦርነት አድርገው ከ20 ሚሊዮን ሰው አልቆ እነአብረሃም ሊንከን አሸንፈው አሜሪካ በጣም ትልቅና ገናና አገር ለመሆን በቃች። ለሁለት ተከፍላ ቢሆን የዛሬ ትልቅነቷ አይኖርም ነበር። ስለዚህ ከዓለም አገራት ታሪክ እንደምንረዳው አንድነት በሠላም ቢሆን ጥሩ ነው፤ ካልሆነ ደግሞ በኃይል ይገነባል። ይህም ለኢኮኖሚም ሆነ ለፖለቲካው ጠቀሜታ አለው። ይህን ያህል የምደክመውና ከፍተኛ ዋጋ ከፍዬ ስለኢትዮጵያ የማስተምረው አገሬን ስለምወድ ነው። አሁንም ድረስ በራሴ ወጪ ነው የምንቀሳቀሰው። በድርጅት አይደለም።

አዲስ ዘመን፡- ይህ ጥረትዎ ምን ያህል ውጤታማ እየሆነ ነው ?

ፕሮፌሰር ፍቅሬ፡- እኔ እንደሚመስለኝ እየዞርኩ በማስተምረውም ሆነ በምጽፋቸው ጽሑፎች የበርካቶችን አመለካከት መቀየር ችያለሁ። ለምሣሌ እኔ በልዩ ምክንያት የጻፍኩት «የአማራና የኦሮሞ እውነተኛው የዘር ምንጭ» የሚለው መጽሐፍ ከወጣ በኋላ እኔ ብቻ ሳልሆን ሌሎችም እንደሚመስክሩት መጽሐፉ ልዩ ተፅዕኖ ፈጥሯል። በተለይም የአንድነትና የኢትዮጵያዊነት ስሜት እንዲያንሰራራ ረድቷል ብዬ አምናለሁ። ደግሞም አዳዲሶቹ መሪዎች ‹‹ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው›› እስከማለት የደረሱት ከዚህ የተነሳ ይመስለኛል። እንደውም ዶክተር አብይ አህመድ ጀርመን በቅርቡ በሄዱበት ጊዜ የእኔን መጽሐፍ እንደሚቀበሉት ገልፀዋል። ስለዚህ መጽሐፌ ከፍተኛ ተፅዕኖ ፈጥሯል ለማለት እደፍራለሁ። በአካልም እየዞርኩ ስለአማራና ኦሮሞ ብቻ ሳይሆን ስለኢትዮጵያዊነት እየሰበኩ ነው። በዚህም ለአርባ ዓመታት ተጣልተው የነበሩ ወገኖችን ማስታረቅ ችያለሁ። እነዚህ ሰዎች ለአርባ ዓመታት በፖለቲካ ምክንያት የማይናገሩ ሰዎች አውሮፓ ውስጥ ተቃቅፈው ተላቅሰዋል። እስካሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ሄጂያለሁ። እዛም «ተፋቀሩ ኢትዮጵያ ናችሁ» ብዬ ሁለተኛ ጎሰኝነትን እንዳያራምዱና በኢትዮጵያዊነት ብቻ ለማንፀባረቅ ቃል ገብተዋል። ስለዚህ እዚህ አገር እስካለሁ ድረስ ስለአገር አንድነት ማስተማሬን፤ መስበኬን እቀጥላለሁ።

አዲስ ዘመን፡- አንዳንዶች ስለሀገር አንድነት የሚሰብኩት የፖለቲካ ተልዕኮ ይዘው እንደሆነ ይናገራሉ። ይህ ምን ያህል እውነት ነው? 

ፕሮፌሰር ፍቅሬ፡- ፖለቲከኛ አይደለሁም። የፖለቲካ አጀንዳም የለኝም። ነገር ግን ፖለቲካ አላውቅም ማለት አይደለም። ከፖለቲካ በላይ ነኝ ብዬ አስባለሁ። ገጣሚ፣ ጸሐፊ ተውኔት ከፖለቲካ በላይ ስለሆነ ለፖለቲካ አያጎነብስም። ስለዚህ ስለምንቀውና ስለማልፈልገው ነው ፖለቲካ ውስጥ የሌለሁበት። ይሰለቸኛልም እንጂ! አዲስ ነገር የለበትም። እኔ ደግሞ አዲስ ነገር መስማትና ማንበብ ነው የምፈልገው። ይሁንና የፖለቲካ ንቃተ ህሊናዬ «ፖለቲከኛ ነኝ» ከሚሉት የሚያንስ ሆኖ አይደለም። በልጅነቴም የንጉሡን ሥርዓት በመቃወም ዴሞክራሲ እንዲመጣ ብዙ ታግያለሁ። አውሮፓም ሄጂ በስነ ፅሁፍ አማካኝነት ደርግን ስታገል ነው የኖርኩት ። ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚና ፍልስፍና ተምሪያለሁ። ስለዚህ ንቃትና እውቀቱ አለኝ፣ ግን አልፈልገውም።

 አዲስ ዘመን፡- የአማራና ኦሮሞን እውነተኛ የዘር ምንጭ የሚለውን መጻፍ የጻፉት በልዩ ምክንያት መሆኑን ገልፀዋል። ልዩ ምክንያትዎ ምን ነበር?

ፕሮፌሰር ፍቅሬ፡- ይህንን መጽሐፍ ለመፃፍ ያነሳሳኝ ዋነኛው ጉዳይ እንደሚታወቀው ከአገራችን ህዝብ 70 በመቶውን ቁጥር የሚይዙት የኦሮሞና የአማራ ህዝቦች ናቸው። እነዚህ ህዝቦች ባለመግባባት እስከ መጋደልና ደም መፋሰስ የደረሱበት ወቅት ነበር። እኔ ደግሞ ባደረጉት የታሪክ ምርምር ሁለቱ ህዝቦች የአንድ አባትና እናት ልጆች መሆናቸው ስላየሁ ይህንን ባለማወቃቸው ለምን ይጋደላሉ? ብዬ እውነተኛ ታሪካቸውን እንዲያውቁና ሠላም ይፈጠራል ከሚል ተስፋ ነው መፅሐፉን የጻፍኩት። እንዳሰብኩትም ጥቅም እየሰጠ ነው ያለው። በሌላ በኩል ደግሞ «ሁለት ዝሆኖች ሲራገጡ የሚጎዳው ሣሩ ነው» እንደሚባለው ሁሉ በእነርሱ ጠብና ጦስ ደግሞ ሌላውም ህዝብ ስለሚጎዳ ሁለቱ እየተጣሉ ሌላው ህዝብ በሠላም ይኖራል ማለት ከንቱ እሳቤ ስለሆነ በእነርሱ ዳፋ አገር እንዳይጎዳ በማለት ሁለቱ መታረቅ እንዳለባቸው አምኜ ነው የጻፍኩት። ሁሌም የምሰጠውን ምሣሌ ላክልልሽ። ጀርመን ሄጄ ጀርመንኛ የሚናገር ልጅ ብወልድ፤ ፈረንሳይ ሄጄ ፈረንሳይኛ የሚናገር ልጅ ብወልድ፤ ጣሊያን ሄጄ ጣሊያንኛ የሚናገር ልጅ ብወልድ፤ እነዚህ ልጆቼ በቋንቋ ባይግባቡም ወንድማማችነታቸው ሊፋቅ አይችልም። እኔም አማርኛ፣ ትግርኛና ኦሮምኛ ስለተናገርኩ አባት መሆኔ አይሰረዝም። እኔና ልጆቼን ያዛመደን በመኃላችን ያለው የእኔ ደም እንጂ ቋንቋ አይደለም። ስለዚህ ኢትዮጵያ ትበቃናለች።  በሰላም በፍቅር ወንድማማችና እህታማማች ሆነን እንኑር የምለው።

አዲስ ዘመን፡-ይህንን መጽሐፍ ከጻፉ በኋላ በርካታ ተከታዮችን ያገኙትን ያህል የሚቃወሙዎትም አሉ። በተለይም ቀድሞ ከተጻፉ የኢትዮጵያ ታሪኮች አንፃር መጽሐፉ ተዓማኒነት እንደሌለው የሚያነሱ የሕብረተሰብ ክፍሎች አሉ። እርስዎ በዚህ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?

ፕሮፌሰር ፍቅሬ፡- ብዙዎቹ ሳይሆኑ ጥቂቶች ናቸው የማይቀበሉኝ በሚለው ይስተካከል። እነርሱ ጉዳዩን ስላልተረዱትና የኢትዮጵያ ታሪክ አስደናቂና ተረት የሚመስል ስለሆነ እንደተረት አይተውት ሊሆን ይችል። ሌላው ደግሞ ይህንን ሃሳብ ህዝብ ውስጥ እንዲሰራጭ ያደረጉ ሰዎች እንዳሉ አውቃለሁ። አንደኛው ጉዳይ ለእነርሱ አቋም ስለማይመቻቸውና የማይጠቅም ስለሆነ፤ ሁለቱ ትላልቅ ህዝቦች ቢካፈሉ የሚጠቀሙ በመሆኑ፤ በነዚህ ምክንያቶች ጥቅማችንን ነካ ከማለት ተነሳስተው ነው የሚቃወሙኝ።

ሌሎች ጥቂቶች ደግሞ «ለምን እኛ እዚህ ታሪክ ውስጥ የለንበትም» በሚል ነው የሚቃወሙት። ይህንን የሚሉት ደግሞ አንዳንድ ምሁራን ናቸው። ይህንን ታሪክ ለምን እኛ መጀመሪያ አልጻፍነውም ወይም ታሪክ ውስጥ የለንበት ወይም እኛን እንዴት አላማከረንም በሚል በምሁርነት ሳይሆን በግል ፍላጎት ተነሳስተው የሚያቀርቡት ነው። የሚገርመው እስከዛሬ ድረስ አንድም ምሁራዊ ትንተና ወስዶ በዚህ በዚህ ምክንያት እንደዚህ ያለኝ ምሁር አላገኘሁም።

እንዲሁ በጅምላ ‹‹ይሄ ተረት ነው››፤ ‹‹ይሄ የማይመስል ነው› የሚሉት። የተከራከርኳቸውም ግለሰቦች አሉ። ተረት ነው ካሉ ተረት ስለመሆኑ አብነት አድርገው እንዲጠቅሱ ጠይቂያቸው ነበር። ነገር ግን እስካሁን ማስረጃ ያቀረበ የለም። በነገራችን ላይ ተረት ወይም አፈ-ታሪክም ቢሆን ክፉ ነገር ነው ብዬ አልወስደውም። ምክንያቱም ብዙ አገሮች በአፈ-ታሪክ ላይ ነው የተገነቡት። የጋራ አፈ- ታሪክ አላቸው። ለምሳሌ ብንጠቅስ የጣሊያን መስራቾች በስፋት በአፈ ታሪካቸው ነው አንድነታቸውን ማጠናከር የቻሉት። የእኛ አገር አፈ ታሪክ በእውነት ላይ የተመሰረተ ነው። አስደናቂ ስለሆነም ነው ተረት የሚመስለው። የ4000ውን ዓመት ብቻ ብናወራ ኢትዮጵ የሚባልና እንቂዮፓ ጊዮን የምትባል እናት አስር ልጆች ወልዳ እነዚያ ተባዝተው ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን ሰዎች ሊፈጠሩ ችለዋል። አፈ-ታሪክ በወረቀት ስላልተጻፈ ታሪክ አይደለም ማለት አይቻልም።

እንደሚታወቀው በርከት ያለው ታሪካችን በንግሥት ዮዲት እንደጠፋ ይነገራል። ግን እውነት አይመስለኝም። ንግሥት አስቴር ብላት ይሻላል። ዮዲት ጉዲት እያሉ ሲሰድቧት ኖሯል። በእኔ እምነት መሰደብ የሌለባት ሰው ናት። ለኢትዮጵያ ውለታ የዋለች ሰው ነች፤ እስከ ዛሬ ስሟን ሲያጠለሹ የኖሩት አረቦች ናቸው። አረቦችን ወይም ከአረብ ጋር ግኑኝነት ያላቸውን ኢትዮጵያውያን ግዕዝን አጥፍተው አረብኛ አምጥተው አገሪቱን ሙሉ አረብ ሊያረጉ ሲሞክሩ ነው አሳድዳ የወጋችው። የአረብ ጳጳሳት ኢትዮጵያኖችንና የዮዲትን ወገኖችን ቤተ-እሥራኤሎች እየሱስን የገደሉ ናቸው ምን ትጠብቃላችሁ ግደሏቸው እያሉ ተቻችለው አብረው የሚኖሩትን ሰዎች እየገደሉ ሲያስቸግሩ በዚህ ተናዳ ነው ይህንን የፈፀመችው። እንዳውም ኢትዮጵያን ከአረብ ወረራ ታድጋለች። ለዚህም ነው ስሟን ያጠፉት። እናም በዛ ወቅት ንግሥት አስቴር (ዮዲት) የአክሱምን መንግሥት ስታባርር ታሪካችን ተበትኖ ነበር።

አክሱም ላይ የታሪክ ዘጋቢ የሆነ የጅናድ የመጨረሻ የአክሱም ልጅ አክሱማዊ ሲራክ የሚባል ትልቅ አዋቂና ጠቢብ ሰው የቤተ መጽሐፍት ቤቱም ኃላፊ ስለነበር የተቻለውን ያህል የተለያዩ መጽሐፍ አትርፎልናል። በዚያ ጊዜ ውስጥ የሱ መጽሐፍ ወደ ላሊበላ ተወስዶ ከ300 ዓመት በኋላ እስከሚባዛ ድርስ ዓፄ ላሊበላ ግብፅ ሄዶ ያንን መጽሐፍ ሰጡት እሱ አስተረጎመው። ከዚያ እንደገና ጠፋና በአምደፂዮን ጊዜ ማለትም ከሁለት ሺ ዓመት በኋላ የኢትዮጵያ ዳግም እስከሚያጽፉ ድረስ በመሃል ያለው ጊዜ በአፈ ታሪክ ነበር የሚታወቀው። ስለዚህ አፈ ታሪክም የሚናቅ አይደለም። ስለዚህ የጻፍኩትን አፈ ታሪክ ነው ቢሉትም ችግር የለብኝም።

አዲስ ዘመን፡- እርስዎ ይህንን ቢሉም ሌሎች ታሪክ አዋቂዎች ግን አፈታሪክ የሆነን ነገር ወደ ጽሑፍ በማምጣት የአገሪቱ የታሪክ አካል ማድረግ ተዓማኒነት ያሳጠዋል ሲሉ ይሞግታሉ። በተለይ ደግሞ አፈታሪክ ሲጻፍ ሰዎች ከነበሩበት ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ስለሚጽፉት ታሪክን ያዛባሉ ብለው ያምናሉ። ለዚህ ምን ምላሽ ይኖርዎታል?

ፕሮፌሰር ፍቅሬ፡- አሁን እኮ ራስሽ መልሰሽዋል። በጽሑፍ ላይ ስለቀረበ ብቻ አንድ ታሪክ አስተማማኝና ትክክለኛ ነው ማለት አይደለም። እንደ ጸሀፊው አያያዝ እንደ አላማው ይወሰናል። ስለዚህ ለእውነተኝነቱ በጽሑፍ ላይ መስፈሩ ብቻ ዋስትና አይደለም። በቃል ስለተደረገ እውነተኛ አይደለም ማለት አይደለም። ስለዚህ ከአፍ ወደ አፍ ሲተላለፍ ቆይቷል። የኢትዮጵያ ማህበረሰብ እኮ የቃል ማህበረሰብ ነው። ኢ-ሜል ወይም ደብዳቤ የቃል ማህበረሰብ ነው። ኢ-ሜል ወይም ደብዳቤ ከሚጽፍልሽ ስልክ አንስቶ ማውራት ይቀለዋል። ይህም ተረት የለመደና በተረት ያደገ ህዝብ መሆኑን ነው የሚያሳየው። ስለዚህ ከሁለቱም በኩል ያለውን አመዛዝኖ መፍረድ ዘመናዊ ባለ ታሪክ ወይም የአንባቢው ፈንታ ነው። ግን ሁለቱም ወሳኝ መሆናቸውን አምናለሁ።

አዲስ ዘመን፡- አሁንም ቢሆን ጥቂት የማይባሉ ምሑራን እርስዎ አለ የሚሉትን ታሪክ እውነተኛ አይደለም ሲሉ ይሞግታሉ። እርስዎ ምን ይላሉ?

 ፕሬፌሰር ፍቅሬ፡- ለምሣሌ አንዱን ጥቀሺልኝ።

 አዲስ ዘመን፡- ለምሣሌ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ አንዱ ናቸው።

ፕሮፌሰር ፍቅሬ፡- ከእርሳቸው ጋር ብዙ ተከራክረናል። ላነሷቸው መልስ 34 ገፅ አጥጋቢ መልስ ሰጥቼ ዓለም በሙሉ ያየው ነገር ነው። ይሄ ጉዳይ ወደ ኋላ ነው የሚወሰደን። እኔና እርሳቸው ያንን ደረጃ አልፈን ከዚህ በኋላ አንነጋገርም ተባብለን አልፈነው የተደመደመ ጉዳይ ነው።

አዲስ ዘመን፡- ተማመናችሁ ማለት ነው?

ፕሮፌሰር ፍቅሬ፡- እኔም የራሴን አቋም ይዤ፤ እርሳቸውም የራሳቸውን ይዘው ነው የተለያየነው። ፕሮፌሰር ጌታቸው ላነሷቸው ጥያቄዎች ሰፊ ማሳመኛ ትንታኔ ነው ያቀረብኩት። እንደሱም ብዙ መልስ የተሰጠበት ህዝብን ያሳተፈ ነገር ጉዳይ የለም። ግን በአጠቃላይ ሁኔታውን ሳየው እርሳቸው ሌላ ምክንያት ስላላቸው እንጂ ከተዓማኒነት ጋር የሚያያዝው ነገር የለም። የእሳቸውን ጽሑፍ ካነበብሽ መጀመሪያ ላይ ሲጽፉም የመጽሐፍ ግምገማ (ቡክ ሪቪውም) አይደለም፤ ሂስም አይደለም ብለው ጠቅሰዋል። እንዳውም አርዕስቱ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳን ለማሞገስ ነው የሚለው። ከዚያ በኋላ ግን የኔ መጽሐፍ ዋነኛ ምንጭ የሆኑትን መሪራስ አማን በላይ ጋር ቅራኔ ስለነበራቸው ብቻ መጽሐፉን ወደ ማጥላላት ሄዱ። ከእኔ ጋር ግን ወዳጆች ነበርን።

አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያን ታሪክ ማን ነው መጻፍ ያለበት ብለው ያምናሉ?

ፕሮፌሰር ፍቅሬ፡- ማንኛውም ታሪክ የሚያፈቅር፣ እውነታውን ተረድቶት በትክክል ተገንዝቦ እውነተኛ ፍርድ ሳያዳላ የሚጽፍ፣ ህዝብ እንዲያውቅ የሚሻ፣ መጻፍ፣ ማንበብ መመራመር የሚችል ሰው መጻፍ ይችላል።

አዲስ ዘመን፡- ሌላው በመጽሐፍዎ ላይ የኦሮሞ ብሔረሰብ አመጣጥን በሚመለከት ከዚህ ቀደም በታሪክ ከምናውቀው በተለየ በ16ኛው ክፍለ ዘመን ከሌሎች አገራት መምጣቱን እንደማይቀበሉት ገልፀዋል። ለዚህ መነሻዎ ምንድን ነው?

ፕሮፌሰር ፍቅሬ፡- የኦሮሞ ብሔረሰብ በ16ኛው ክፍለ ዘመን መጣ የሚለው ነገር ፈጽሞ አልቀበለውም።ለአብነት መጥቀስ ካስፈለገ ዓፄ ይኩኑ አምላክ በ13ኛው ክፍለ ዘመን እናታቸው ሃዊ ጊፍቲ መንዲያ ይባላሉ፤ የሸዋ ኦሮሞ ነበሩ። ኦሮሞ በ16ኛው ክፍለ ዘመን ከሆነ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት እንዴት ሊሆን ቻለ? የእርሷስ አባት አዛዥ ጫላ በሸዋ ላይ ሥልጣን ያላቸው ኦሮሞ እንዴት ሆኑ? ዓፄ ልብነድንግል ራሳቸው ሚስታቸውና እናታቸው እንዴት ኦሮሞ ሆኑ? ስለዚህ ኦሮሞች በ16ኛው ክፍለ ዘመን መጡ የሚለው ታሪክ እውነት አይደለም ማለት ነው። ግን በተጠቀሰው ወቅት የመጡ ሰዎች አሉ። አረንጓዴ መሬት የያዙ። እነርሱም ቀደም ብለው ከብቶቻቸውን ሣር እያጋጡ በገዳ መስፋፋት ሥርዓት መሰረት ሆነ በጀብደኝነት ወደ ሱማሌ አካባቢ ኬኒያ ድንበር፤ ማዳጋስካር ድረስ የሄዱ ነበሩ።

እናም በ16ኛው ክፍለ ዘመን ቦረንና ቤረቱማ የሚባሉ ወንድማማቾች ከነጎሳዎቻቸው የግራኝን ኮቴ እየተከተሉ ከዓፄ ልብነድንግል ጋር ሲዋጋ የሚከላከል መሬት የሚጠብቅ ስላልነበር ዘላለም ከኢትዮጵያ ያልወጣውን ኦሮሞ ጭምር ያደረጉትን እንቅሳቅሴ ነው የኦሮሞ ወረራ የሚሉት። አማራውንም ከደቡብ አረቢያ ከኦሮሞ በፊት የመጣነው ብለው ተክለፃድቅ መኩሪያ የጻፉት ስህተት ነው። እዚሁ ጎጃም ላይ ‹‹ደሸት›› ወይም ደሴት የሚባለው ንጉሥ የኢትዮጵ ዘር የሆነው 3ሺ600 ዓመት አካባቢ እሱ አራት ወንድ ልጆችን ወለደ። እነሱም መንዲ፣ መደባይ፣ ጂማ፣ ማጂ የሚባሉ ሲሆኑ ማጂ አማራን ወለደ ። እነዚህ ስሞች አሁንም አሉ። መንዲ ወለጋ ውስጥ የቦታ ስም ነው። መደባይ ከትግራይ ወረዳ ውስጥ መደባይ ዛና መደባይ ወለል ይባላሉ።

መደባዮች ራሳቸው የደሸት ዘር እንደሆኑ አያውቁም ትግሬ ነን ነው ብለው የሚያስቡት የሚናገሩት ትግርኛ በመሆኑ ነው። ጅማና ማጂም የቦታ ስም ናቸው። ሁሉም የደሸት ልጆች ናቸው። ጎጃም ላይ ሳሉ ሱባ የሚባል ቋንቋ ነበር የሚናገሩት። በመጸሐፌ ሽፋንና ውስጥ ፊደሎቹ አሉ። ከ3200 ዓመት በፊት ቀድሞ ካሉ ህዝቦች ከነጋፋት ጋር ሲቸግራቸው መጋፋትና መዋጋት ወደ ሸዋ መጡ የአማራ ልጆች ኦሮሞዎች ወገኖዎቻቸውን ተከትለው። ጅማ የወለዳቸው ኦሮምኛ ሲናገሩ ኦሮሞ ተባሉ። ሌሎቹ ደግሞ ሱባን ትተው አማርኛ ሲናገሩ አማራ ናቸው ተባሉ። ሁለቱም ግን ዘራቸው የደሸት ልጆች ናቸው። ጀማ የሚባለው ልጅ ደግሞ አሁንም ጀማ የሚባል ወንዝ አለ። ስለዚህ በአጠቃላይ ያኔ የነበሩ ሰዎች ናቸው። ከውጭ የመጣ የለም። አሁን እኔ አሜሪካን አገር እኖራለሁ አርባ ዓመት ቆይቼ ስመጣ ኢትዮጵያዊነቴን ልክድ አልችልም። ቋንቋችን 84ቢሆንም ይበታትነናል እንጂ አንድ አያደርገንም። ከልዩነቶቻችን ይልቅ አንደነታችን ላይ ማተኮር ይገባናል።

አዲስ ዘመን፡-በመጽሐፍዎ ላይ ኦሮምኛ ቋንቋ የግዕዝ ፊደላትን ቢጠቀም አምስት የተለየዩ ጥቅሞች እንደሚኖሩት ዘርዝረዋል። ከእነዚህ ውስጥም ከላቲን ይልቅ ግዕዝን መጠቀሙ ኦሮሞዎችን እንደ ባዕድ ከመታየት እንደሚያድናቸው ጠቅሰዋል። ይህን ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?

ፕሮፌሰር ፍቅሬ፡- ምን ማለቴ እንደሆነ ገብቶሻል። ግን ከእኔ አፍ ከሆነ መስማት የፈለግሽው ልነግርሽ እችላለሁ። እንደምታውቂው አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በግዕዝ ፊደል ነው የሚጽፈው። በሌላ በኩል ኦሮሞዎች፣ ሱማሌዎችና አፋሮች በላቲን ነው የሚጽፉት። ይህ መሆኑ ከሌሎች ወገኖች ዘንድ እንደ ባዕድ እንዲታዩ ያደርጋቸዋል። ስለዚህ ይሄ ደግሞ ጥሩ አይደለም። ከሰው ይለያቸዋል፣ ያርቃቸዋል፣ ያገላቸዋል። ሌሎችም ተጨባጭ ምክንያቶች አሉኝ። ለምሣሌ በላቲን ከመጻፍ ይልቅ በግዕዝ ቋንቋ ቢጻፍ በጥቂት ቃላት ሃሳብን መግለጽ የሚቻል በመሆኑ ጊዜን፣ ገንዘብንና ጉልበትን ይቀንስልናል። አንዳንዱ ቃላት እንዳውም «ጨ» የለውም። በፊት የሚሰጠው ምክንያት የአማርኛ ፊደል እንደማይበቃ ተደርጎ ነው። ግን በቀላሉ ድምፆችን መጨመር የሚቻልበት መንገድ አለ። ግን ቀደም ያሉት ፖለቲከኞች እንደ ኃይሌ ፊዳ ያሉ ሰዎች የግዕዝን ፊደል የአማራና የትግሬ ሀብት ብቻ አድረገው ያምኑ ስለነበር «በእነሱ ፊደል አንጽፍም የእነሱንም ቋንቋ አንናገርም» ብለው ያደረጉት ነገር ነው።

በጣም የሚገርመው ኤርትራ ስትገነጠል ቋንቋዋንም ይዛ ነው የተገነጠለችው እስካሁንም የእኛን ፊደል ነው የምትጠቀመው። ቢገባን የግዕዝ ፊደል የኦሮሞም ነው። ስለዚህ ኦሮሞ እህትና ወንድሞቼን የምመክረው በተለያየ ምክንያት ከሌሎች ኢትዮጵያን ጋር እንድንቀራረብ በአገራችን ፊደል መጻፍ ይገባናል የሚል ነው።በተጨማሪም መታወቅ ያለበት ጉዳይ ኦሮሞዎች የራሳችን ፊደል በሆነ በግዕዝ መጻፋችን በኢትዮጵያዊነታችን ክብርና ኩራት ያስገኝልናል። ምክንያቱም ከአፍሪካ የራሳችን ፊደል ያለን እኛ በመሆናችን። በተለይም ኦሮሞ የኢትዮጵያ ልጅ ሆኖ መገለል የለበትም። ወደ ቀድሞው መመለስ አለበት። እንደ ችግር የሚነሱት ድምፆችም ቢሆኑ ሁሉ ዶክተር አበራ ሞላ በሚባል ኢትዮጵያዊ ሳይንቲስት ተቀርፀዋል። ስለዚህ ቀና መንፈስ ካለ መመለስ ይቻላል ማለት ነው። ይሁንና በአሁኑ ወቅት ምንአልባት ይህንን ከቁምነገር የቆጠረው ሰው ላይኖር ይችላል። ወደፊት ግን አገር ስትረጋጋ የማይቀር ነገር ነው ብዬ አምናለሁ።

አዲስ ዘመን፡- ባለፉት 27ዓመታት በስፋት ተሰራጭቶ የነበረና የአማራና የኦሮሞን ህዝብ ሲያጋጭ የቆየው የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ዋነኛው የዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ጉዳይ ነው። በተለይም ንጉሡ «የሴቶችን ጡት ቆርጠዋል፤ አልቆረጡም» የሚለው ጉዳይ ሲነሳ እርስዎ አልቆረጡም ከሚሉት ወገን ነዎት። ለዚህ አባባልዎ ምን ማስረጃ አለዎት?

ፕሮፌሰር ፍቅሬ፡- በዚህ ጉዳይ ላይ መጽሐፌ ላይ በደንብ አብራርቼዋለው። ግን ለአንቺ ለመመለስ ያህል ዳግማዊ ዓፄ ምኒልክ ጡት ስለመቁረጣቸው በጽሑፍ የቀረበ ወይም የዓይን ምስክር የተናገረ ተመዝግቦ ካለ እኔ ለመቀበል ዝግጁ ነኝ። እኔ የዓፄ ምኒልክን ባህሪ ሳስበው እንደዚህ የሚያደርጉ አይመስለኝም። በተባለው ወቅት ንጉሡ ያንን ጦር አላዘዙም። ራስ ዳርጌ ነበሩ የበላይ። ራስ ዳርጌም ቢሆን ይህንን የሚያደርጉ ሰው አይደሉም፤ ትልቅ ጀግና ነበሩ። ደግሞም እኮ ጡት መቁረጥ የኢትዮጵያን ባህሪ አይደለም። አረብ ሊያደርግ ይችላል። ኢትጵያውያን ጀግኖች የእህቶቻቸውን ጡት አይቆርጡም። ባይሆን ወስደው ሚስት ያደርጋሉ እንጂ። ምንአልባትም ጀግንነታቸውን ለማሳየት የወንድ ብልት ሊቆርጡ ይችላሉ። ከወንድ ጋር ተዋግተው ሳለ ምን ስላደረጉ ነው የሴቶቹ ጡት የሚቆረጠው? ስለዚህ ዓፄ ምኒልክ ጡት ቆርጠዋል የሚባለው ጉዳይ በመላ ምትም አያስኬድም። በእኔ እምነት ይህንን የሀሰት ታሪክ የሚነዙት ከኦሮሞዎች ይልቅ ሌሎች ዓፄ ምኒልክን የሚጠሉ አክራሪ ሰዎች ናቸው ብዬ ነው የማምነው።

ዘላለም ኦሮሞና አማራ እንዲቃቃሩ የሚደረግ የተንኮል ሸፍጥ ነው። ሐውልት ከሚተከል ይልቅ በዚያ ቦታ ፋብሪካ ቢተከል ለዚያ ህዝብ ይጠቅመው ነበር። ስለዚህ ይህ ጉዳይ የምኒልክን ስም ለማጥፋት ታስቦ የተደረገ ነው የሚል እምነት አለኝ። እንደውም ዛሬ የምንጠቀምብትን ከባቡሩ ጀምሮ መሰረተ ልማት በዘረጉት ለአገራችው ብዙ ቁም ነገር የሠሩ ንጉሥ ናቸው። በዚያም የጣሊያን ባሪያ እንዳንሆን ነፃነታችንን ያረጋገጡልን የመላው ጥቁር መሪ የሆኑ ትልቅ ሰው ናቸው። ደግሞም በአገራችን ከነበሩት መሪዎች በላይ ሰብአዊ ርህራሄ ባህሪያቸው ይታወቃሉ። ስለዚህ ስለእርሳቸው የሚባለው ነገር ከእውነት የራቀ ነው የሚል እምነት አለኝ።

አዲስ ዘመን፡ – የሀገሪቱን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ እንዴት ይመለከቱታል?

ፕሮፌስር ፍቅሬ፡ – ጥሩ ነው የሚል አመለካከት አለኝ። ባለፉት 40 ዓመታት ሀገር ተንቃ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር የለችም፤ ኢትዮጵያዊስ ማነው? ኢትዮጵያዊነት አይረባም እየተባለ ሲጣጣል ከርሞ አሁን «ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው፤ ስንኖር ኢትዮጵያዊ ስንሞት ኢትዮጵያ ነን» የሚሉ መሪዎች ተፈጥረዋል። እነዚህ መሪዎች ደግሞ በፍትህ፣ በዴሞክራሲ፣ በሀገር እድገትና ብልፅግና ያምናሉ። ከሙስና ነፃ የሆኑ ናቸው። የታሰሩ ፖለቲከኞችንና ጋዜጠኞችን እንዲፈቱ አድርገዋል። ከውጭ ያሉትንም ጭምር ጠርተው ‹‹ውጭ ከምትሞቱ መጥታችሁ ተሳተፉ›› ብለው ዕድል ሰጥተዋቸዋል። በሃሳብ ልዕልና ካሸነፉ ስልጣን የሚይዙበት ምቹ ሁኔታ ፈጥረውላቸዋል። ወታደሩም ቢሆን ከሁሉም የተውጣጣ እንጂ ከአንድ ብሔር ብቻ እንዳይሆን ያንንም ከልሰው በፀጥታውም ያለውን ሁሉ ግፍ የሚሰሩና የሚያሰቃዩ መርማሪዎችን በሕግ እንዲጠየቁ አድርገዋል። ወደፊት ለመራመድ በሰላም በፍቅር በአገር ግንባታ በነፃነት እንድንራመድ እያደረጉ ናቸው። ከእነርሱ ጋር ተባብሮ ኢትዮጵያ ወደ ፊት እንድትራመድ ማድረግ ይገባናል።

 አዲስ ዘመን፡- ባለፉት 27 ዓመታት የብሔርተኝነት አስተሳሰብ ስር ሰዶ ቆይቷል። አሁን እርስዎ የሚያቀነቅኑትን ኢትጵያዊነት መመለስ እንዴት ይቻላል? ምንስ መሥራት ይገባል?

ፕሮፌሰር ፍቅሬ፡- እኔ የምመክረው ኢትዮጵያዊነትን ማስፋፋት ነው። ምክንያቱም በጎሳ ላይ የተመሰረተው ክልል አልበጀም። ስለዚህ የጥፋት ሁኔታን ስለፈጠረ አሁን ኢትዮጵያዊነት ላይ አተኩረን መሥራት ይገባናል። የአንድ እናት አባት ልጆች መሆናችንን ተገንዝብን ያለፈውን ትተን ወደፊት መራመድ ይገባናል። ደግሞም በሰላም በፍቅር መኖራችን ለሁላችንም ነው የሚበጀው። ከጥፋት ያድነናል። ለዚህ ኢትዮጵያዊነት በደንብ መሰበክ አለበት። በትምህርት ቤት ውስጥ ማስተማር አለብን። ኢትዮጵያዊነትን የሚያንጽባርቁ መጽሐፍት በደንብ መነበብ አለባቸው። መገናኛ ብዙኃንም ማስተማር አለባቸው።

አዲስ ዘመን፡- በኪነጥበብ ዘርፉ ምን ያህል ሥራዎች አበርክተዋል? በቀጣይስ ምን ለመሥራት አቅደዋል? ፕሮፌሰር ፍቅሬ፡- በርካታ ናቸው። በልጅነቴ አገር ውስጥ ሳለሁ አዲስ ዘመንን ጨምሮ በበርካታ ጋዜጦችና ሬዲዮ ጣቢያዎች ግጥሞቼ ይወጡ ይነበቡ ነበር። «ወላለ» የሚባል አጭር ልቦለድም ጽፊያለሁ። መታወቅ ስጀምር በቴሌቪዥን ድራማ እሰራ ነበር። በቴአትር በእንግሊዘኛና በአማርኛ ያሉት ሲደመሩ ወደ 30 የሚደርሱ ተውኔቶችን ጽፊያለሁ። ግጥም ከልጅነቴ ጀምሮ የጻፍኳቸው ወደ አስር ቅጽ ሊሆኑ ይችላሉ። የእንግሊዝኛ ደግሞ ፍልስፍና ላይ የሚያጠነጥን ድራማ ጽፌያለሁ። ከፍተኛ ተቀባይነት አግኝቷል። ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የኪነጥበብ ማህበራት ድርጅቶች ዘንድ ተቀባይነት አግኝቻለሁ። በታሪክ በኩልም «የአማራና ኦሮሞ እውነተኛ የዘር ምንጭ» ከሚለው መጽሐፌ ውጭ የተሰወረውና ያልተነገረው «የአይሁዳውያንን የኢትዮጵያውያን ታሪክ» የሚል መጽሐፍ ጽፌ በይብራይስጥኛ ተተርጉሟል፣ በእንግሊዘኛም ጽፌዋለሁ። ከፍተኛ አድናቆት አስገኝቶልኛል። ሦስተኛ «ይህች ናት የኔ ምድር» የምትል የግጥም መድብል በሲዲም ጭምር አስቀርጬዋለሁ።

አዲስ ዘመን፡- የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር አባል ነበሩ? የውጭ አገር የትምህርት ዕድልስ ያገኙበት አጋጣሚ ምን ነበር?

ፕሮፌሰር ፍቅሬ፡- አይ እኔ ውጭ አገር ስለምኖር ከኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ጋር ምንም አይነት ግንኙነት የለኝም። የጀርመን ደራሲያም ማህበር አባል ነበርኩ። ግን ሰዎች ማህበር ውስጥ ከተውሃል ብለውኛል። የአባልነት መዋጮም አልከፍልም። በስብሰባቸውም ላይ ተገኝቼ አላውቅም። ምንአልባት ወደፊት ልገባ እችላለሁ። የውጭ ዕድሉንም ያገኘሁት 12ኛ ክፍል እንደጨረስኩ በግጥም ተወዳድሬ ነው። ሁለተኛው ደግሞ «ወለለ» የተባለው ግጥም ተተርጎሞ ሩሲያ የትምህርት ዕድል አግኝቼአለሁ። በነገራችን ላይ እኔ የመጣሁት ከሀብታም ቤተሰብ አይደለም፤ ግን በእግዚአብሔር ቸርነትና በእኔ ትጋት እዚህ ልደርስ ችያለሁ። አዲስ ዘመን፡- ወደ አገርዎ ተመልሰው የማገልገል ዕቅድ የለዎትም? ፕሮፌሰር ፍቅሬ፡- አለኝ። ወደፊት እመጣና በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እየዞርኩ የተለየዩ የትምህርት አይነቶችን ለማስተማር ሃሳብ አለኝ። ደግሞም ቴአትር ቤት በሌለበት አካባቢ ቴአትር ቤቶችንና የባህል ማዕከል ለመክፈት ዕቅድ አለኝ።

አዲስ ዘመን፡- መሥሪያቤታችን ድረስ በመምጣት ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ሰፊ ውይይት በማድረግዎ በዝግጅት ክፍሉና በአንባቢዎቼ ስም ከልብ አመስግናለሁ።

ፕሮፌሰር ፍቅሬ፡- እኔም አመሰግናለሁ።

አዲስ ዘመን የካቲት 16/2011

ማህሌት አብዱል

Filed in: Amharic