>

የኦሮሞ ብሔርተኞች ግብዝነት [Hypocrisy]! (አቻምየለህ ታምሩ)


የኦሮሞ ብሔርተኞች ግብዝነት [Hypocrisy]!
[ክፍል ፪]
አቻምየለህ ታምሩ
እንደሌሎች ብሔርተኞች ሁሉ የኦሮሞ ብሔርተኞች አማራውን የሚከሱት በአሕዳዊ ስርዓት አራማጅነት ነው። እውነታው ግን በተቃራኒው ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ እንደ ኦሮሞ ብሔርተኞች  ጸረ-ፌዴራላዊ፣  ሲበዛ አሕዳዊ ብቻ ሳይሆን እጅግ ፍጹም የሆነ አሕዳዊ ስርዓት አራማጅ የሆነ ቡድን የለም። በተቃራኒው ኢትዮጵያ ውስጥ  እንደ አማራ ፌዴራላዊ የሆነ እሳቤ ያለውና  የፌዴራል ሥርዓት የሚያራምድ ቡድን የለም።
የኦሮሞ ብሔርተኞች ስለ ፌዴራሊዝም መብት አጎናጻፊነት ይሰብካሉ። በነሱ  ትርጉምና መስፈርት ፌዴራሊዝም  ማለት ለማንነት እውቅና መስጠትና ራስን በራስ ማስተዳደር ነው። በመሰረቱ በፌዴራል ስርዓት ከፍተኛው የአስተዳደር አደረጃጀት ቀበሌ ነው። በዚህ በኦሮሞ ብሔርተኞች የፌዴራሊዝም  ትርጉምና አደረጃጀት መርሆ መሰረት ስራቸው በተግባር ሲታይ  እንደ ኦሮሞ ብሔርተኞች  ፌዴራሊዝም የሚሰጠውን መብት ገፋፊና ፍጹም አሐዳዊና እጅግ የተማከለ  ስርዓት አራማጅ የለም።
በኦነግና በወያኔ ፕሮግራም መሰረት ከተከፋፈሉ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ግዛቶች መካከል ኦሮምያና አማራ የሚባሉት ሁለቱ የፌዴሬሽኑ አካሎች  ዋና ዋና የሕገ መንግሥት ተብዮው ውሉድ የሆኑ ክልሎች ናቸው። አሐዳዊ ስርዓት አራማጅ ነው ተብሎ የሚከሰሰው አማራ ያስተዳድረዋል በሚባለው የአማራ ክልል  ውስጥ  በኦሮሞ ብሔርተኞች የፌዴራሊዝም ትርጉምና መስፈርት መሰረት ቢያንስ ስድስት ለማንነት እውቅና የተሰጠባቸውና ራሳቸው በራሳቸው የሚያስተዳድሩ የፌዴራል አደረጃጀቶች [federal units] አሉ። እነሱም የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የዋግ፣ የአዊ፣ የቅማንትና የአርጎባ የፌዴራል አደረጃጀቶች ናቸው። በነዚህ አማራ ያስተዳድረዋል በሚባለው ክልል ውስጥ የሚገኙ የፌዴራል አደረጃጀቶች ውስጥ ስድስቱም የፌዴራል አደረጃጀቶች የራሳቸው ፓርላማ ያላቸው፣ በኦሮሞ ብሔርተኞች መስፈር ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩ፣ ለማንነታቸው እውቅና የተሰጠጣቸውና በቋንቋቸው የሚማሩ፣ የሚዳኙና  የሚሰሩ ናቸው።
አማራውን በአሕዳዊ ስርዓት አማራጅነት በሚከሱት የኦሮሞ ብሔርተኞች የሚተዳደረው  ኦሮምያ በሚባለው አሕዳዊ ክልል ውስጥ በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠር አማራ፣ በሚሊዮኖች፣ በመቶ ሺዎችና በአስር ሺዎች የሚቆጠር ጉራጌ፣ አርጎባ፣ ትግሬ፣ ዝይ፣ ዳዋሮ፣ ጌዲዮ፣   ሐድያ፣ ካፊቾ፣ ከምባታ፣ ኮንሶ፣ ማኦ፣ ሲዳማ፣ ሲልጢ፣ ሶማሌ፣ ዎላይታ፣ የም፣ ወዘተ ይኖራል። በኦሮሞ ብሔርተኞች የፌዴራሊዝም ትርጉምና መስፈርት መሰረት እነዚህ ሁሉ  ኦሮምያ ክልል በሚባለው አሕዳዊ  “ፌዴራላዊ” ክልል ውስጥ የሚገኙ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች  ማንነታቸው እውቅና ተሰጥቶት ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር ነበረባቸው። ሆኖም ግን ኦሮምያ በሚባለው ክልል ውስጥ ከላይ ከክልል እስከ ታች  ቀበሌ ድረስ ከኦሮሞ በስተቀር ማንነቱ የታወቀና ራሱን በራሱ የሚያስተዳድር አንድም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ የለም!  ኦሮምያ የሚባለው ክልል  ማንነቶች የታፈኑበት፣ ራስን በራስ  ማስተዳደር  ፈጽሞ የማይቻልበትና  በዋለልኝ ቋንቋ  ክልሉ የብሔሮፕ፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እስር ቤት ነው ማለት ይቻላል።
እንግዲህ! ከኦሮሞ ውጭ ክልላችን በሚሉት ውስጥ የሚኖርን  አንዱንም  የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ ማንነት እውቅና ያልሰጡ፣ የራሱን ፓርላማ እንዲያደራጅ ያልፈቀዱ፣ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር ያላደረጉ፣ በቋንቋው እንዲማር፣ እንዲዳኝና ቋንቋው የስራ ቋንቋ እንዳይሆን  በሕግ  ያገዱና  እጅግ  የጠጠረና ልሙጥ የሆነ  አሐዳዊ ስርዓት የገነቡና የሚያራምዱ የኦሮሞ ብሔርተኞች ናቸው እንግዲህ  በነሱ የፌዴራሊዝም መስፈርት ማንነታቸው ታውቆ፣  የራሳቸው ፓርላማ ያላቸው፣ ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩ፣ ለማንነታቸው እውቅና የተሰጠጣቸውና በቋንቋቸው የሚማሩ፣ በቋንቋቸው የሚዳኙና ቋንቋቸው የስራ ቋንቋ የሆነ  ቢያንስ ስድስት የፌዴራል አደረጃጀት [units] የተዋቀሩበትን የአማራ ክልል የሚባለውንና መላውን አማራ በአሐዳዊ ሥርዓትና በተማከለ አስተዳድር አራማጅነት የሚከሱት!
ባጭሩ  የፌዴራሊዝም ጠብቆች ነን  የሚሉን አፈ ጮሌዎች የኦሮሞ ብሔርተኞች በተግባር አክራሪ የአሐዳዊ ስርዓት አራማጆች ናቸው። ቀደም ሲል የዘረዘርኳቸው ጨምሮ ዛሬ ኦሮምያ በሚባለው ክልል ውስጥ  የፌዴራል ስርዓት አራማጅ ነን በሚሉን የኦሮሞ ብሔርተኞች  መብታቸው ተገፎ ኦሮምኛ እንዲናገሩ የተገደዱ፣ ራሳቸውን በራሳቸው የማያስተዳድሩ፣   በቋንቋቸው የማይማሩና የማይዳኙ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቁጥር  ወደ ከ60  ይበልጣል። በተቃራኒው የአሐዳዊ ስርዓት አራማጅ ተደርጎ የሚከሰሰው የፈረደበት አማራ በተግባር ሲፈተሽ በእንደራሴነት የተሾሙትን ጨምሮ  መላው የአማራ የፖለቲካ ማኅበረሰብ  የፌዴራል ስርዓት አራማጅ ነው።
ሆኖም  ግን  ነገሩ ጩኸቴን ቀሙኝ  ሆኖ ከኦሮሞ ውጭ ላንድም ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ እውቅና ሳይሰጡ፣ ራሱን በራሱ እንዲያስተዳድር ሳይፈቅዱንስ እስከ ቀበሌ ድረስ አንድ አይነትና ልሙጥ የሆነ አሕዳዊ አገዛዝ የዘረጉት የኦሮሞ ብሔርተኞች የፌዴራል ስርዓት ተግባሪና አስተማሪ የሆነውን የአማራውን የፖለቲካ ማኅበረሰብ የእነሱ መገለጫ በሆነው የአሐዳዊ ስርዓት አራማጅና በጸረ ፌዴራል ስርዓት  አራማጅነት ይከሱታል! In fact they are  a perfect example of hypocrisy at its best!
Filed in: Amharic