>
5:01 pm - Wednesday December 3, 4380

ለጋራ ህመም በጋራ እንጩህ!! (ዘውድአለም ታደሠ)

ለጋራ ህመም በጋራ እንጩህ!!
ዘውድአለም ታደሠ
* ከኦሮሞ አባት ነው የተወለድኩት። ሊያውም በኦሮሞነቱ ከሚኮራና ከማይደራደር ኩሩ አባት!  ብቻውን ለመብቱና ለማንነቱ ተፋልሞ ዋጋ የከፈለና መብቱን ያስከበረ ድንቅ አባት ነው የወለደኝ።
* ከአማራ እናት ነው የተተወለድኩት። እመቤት የሆነች እናት ነች ያለችኝ። የፍቅርና የደግነት ጥግ የሆነች እናት!
ስጋዋን ቆርሳ ለመስጠት የማታመነታ ውብ እናት!!
ሁለቱ አዲስ አበባ ላይ ተፋቅረው፣ ተዋደው፣ ቡጊ ቡጊ ጨፍረው፣ አንድም ቀን ፍቅራቸው ውስጥ ብሔራቸውን ጣልቃ ሳያስገቡ እኛን ወልደው በፍቅር አሳደጉን!!!
ማታ ማታ አባታችን እስከሰባት አያቱ ድረስ ስማቸውን
እያስጠና ስለሐገሩ በፍቅር ያወራናል። እናታችን የአፄ ቴዎድሮስና የበላይ ዘለቀን ታሪክ እንደ ቤድ ታይም ስቶሪ ታነብልናለች!
እኛ ልጆቻቸው ኦሮሞን እየወደድን አማራን እያከበርን አዲስአበባዊ ሆነን ነው ያደግነው። ስለዚህ እኔ የቅም አያቴ ቶሌ መንፈስ ፣ የበላይ ዘለቀና የቴዎድሮስ ጀግንነት በደሜ ውስጥ አለ። ሁለቱንም አቅፎ በሚያኖር አዲስአበባዊ ማንነት ደግሞ ተገንብቻለሁ። እንደአዲስ አበባዊነቴ ደግሞ ከወላጆቼ ብሔር ባለፈ ከትግሬውም ፣ ከአፋሩም ፣
ከጉራጌውም፣ ከሲዳሞውም፣ ከወላይታውም፣ ከሀደሬውም፣ ከሙስሊሙም፣ ከፕሮቴስታንቱም፣ ከካቶሊኩም፣ ከኦርቶዶክሱም፣ ጋር በፍቅር የመኖር ክህሎትን አዳብሪያለሁ።
እስከማውቀው ድረስ የትኛውም ኢትዮጵያዊ ማንንም ገፍቶና አፈናቅሎ የመኖር ፍላጎት የለውም። ወደኦሮሚያ ሄዶ ጎጆ የቀለሰው አማራ ሐገሬ ነው ብሎ ኦሮሞን አምኖ እንጂ ማንንም የመውረር እኩይ አላማ ኖሮት አይደለም። ደሃ ነው። ፖለቲካ አያውቅም። ደሃ ራሱን የሚያስጠጋበት ስፍራ ማግኘት ብቻ ነው አላማው።
በአዲስ አበባ ዙሪያ ያለችውን ጥሪት አሟጦ የቆርቆሮ ቤት ይቀልስና ወደሸገር ጠጋ እያለ ያገኛትን ሰርቶ ወደቤቱ ይገባል። በቃ ሌላ ፖለቲካዊ አጀንዳ የለውም።
ኦሮሞውም እንደዚያው ነው። የትኛውም የኦሮሞ ገበሬ ወገኖቹን የማፈናቀል አላማ የለውም። እሱ ራሱ የኑሮ ሰማይ ሲጠቁርበት ወደተለያዩ ክልልሎች ሄዶ ይኖራል። ከመሬቱ አፈናቅለው ብጣሽ ሳንቲም ወርውረውለት ይሸሽግበት ጥግ ሲያጣ በገዛ መሬቱ ላይ በቀን ስራ ተሰማርቶ ልጆቹን ያሳድጋል። በኦሮሞ ባህል የሰው ሃቅ ነውር ነው! በኦሮሞ ስርአት እንግዳ ክቡር ነው። በኦሮሞ ስነልቦና ምስኪኖችን መግፋት እርም ነው። ለዚህ ነው በደደብ ባለስልጣኖች መሬቱ ተቀምቶ ሲቸገር የቂሙን በትር እንደርሱ ያሉ ምስኪኖች ላይ አሳርፎ ማያውቀው።
ለዚህ ነው አምና ፉሪ ላይ ስድስት ሺ ቤቶች l ህገ ወጥ ተብለው ሲፈርሱ ገበሬው ከነዋሪው ጋር አብሮ ሲያለቅስ ያየነው። ወዳጄ ኦሮሞኮ ማቀፍ ባህሪው ብቻ ሳይሆን መተዳደሪያ ህጉ ነው። አለም “አዶፕሽንን” ህጋዊ ከማድረጓ በፊትኮ ኦሮሞ “በጉዲፈቻ” ልጅ እየወሰደ ከልጆቹ በላይ አንቀባሮ ያሳድጋል። አለም የተጠጓትን “ሲቲዝን” አድርጋ
ከመቀበሏ በፊትኮ ኦሮሞ “በሞጋሳ” ወደሱ የተጠጋውን መፃተኛ ሁሉ በኦሮሙማ አጥምቆ ከራሱ ግንድ ጋር ሲቀላቅል ነው የኖረው። እንዴ ወዳጄ … የዘርና የጎጥን አጥር አልፎ ሰውን ሰው ሆኖ በመቀበልኮ ኦሮሞ ከአለም ሁሉ ይቀድማል!
አዲስ አበባዊም አሁን ፖለቲከኞች እንደሚጠመዝዙት አይነት ማንነት የለውም። ከንጉሱ ዘመን ጀምሮ ገጠር ላለ ገበሬ ሲጮህ የኖረ ህዝብ ነው። ማንንም አፈናቅሎ የመኖር ፍላጎት የለውም። እውነተኛው የአዲስ አበባ ሰው ከዘርና ከጎሳ ከፍ ያለ ነው። ለበቀለ ገርባም ሆነ ለመረራ ጉዲና ፣ ለእስክንድር ነጋም ሆነ ለአንዷለም አራጌ፣
እኩል ሲጮህ የኖረ ህዝብ ነው አዲስ አበባዊ። በኢህአዴግ የግፍ ጡጫ መከራውን ሲበላ የኖረ፣ በቤት እጦትና በኑሮ ውድነት አሳሩን እያየ ያለ ህዝብ ነው የሸገር ሰው። የአዲስ አበባ ሰው ከኦሮሞው ጥያቄም ሆነ ከየትኛውም ንቅናቄ ጋር ጠብ የለውም። የኦሮሞውን ጥያቄና ከመሬቱ ተፈናቅሎ የተበተነው የእልፍ የኦሮሞ ገበሬን ጩኸት
በጥሞና የሚያስረዳው ሰው ቢያገኝ ለገበሬው መብት መከበር ሆ ብሎ እንደሚወጣ ታሪክ ምስክር ነው።
በሰከነና በሰለጠነ መንገድ ሚነግረው ቢያገኝ ዛሬም እንደትናንቱ «መሬት ላራሹ» ብሎ እንደሚጮህ እርግጠኛ ነኝ።
ዛሬ ዛሬ የምናየው ጫፍ የያዘ የጥላቻ ፖለቲካ የትኛውም ህዝብ ውስጥ የለም። 85 ሚሊየኑ
የኢትዮጵያ ገበሬም ሆነ የአዲስአበባ ነዋሪ ልብ ውስጥ አስቀያሚው ዘረኝነት የለም! ዘረኞቹ አወቅን የምንለው ተማርን የምንለው ዛሬን እንጂ ነገን አሻግረን ማየት  ፣ ለኑሯችን እንጂ ለታሪካችን በማንጨነቀው በኛ ልብ ውስጥ ነው ጥላቻ ያለው።
ስለዚህ ለራሳችን ስንል እንስከን! እልፍ ጥያቄ ቢኖረንም የዘመናት ጥያቄን በአንድ ጀንበር ካልፈታን አንበል።
ሰከን ብለን የኦሮሞ ገበሬን ጥያቄ እንመልስ፣ በውይይትና በድርድር ለመቶ አመታት የሚያኖረንን ዲሞክራሲ እንገንባ! የአንዱን ጩኸትና ጥያቄ ዘር ሳንመርጥ ፣ አጥንት ሳንቆጥር አብረን እንጩህ! የምንጣላው ከጣሊያን ጋር አይደለም። በአጋጣሚ ከሌላ ብሔር የተወለደ ወንድማችን ጋር እንደሆነ እናስብ! በመጨረሻም እኔ እንደአዲስ አበባ ልጅነቴ እንዲህ እላለሁ ….
«ማንም ሰው ከየትኛውም ክልል አይፈናቀል! የተፈናቀለም የወደፊት ኑሮውን የሚያቋቁምበት ድጋፍ ይደረግለት»!
አዎ እንደአዲስ አበባ ልጅነቴ እንዲህ እጠይቃለሁ ..
«አዲስ አበባን በማስፋት ስም ከመሬቱ በግፍ የተፈናቀለ ገበሬ እምባ ይታበስ! አዎ … መሬት ላራሹ! »
Filed in: Amharic