>

* ዶሮ ሳይጮህ ጴጥሮስ ጌታውን " አላውቀውም" በማለት ሶስት ጊዜ እንደካደው ሁሉ ኦዴፓም ኢትዮጵያን ክዷታል!!! [ቢንያም ፈንቴ]

“በእውነት እልሃለሁ በዚች ሌሊት ዶሮ ሳይጮህ ሶስት ጊዜ ትክደኛለህ “ ማቴ 26÷34
* ዶሮ ሳይጮህ ጴጥሮስ ጌታውን ” አላውቀውም” በማለት ሶስት ጊዜ እንደካደው ሁሉ ኦዴፓም ኢትዮጵያን ክዷታል!!!
ቢንያም ፈንቴ
ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ልጅ ለመታደግ ከሰማዬ ሰማያት ወርዶ ከድንግል ማርያም ተወልዶ ወደዚህ ምድር መጥቶ ሲኖር አስራ ሁለቱን ሐዋርያት ከመረጠና የሶስት ዓመት አገልግሎቱን ጨርሶ ለሰው ልጆች የሚገባውን ዋጋ ለመክፈል በተዘጋጀበት ወቅት ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አላቸው “እረኛውን እመታለሁ÷ የመንጋውም በጎች ይበተናሉ” ተብሎ ተፅፏልና በዚህች ሌሊት ሁላችሁም ትክዱኛላችሁ። ነገር ግን ከሞት ከተነሳሁ በኋላ ወደ ገሊላ ቀድሜያችሁ እሄዳለሁ።”
በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ “ሌሎቹ እንኳ ቢክዱህ እኔ ከቶ አልክድህም።” ብሎ ተናገረ። ኢየሱስም “በእውነት እልሃለሁ÷ ዛሬ በዚህች ሌሊት ዶሮ ከመጮሁ በፊት አንተ ሶስት ጊዜ ትክደኛለሁ” አለው። ጴጥሮስ ግን “ከአንተ ጋር መሞት እንኳ የሚያስፈልግ ቢሆን እሞታለሁ እንጂ ከቶ አልክድህም” አለው።
በታሪክ ውስጥ አንድን ህዝብ ከወደቀበት መከራ አንስተው ወደ ከፍታ ለማውጣት በዘመናት ሁሉ የሚነሱ ታሪክ ሰሪ መሪዎች ተነስተዋል÷ ወደ ፊትም ይነሳሉ። ከእነዚህ መሪዎች ውስጥ አንዱ የሆነው ኢየሱስ በእስራኤላዊያን ዘንድ ትልቅ ተስፋ ተጥሎበት ነበር። ምክንያቱም በዚያ ዘመን እስራኤላዊያን በሮሞ ግዛት ስር ወድቀው እየተሰቃዩ ነበር። ዛሬም አገራችን ኢትዮጵያ ላለፉት 27 ዓመታት በህወኃት የጭቆና ቀንበር ስር ወድቃ ብዙ ዋጋ እየከፈልን ኖረናል። ነገር ግን በስርዓቱ ላይ ህዝባዊው አመፅ እየተቀጣጠለ ሲመጣና በኢህዴግ ውስጥም ለውጡን የሚደግፉ ደቀ መዛሙርት ተፈጠሩ። ህዝባዊው አመፅ በሁሉም አቅጣጫ እየተቀጣጠለ ሲመጣ ኢህአዴግ ከሶስት ተከፈለ። ለውጡን የሚደግፉ÷ ለውጡን የሚቃወሙና በሁለቱ መካከል የቆሙ ኃይሎች።
ከ2007 ዓ. ም ጀምሮ የኦሮሞና የአማራ ህዝባዊ እምቢተኝነት የመንግስትን አቅም እየተገዳደረ በመጣበት ወቅት ለማ መገርሳ÷ ገዱ አንዳርጋቸው÷ ደመቀ መኮንንና ዶ/ር አብይ አህመድ ጨለማውን ሰንጥቀው ለትውልዱ የለውጥ ሻማ ለኮሱ÷ ኢትዮጵያዊነትን አቀነቀኑ÷ አንድነትን ዘመሩ÷ ነጋችንን በብሩህ ተሰፋ ሞሉት። በዚህ ወቅት ዶ/ር አብይ አህመድ ከኋላ ወደ ፊት መጥተው ትውልዱን ወደ ከበረ የተስፋ ማማ አወጡት። ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድ ልብ አጨበጨበቸው። ነገር ግን የሌሊቱ ድቅድቅ ጨለማ መንጋት ሲጀምር÷ ወፎችም የከበረ የነፃነት ዝማሬያቸውን በምድሪቷ ዙሪያ ማሰማት ሲጀምሩ የለውጡ ጠረን ተቀየረ። በዚህ የጨለማና የብርሃን የሽግግር ወቅት አራት አስደንጋጭ ብሎም አሳፋሪ ክስተ በምድሪቷ ላይ ተፈጠሩ። በመጀመሪያ አንድ ወጣት በሻሸመኔ በግፍ በእንጨት ላይ ተሰቅሎ ተገደለ። በሁለተኛ ደረጃ በቡራዮና አሸዋ ሜዳ የሰው ልጅ እንደ እንስሳ ታርዶ ተገደለ። በሶስተኛ ደረጃ ይህንን አረመኔዊ የሰው ልጅ ጭፍጨፋ አውግዘው በሰላማዊ መንገድ ሀሳባቸውን የገለጡትን የአዲስ አበባ ወጣቶች በጥይት መግደልና ማሰር። በአራተኛ ደረጃ ደግሞ በለገጣፎ ከ1989 ዓ. ም ጀምረው ቤት ሰርተው÷ ሀብት አፍርተው የኖሩ ዜጎችን ቤታቸውን በማፍረስ ወደ ጎዳና በተኗቸው።
በዚህ ሁሉ ውስጥ ብዙ የተዘመረለት÷ ብዙ ተሰፋ የተጣለበት÷ ኢትዮጵያዊ ሙሴ ተብሎ የተወደሰው÷ የኢትዮጵያን ስም ጠርቶ የማይጠግበውና እንዲሁም “ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው!!” በማለት የሚሊዮኖችን ድጋፍ ያገኙት ዶ/ር አብይ አህመድና አቶ ለማ መገርሳ ድምፃቸው እየቀጠነ መጣ÷ ኢትዮጲያዊነት እየተዳከመ ዘረኝነት ደግሞ ጡንቻውን እያፈረጠመ መጣ።
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያንም ዶሮ ሳይጮህ ሶስት ጊዜ ተካዱ። እነሱም:-
ክህደት 1:- የኦህዴድ አመራሮች ከኢትዮጵያዊነት ዝማሬ ወደ ዘረኝነት ዝማሬ በፍጥነት መውረድ
ክህደት 2:- ኢትዮጵያ ሰባት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከህወኃት የበላይነት ወደ ኦዴፓ የበላይነት በፍጥነት መሸጋገር
ክህደት3:- “ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው!!” የሚለው ወርቃማ አበባል በአጭር ጊዜ ውስጥ “ፊንፊኔ ኬኛ” በሚለው መቀየሩ።
ዶሮ ሳይጮህ ጴጥሮስ ጌታውን አላውቀውም በማለት ሶስት ጊዜ እንደካደው ሁሉ ኦዴፓም ኢትዮጵያን ክዷታል።
የኦዴፓ የክህደቱ መገለጫዎችም:-
1. አዲስ አበባን በህዝብ ባልተመረጠ ከንቲባ እንድትተዳደር ማድረቸው÷ በከተማዋ ቁልፍ የመንግስት የኃላፊነት ቦታዎች ላይ የኦሮሞ ተወላጆችን መሾማቸው።
2. የአዲስ አበባ ፓሊስ በአብዛኛው በኦሮሞ ተወላጆች እየተተካ መምጣቱ
3. የአዲስ አበባ ከተማን ዲሞግራፊ ለማዛባት በከተማዋ ነዋሪ ላልሆኑ የኦሮሞ ልጆች መታወቂያ ማደል።
4. በአዲስ አበባ ከተማ በእያንዳንዱ የመንግስት ት/ቤት አምስት አምስት የኦሮሞ መምህራንን ከህግ ውጭ መመደብ።
5. የአዲስ አበባ ከተማ ቀስ በቀስ በኦነግ ስር እንድትወድቅ እየተሰራ ያለ ስራ መኖሩ።
6. ኦዴፓ ከተነሳበት የኢትዮጵያዊነት ከፍታ በከፍተኛ ፍጥነት ወርዶ ወደ ዘረኝነት ካምፑ ውስጥ መግባቱ።
በአጠቃላይ የዶ/ር አብይ አህመድ መንግስት እየተጓዘበት ካለ የስህተት ጎዳና ወጥቶ ቀድሞ ወደ ተነሳበት የኢትዮጵያ ከፍታ በፍጥነት ካልተሸጋገረ አገራችንን ከድጡ ወደ ማጡ ማስገባታቸው የማይቀር ሆኖ ይታየኛል።
Filed in: Amharic