>

የኦ.ዴ.ፓ መግለጫ በኦሮ-ማራ ቅንጅት ላይ ተመሥርቶ የነበረው ሽግግር መጨናገፉን የሚያሳይ ነው!!!  (ያሬድ ጥበቡ)

የኦ.ዴ.ፓ መግለጫ በኦሮ-ማራ ቅንጅት ላይ ተመሥርቶ የነበረው ሽግግር መጨናገፉን የሚያሳይ ነው!!! 
ያሬድ ጥበቡ
 
ማለቂያ የሌለው የቄሮ ጥያቄ እየጨመረ ሲሄድ መመለስ የማይችሉበት ቀን ስለሚመጣ፣ ያን ጊዜ እናንተ ኦህዴድ በነበራችሁበት ወቅት በወያኔ ተላላኪነት ይህን ይህን በደል ፈፅማችሁብን ነበር የሚል ሂሳብ ማወራረድ አይቀሬ ነው!!!
የኦሮሞ ክልላዊ መንግስት መግለጫ አሳፋሪና ቄሮን ለማስደሰት ያለመ ጠባብ ብሄርተኛ መግለጫ ነው። ኢትዮጵያውያን ከ2005 ዓም ጀምረው ከእለታዊ ምግባቸው እየቆጠቡ የገዙዋቸውን ቤቶች፣ አናስገባም የሚል መግለጫ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚመሩት ብሄርተኛ ፓርቲ መወሰኑ በኦሮማራ ቅንጅት ላይ ተመሥርቶ የነበረው ሽግግር መጨናገፉን የሚያሳይ ነው።
ዶክተር አቢይም ከተጠያቂነት ለመሸሽ በሚመስል መልኩ የአፍሪካ ቀንድ አስታራቂ ሚና ለመጫወት ቤተመንግስታቸውን ትተው በሚዞሩበት ወቅት የሚመሩት ፓርቲ ያወጣው መግለጫና በህገወጥ መንገድ የጎለቱት ከንቲባ “ያለሎተሪ እጣ ቤት ይሰጣችኋል” ብሎ ቆመጥ ዱላ ይዘው ለወጡ የኦሮሞ ወጣቶች የሰጠው መልስ፣ መንግስት ብሄራዊ ፀጥታዉ እንዲደፈርስ የበኩሉን ድርሻ እየተጫወተ መሆኑን ይጠቁማል። ሃገሪቷ እጅግ አሳፋሪ ወደሆነ ሥርአተአልበኝነት የምትገባበትን አደጋ ሥልጣን ላይ ያሉት የኦሮሞ ብሄርተኞች እየገፉት መሆኑን ያሳያል። ዛሬ ቄሮን ለማስደሰት የሚወስዷቸው እርምጃዎችና የህግ ጥሰቶች የሚፈጥረው ሥርአተአልበኝነት የመጀመሪያ ተጠቂ የሚሆኑት ራሳቸዉ የኦዴፓ መሪዎች መሆናቸውን ማወቅ አለባቸው። የቄሮ ጥያቄ እየጨመረ ሲሄድ መመለስ የማይችሉበት ቀን ስለሚመጣ፣ ያን ጊዜ እናንተ ኦህዴድ በነበራችሁበት ወቅት በወያኔ ተላላኪነት ይህን ይህን በደል ፈፅማችሁብን ነበር የሚል ሂሳብ ማወራረድ አይቀሬ ነው።
የኦዴፓ መሪዎች የጀመሩት የኦነግን አስተሳሰብ የሚከተል የቄሮ ጥያቄን ሁሉ የማስፈፀም ሥራ፣ አዴፓንም በአብን ግፊት በሚነሳሱ ወጣቶች ጥያዌ የመመራትን አደጋ ስለሚያስከትል፣ ይህ በመፍረስ ላይ ያለውን የኢህአዴግ አንድነት ክስመት በማፋጠን ሃገሪቱን ወደለየለት ሥርአተአልበኝነት እንዳይከታት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጉዟቸው ቀነስ፣ ኦዴፓ ላይ ያላቸውን ቁጥጥር ጠበቅ አድርገው፣ ተገቢውን ሃገራዊ አመራር ማሳየት አለባቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እየመሩ አይደለም። ተክለሰውነታቸውን እየገነቡ ነው።
በእኔ አመለካከት የብሄራዊ ፀጥታ መደፍረስ ክልሎቹን አዳርሶ የአዲስአበባን በር እያንኳኳ ስለሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃላፊነት ማሳየትና ተግባር ላይ መሰማራት አለባቸው። የኢህአዴግን ምክርቤት ስብሰባ ጠርተው ድርጅቱ ተገቢውን አመራር ሊሰጥ የሚችልበትን ሁኔታ መፍጠር አንዱ አማራጫቸው ነው። ኢህአዴግ እኮ ፈርሷል የቀረሁት እኔ ብቻ ነኝ የሚሉም ከሆነ፣ ኢትዮጵያን የምታህል ሃገር ብቻቸውን መምራት ስለማይችሉ፣ የኢህአዴግ አባልና እህት ድርጅቶችም የሚወከሉበት፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችንም ያካተተ የሽግግር ምክርቤት አቋቁመው ሽግግሩ የሚጎድለውን አመራር የሚያገኝበትን ሁኔታ ማመቻቸት ቅድሚያ ሊሰጡት የሚገባ ሥራ ይመስለኛል። ኦዴፓ ዛሬ በአዲስአበባ ላይ ያወጣው መግለጫ ከኦሮሞ ጠባብ ብሄርተኛ ፍላጎቶች ርቆ አመራር ሊሰጥ የሚችል በተለምዶ “ቲም ለማ” የሚባለው ቡድን ሥርአተ ቀብሩን የፈፀመበትና  ከኢትዮጵያ ህዝብ የተፋታበት ሰነድ እንጂ ነው። ሌላ ትርጉም ያለው አይመስለኝም።
Filed in: Amharic