>
9:50 am - Saturday November 26, 2022

ለመደመርም ጊዜ አለው - ለመቀነስም... ! (ሳምሶም ሚሀይሎቪች)

” ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው – የኦሮሞዎችን ልዩ ጥቅም እስካስቀደመ ድረስ!!! ” 
ሳምሶም ሚሀይሎቪች
ለመደመርም ጊዜ አለው – ለመቀነስም ! 
አስታውሳለሁ የዛሬ 10 ወራት በፊት እንደዛሬው ባለ ምሽት ሀገረ እሜሪካ ሚኖሶታ ይካሄድ የነበሩውን ” የመደመር” ትዕይንት ከአንድ ወዴጄ ጋር በማህበራዊ ሚዲያ እከታተል ነበር። አብይ ፣ ለማ እና ወርቅነህ ገበየሁ በአንድ መድረክ የታደሙበት ኢትዮጵያዊነት የገነነበት መቻቻል ከእነ ዕንከኑ እውን የሆነበት ድንቅ ዝግጅት ነበር። አራት የአንድ ብሄር ሰዎች መድረኩን ሲሞሉት (ኦቦ ጃዋርን ጨምሮ) ወዳጄ ምነው ከሌላ ብሄር ሰው ቢቀይጡ ? ሲል ሙግት ቢጀምር ” ብሄራቸው ነው ኢትዮጵያዊ ህልማቸው የሚቀድመው? ” ስል የተከራከርኩት አሁን ድረስ ትውስ ይለኛል። ያንን ኦሮሞ ከአማራ ፣ ሶማሌውን ከሸገር ልጅ ጋር አብሮ ያጫፈረ ትዕይንት እየተመለከትኩ በየደቂቃው ” ዕውን ይሄ በእኔ እድሜ ዘመን ሆነ ? ” ስል በደስታ ሲቃ አንብቻለሁ። ኢትዮጵያ ከተቀረው 110 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊ ለእኔ ፣ በአዳራሹም በደስታ ለሚቦርቁት ወገኖቼ ፣ እንደ እኔው እቴሌቪዥንና ኮምፒዩተር መስኮት ላይ አይናቸውን ተክለው ለሚፈነድቁት ብዙ ሺዎች የተለየ የምታደርግልን ኖሮ ሳይሆን ተስፋዋ ነበር በደስታ ያነሆለለን። የኢትዮጵያ ተስፋ ሌላም አልነበር ዜጎቿ አንተ ትብስ አንቺ ተባብለው በእኩልነት የሚኖሩበት ሀገር ትሆን የተያዘ ጽኑ ምኞት እንጂ።
እስከ ትናንት ምሽት ድረስ ያ ተስፋዬን ይዤው ዘልቄያለሁ። ታከለ ኡማን ለሚተቹ ወጣት ነው ይሳሳታል ደግፈን መሪ እናድርገው ስል ሞግቻለሁ። ለማ መገርሳን በሰላ ሂስ የሚጠርቡትን አንዳንዴም ቢሳሳቱ ባላየ እንለፍ benefit of doubt እንስጥ እያልኩ ድጋፌን ቀጥያለሁ። ኦህዴድ ያየሁት ሁሉ አማረኝ ሲልም ግዴለም መሪነትን እንደ አዲስ የተረከበ ድርጅት ነው ጥፋቱ ላይ አናትኩር ስል ቆይቼያለሁ። የተስፋዬ መሰረቱ ገዢው ፓርቲ ኦህዴድና አመራሩ ሁለተኛ ዜግነትን ለ 27 አመታት ኖረውታል አስተዳደራዊ ግድፈት ቢያሳዩም በዜጎች ዕኩልነት መርሆዎች ላይ ዳግም አይደራደሩም የሚል ጽኑ እምነት ስለነበረኝ ነው ። እኔ ተመኝቼ ሳይሆን የድርጅቱ መሪዎች በአደባባይ ለህዝብ የገቡትን ቃል መሰረት አድርጌ ! ቢያንስ ቢያንስ በአደባባይ ” ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው ” ሲል ያደመጥኩት ኦቦ ለማ መገርሳ ሱስ የሆነበት ኢትዮጵያዊነት ውስጥ አማራነት ፣ ጉራጌነት ፣ ጋሞነት ወዘተ ህብረ ብሄራዊነት ያለ መስሎኝ አምኜያለሁ። የዛሬው የኦህዴድ መግለጫ ግን ” ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው ” ከሚለው ለጥቆ በደቃቅ ፊደላት small print ” የኦሮሞዎችን ልዩ ጥቅም እስካስቀደመ ድረስ ” የሚል እንደነበረበት በቁርጥ አሳይቶኛል። ይህ ብቻም አይደለም 12 ሺ ገደማ ኢትዮጵያውያንን በለገጣፎ ቤታቸው እላያቸው ሲፈርስ የእነ ለማ ኢትዮጵያ እንደ ወያኔ ዘመኗ ጦቢያ ሰብአዊነትን በጎሰኝነት የሰረዘች አረመኔ ለመሆኗ ተመልክቼ ሌላ ጎሰኛ ስርዐት በሩ ላይ እንደቆመ ለመደምደም ከበቂ በላይ ማስረጃ ሆኖኛል። ዛሬ ኦሮሞዎች ከመሬታቸው ተፈናቀሉ ብለው የሚሞግቱን ሰዎች በለገጣፎ ተፈናቃዮች ላይ እንዴት እንደተሳለቁ ላስተዋለ እዚህች ሀገር ላይ ካሁን በኃላ ባለሙሉ መብት ዜጋ ነኝ ቢል ” አዎ ኦቦ ጃዋር ይሁን እስካለ ድረስ” እያልን ማስመር ግድ ሆኗል።
ከዛሬ ጀምሮ ” ሳልሳይ ወያኔ ” ስል የምጠራው ኦህዴድ መራሹ ዘረኛ አገዛዝ እንዲህ ተስፋዬን-ህልሜን በአጭሩ ከበላው መጪው ጊዜ እንዴት ሊሆን ነው ? ስል ራሴን መጠየቄ አልቀረም። በኦህዴድ የሀሰት ቃል ተስፋ ቆረጥኩ እንጂ በሀገሬ አሁንም እምነቴ እንዳለ ነው። ከአማራው ፣ ጉራጌው ፣ ትግሬው ፣ ኦሮሞው ጋር አብሮ ያኖረኛል ስል ተስፋን ያደረግሁበትን ” የመደመር” ካናቴራ ለአካባቢዬ የኦህዴድ ወኪል መልሼ እሰጣለሁ እንጂ አረንጔዴ ቢጫ ቀይ ሰንደቄን ከትከሻዬና የመኝታ ቤቴ ግድግዳ ከቶም አላወርደውም። ኦህዴድ ታሪክና ህዝብ የጣሉበትን ሀላፊነት በስግብግብነትና የአመራር ክህሎት ማጣት ገደል ከተተው ስል ደምድሜያለሁ እንጂ ኢትዮጵያ ችሎታ ያላቸው መሪዎች መውለድ አትችልም ስል ተስፋዬን አልጥልም።
በአጭሩ ከአስር ወራቱ የመደመር ጉዞ በኃላ ዛሬ በገዛ ሀገሬ ፣ በተወለድኩባትና አሁንም ድረስ ቤተሰቦቼ በሚኖሩባት ከተማ ሁለተኛ ዜጋ ላለመሆን ተቀንሼያለሁ !
Filed in: Amharic