>
5:16 pm - Wednesday May 23, 2903

በገዛ ፍጡሮቻቸው የተጠለፉት ወያኔዎች ! (አሰፋ ሀይሉ)

በገዛ ፍጡሮቻቸው የተጠለፉት ወያኔዎች !
አሰፋ ሀይሉ
* እና ግን እነዚህ ወያኔዎች ኢትዮጵያን በአምሳላችን እንሸንሽን ብለው የፈጠሯቸው ሶስት የወያኔ እጅ-ሥራዎች ዛሬ ወያኔዎችን የሚያስከነዱ ታላላቅ ኢምፓየሮች (ወይም “ቫምፓየሮች”) ሆነው ወያኔዎቹን በቁማቸው ሊውጡ ሊሰለቅጧቸው “አሞራ በሠማይ ሲያይሽ ዋለ” እየዞሯቸው ነው!!!

በአስመራ መንገድ ነው የተወለድኩት። አስመራ መንገድ በኤርትራ ክፍለሀገር ወይ በአስመራ ከተማ ያለ መንገድ አልነበረም። በአዲሳባ የሚገኝ መንገድ ነበር። 22 – ውሃ ልማት አካባቢ – የሚገኝ መንገድ። አንዳንዴ ይሄን ሳስበው – እዚያ አስመራ መንገድ የተቀበረ እትብቴ ነው ለካ ቀልቤን እያሸፈተ ወደ ኤርትራ እየወሰደ ያስቸገረኝ – እላለሁ። አሁን ግን የዚያ ሰፈር ስም ምናልባት “አዲግራት” ሠፈር በሚል ስያሜ አልተቀየረ ይሆን?? (lol)
እናማ እኛ ለወትሮው እንዲያ ነበርን። አዲሳባ ሆነህ ሁሉንም ማየት ትችል ነበር። ለምን በለኛ?!
… አዲሳባ ውስጥ አሜሪካን ግቢ የሚባል አለ። እደግመዋለሁ አሜሪካ አይደለም። እዚሁ አዲሳባ ነው። ወሎ ሰፈር አለ። በአዲሳባ። ጎጃም በር አለ። ጅማ በር አለ። አፍንጮ በር አለ። ወለጋ በር አለ። የረር አለ። ልደታ አለ። ላም በረት አለ። ብሔራዊ ቤተመዘክር አለ። ኢትዮጵያ ሲኒማ አለ። ሲኒማ ከተማ አለ። አዲስ ከተማ አለ። አርበኞች አደባባይ አለ። በላይ ዘለቀ መንገድ አለ።
ዶርዜ (ሀይዞህ) ሰፈር አለ። እንደራሴ ሰፈር አለ። ፊታውራሪ ኃብተጊዮርጊስ ድልድይ አለ። ሺ ሰለሞን ድልድይ አለ። አድዋ ድልድይ አለ። ዘነበ ወርቅ ሰፈር አለ። መስጊድ ሰፈር አለ። አዲሱ ሚካኤል ሰፈር አለ። ጎላ ሚካኤል፣ ተረት ሰፈር፣ መካነ እየሱስ አለ። ቦሌ አለ። ቦሌ ቡልቡላ አለ። ላም በረት አለ። ሌላ ቀርቶ ቫቲካን ራሱ አላት። አዲሳባ። ሁሉም አለ ባዲሳባ።
እንዳልኩት – በአዲሳባ – ሁሉም አለ። አዲሳባ የሁሉም ነቻ። ሁሉንም እንድትሆን ተደርጋ ነዋ የተቆረቆረችው። በኢትዮጵያ ታሪክ – ይህን የአዲሳባን የሁሉምነት ተፈጥሮ ሊቀይር የተነሳ ማንም የለም። ከወያኔ በቀር።
ወያኔዎች (በትክክለኛ ስማቸው “ህወኀቶች”) በ83 ዓ.ም. መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ የማስተዳደር ታሪካዊ አጋጣሚውን ሲያገኙ በዕድሉ መጠቀም ከበዳቸው። ኃላፊነቱ ከትከሻቸው በላይ እጅግ ሰፋባቸው። ለኢትዮጵያ የቆዳ ስፋት የሚመጥን አስተሳሰብ በእነሱ ዘንድ አልነበረም። ስለዚህ በጥበታቸው ልክ ሌሎች አርበ ጠባቦችን ፈለጉ።
እና ያ የጠባቦች ፍለጋቸው በኢትዮጵያ ታሪክ ታይተው ተሰምተው የማይታወቁ ሶስት “ጠባቦችን” ያስገኘላቸው መሠላቸው። ያን ሰፊ የኢትዮጵያ ሕዝብ በእነርሱ ወርድና ቁመና አምሳል ከተፈጠሩ፣ ከራሳቸው ውጭ የሌሎች ነገር የማይመለከታቸው “ቆዳ ሰፋፊ” ግን “አምሳለ ጠባብ” አብሮ-አስተዳዳሪዎችን ፈጠሩ።
አንደኛውን አምሳለ ጠባብ አስተዳደር “ኦሮሚያ”፣ ሌላኛውን “አማራ”፣ ሌላውን ደሞ “ደቡብ” እያሉ በእነርሱ አምሳል እንደዶሮ የጠበበ ዓይን ያላቸውን ክልሎችና አስተዳዳሪዎች ፈጠሩ። እነርሱ የጠሉት እና አምርረው የፈሩት “የሁሉም ነኝ” የሚል አካል ዳግመኛ የማይፈጠርበትን መላ ሁሉ አስሰው ተገበሩ። ሸነሸኑ። እነርሱ ከበላይ እና ከጀርባ ሆነው ከራሴ አልፌ ከሌላኛው ጋር እጅ ለእጅ እያያዛለሁ ያለውን አስተዳደር በልጓም ሊስቡ። ይህ ነበረ ዕቅዳቸው።
ዕቅዳቸው ያን “የሁሉም” የተባለ ነገር ማጥፋት ነበረ። ውጤቱስ? ፍፃሜውስ?? ውጤቱማ፣ ፍፃሜውማ…  የ”ፍራንከንስታይን” ፍፃሜ ሆነ። ፍራንከንስታይን የዛሬ 200 ዓመት ገደማ የተፃፈ የሜሪ ሼሊ ድርሰት ነው። ካነበብኩት ግን 15 ዓመት (ብቻ) ይሆነዋል። ሳይንቲስቱ ቪክቶር ፍራንከንስታይን ከቤተሰቡ ተነጥሎ በሩቅ ደሴት በመሄድ  እስከ ዘመኑ ከነበረው የሰው ልጅ እጅግ የላቀ ግዙፍ ፍጡር በቤተ ሙከራ (በላብራቶሪ) ይፈጥርና – በመጨረሻ ያ ፍጡር የራሱን የፍራንከንስታይን ዘርማንዘር አንድ በአንድ እያደነ ያጠፋቸዋል፣ እና ሳይንቲስቱ በባከነ ሰዓት ራሱ የፈጠረውን ምጡቅ ፍጡር ላጥፋው ብሎ አዲስ ዓይነት ሰዶ-ማሳደድ ውስጥ ይገባል። (Frankenstein, or, The Modern Prometheus, 1823, is a novel written by English author Mary Shelley that tells the story of Victor Frankenstein, a young scientist who creates a hideous, sapient creature in an unorthodox scientific experiment.)
ወያኔዎችም “ሁሉንም ኢትዮጵያ” እወክላለሁ የሚልን ነገር ሁሉ ከምድረገፅ ጠራርገው ለማጥፋትና በአምሳላቸው እንደነርሱ ጎራና ፈፋ ለይቶ የጠበበች የቆዳ ስፋትን እወክላለሁ ብሎ የሚነሳ አዲስ ሽንሽን ሰፍተው ኢትዮጵያን የተቦጣጠቀ ድሪንቶ ለማልበስ ከነበራቸው ችኮላ የተነሳ ነገ በእኛ በራሳችን ላይ ቢመጡ ጉድ ይሠሩናል ብሎ የሚያስብ ፀጋቸው ተገፈፈ።
ስለዚህ ወያኔዎች በታሪክ አንድ ሆኖ በአንድ አስተዳደር ተዳድሮ የማያውቅን የወለጋን፣ የባሌን፣ የአርሲን፣ የነገሌን፣ የሸዋን፣ የሐረርጌን፣ የጅማን፣ የኢሉባቦርን፣ የሰላሌን፣ ሌላውንም የኢትዮጵያ ሕዝብ ባንድ በማይችለው ጠባብ ኮሮጆ “ኦሮሚያ” ብለው በአምሳላቸው ጠፍጥፈው ሠሩ። ይሄ ብቻ ግን አይደለም።
ወያኔዎች ራሳቸውን እንደ “ፊዥን” በመላው ኢትዮጵያ ለማባዛት “ኦሮሚያ” የሚለው ፍጡራቸው ብቻ በቂ አይደለም። ስለዚህ “አማራ”ን ደግሞ ፈጠሩ። ወያኔዎች በታሪክ አንድ ሆኖ በአንድ አስተዳደር ተዳድሮ የማያውቅን ጎጃምን፣ ጎንደርን፣ ወሎን፣ ሸዋን፣ በአንድ በአምሳላቸው በጠፈጠፉት ጠባብ “አማራ” የተሰኘ የክልል ከረጢት ውስጥ አስገብተው ፈጠሩት።
ይሄ ብቻም አይደለም። ወያኔዎች የእነርሱን የጥበት ፖለቲካ በኢትዮጵያ ምድር ለማስረፅ ሲሉ – በታሪክ አንድ ሆነው በአንድ አስተዳደር ተዳድረው የማያውቁትን – በነገድ በቋንቋ የማይገናኙ ከ20 በላይ “ብሔሮች” ያሏቸውን ሕዝቦች በአንድ የጠበበ ከረጢት ሰፍተው “ደቡብ” ብለው በአምሳላቸው ጠፍጥፈው ሠሯቸው። /ስለዚህ ጉዳይ ነፍሱን ይማረውና የታላቁን የኢትዮጵያዊነት ውሉን በወያኔዎች የፖለቲካ ኦሪት ፈፅሞ ያልሳተውን የአሰፋ ጫቦን መፅሐፍና መጣጥፎች ያገኘ እንዲያው በሞቴ ቢያነባቸው!/
እና ግን እነዚህ ወያኔዎች ኢትዮጵያን በአምሳላችን እንሸንሽን ብለው የፈጠሯቸው ሶስት የወያኔ እጅ-ሥራዎች ዛሬ ወያኔዎችን የሚያስከነዱ ታላላቅ ኢምፓየሮች (ወይም “ቫምፓየሮች”) ሆነው ወያኔዎቹን በቁማቸው ሊውጡ ሊሰለቅጧቸው “አሞራ በሠማይ ሲያይሽ ዋለ” እየዞሯቸው ነው።
ከእነዚህ ወያኔ-ፈጠር የአስተዳደር ክልሎች የተፈለፈሉና ወያኔዎቹ በፍጥረት ቀኖቻቸው እንደተመኙት የኢትዮጵያዊነታቸው ውል የጠፋባቸውን እልፍ አዕላፋት ዜጎች ወደ እናት ሀገራቸው አቅል ለመመለስ ገና ነገና ከነገ ወዲያ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚከፍለው የደም ግብር ልኬቱ ተሰፍሮ ካሁኑ በውል አይታወቅም። እዝጌሩ በጥበቡ ይጋርድልን ማለት ነው እንጂ።
እና ግን ወያኔዎቹ – እንደ ቪክቶር ፍራንከንስታይን – በገዛ ፍጡራቸው ሊጨረገዱ እንደሆነ ከዘገየ ሲገነዘቡ – እንደ ሳይንቲስቱ ቪክቶር ፍራንከንስታይን – ነገ ጥርስ አውጥተው የሚከረታትፏቸውን – የገዛ ፍጡራኖቻቸውን ለማጥፋት –  ቆርጠው ተነሱ። እርስ በእርሳቸው የማጫረስ አጀንዳን ነድፈው። አጀንዳውን ብቻ አይደለም። ሥፍራውን ጭምር መርጠው።
በመነሻዬ እንዳነሳሁት አዲሳባ የሁሉም እንድትሆን የተቆረቆረች፣ የሁሉም ሆና የኖረች፣ የሁሉም፣ የሁላችንም  መዲናችን ነች። ወያኔዎቹ ግን ይህችን መዲና በወደፊት  በአርማጌዶንነት መረጧት። እና የጠብ ምድር አኬልዳማ የምትሆንበትን የወደፊት የግጭትና የቁርሾ ማስተርፕላን ቀየሱ። በቅድሚያ – ከሌሎች ፍጡራኖቻቸው ተነጥሎ – የፍጡራቸውን የኦሮሚያን ብቻ ልዩ መብት – በአዲሳባ እናስከብርለታለን አሉ።
ወያኔዎቹ ቀጠሉና “ኦሮ” የሚል ቅጥያ የተለጠፈላቸው የንግድ ተሽከርካሪዎችን በአዲሳባ አሰማሩ። ቀጠሉና በአዲሳባ የኦሮሚያ ልዩ አስተዳደርን ተከሉ። ቀስ አሉና ጋምታ ኦሮሚያ – ማለትም የኦሮሚያ የኅብረትሥራ ባንኮችን – በአዲሳባ አፈሉ። ቀጠሉና የኦሮሚያ ባንክ፣ የአዋሽ ባንክ፣ የኦሮሚያ ልማት ባንክ፣ ወዘተ እያሉ ቀጠሉ። ቀጠሉ አሁንም። ሀገረ ኤርትራ የኦነጎች መናኸሪያ ሆና አስቸግራቸዋለች። ስለዚህ አንድ መላ ታያቸው።
መላው ይህ ነው። በአዲሳባ ስቴድየም ፊትለፊት በሚገኘውና በወያኔዎች ተከፍቶ በወያኔዎች በታሸገው የኤርትራ ኤምባሲ ሥፍራ ላይ ተጎራብቶ ቁልቁል ኤምባሲውን እያየ ሽንቱን የሚሸናበት የሚመስል ከፍ ያለውን የከተማዋን እምብርት ሥፍራ መርጠው በሚሊየን ብሮች ከስክሰው “የኦሮሞ የባህል ማዕከል” (“ገላን ኦሮሙማ..”) ብለው ሙዝየምና አዳራሽ በኦሮሚያ ስም በአዲሳባ ከፈቱ።
ይህ ሁሉ ሲሆን ወያኔዎች እንደተመኙት አንድም በአዲሳባ በስሜ ባንኮችና ሙዝየሞች ይከፈቱልኝ ብሎ የጠየቀ የወያኔዎች ፍጥረት ስለመኖሩ በበኩሌ አልሰማሁም። አንዳንዶቹ የ”ኦሮሚያ” ነዋሪዎች ራሳቸው – የአዲሳባ ስቴዲየሙን የኦሮሞ ማዕከል – በስማችን የተገነባው የወያኔዎች የስንብት ሕንፃ – እያሉ ማላገጫ ሲያደርጉት – በጆሮዬ በታምቡሩ ሰምቼያለሁ። ቅሌት ብርቁ አይደል – ደሞ ይሄ ውርደት ለወያኔ ምኑ ናት??!! /በነገራችን ላይ … ዶ/ር አብይ አህመድ ብሔራዊ ቤተመንግሥቱን “የብሔር ብሔረሰቦች ሙዝየም-ፓርክ” አደርገዋለሁ ሲል… ትልቁ “የወያኔዎች የስንብት ሕንፃ” ትዝ ብሎኝ ሳቅ ከጅሎኝ ነበር!!😁😁
የሆነስ ሆነና። የአርበኞች መዳረሻ፣ የመሪዎች መናገሻ፣ የሁሉ መጠጊያ፣ የሁሉ ማረፊያ – ውቢቱ አዲሳባ – የሁላችን ናት።
ዘለዓለማዊ ክብር – ሀገራቸውን ከፋሺስቶች መዳፍ በደማቸው ተዋጅተው – የክብር ባንዲራቸውን ከፍ አድርገው እያውለበለቡ – ወደ መዲናቸው ወደ አዲስ አበባ ለገቡ –  ለመላው ኢትዮጵያውያን የሁሉም ኢትዮጵያውያን ጀግኖች አርበኞች – ይሁንልኝ!!!
Filed in: Amharic