>
7:24 am - Tuesday December 6, 2022

የማያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል!!! (ዳንኤል በቀለ)

የማያጠግብ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል!!!
ዳንኤል በቀለ
አሁን አዲስ አበባ ላይ ለተፈጠረው  ውጥረት የጠሚ ዓብይ አህመድ በመዲናዋ ዋና ፖለቲካ ጥያቄ ላይ ቸል የማለትና የ ‘አላየሁም ፥አልሰማሁም፥ እባካችሁ አትንገሩኝ” ፖለቲካም አስተዋጽኦ አበርክትዋል።
ሐሙስ ገዥውኦዴፓ ላወጣው መግለጫ የጠሚው መልስ ይሄ ካኦሮሚያ ክልልና ካዲሳባ መስተዳደር የተወጣጣ የክልል ኮሚቴ ማቁዋቁዋም ከሆነ አገሪቷ ገና ብዙ ፈተና ይጠብቃታል።
 የኮሚቴው መቁዋቁዋም ባዲሳባ የባለቤትነት ወይም የልዩ ጥቅም ፈላጊዎችን ጥረት አይገታም፥ አያረካም።
 አዲሳቤዎችንም አሁን ከገጠማቸው ስጋት አያረጋጋም። ኮሚቴው በሳቸውና በመንግስታቸው ላይ የነበረውን አሁን
ግን በፍጥነት እየተሸረሸረ የ መጣውን ያዲሳቤዎችና የኢትዮጵያኖች አመኔታም አያቆመውም።
እሳቸ ው በሊቀ መንበርነት የሚመሩት ፓርቲ አዲሳባ የኦሮሚያ ክልል ናት የሚል መግለጫ አውጥቷል። ይሄ አቁዋም መዘንጋት የለበትም። ከተማዋ ተካለለችም አልተካለለችም እንደ ገዢው ፓርቲ ኦዴፓ መግለጫ አዲሳባ የኦሮሚያ ክልል ናት።
ስለዚህ ጥያቄው ከተማዋን የማካለል ብቻ ሳይሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሄ አሰከብራለሁ የሚሉትን ሕገ መንግስትን በጣሰው የፓርቲያቸው መግለጫና አቁዋም ይስማማሉ አይስማሙም የሚልም ነው።
በዚህ ላይ ጠሚው በግልጽና በቀጥተኛ ቁዋንቁዋ ሕዝባቸውን ማናገር ያለባቸው ይመስለኛል።
ጊዜ ክፉ ነው። ባማሩ ቃላቶች ይሄንን ጥያቄ ሸፋፍነው ቢሄዱ ክፉው ጊዜ ቀድሙዋቸው ሄዶ፥ ወንድማማች ሕዝቦችን ለጦርነትና ለእልቂት የሚጋብዙ እብሪተኞች በከተማዋና በኢትዮጵያ ላይ ጉልበት ያገኛሉ።
 
የኮሜዲው … ማለቴ የኮሚቴው ጉዳይ 
ኮሚቴው በአዲስና በኦሮሚያ መካከል የድንበር አካላይ ኮሚቴ ከሆነ በዚሁ ኮሚቴ ምስረታ ሎጂክ መሰረት አዲስ አበባ እና ኦሮሚያ በአሁኑ ፌዴራሊዝም በድንበር የሚለያዩ ሁለት የመንግስት መዋቅርን የሚከተሉ ለየቅል አስተዳደር ያላቸው ሊሆኑ ነው። በይፋ ኦሮሚያ ከአዲስ ባለቤትነት ልትወጣ ይሆናል።
 ይህ የጨነቃቸው እነጃዋር “ኮሚቴው በኦሮሚያ ልዩ ዞን እና በፊንፊኔ/አዲስአበባ መካከል የአስተዳደር ድንበር የሚያበጅ እንጂ በአዲስ አበባና በኦሮሚያ መካከል አይደለም” እያሉ ነው። ልዩ ዞኑ ኦሮሚያ ውስጥ ልክ የሌለ ይመስል።
 ነገሩ ወዲህ ነው። ድንበር የሚሰመረው በአንድ ክልል መካከል (ልክ በአዳማና በአደማ ገጠር ቀበሌ) ነው ለማለት ነው። አዲስ አበባ የኦሮሚያ አንዷ ከተማ መሆኗን ኮሚቴው አምኖ ይነሳል ማለት ነው። ይህ ቀልድ ነው ለማሳመኛ የሚያቀርቡት። ኦሮሞን ከሌላው ህዝብ ጋር የሚያጣላ ከባድ ነገር ነው። ጠቅላዩ ሲጀመር በድምፅ ብልጫ ቢወሰን ሊያሸንፍ የሚችልን የእራስህ ቡድንን አዋቅሮ፣ በጥቅም ግጭት እና “ማንም ሰው በእራሱ ጉዳይ ላይ ደኛ ሊሆን አይገባም” የሚለውን የህግ ጥንታዊ መርህ በመጣስ ኮሚቴ ብሎ ፈርሞ ደብዳቤ ማውጣቱ በጣም የሚገርም ነው!
በነጃዋር ሎጂክ ከሄድን በአንድ ክልል መካከል የወሰን ጉዳይ ከተነሳ (መቼም ክልሉ ከፈሱ የተጣላ ሆኖ ማለት ነው) የሚመለከተው ያንን ክልል ነው። ፌደራል ማን ነኝ ብሎ ነው በክልል ጉዳይ ጣልቃ የሚገባው? ታከለ ኡማስ ማንን ወክሎ ነው ኮሚቴ ውስጥ የሚገባው?
እነ ጃዋርን መስማት ለእንደዚህ የተሳከረ ኮሚቴና ወዝጋባ ሁኔታ ይጋብዛል። ተዉ፣ ተዉ ህዝቡን አታስመርሩት። ተዉ!
ተዉ ግፍ ነው!
የፋና ዘገባ ከዚህ በታች
በኦሮሚያ ክልልና በአዲስ አበባ ከተማ መካከል ላለው የአስተዳደር ወሰን ውዝግብ መፍትሄ የሚያቀርብ ኮሚቴ ተዋቀረ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 30፣ 2011 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት እና በአዲስ አበባ ከተማ መካከል ያለውን የአስተዳደር ወሰን ውዝግብ በተመለከተ ዘላቂ መፍትሄ የሚያስቀምጥ ኮሚቴ ተቋቋመ።
የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት እና በአዲስ አበባ ከተማ መካከል ያለው የአስተዳደር ወሰን በአግባቡ አለመካለሉን አንስቷል።
ይህን ችግር በዘላቂነት በመፍታት የአስተዳደር ወሰን አካባቢዎች የግጭት እና የንትርክ አጀንዳ ከመሆን ይልቅ የልማት እና የፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚረጋገጥባቸው አካባቢዎች እንዲሆኑ በማሰብ ችግሩን በጥናት ላይ የተመስርቶ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት ከኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት እና ከአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር የተውጣጣ የጋራ ኮሚቴ ተዋቅሮ ጥናቶች ቢደረጉም የጥናቱ ውጤት ላይ ጉዳዩን መቋጨት አለመቻሉን ነው ፅህፈት ቤቱ ያመለከተው።
ይህም በመሆኑ የኦሮሚያ ክልል እና የአዲስ አበባ ከተማ ወሰን ጉዳይ አወዛጋቢ ሆኖ ቀጥሏል ብሏል።
በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት እና በአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር መካከል እልባት ያላገኘ የአስተዳደር ወሰን ይገባኛል ጥያቄ መፍትሄ ሳይሰጠው የጋራ መኖሪያ ቤቶች እጣ መውጣቱም ውዝግብ ማስነሳቱን ገልጿል።
በአዲስ አበባ ከተማ እና በኦሮሚያ ክልል መካከል ያለውን የአስተዳደር ወሰን ጥያቄን በዘላቂነት ለመፍታት ከዚህ በፊት የተጠኑ ጥናቶችን መሰረት በማድረግ እና ህዝቡን በማሳተፍ ዘላቂ መፍትሄ ማስቀመጥ ወሳኝ ሆኖ መገኘቱን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት አስታውቋል።
በዚህም መሰረት ስምንት አባላት ያሉት ከፌደራል መንግስት፣ ከኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት እና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር የተውጣጡ አባላትን የያዘ ኮሚቴ ተዋቅሮ ለጉዳዩ መፍትሄ የሚሆን ምክረ ሀሳብ እንዲያቀርቡ አቅጣጫ ተቀምጧል ነው ያለው።
የኮሚቴው አባላትም፦
1. ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል፦ የሰላም ሚኒስትር (የኮሚቴው ሰብሳቢ)
2. ወይዘሮ ጠይባ ሀሰን፦ የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርእሰ መስተዳድር (የኮሚቴው አባል)
3. አቶ አህመድ ቱሳ፦ በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርእሰ መስተዳድር ማእረግ የከተማ ልማት ክላስተር አስተባባሪ (የኮሚቴው አባል)
4. ዶክተር ግርማ አመንቴ፦ በኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርእሰ መስተዳድር ማእረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪ (የኮሚቴው አባል)
5. ኢንጂነር ታከለ ኡማ፦ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ (የኮሚቴው አባል)
6. አቶ እንዳወቅ አብ፦ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማእረግ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ (የኮሚቴው አባል)
7. ዶክተር ሰለሞን ኪዳኔ፦ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማእረግ የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪ (የኮሚቴው አባል)
8. አቶ ተስፋዬ በልጅጌ፦ የአዲስ አበባ ከተማ የከንቲባው የህዝብ አደረጃጀት አማካሪ (የኮሚቴው አባል)
Filed in: Amharic