>

የ ETV ውትወታዋ የገባው አለን?  ምን ፍጠሩ፤ ምንስ ይጠበስ እያለች ይሆን? (ዘመድኩን በቀለ)

የ ETV ውትወታዋ የገባው አለን? 
ምን ፍጠሩ፤ ምንስ ይጠበስ እያለች ይሆን?     
 ዘመድኩን በቀለ
★ ልብ በሉ የዚህ ሁሉ ሰቆቃ ዘጋቢና አቅራቢ ጉደኛዋ ETV ናት። የሰቆቃው ፈጻሚ ደግሞ ጠ.ሚ.ዶኮ ዐቢይ አህመድ የሚመራው የኦሮሞው ወኪል ኦህዴድ ነው። እናም ኢቲቪ ይሄን ስሜት ቀስቃሽ ዘገባ በዜና መልክ ሠርታ ሲታቀርብ ምን አስባ ነው ብሎ ያለመጠርጠር ጅልነት ነው። 
 
★ ወዳጆቼ መጠርጠር ደግ ነው። የሩዋንዳው እልቂት መነሻው በመንግሥት ሚዲያ የሚቀርብ የተበድለሃል፣ ተገፍተሃል ዘገባ መሆኑን ማስታወስም መልካም ነው። ወንድ ልጅ እያስለቀሱ በቴሌቭዥን ማቅረቡም እኔ ደስስስ አላለኝም። ትከሻዬን እየከበደውም ነው። እየሸከከኝ ነው።  ያውም በETV። 
#ETHIOPIA | ~ አዲስ አበባ።
•••
የኢቲዮጵያ ቴሌቭዥንና ራዲዮ ድርጅት የመጣ ገዢ ሁሉ የሚያገባትና ባሏም፣ ጌታዋም፣ ሚስትም አሽከርም የሚያደርጋት ጋለሞታን የመሰለች ተቋም መሆኗ ይታወቃል። ኢቴቪ ከመሥራቿ ግራማዊ አጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጀምሮ እስከ አሁን ለ 5 መንግሥታት እንደ ሚስትም እንደ አሽከርም ሆና አገልግላለች። የጃንሆይን በሞት ስታጣ የባሏን ገዳይ ወታደሩን ደርግን ለማግባት ዐይኗን አላሸችም። ንጉሡ ሞተው ሳይቀበሩ ነው ገዳዩን ወታደር በቬሎ ያገባችው። ቀጥሎ 17 ዓመት ሙሉ ከሁለተኛው ባሏ ከወታደሩ ጋር ካኪ ለብሳ ሀገር ምድሩን ስታካልል ከርማ ወታደሩን የጫካ ሽፍቶች አባርረው ዚምባቡዌ ካስገቡት በኋላ አሁንም በማግሥቱ ከጫካ ከመጡት ሽፍቶችና ወንበዴዎች ስትላቸው ከከረመችው ቡድን ጋር ደርግ ሐራሬ በገባ በሳምንቱ ግንቦት 20/1983 ዓም ከጠዋቱ 2 ሰዓት አካባቢ የቃል ኪዳን ቀለበት አስራ ሀገር ምድሩን ጉድ አሰኝታለች።
•••
ይሄም ፍቅር 21 ዓመት አካባቢ እንደ ባል ይዛ ከቆየችው መለስ ዜናዊ ጋር ስትዳራ ቆይታ እሱ በተፈጥሮ ሞት ሲለያት የሃዘን ልብሷን እንደለበሰች ኃይለማርያምን አግብታ ጉድ አሰኘችን። ኃይለማርያም ኑሮ ከብዶት ቤተሰቡን ማስተዳደር ሲያቅተው ጊዜና ወዳጅ ዘመድ ተመካክሮ ከቤት ሲያስወጣው አዲስ ባል መማግባት ጊዜ አልፈጀባትም። ኢቲቪ አሁን ያገባችው ባሏ አዲስ ጉልበት ያለው ወታደርም፣ ዶክተርም፣ ፓስተርም የሆነ እሳት የላሰ ባል ነው ያገባችው።
•••
እናላችሁ ይኽቺ ኢቲቪ ከመጣው ጋር ስትሞዳሞድ አንድም ቀን ተሳስታ ከህዝብ ወገን ቆማ ተሟግታ አታውቅም። በዘመነ ጃንሆይ ከንጉሡ እግር እግር እየተከታተለች ፎቶ ስታነሳ፣ ቪድዮ ስትቀርጥ ነበር የከረመችው፣ “ ጠሐዩ መንግሥታችን ” ስትል ቅሽሽም አይላት ነበር። በወሎ ሚልዮኖች ተርበው ሳሉ እሷግን ለንጉሡ ልደት ከፈረንሳይ የሚመጣ ኬክ ለመቅረጽ ካሜራዋን ወልውላና ደግና ቦሌ አየር ማረፈያ ወርጭና ፀሐይ ስትከካ ነበር። ፈረንጆች መጥተው ነው እሷ መሥራት የነበረባትን ሠርተው ረሃቡን ለዓለም የገለጡባት።
•••
ከደርግም ጋር እንዲሁ ነበረች። ሰማያዊ ካኪዋን ለብሳ ሀገር ምድሩ አይብቃኝ ሥትል ነበር የከረመችው። ከጓድ መንግሥቱ ኃይለማርያም አመራር ጋር ወደፊት እያለች በየአደባባዩ ግራ እጇን ስትቀስር ነበር የከረመችው። መቼም የቆየና አብሮ ያደገ ልማድ በቶሎ አይተውምና ኢቴቪ ሆዬ  በ1977 ዓም የነበረውን ረሃብ እንደ ቀድሞ ባሏ ዘመን በመደበቅ የአዲሱን ባሏን የአብዮቱን 10ኛ ዓመት ቅልጥ አድርጋ ታከብር ነበረ።
•••
በዘመነ ኢህአዴግም እንደዚያው ናት። በዚህ ዘመን እንዲያውም ይባስ ብላ ከአንድ ቤት 3 ሰው ነበር ያገባችው። የመጀመሪያው የኢህአዴግ የበኩር ልጅ መለስ ዜናዊ አግብቷት ሲሞት የማደጎ ልጅ የሆነውን ኃይለማርያምን አገባች። ኃይለማርያም እንደ አንበሳ ከቤት ተቀምጦ የበሬ ሥጋ ከመብላት ውጪ ቤቱን ማስተዳደር አልቻልክም ተብሎ ቤተሰቡም፣ ጎረቤቱም ከቤት ባባረረው ጊዜ እዚያው ኢህአዴግ ቤት ያደገውን ጩጬውና አፈ ቅቤው እስማርቱ አቢቹን አገባች። ይሄ ባሏ ከልጅነቱ ምላሱ ጤፍ መቁላቱ አስደናቂ ነው። ብር ካለው ይልቅ ምላስ ያለው ያግባኝ እንዳለችው ዚፒ ማለት ነው። ይኸው አቢቹን ካገባች እነሆ አንድ ዓመት ሊሞላት ነው።
•••
እኔን የገረመኝ የዚህች ከሁሉ ጋር፣ መስላ አዳሪ ምላስ ብቻ የሆነች ካድሬ ጣቢያ ሰሞኑን እያሳየች ያለው አመል ለእኔ ግራ የሚያጋባ መስሎ ታይቶኛል። ምን አስባ እንደሆን መድኃኔዓለም ይወቀው። ከዐቢይ አህመድ ጋር ሆና ወይ ሌላ ውሽማ በድብቅ ይዛለች አልያም አዲሱ ባሏ በእሷ በኩል ሊያበሳጨው የሚፈልገው ህዝብ አለ ማለት ነው። እንጂ በጤናዋ እንዲህ ሚሊዮኖችን ለቁጭት፣ ለእልህ፣ ለቂም በቀል የሚያነሳሳ ዘገባ አትሠራም ነበር።
•••
የ12 ዓመት ህጻን ባንክ ሲዘርፍ ነው የገደልኩት ይል የነበረውን የ3ኛው ባሏን ጉድ ለመሸፈን ቀሚሷን ገልባ ያዙኝ ልቀቁኝ ትል የነበረችዋ ኢቴቪ፣ በባህርዳር፣ በጎንደር ፣ በደብረ ዘይት ንፁሐን በ4 ተኛ ባሏ በኃይልሻ  ትእዛዝ በአግአዚ ጦር በአደባባይ ተረሽነው ተረፍርፈው ሳለ ፀረ ሰላም ኃይሎች ናቸው ብላ እንዳልለፈፈች አሁን በአዲሷ ባሏ ላይ ምን አስባ እንዲህ ብሶት ያዘለ የህዝብ ሮሮ ደረት እያስመታች እንደምትቀሰቅስ አልገባኝም።
•••
እኔ ይሄንን ከለውጥ ጋር አላየውም። የሆነ የተደገሰልንማ ነገር አለ። የሩዋንዳውን ራዲዮ ጣቢያ ማስታወሱ በቂ ነው። ጥሩም ይመስለኛል። መንግሥታዊ የቴሌቭዥን ጣቢያ በዚህ መጠን ጉዳዩን ካራገበው ነገሩ የከፋ ስለመሆኑ አትጠራጠሩ። ኢንተር ሃምዌይን በፉጨት እንደመጥራት ነው የምቆጥረው።
•••
ልብ በሉ አፈናቃዩ አዲሱ ባሏ ነው። አዲሱ ባሏ ዐቢይ አህመድ። እሱ የሚመራው የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ነው ዜጎችን በጠራራ ፀሐይ እያፈናቀለ ያለው። አፈናቃዩ ሲበዛ ጨካኝ መሆኑን የኢቲቪም ሆነ የመሰሎቿ ዘገባ ያሳየናል። ኦሮሞ አቋፊ ነው የሚለውን ትርክት የአቢቹ መንግሥት አፈር ከድሜ አስግጦታል። በሶማሊያ ክልል ሶማሌዎችን። በአዲስ አበባ ዙሪያ ዐማራዎችን፣ ጉራጌና ዶርዜዎችን በግሬደር እያፈረሱ ሲያባርሩ እነ ኤቴቪ እያሳዩን ነው። በጉጂ ዞን 9 መቶ ሺ የጌዲኦና የሌሎች በቁጥር አናሳ የሆኑ ብሔሮችን ይኼው የኦሮሞ ነገድ እያፈናቀለ ነው ብለው ሚዲያዎች እየዘገቡ ነው። ከወለጋ፣ ከኢሉአባቦራም ኦሮሞ ሌላ ብሔር ከመካከላችን ይውጣ ብለው እያስወጡ ስለመሆኑ እየተዘገበ ነው። የነገሩ ፍጻሜ አስፈሪ ነው።
•••
ይሄ አካሄድ ለኦሮሞ ለራሱ ይበጀዋል ወይ? አዋጭስ ነው ወይ? ከሁሉም ብሔር ብሔረሰብ ጋር ተናጭቶ ለብቻው ይዘልቀዋል ወይ? እኔ እንጃ። አይመስለኝም። ግጭቶች፣ ብሶቶች በኢቲቪ እስፖንሰር እየተደረጉ መቅረብ ከጀመሩ የጌታ መምጫው ቀርቧል ማለት ነው።
•••
እነ ኢቲቪ መጀመሪያ ቤቱ የፈረሰባቸውን ዜጎች አሰቃቂ ሰቆቃ ቀርጸው ያቀርባሉ። ሚሊዮኖች ያለቅሳሉ፣ ያስለቅሳሉ። ይቀጥሉና አፈናቃዩን የኦሮሚያ ክልል የሥራ ኃላፊዎች በመሄድ ያነጋግራሉ። የሥራ ኃላፊዎቹም እንደጀብዱ በሠሩት ግፍ ተኩራርተው ይመልሳሉ። ተፈናቃዮቹ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ስላልሆኑ አያገባንም ብለውም ያላግጣሉ። እና ማንን ነው የሚያገባው ሲባሉ ደግሞ የሚያገባው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርንነው። እኛ አፈናቅለን ከክልላችን አስወጥተናል። ተፈናቃዮቹ የሚገኙት አዲስ አበባ ክልል ሥለሆነ አያገበናም ብለው ያርፉታል። አዲስ አበባ የምትመራው ደግሞ በዚያው በኦሮሞው ከንቲባ በአባ ገዳው ልጅ በታከለ ኡማ ነው። ይሄን የሚሰማው ህዝብ ምን ሊያስብ እንደሚችል መገመት ብቻ ነው።
•••
የዘር ፍጅቱን በደንብ እየሠራበት ያለው የመንግሥት ጣቢያዎች ጭምር ናቸው ማለት ነው። የአማራ ክልልም፣ የትግራይ ክልልም እንዲሁ የነገዶቻቸውን ብሶት ከጫፍ እያደረሱት ህዝባቸውን በቁጭት እየሞሉ ለጀግና ሞት እያዘጋጁት ይመስላል።
•••
የጽነፈኛው ጃዋር ሚድያ የሆነው OMN ደግሞ ከዚህ በባሰ መልኩ ራቅ ብሎ እያሠራና እያሰበ ይገኛል። ዐማራን ለ3 ለመክፈል በጀት በጅቶ መከራውን እየበላ ይገኛል። የሆኑ ወጠጤዎችን በሚዲያው ሰብስቦ አገው፣ ቅማንት እያለ ለመከፋፈል እየጣረ ይገኛል። ትናንት ያየሁት የኦኤም ኤን የአገው ፓርቲ ኃላፊ ነኝ ያለ እንግዳ እንዴት እንዴት ያደርገው እንደነበር ያየ ሰው ብቻ ነው የሚገባው። ኦኤም ኤን ከትግሬው አሉላ ሰለሞን ጋር እንደሚሠራም ይታወቃል። አሉላ ዐማራው ይከፋፈልለት እንጂ ከሠይጣንም ጋር ቢሠራ ፈቃደኛ የሆነ ግለሰብ ነው።
•••
የሚገርመው ነገር እነሱው በዐማራ ላይ ኮትኩተው ያሳደጉት የአገው ፓርቲ የተባለው ስብስብ በትናንትናው ቃለ መጠይቁ ተንቤን በሙሉ አገው ነው ካለ በኋላ ሲያስበው የሚረዷቸው ትግሬዎቹ ናቸው እናም ደንገጥ አለና እነሱ ግን በሰላም እየኖሩ ነው። የተጨቆነው በዐማራ ክልል ያለው ነው ብሎ አረፈው። ለማንኛውም የዘር ቅስቀሳው ለማንም አይበጅም። እነ ጃዋር ዐማራን ለመከፋፈል ስትዳክሩ፣ ሸዋ፣ ባሌ፣ ወለጋ፣ አሩሲ፣ ጅማ፣ ሐረር ወዘተ የራሱን ጎራና ግሩፕ ይዞ አንዱ አንዱን ውጦ ለመጠቅለል ማሰፍሰፉን ባትዘነጉ ጥሩ ነው።
•••
እናም መፍትሄ ለሌለው ነገር መንግሥት ያፈናቀላቸውን ዜጎች ሳይረዱ፣ ሳይደግፉ፣ ዘወትር በሚዲያ አቅርበው እያስለቀሱ ለሕዝብ ማቅረብ ጥቅሙ የገባው ካለ ቢነግረኝ ወሮታውን ለመክፈል እገደዳለሁ። ተዘጋጁ ነው? ተበሳጩ ነው? ምን አባታችሁ ታመጣላችሁ ነው? እኛ እንዲህ ነን ማለታቸው ነው? ገና እያንዳንድሽን እንዲህ ነው የምናደርግሽ ለማለት ነው? ወይስ ደግሞ ብሔር ብሔረሰቦች ሆይ አፈናቃይህን ተደራጅተህ አንተም ዝመትበት ለማለት ነው? እኔ ነገሩም፣ አካሄዱም ጨርሶ ምንም አልገባኝም።
ሻሎም  ! ሰላም  !
መጋቢት 4/2011 ዓም
ከራየን ወንዝ ዳር

https://www.facebook.com/176519726046261/posts/800127243685503/

Filed in: Amharic