አምባቸው ደጀኔ (ከወልዲያ)
ሰዎች የተለያዬ ተፈጥሮ አላቸው፡፡ ሰውን እያሳቀ ራሱ የማይስቅ አለ፡፡ እያስለቀሰ የማያለቅስ አለ፡፡ ራሱ እየበላ ሌላውን የማያስበላ አለ፡፡ ራሱ እየተራበ ሌሎችን የሚመግብ አለ፡፡ ራሱ እየበረደው የተራቆቱትን የሚያለብስ አለ፡፡ እየሳቀና እያሳሳቀህ ይቆይና ምቹ ሁኔታን ጠብቆ ዥው ባለ ገደል የሚለቅህ አለ፡፡ ሰው ዓይነቱና ሥሪቱ ብዙ ነው፡፡ ቢቻልህ ሰው አትሁን፤ የተረገመው ዕድልህ ሰው ካደረገህም የዘመናችን ኢትዮጵያዊ አትሁን፡፡ በተቻለህ መጠን ከአፍሪካ ራቅ ብለህ ተፈጠር – በሶሎሞን ደሴቶችም ቢሆን፡፡
ካነበብኩት ትዝ የሚለኝንና ዶ/ር አቢይ አህመድን የሚመሳሰልብኝን አንድ ሰው ላስታውሳችሁ፡፡
ያ ሰው በቀን ውስጥ በሽዎችና በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አህዛብንና በፈጣሪ መኖር ጭራሹኑ የማያምኑ ከሃዲ ሰዎችን በጣፋጭ ስብከቱ ወደ እግዚኣብሔር እንዲመለሱና እንዲያምኑ ያደርጋል፡፡ አንደበቱን ከመክፈቱ በዙሪያው የሚገኝ ኢ-አማኒ (atheist) ሁሉ በዕንባ እየተነፋረቀና ፈጣሪውን በማሳዘኑ በጸጸት እየተገረፈ ወደ አምላኩ ይመለሳል፡፡ ያ ሰው ይህን ተዓምር ያደርጋል፡፡ ልዩ የንግግርና የማሳመን ተሰጥዖ አለው፡፡ የሚናገረው መሬት ጠብ የማይልና ሰማይና ምድር ሰጥ ለምበጥ ብለው የሚገዙለት መተተኛ ቢጤ ነው፡፡
ነገር ግን እርሱ ራሱ በእግዚአብሔር መኖር አያምንም፡፡ ሙልጭ ያለ አሹዋፊና በእግዚአብሔር ኅልውና የሚያላግጥ አጩልግ ነው፡፡ እርሱን አምነው ፈጣሪን የተቀበሉ ሰዎች ላይ ጭምር ያሾፍባቸዋል፤ “ድንቄም እግዚአብሔር” እያለ በጎንዮሽ ያላግጥባቸዋል፡፡
አንዳንድ ሰዎች እንዲህ ናቸው፡፡ ገራገርና የዋህ ናቸው ስትላቸው ሸረኛና ተንኮለኛ ናቸው፡፡ ብልኅና አስተዋይ ናቸው ስትላቸው ብልጣብልጥና መሠሪ ናቸው፡፡ የፊት ገጽታቸውንና የአነጋገር ለዛቸውን ተመልክተህ ደግና ሩህሩህ ናቸው ስትላቸው ውስጣቸው እባብ መሆኑን በተግባራቸው ትረዳለህ፡፡ እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች በአፍዝ አደንግዛቸው (satanic abracadabra) ሁለመናህን ከተቆጣጠሩ በኋላ እንደመጋጃ ያሻቸውን ይጭኑብሃል፡፡ እስስታዊ ባሕርይ ለነዚህ ሰዎች ዋና የኅልውና መሠረታቸው ነው፡፡ ሲያጃጅሉ አይጣል ነው፡፡ ምናልባት ከጨለማው ንጉሥ አንዳች ዕርዳታ ሳያገኙ አይቀሩም፡፡ አለነገር እንዲህ አይሆኑምና፡፡
ከእንደነዚህ ዓይነቶቹ አስመሳይ የዓለም ዜጎች መካከል አንዱ ጠ/ሚኒስትር አቢይ አህመድ መሆኑን ለመረዳት መጽሐፍ ገላጭ ዘንድ መሄድን አይጠይቅም፡፡ እስላሞች መስቀል ቢኖራቸው ኖሮ ከመሳለም ወደኋላ የማይል ልዩ ችሎታ ያለው ሰው ነው፤ በዚህ አደንቀዋለሁ፡፡ ሲሞቱ ቢያይ “ይሞታል”፡፡ ሲታመሙ ቢያይ ‹ይታመማል›፡፡ አባባ ታምራትን ተክቶ አንድም ብዙ ይሆንልሃል፡፡ ኬንያ ነው ስትለው በሱዳን በኩል ብቅ ይልልሃል፡፡ ጀርመን ገባ ስትለው ደምቢዶሎ ላይ በደስታ በሽታ የተጠቁ ከብቶችን ሲከትብ ወይም ቅምብቢት ላይ በኳሻርኳርና ቤሪቤሪ በሽታ የተያዙ ሰዎችን ሲመግብ ልታይ ትችላለህ፡፡ አስገራሚው ዶክተር ሲያለቅሱ ቢያይ ያለቅሳል – ዕንባው “ቅርብ” ነው፡፡ ለነገሩ ዓዞም እኮ ለሚበላቸው ፍጡራን “ያለቅሳል”፡፡ አቢቹ ሴቱን ቀርቶ ስንቱን ፍናፍንት አለሌ መሰላችሁ በፍቅሩ ያነሆለለው – በጎን ግን ኦሮሞን….፡፡ እናቱ “ወንድ ወለድኩ” ትበል! እሙት! አልዋሽህም – እውነቴን ነው፡፡
የኢትዮጵያን ተጨባጭ ሁኔታና የእርሱን ዲስኩር ብታነጻጽር ባሳለፍናቸው 11 ወራት ውስጥ ብቻ ከወያኔ 27 ዓመታት ዕጥፍ ድርብ በሚያስከነዳ ሁኔታ ስንትና ስንት የዘረኝነት አጸያፊ ተግባር እንደተከናወነ ትገነዘባለህ፡፡ ይህን አሰለጥ ሰውዬ አሁንም አምነህ የምትንከራፈፍ ዜጋ ካለህ መብትህ ነው – “ዐውቆ የተኛን ምንትስ ሲሆን ቀስቅሰው” ይባላልና ከፍቅርህ ብዛት ከፈለግህ እንደነግንቦት ሰባት ትከሻህ ላይ አድርገህ ልትዞር ትችላለህ፡፡ ወንድሜ – ሰው በወደደው መቁረቡ ዛሬ አልተጀመረም፡፡ አዝለኸው ዙር፡፡
ግንቦት ሰባት ስለዚህ ሰውዬና አስነዋሪ ድርጊቱ ትንፍሽ አይሉም፡፡ ምክንያቱም አማራን ለማጥፋት ከዚህ ሰውዬ የተሻለ አማራጭ አያገኙም – ዋና ዓላማቸው ፀረ አማራ መሆኑን እዚህ ላይ መጥቀስ ለቀባሪ እንደማርዳት ነው፡፡ እነዚህ ምስጦች በአንድ ነገር ውስጥ ከሚገኙ ሁለት ነገሮች አንዱን ይጠላሉ ሌላውን ይወዳሉ፤ ትልቅ ተቃርኖ፡፡ ኢትዮጵያና አማራ በመሠረቱ አይነጣጠሉም፡፡ ተለያዩ ብትላቸውም አይለያዩም፡፡ ግንቦቶች ግን አማራን ነጥለው ማስመታትና እነሱ በቀረጹዋት መልክ የሚቃዡባትን አዲስ ኢትዮጵያ ከመሰል ዘረኛ ቢጤዎቻቸው ጋር መጋለብ ነው ዕቅዳቸው፡፡ ይህ ደግሞ ሳይታወቅባቸው የቀረ አይመስለኝም፡፡ ሞኛሞኙ አማራ ግን አማራጭ ከማጣትም ሊሆን ይችላል ከነሱ ጋር ሲጃጃል ይስተዋላል – ከሞኝ ደጃፍ ሞፈር መቁረጥ የዱሮ አራዳዎች ዋንኛ ዘዴ እንደመሆኑ አማራን በመናጆነት ለመጠቀም ግንቦት 7 እየታተረ ነው – በሌሎች አካባቢዎችማ ማን ውር ያስብለውና፡፡
አማራን ያገለለች ኢትዮጵያ እንዴት እንደሚመሠርቱ ልናይ ነው፡፡ በዘረኝነት በተበከለ የሰውዬኣቸው አስገራሚ ጥላ ውስጥ ተጠልለው እስከምን እንደሚጓዙም ልናይ ነው፡፡ ፍላጎታቸው አማራን ከያለበት መንቀልና እልፍ ሲልም በአማራው መስዋዕትነት በአቋራጭ ሥልጣን መያዝ እንደሆነ እየተረዳን ነው፡፡ ወደዚህ ድምዳሜ የሚያደርሱ ብዙ ምልክቶች አሉ፡፡ የነዚህ ጉዶች ሚዲያዎች ለምሣሌ የተረኞቹን ወንጀልና ግፈኛ ተግባር አይዘግቡም፡፡ በስማም እንደተባለበት ሰይጣን ልጉም ናቸው፡፡ ዝምታ ደግሞ ከድጋፍ አንድ ነው፡፡ ነገን ደግሞ ማየት ነው፡፡ ሁሉም ነገር እንዳለ አለመቅረቱ ግን ትልቅ መጽናኛ(ችን) ነው፡፡….
ጥላሁን ገሠሠ ምን ብሎ ዘፈነ?
ወዶ የጠላ ሰው፣
የቆረጠ አንጀቱ፣
እርቆ ይሄዳል፣
አያሳይም ፊቱን፡፡….
ቆንጆ ዘፈን! ልክ እንደኔው እናንተም ተዝናኑባት፡፡
መጽሐፍ ቅዱስ ምን አለ?
እግዚአብሔርም ሰውን በመልኩ ፈጠረ፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፡፡ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው፡፡ ዘፍጥረት 1፡ 27
ቀጣዩ ጥቅስ ምን ይላል – አንብብልኛ!
“I have grown to understand that no matter where we come from, human beings, at heart, are the same. Defining ourselves based on race, religion, and ethnicity is like betraying that.” Shenaz Treasury
ለማ መገርሳና ምሥጢረኛው ዶክተር አሰለጥ አቢይ ምን አሉ?
“ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው!!!!!!!!”
ፀሐዬ ዮሐንስ ምን ብሎ ዘፈነ?
ሳቂልኝ ሳቂልኝ ሳቂልኝ — ሳቂልኝ … ሳቂልኝ… (እኛም ለዚህ ሣቅ እንተባበራ! …. ቂቂቂቂቂቂቂቂ……)
ፀሐዬና ጓደኞቹ በኅብረት ምን ብለው ዘፈኑ?
ተባለ ተባለ እንዴ… ተባለ ተባለ እንዴ….
እውነትም ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው፡፡ ወያኔ በሁሉም ርብርብና የደም መስዋዕትነት መቀሌ እስክትመሽግ ድረስ ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነበር፡፡ ሕወሓት መቀሌ ላይ እስክትከትም ድረስ “ስንኖር ኢትዮጵዊ ስንሞትም ኢትዮጵያዊ” ነበርን … አዎ፣ የቅፈላ ፖለቲካ ጊዜው ነውና ለአንዴና ምናልባትም ለመጨረሻ ጊዜ ይንደላቀቅበት፡፡ ዘና ብለው ይቀፍሉን — አጫፋሪም ሞልቷል፡፡