ነጋሽ አቦነህ
የታደሉትና ጥንቁቅ ስደተኞች ፣ ለመሰደድ ወስነው አንድ እርምጃ ከመውሰዳቸው በፊት ፣ ጊዜውንና የአየር ጠባዩን አጣርተው ፣ መድረሻቸውንና መንገዳቸውን ከወጪአቸው ጋር ተምነው ፣ የሚይዙትን ጔዝ አስልተው ፣ ለጊዜው የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ አንግበው ፣ የደህንነትና የግንኙነት መስመራቸውን አስተካክለው ፣ ለሚገጥማቸው ማንኛውም ችግር ተዘጋጅተው ፣ ከቤታቸው ይወጣሉ።
ያልታደሉት ደግሞ ፣ ድንገት ባዶ እጃቸውን ከቤታቸው እንደወጡ በዚያው ይቀራሉ። እነዚህኞቹ ከሌላው በበለጠ ፣ ለተለያየ አደጋም በይበልጥ ሊጋለጡ እንደሚችሉ ዕሙን ነው። በእርግጥ ልዩ ልዩ የስደትና የስደተኛ ዓይነቶች መኖራቸው ይታወቃል። ሁሉንም የሚያመሳስሏቸው አማካኝ ጉዳዮች ግን ብዙ ይኖራሉ።
ከብዙ ዓሥርተ ዓመታት በፊት ፣ ከድሬዳዋ አየር ማረፊያ በድንገት ለስደት የተዳረግንበትን ወቅት አንረሳውም። አንዳንዶቻችን ከለበስነው ልብስ ሌላ ምንም ነገር በእጃችን ሳንይዝ ካረፍንበት ሆቴል እንደወጣን ፣ ሳናስበው በዚያው ቀረን። በእኔ በኩል ፣ በወቅቱ ለቆላው አየር ጠባይ ስል ፣ ስስ ጉርድ ሸሚዝ ፣ ሳሳ ያለ ሱሪና ፣ የስፓርት ጫማ ለብሼ እንደ ነበርና ፣ ባዶ እጄን እንደነበርኩም አስታውሳለሁ።
ቀደም ብሎ ፣ ወደ ድሬዳዋ ከመነሳታችን በፊት ፣ በአንደኛው አየር ምድብ በነበርንበት ጊዜና ፣ እዚያም እንደደረስን ፣ የተነጋገርነውንና ፣ አምነን የተስማማንበትን ሃሳብ ይዘን ፣ እየተጠባበቅን እያለን ፣ አንድ ባለሥልጣንን (ሥሙን እዚህ ላይ አልጠቅሰውም)፣ ከደብረዘይት መልዕክት ይዞ ፣ በሄሊኮፕተር ወደ እናንተ እየመጣ ነው ፣ የሚል መልእክት ደረሰን።
ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ደግሞ ፣ ያ ሄሊኮፕተር ተጠልፎ ወደ ጂቡቲ እያመራ ነው ተባልን። ይህ ዜና እንደ ተሰማ ወዲያውኑ አንድ አንቶኖቭና አንድ Mig 23 ተነስተው ፣ አንዱ ወደ ጂቡቲ ፣ ሌላው ወደ ናይሮቢ ኬንያ ፣ መጭ አሉ። የተወሰኑ ያልታደሉት ደግሞ ፣ ግርር ብለው አንድ ሄሊኮፕተር ውስጥ ተጠቀጠቁና ካፒቴኑ ብቻ ሲተርፍ ፣ የቀሩት በሙሉ በእሳት ጋይተው አለቁ።
በዚያ ግርግር ጊዜ ፣ የሄሊኮፕተሩ መጋየት ፣ ምክንያቱ በውል ባይታወቅም ፣ ለመነሳት ሲሞክር ክብደት በዝቶበት ወይም በግቢው የጥበቃ ኃይል በጥይት ተደብድቦ እንደሆነ ይገመታል። እነማን በዚያ ሄሊኮፕተር ውስጥ እንደነበሩ ፣ በግምት ካልሆነ በስተቀር ፣ እስከዛሬ በውል የሚያውቅ ያለ አይመስለንም።
እንዲያውም ከሄሊኮፕተሩ ካፒቴን ጋር ፣ በስደት አብረን በቆየንበት ወቅት ስለዚያ አደጋ ጉዳይ ፣ አንድም ነገር እንዲነሳበት ወይም እንዲወራ አይፈልግም ነበር። ምስጢሩን እንደያዘ ፣ ያለመታደል ሆኖ ፣ እዚያው በስደት ምድር ሕይወቱ አለፈ።
ታዲያ ጥቂት ሳይቆይ ፣ በወቅቱ የነበረው የምሥራቅ ዕዝ ምድር ጦር ሠራዊት ኃይል ፣ የድሬዳዋን አየር ማረፊያ ተቆጣጥሮ ፣ ምንም ዓይነት የአውሮፕላን እንቅስቃሴ እንዳይኖር አገደ።
ግራ በተጋባ ሁኔታ ውስጥ እያለን ፣ ስማቸውን እዚህ ላይ መጥቀስ የማልፈልገው ፣ እጅግ አስተዋይና ብልህ የሆኑት ፣ በወቅቱ የአየር ምድቡ የዘመቻ አለቆች ፣ ከምሥራቅ ዕዝ አዛዥ ጋር በመመካከር ፣ አየር ማረፊያውን እንደገና ለበረራ እንዲከፈት አደረጉ።
ይህ ችግር ሲፈታ ፣ ሌላው ከባድና ፈታኝ የሆነብን ፣ አንድ የጊዜው የአየር መቃወሚያ አዛዥ የነበረ ሻምበል ፣ እንኳን አውሮፕላን ፣ ወፍ እንኳን በአየር ማረፊያው ላይ ዝር እንዲል አልፈቅድም ፣ ደፍሮ ለመንቀሳቀስ የሚሞክረውን ደግሞ በሚሳይል አቦነዋለሁ ብሎ ፣ ግግም አለ።
እነዚያው ፣ አስተዋይ የሆኑት የአየር ምድቡ ዘመቻ አዛዦች ፣ እሱንም አግባብተው ፣ እንዲያዉም አብረህ ከእኛ ጋር ትሄዳለህ ፣ የሚል ቃል ተገብቶለት ፣ ተስማማና ፈቃድ ሰጠ።
ዕድለኛው ሻምበል ፣ ወዲያው ሽክ ብሎ ፣ ፂሙን ተላጭቶ ሱፍና ከረባቱን ግጥም አድርጎ ፣ ሳምሶናይቱን አንግቦ ከች አለ። ሌሎችም እንዲሁ የታደሉት ፣ ዘንጠውና ተዘጋጅተው የመጡ ነበሩ። ሁላችንም በባለ አራት ሞተር የካርጎ አውሮፕላን አንቶኖቭ 12 ተሳፍረን ወደ ናይሮቢ አመራን።
ታዲያ ብሽሽቁ ስለበዛበትና ፣ ለሕይወቱም ስለፈራ ፣ ሻምበሉ ፣ ብዙ ሳይቆይ ፣ ወዲያው ከናይሮቢ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ። የተወሰኑትም ችግሩን መቋቋም ተስኗቸው ፣ እንዲሁ እየተንጠባጠቡ ሲመለሱ ፣ የቀረነው ደግሞ ስደቱን በስፋትና በጥልቀት ተጋፈጥነው።
ጥቂቶች እንዳደረጉት ፣ ቀደም ብለን ፣ የምንበርረውን አውሮፕላን ይዘን ፣ ያለምንም ችግር ወደምንፈልግበት አገር የመኮብለል ዕድል ነበረን። ወይም እንደ ሌሎች ፣ ዕድል አጋጥሞን ፣ በተለያየ ምክንያት በሄድንባቸው አገሮች ፣ እዛው እጅ ሰጥተን መቅረትም እንችል ነበር። ነገር ግን ፣ በተለያዩ ምክንያቶች ፣ እነዚያን እንደ አማራጭ አድርገን ሳንወስድ ቀረንና ፣ መጨረሻ ላይ ተገፍትረን ወጣን።
በስደት እየቆየን ሲሄድና ፣ ርካሽ የሆነው የዘር ፓለቲካ አተላ ፣ በአገሩ ላይ ሞልቶ ሲፈስስ በሰማን ጊዜ ፣ ከዚያም አልፎ ድምበር ተሻግሮ ፣ በስደት ምድር ፣ ቡቱቶውን ደርቦ ዘረኝነትን በአካል ስናየው ፣ ወደን ሕይወታችንን ልንሰዋላት የነበረችውን አገር ፣ ሥሟን እንኳን ማንሳት ፣ ለስላቅ እንደሚዳርግ አስተዋልን።
ከዚያ የተነሳ ፣ ያልተነካካ ማንም ያለ እስኪመስለን ድረስ ፣ ሁሉንም ወደ መጠራጠር ፣ ውሉ እንደጠፋና መላ እንደ ሌለው ስለገመትን ፣ ነገር ሁሉ ኪሳራ መስሎ ታየን። አልፎም ስለ አገር ጉዳይ ፣ መስማት እንኳን እስኪታክተን ደርሰን ነበር።
ፈጣሪ ቸር ስለሆነ ፣ ዛሬ የተስፋ ጭላንጭል እያሳየን ነው። ሞልቶ የፈሰሰው የዘረኝነት አዛባ ተጠራርጎ እስኪፀዳ ግን ብዙ ጊዜ ይፈጅ ይሆናል። ከእንግዲህ ወዲያም ፣ እስካሁን የነበረውን ያህል የስደት ፍልሰት የሚኖር አይመስለንም።
ፈጣሪ ይርዳን።