>

እግዚአብሔር ይመስገን  የጌዲኦ ህዝብ ሰቆቃ እየተሰማ ነው!!! (ዘመድኩን በቀለ)

እግዚአብሔር ይመስገን 
የጌዲኦ ህዝብ ሰቆቃ እየተሰማ ነው!!! 
  ዘመድኩን በቀለ
★ ይሄ የክተት ዓዋጅ ቤተ ክርስቲያንና መስጊድ ከመገንባትም በላይ ነውና ፈጣን ምላሽ እንስጥ። እኔ መቼም በጓደኞቼ አላፍርም። በጭራሽ። አበደን። 
 
 ★ የሰብዓዊ መብት ተሟጓቹ ታማኝ በየነ ደግሞ ጎፈንድሚ አካውንት ከፍቶ ለጌዲኦ ህዝብ በተለመደው መልኩ እያለቀሰ ከፊታችሁ ቆሟል። ታማኝን እንስማው። ወገኖቻችንንም እንርዳ። 
 
                 
•••
ወዳጄ ሰውየው የከባድ ሚዛን ተፋላሚ ነው። የጠነቀቀም መድረክ መሪ ነው። የሙዚቃ መሳሪያ ተጫዋችም ነው፣ በብሔረሰብ ሙዚቃዎች ይወዛወዛል አይገልጸውም፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ነው። አልቃሻ ሆደ ቡቡም ነው። የቴሌቭዥን ሾው አዘጋጅም ነው። አማኝ ነው ታማኝ ጥርት ያለም ኢትዮጵያዊ ነው። ዘር ቀለም፣ ጎጥ የማያወቅው፣ ጥርት ያለ ኢትዮጵያዊ። ኢንዴዢያ ነው። ሰውየው።
•••
እንደኔ እንደኔ ከሆነ ታማኝ በየነ ማለት በባለቤትነት ደረጃ ያየነው እንደሆን ታማኝ የራሱ የታማኝ እንኳ አይደለም። እኔ ብሎ በራሱ ላይ ማዘዝ እንኳ የሚችል ዓይነት ግለሰብ አይደለም። ታማኝ የክብርት ባለቤቱም ሀብት አይደለም። ታማኝ የጓደኞቹም ንብረት አይደለም። ታማኝ የጎንደሬዎችም አይደለም። ታማኝ የዐማሮችም አይደለም። ታማኝ ልክ እንደ ኮካኮላ ነው። ልክ እንደፔፕሲ ኮላም ነው። ታማኝ ልክ እንደ አዲዳስ ነው። ልክ እንደ ሶኒ ምርት። ታማኝ ሜድ ኢን ኢትዮጵያ ነው። ታማኝ ልክ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ያለ ከፍ ያለ ብራንድ ያለው ሁሉም የኔ የሚለው ልዩ ሰው ነው። ታማኝ ጤፍ ነው። የጤፍ እንጀራ። በሁሉም ማዕድ ላይ ያለስስት የሚቀርብ። እስላም ክርስቲያን የማይጠየፈው። ተቃዋሚ ደጋፊው ሁሉ የሚንሰፈሰፍለት ልዩ ሰው ነው።
•••
ታማኝ ከኦሮሞ ልጆች ጋር በአሜሪካ ጎዳናዎች ለኦሮሞ መብት ብቻውን ጮኋል። በኋይት ሀውስ ፊትለፊት ለአማሪካ መንግሥት አቤት ሲል ከርሟል። ታማኝ ፀቡ ከህውሓት ጋር ቢሆንም በባድመ ጦርነት ወቅት ገንዘብ ለምኖ ለኢትዮጵያ መንግሥት ልኳል። ያውም የሚጠየፈው መለስ ዜናዊ በህይወት እያለ ማላት ነው። ከሞያሌ ለተፈናቀሉ፣ በጎንደርና በባሕርዳር በተለያዩ መጠለያዎች ተፈናቅለው ለሚገኙ ሁሉ ታማኝ በየነ እያለቀሰ ለምኗል። ታማኝ የኢህአዴግም የተቃዋሚውም ንብረት አይደለም። ታማኝ በየነ የኢትዮጵያውያን ሁሉና የኢትዮጵያውያን የጋራ ንብረት ብቻ ነው። አከተመ።
•••
ሲጠቃለል ታመኝ በየነ ብቻውን ራሱን የቻለ መንግሥት ነው። ህዝብ እሱ ያለውን የሚሰማው መንግሥት ነው። ለዚህ ነው በትናንትናው ዕለት አክቲቪስት ታማኝ በየነ በግሎባል አሊያንስ በኩል በጌዲኦ ችግር ላይ ለሚገኙ ወገኖች የእርዳታ ገንዘብ ለማሰባሰብ በአደባባይ የወጣው። እንባ እየተናነቀው ነበር ልመናውን የቃረበው። እናም ህዝቡ ታማኝን ሰማው። አደመጠው። በጥቂት ደቂቃዎችም ከ600 ሺ ዶላር በላይ ዘር፣ ቀለም፣ የፖለቲካ አመለካከት ሳይለየው ወገን ለወገኑ ለመድረስ ተረባረበ። እስከ አሁን ባለው መረጃ መሠረት እየተሰበሰበ ያላው ገንዘብ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ብቻ ከ 600 ሺህ ዶላር በላይ ዘሏል።
ይሄ ነው ኢትዮጵያዊነት፣ ይሄ ነው ወገን ለወገን መድረስ። ይሄ ነው ይሄ ሃገር እና ሕዝብን የሚያኮራ ተግባር። ይሄ ነው ደግነት። ይሄ ነው ምጽዋት። እናም ወገኖቼ ውድ የፔጄ ተከታታዮች መረጃው የሚደርሳችሁ ሁሉ ከስር ባለው ሊንክ ገብታችሁ የአቅማችሁን አድርጉ!
•••
ተመስገን ጌታ ሆይ!  የጌዲኦዎችን የሰቆቃ ዜና ሠርቼ ለዓለም ህዝብ እንዲመለከተው ካደርኩ በኋላ ዜናውን ያየ የተመለከተ ሁሉ እንዴት ነው መርዳት የምንችለው ብሎ ሲያስጨንቀኝ ምንም አላውቅም ብዬ እመልስ ነበረ። አሁን ግን በውጭ ለምንገኘው ታማኝ በየነን። ኢትዮጵያ ለምንገኘው ያሬድ ሹመቴንና መሐመድ ካሳን አስነስቶልናል።
አዲስ አበባዎችም ከመጋቢት 16 – 21 ድረስ ከገንዘብ ውጪ በዓይነትና በቁሳቁስ በፌስታል፣ በከረጢት፣ በማዳበሪያ፣ በኩንታል፣ በካርቶን፣ በበርሜል፣ በአይሱዙና በኤሮትራከር ከያላችሁበት እየጫናችሁ ወደ እርዳታ መሰብሰቢያው ስፍራ ትተምማላችሁ። አደራ፣ አደራ፣ አደራ እንዳትረሱ። ከአሁኑ በሰፈር፣ በወረዳና በከተማችሁ ጀምሩ። ኢትዮጵያ፣ ቡና፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ሀዋሳ ከነማ፣ ፈሲል፣ መቐለ ከተማ፣ ባህርዳሮችና ሌሎቻችሁም የእግር ኳስ ደጋፊዎችም በዘመቻው ላይ ብትሳተፉ መልካም ነው።
•••
በአዲስ አበባ የምትኖሩ ግን እስከዚያው ከምሳና ቁርሳችሁ እየቀነሳችሁ ተዘጋጁ። አሁን ከእናንተ ገንዘብ አይፈለግም። በገንዘብ የሚታማም፣ የሚነካካም አይኖርም። የባንክ አካውንትም አይከፈትም። የሚፈለገው ዕቃ ብቻ ነው። ምግቦች፣ የንጽሕና መጠበቂያ ቁሳቁሶች፣ አልባሳት ከእናንተ ይጠበቃል።
#የማይበላሹ_ምግቦች
•ስንዴ
•ምስር
•ፓስታ
•መኮረኒ
•ሩዝ
•ፉርኖ ዱቄት
•ዘይት
•ሴሪፋም /ፋፋ/
•ብስኩት /ጋቤጣ/
#የንጽህና_ቁሳቁሶች
•ሳሙና
•ኦሞ
•ሳኒታይዘር
•የሴቶች ንጽህና መጠበቂያ /ሞዴስ/
#አልባሳት
•ብርድ ልብስ
•ነጠላ ጫማ (ብቻ)
•የተለያዩ አልባሳት (ያገለገሉም ቢሆን) አዘጋጁ ተብላችኋል።
አስተባባሪዎቹ የጊዞ ዓደዋ መስራቾቹ ቅድሚያ ለሰብዓዊት ቡድን ጊዜያዊ አስተባባሪዎችና የቡድኑ ተወካዮች የሆኑት ያሬድ ሹመቴና መሐመድ ካሳ።
#ማስታወሻ | ~ የእርዳታ መሰብሰቢያውን ቦታ ከመጋቢት 16 ሁለት ቀን በፊት መጋቢት 14 በይፋ እናሳውቃለን።
እስከዚያው ድረስ ግን ሁላችንም በዕድር፣ በመሥሪያ ቤት፣ በቤተሰብ፣ በመኅበር፣ በየሠፈራችሁ እያሰባሰባችሁ። በማዳበሪያ፣ በማዳበሪያ እየከተታችሁ ጠብቁ። በውጭ የምትኖሩም ኢትዮጵያውያን በቤተሰብ በኩል ገንዘብ እያስላካችሁ የፈለጋችሁትን ዕቃ እየገዛችሁ አዘጋጅታችሁ ጠብቁ። ከእኛ በላይ ለእኛ የሚደርስልን የለም።
ሻሎም  !  ሰላም  !
መጋቢት 7/2011 ዓም
ከራየን ወንዝ ዳር።
Filed in: Amharic