>
4:13 pm - Tuesday July 5, 2022

"አርበኝነት ያለ አርበኞቹ ከንቱ ነው!!!! (ጋዜጠኛ አበበ ገላው)  

“አርበኝነት ያለ አርበኞቹ ከንቱ ነው!!!!
ጋዜጠኛ አበበ ገላው
የአርበኞች ግንቦት 7 ከፍተኛ አመራር አባል የነበረው ነአምን ዘለቀ ለድርጅቱ የጻፈውን የመልቀቂያ ደብዳቤ በጥሞና አነበብኩት። ነአምን ኢትዮጵያን ከህወሃቶች መንጋጋ ለማላቀቅ በተደረገው ትግል ጉልህ ሚና የተጫወተ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ መሆኑን በቅርብ የምናውቀው ሁሉ መመስከር እንችላለን።
በተለይ ብዙዎች ፖለቲካን የግልና የቡድን ጥቅም ማራመጃ፣ ሴራ መጎንጎኛ በሚያደርጉበት በዚህ ጠልፎ የመጣጣል ዘመን የራሱና የቤተሰቡን ጉዳይ ወደ ጎን ትቶ ህዝብን ለማገልገል ከልቡ የሚተጋ እንደ ነአምን አይነት ሰው በጣት የሚቆጠር ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።
ነአምን ለህሊና ያደረ ሰው ነው። ለነአምን ስንብት ዋና ምክንያት የሆነው ህይወታቸውን ለትግሉ ገብረው ግንባራቸውን ለጥይት ሰጥተው በረሃ ወርደው መከራን የተቀበሉ ታጋዮችን መልሶ ለማቋቋም በድርጅቱም ይሁን በመንግስት በቂ ትኩረት አለማግኝታቸው እንቅልፍ ስለነሳው መሆኑን በጻፈው ደብዳቤው ግልጽ አድርጓል።
የቀድሞ የድርጅቱ ደጋፊ እንደነበረና አሁን ደግሞ እንደ ታዛቢ አስተያየት ለመስጠት ያህል ጉዳዩ በድርጅቱ ውስጥ ያለውን የአመራር ክፍተት የሚያሳይ አንድ እውነታ ነው። በወረታ ካምፕ እንዲገቡ የተደረጉና ከካምፕ ውጭ ሆነው ጉዳያቸውን የሚከታተሉ የድርጅቱ የቀድሞ ታጣቂዎች በድርጅቱና በአመራሩ ላይ ከፍተኛ ቅሬታ ማሰማት ከጀመሩ ሰነባብተዋል። እነዚህ ታጋዮች ድርጅታችን ተጠቅሞ ጣለን የሚል ቅሬታ ሲያሰሙ አላየንም አልሰማንም ማለት ለማንም የማያዋጣ የህሊና ሸክም መሆኑ ብዙም አያጠያይቅም።
በተለይ ድርጅቱ እራሱን አፍርሶ ከሌሎች ጋር በጣምራ ለስልጣን የሚወዳደር የፖለቲካ ፓርቲ ከመሆኑ በፊት በግልጽ እራሱን ገምግሞ የተሻለ አሰላለፍ ማድረግ ይጠበቅበታል። በተለይም የዜጋ ፖለቲካ እየሰበኩ የሴራ ፖለቲካ የሚያራምዱ አንዳንድ የድርጅቱ ከፍተኛ አመራር አባላት ጥፋት እያደረሱና ድርጅቱ እምነት እያጣ እንዲሄድ እያደረጉት መሆኑን የምናውቅ እናውቃለን። በስብከትና ተግባር መሃል ክፍተት መኖሩ ጊዜ ጠብቆ ትልቅ ችግር መፍጠሩ አይቀሬ ነው።
ለማንኛውም የነአምን ስንብት ዋና ምክንያቶችን ድርጅቱ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ አፋጣኝ መፍትሄ መስጠት ይጠበቅበታል።
“እኔ እስከማውቀው  “የሴራ ፖለቲካ “ በንቅናቄያችን ውስጥ የለም!!!
አቶ ነአምን ዘለቀ
 ወዳጄ አበበ ገላው፦ እኔን በሚመለከት ምስክርነት በይፋ  ስለጻፍክ   በምስጋና ልጀምር፡፡ ሆኖም የእኔ ከአርበኞች ግንቦት 7 አመራር ሃላፊነት  በገዛ ፈቃዴ መልቀቅ   ምክንያት በማድረግ ስለአርበኞች ግንቦት 7 ከፍተኛ እመራሮች የጻፍከው ለረጅም አመታት እብሬያቸው በዚህ ብዙ ውጣ ውረድ ባሳለፍናቸው የትግል እመታት  የማውቃቸውን ከፍተኛ አመራሮች ስብእና አይገልጽም።  ወፍራም መተማመን፣ መከባበር፣ ግልጽነት፣ በሃሳብ  ተሟግቶ፣በጋለ ስሜት ጭምር  በሀገራዊና በድርጅታዊ ጉዳዮች ላይ ተጨቃጭቆና፣ ተፋጭቶ ወደ ጋራ ዴሞክራሲያዊ ውሳኔ መሄድን፣ ስሜቶች ቢጎዱም፣ የዚህ ወይንም የዚያ ሃሳብ አሸናፊ ቢሆንም ፣ ሁላችንም ለቆምንለት ሀገራዊና ህዝባዊ  አላማና ግብ በማስቀደም፣ ውጦ፣  ተዋውጦ አብሮ  መራመድን ያጎለበተ  ከፍተኛ እመራር ነው። መላእክት አይደለምና ስህተቶች ሊሰሩ ይችላሉ። እኔ እስከማውቀው ግን  “የሴራ ፓለቲካ “ በንቅናቀው ውስጥ በበኩሌ አላውቅም። አንተም የንቅናቄውን ከፍተኛ እመራሮች  እንደኔ በቅርበት ስለማታውቃቸው እንዲህ አይነት ድምዳሜ በአደባባይ መስጠት ፋይዳ ያለው ነው ብዮ አላምንም።
ሌሎች ጉዳዮች እንደሚከነክኑህ የማውቀው ስለሆነ እነዚህ ችግሮች ለመፍታት ባስቀመጥነው ያጋራ መዋቅርና አቅጣጫ መሰረት ትህትናን ተላብሰን፣ ማናችንም ከተቋም በላይ አለመሆንችንን ተረድተን፣ ሁሉም ባለድርሻዎች  በጋራ ተነጋግረን፣ በጋር መፍትሄዎች ማምጣት ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበት መንገድ ነው ብዮ በድጋሚና በአደባባይ ለመምከርና ለማሳሰብ እወዳለሁ።  እኔም፣ አንተም፣ ሌሎችም ባለድርሻዎች ብዙ ጊዜ የተነጋገርናቸውን ችግሮች  ከአርበኞች ግንቦት 7 ከፍተኛ አመራሮችም ሆነ ከእኔ የስራ መልቀቅ ጋር በማያያዝ ባናሳክረው የተሻለ ነው ብዮ እመክራለሁ።
ከአክብሮት ሰላምታ ጋር
ነአምን ዘለቀ
Filed in: Amharic