>
8:06 am - Wednesday July 6, 2022

አታብዳት!!! (ደረጀ ደስታ)

አታብዳት!!!
ደረጀ   ደስታ
እንደሱማ አይሆንም። ዝምብሎ በብላሽ እንዲሁ በሜዳ ይታበዳል እንዴ! እንዲሁ እንዳማረህ እብድና ዘመናይ የልቡን ይናገራል ይላሉ እንዳልክ ከሁለቱ አንዱን እንደጎመዥህ ትቀራታለህ። እንጂማ የልብህን አታወራትም። ደልቶ ገብቶህም አልዘመንክ፤ ቀርተህም አልተረፍክ- እንዲሁ ቀርተሃል። የሆነውን መልሰህ ትደግማታለህ። የተፋሃትን ትውጣታለህ። አንድነትህን በልዩነትህ ትሰብራታለህ። ልዩነት ጌጥ ነው ብልሃል፤ በተመኘኸው ስታጌጥ ትመላለጣታለህ። ተማክረህ ያንቶሰተስከው ምንትስህ አይሸህትም። እንደ ግም ለግም ወዲህ ለወዲያ ሆነህ ህዝብ ለህዝብ ታዘግማታለህ እንጂ ተነጥለህ አታብዳትም። እዚያው በዚያው ትርመሰመሳታለህ እንጂ አንተ ከማን በልጠህ ወጣ ብለህ ንጹሁን አየር ትምገዋለህ?
አገርህ በማዕበል እንደተናጠች ባህር ናት። ከማዕበል ውሃ መሃል የተጣለ ሰው ደግሞ እዚያው ይዳክራታል እንጂ ይዞ ጨብጦ፣ ቧጦ ግጦ፣ የሚወጣው ነገር የለውም። አንተም የለህም! ከውቅያኖሱ መሃል ነህ። አትቆም አትቀመጥ መተኛትም መዋኘትም አይሆንልህ። ቢሆንስ ስንት ዘመን ትዋኛለህ?
ያየኸው ይውጥኻል የፈራኸው ይበላሃል። ወደየትስ እንደሆነ ደግሞ ዋኝተህ እንደምትወጣ አታውቅም። እንኳን እውቀትህ ግምትህ እንኳ የሚነግርህ አቅጣጫ አይታወቅም። ዝምብለህ ቀረሁ በል! ቢሆንልህና ብታውቅበትማ በዘየድክ! ችለህበት ባበድክ! ሁልሽም አመድ በዱቄት ነሽ! ህዝብ ሆንሽ አልሆንሽ፣ የዚህኛው ወይ የዚያኛው እንዲህ የሚያደርግሽ ምን አባሽ ሆነሽ ነው ጫጫቴ ሁላ! ከፈለግሽ ደግሞ ሁልሽም ገደል ግቢ…ማለትን በቻልክ ኖሮ አገር ስቆ ተሳስቆ በቆመ፣ ከገደልም ጫፍ ቆሞ ድኖ በተገረመ ነበር።
ወይ ጉድ ለካ ህዝብ አይደለም መንግሥትን እየጣለ ያለው፣ መንግሥት ነው ህዝብን እየገለበጠ ያለው… ማለትን ብታውቅበት ህገመንግሥታዊውን ህዝብ በኃይል ለመጣል የሚገሰግሰውን እያንዳንዱን የክልል መንግሥት እንደ ስልባቦት በቀላሉ ገፈህ በጣልከው ነበር። ችግሩ መጣል መንቀልህ አይደለም። ምትኩን መትከልህ ነው። ሁል ጊዜም ልማድህ ነው፣ መንቀል እንጂ መትከል አታውቅም።
 ተከልኩ ያልክ እንደሆነም ያው ወዲያው አበቀልኩ ወዲያው ቀጠፍኩ ነው። አቤት ፍጥነትህ! እቤት ውዳሴህ ፣ እሚያጠግበ እንጀራ ከምጣዱ ያስታውቃል ትላለህ፣ ወዲያው ደግሞ እንጀራህ ገና ከምጣዱ እያለ ይሻግትብሃል። ድጋፍህ እንደጤዛ ቁምነገርህ እንደዋዛ ነው። ግን ህዝብ ነሃ፣ አዋቂ ነሃ ብዙ ነሃ ! ኃያል ነሃ! ማን ይነገርሃል? ከህዝብሽ ህዝቤ ይበልጣል እያልክ ለፍጅት ስትፎካከር ህዝብ ሆነህ ህዝብ ስትንቅ፣ ስትጠራራ ለትንቅንቅ፣  ማን ደፍሮ ማንስ ይናገርሃል? ማንስ በልጦ ማንስ ያዝንብሃል? የዚህ ሁሉ መሠረቱ ጥቂቶች ናቸው እንዳልክ፣ መብዛት አቅቶህ እንዳነስክ፣  ጥቂቶች እንደነዱህ ጥቂቶች እንደጎዱህ፣ አንዴ ስታጨበጭብላቸው አንዴ ስታጨበጭብባችው…..ሲያምሩህ ሲያቅሩህ …
እና አንድ የገባህ ቀን ህዝብ መሆን መንጋጋት መነዳት የሰለቸህ ቀን ፣ እንደኔ ብድግ ብለህ፣ ወይኔ ግለሰብ! ዘራፍ ግለሰብ፣ መብት ለሰው፣ አንድ አገር ለአንድ ሰው ፣  ድል ለግለሰብ! ብትል ምን ይቀርብሃል? ግለሰብ ይጨበጣል ይዳሰሳል በስም ይጠራል ይቆጠራል ህዝብ ግን አጭበርባሪ እንኳ ባይሆን ተጭበርባሪ እንደሆነስ ማን ያውቃል?  መቸም ህዝብ ከሚያቅል ህዝብ ቢያልቅ ይሻላል ተብሎ እንዴት ይፎከራል? እደግመዋለሁ ይህን አማርኛ ይላል እብዱ- ህዝብ ከሚያልቅ ህዝብ ቢያልቅ ይሻላል ወይም በህዝቦች መቃብር ላይ የተመሰረተ የህዝቦች ድል!  ያዝ እንግዲህ!
Filed in: Amharic