>
4:58 pm - Wednesday July 6, 2022

በመግለጫ ጋጋታ በእስር እንዲሁም በግድያ የህዝብን ጥያቄ ማስቆም አይቻልም!!!  (ብርሀኑ ተክለ-ያሬድ)

በመግለጫ ጋጋታ በእስር እንዲሁም በግድያ የህዝብን ጥያቄ ማስቆም አይቻልም!!!
 ብርሀኑ ተክለ-ያሬድ
* በመግለጫ ለማስፈራራት ቀርቶ በአዲስ አበባ መንገዶች ለማለፍ እንኳን ሞራል የላችሁም!! በእናንተ ጫጫታ ሳንደናገጥ ወደ መፍትሄው እናመራለን መፍትሄው መደራጀት መደራጀት መደራጀት ብቻ ነው!!!
 
ማፈሪያ ሁሉ!!!!
“የአዲስ አበባ ምክር ቤት” ተብዬው በመግለጫው “ወኪላችሁ በመሪ ድርጅቴ ኢህአዴግ በኩል ልማትንና ብልፅግናን ያረጋገጥኩላችሁ እኔ ብቻ ነኝና እኔን አምናችሁ እጃችሁን አጣጥፋችሁ ተቀመጡ”እያለን ነው ይህ የድፍረቶች ሁሉ ድፍረት ነው ይህን የሚለን መቼ በድምፃችን ያቋቋምነው ምክር ቤት ነው?በአዲስ አበባ ህዝብ ጥቅም ጉዳይስ መቼ መግለጫ አውጥቶ ያውቃል?የእውነት ወጉ ደርሶን አዲስ አበቤዎች ምክር ቤት አለን እንዴ?
እውነቱን ስንነጋገር አዲስ አበቤዎች የወከልነውና ያቋቋምነው መንግስታዊ ምክር ቤት በከተማይቱ የለም ኖሮም አያውቅም ይህ ዛሬ ያለው ምክር ቤትም የ1997ቱ የክፉው መለስ የሕዝብ ድምፅ ዘረፋ ውጤት አምጦ የወለደው አሻንጉሊት፣ከአዲስ አበባ ሕዝብ ውክልና ይልቅ የ4ቱ የኢህአዴግ መሰረታዊ ድርጅቶች ኮታ የሚያስጨንቀው፣ከከተማዋ ልማት ይልቅ ዘረፋው  የጣፈጠው የመዋጮ ስብስብ እንጂ በየትኛውም ህዝባዊ ፍላጎት ተደግፎ የመጣ የየትኛውም ሕዝብ ውክልና የሌለው ቡድን ነው ይህ ህገወጥ ቡድን ነው እንግዲህ በድምፄ እቀጣዋለሁ ብሎ ላሰበው የአዲስ አበባ ህዝብ “የአርፈህ ተቀመጥ” ማስፈራሪያ የሚልከው ድንቄም ህጋዊ ምክር ቤት እቴ!!!
ለመሆኑ ይህ ምክር ቤት ነኝ ባይ እስካሁን የት ነበር?
– በአዲስ አበባ  ወገኖቻችን የቆሻሻ ክምር ተደርምሶባቸው በስማቸው የተሰበሰበ ገንዘብ ሲዘረፍና ብዙዎች ሜዳ ሲበተኑ የት ነበር?
የከተማዋን ዲሞግራፊ ለመቀየር በተጠና መልኩ እየሰራን ነው ሲሉ ክቡር ሚኒስቴሩ ያንንም በሰዎቻቸው አማካኝነት መሬት ላይ አውርደው ተፈፃሚ ሲያደርጉ የት ነበር?
– አዲስ አበባን ለማተራመስ ቀን ለሊት እየተጉ ያሉ ቡድኖች በግልፅ አቋማቸውን ሲገልፁ እንዲሁም በከተማዋ ነዋሪዎች ላይ በፌደራል ፖሊስ ታጅበው አልተሳካላቸውም እንጂ ጥቃት ለመሰንዘር ሲሞክሩ የት ነበር?
– መስከረም መጀመሪያ ላይ በአዲስ አበባ ህዝብ ላይ ገጀራ ሲመዘዝ ራሱን የሚከላከለውን ህዝብ ፖሊስ በጥይት ሲገለው በመጨረሻም አዲስ አበቤ እንደ ወንጀለኛ ጦላይ ተወስዶ ሲሰቃይና ሲሞት ይህ ምክር ቤት የት ነበር?
– ከራሱ ከምክር ቤቱ መሀል “የሚረባ ሰው የለም” ተብሎ የምክር ቤቱ አባል ያልሆነው ታከለ ኡማ በምክትል ከንቲባነት በላዩ ላይ ሲሾምበት ይህ ምክር ቤት የት ነበር?
– በቅርቡስ አዲስ አበባ ውስጥ ያለ ኦሮሚያ ፈቃድ ዛፍ እንኳን መትከል አይቻልም ሲባል የት ነበር?
– ህዝቡ ቆጥቦ የሰራውን መኖሪያ ቤት በጉልበተኞች ሲነጠቅ መታወቂያ በህገወጥ መንገድ በገፍ ሲታደል የት ነበር?
ዛሬ የከተማው ህዝብ ተደራጅቶ በፍፁም ሰላማዊ መንገድ ሃሳቡን ቢያቀርብ ድምፁን ሰምተነው የማናውቀው “አዲስ አበባ ም/ቤት” ዛሬም እንደ ትናንቱ የአዲስ አበባን ህዝብ ለማስመታት ዱላ እያቀበለ ነው
ኢህአዴግ መቼም ኢህአዴግነቱን አይለቅም የትናንቱን ስህተት ዛሬ በመድገም ላይ ነው ያልተረዱት ነገር ትናንት ወያኔን በአፅንኦት ስንቃወመው የነበረውን አካሄድ ዛሬም ኦዴፓ እየደገመው ነውና መቃወማችንን እንደማናቆም ነው
በመግለጫ ጋጋታ በእስር እንዲሁም በግድያ የህዝብን ጥያቄ ማስቆም አይቻልም እየተነሳ ያለው የህዝብ ጥያቄ ነው ይህን ደግሞ ማንም እንዲሁም ምንም ሊያስቆመው አይችልም።
ነገሩን ትንሽ እናፍታታው ካልን ደሞ:-
 በምክር ቤቱ ውስጥ ንጋቱ ዳኛቸው ከሚባል 1 አባል ውጪ(እርሱም ከወጣቶች ማህበር ጀምሮ በሕወሓት እቅፍ ያደገ ነው) አንድም አዲስ አበቤ በውስጡ የለበትም። ይልቁኑ በየክልላቸው አንፈልጋችሁም ውጡልን ተብለው በህዝብ አመፅ ቤታቸው እየተቃጠለና እንዳትደርሱብን እየተባሉ የተባረሩ ሙሰኞች ስብስብ ነው ምን ይደረጋል አዲስ አበቤዎች ያለምርጫችን እንደ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ አይነት የሳውላ ዘመዶቹ ቤቱን አቃጥለው አትምጣብን ብለው የሸኟቸው ሰዎች በስራ አስኪያጅነት ይሾሙብናል። እንደ ወ/ሮ አበበች ነጋሽ አይነት የጉለሌ ትምህርት ቢሮ ሀላፊ ሆነው የፅ/ቤቱን በጀት በድፍረት ወደ ምርጫ ቅስቀሳ በጀት ያዞሩ ግለሰብ በመወቀስ ፈንታ በእድገት በመጀመሪያ የከተማው ትምህርት ቢሮ ሀላፊ በኋላም የከተማው አፈጉባኤ ተደርገው ይሾማሉ ። ይህን እፍረተ ቢስ ምክር ቤት በደንብ ለመግለፅ ያህል የ2010 በጀት አመት የከተማ አስተዳደሩ ዋና ኦዲተር ለከተማው ምክር ቤት ያቀረበውንና ምክር ቤቱም አንድም ሰው ተጠያቂ ሳያደርግ በዝምታ ያለፈውን  የሚሊዮናት ጉድለቶች እንመልከት
1 ከደንብና መመሪያ ውጭ የተፈፀመ ግዢ ………..   112 ሚሊየን ብር በላይ
2 በወቅቱ ያልተሰበሰበ……329 ሚሊየን ብር በላይ
3 ጥሬ እቃ ተሰጥቶ ምላሽ ያልተደረገ……41 ሚሊየን ብር በላይ
4 ለማን እንደሚከፈል የማይታወቅ ተከፋይ ሂሳብ………123 ሚሊየን ብር በላይ
5 በወቅቱ ያልተከፈለ ተከፋይ ሂሳብ……..4 ሚሊየን ብር በላይ
6 ከመመሪያ ውጭ የተከፈለ አበል ………..298ሺ ብር በላይ
7 ከውል በላይ የተከፈለ ሂሳብ………….4ሚሊየን ብር በላይ
8 ማስረጃ ሳይቀርብ የተከፈለ………….96ሺ ብር በላይ
9 ያለአግባብ ለተለያየ ሕትመት የዋለ…………13 ሚሊየን ብር በላይ
10 የስራ ግብር ያልተከፈለበት ክፍያ…………..840 ሺ ብር
11 ለፋርማሲ አገልግሎት ተገዝተው ስራ ላይ ያልዋሉ የጋራ መኖሪያ ንግድ ቤቶች……….11 ሚሊየን ብር በላይ
12 በቁጠባ ቤቶች ኢንተርፕራይዝ በኩል በራሳቸው ስም ለ9 ዩኒቨርሲቲዎች 7ሺ ቶን ብረት 4 ሚሊየን ዶላር ወጪ ተደርጎ ቢገዛም ዩኒቨርስቲዎቹ ስለመረከባቸው ማረጋገጫ አልተገኘም
ልብ በሉ ይህን ጉድለት ዋና ኦዲተሩ ለምክር ቤቱ ቢያቀርብም አንድም የተጠየቀም የተገሰፀም ሰው የለም እናሳ ምክር ቤት አለን?ማፈሪያ ሁሉ!!እንኳን በመግለጫ ለማስፈራራት ቀርቶ በአዲስ አበባ መንገዶች ለማለፍ እንኳን ሞራል የላችሁም ሞተናላ!!! በእናንተ ጫጫታ ሳንደናገጥ ወደ መፍትሄው እናመራለን መፍትሄው መደራጀት መደራጀት መደራጀት ብቻ ነው ያኔ አዲስ አበቤ ከአይን አውጣ ዘራፊዎችና ከዘረኞች ነፃ ይወጣል ምክንያቱም ከእውነት ጋር ታግሎ ያሸነፈ የለማ!!!
Filed in: Amharic