>
11:23 am - Wednesday November 30, 2022

ዓቢይ ቅድምና አሁን (ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም)

ዓቢይ ቅድምና አሁን

 

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም

 

ያልተረጋጋው የለውጥ አስተዳደር በሚጫወተው ጅዋጅዌ እኛንም እያወዛወዘን ነው፤ እኔን ያለጥርጥር አወዛውዞኛል፤ ጅዋጅዌ አልወድም፤ ሃይማኖትን፣ እምነትን፣ መለዋወጥ የብስለት ምልክት አይደለም፤ ዛሬ አንድ መልክ፣ ነገ አንድ መልክ፣ ተነገ ወዲያ ደግሞ የማያስተመምን መሆን እንኳን ለአገርና ለሕዝብ ለቤተሰብም አይጠቅምም፤ ይህንን በመገንዘብ የኢትዮጵያን ሕዝብ የጊዜውን ሁኔታ በጥልቀት አሰብሁበት፤ ከጅዋጅዌው ጨዋታም ለመውጣትና ራሴን ችዬ ለመቆም ወሰንሁ፤ ይህ ጽሑፍ የዚህ ውሳኔ መግለጫ ነው፤ ምናልባት እንደኔ ጅዋጅዌው ጥርጣሬና ስጋት ውስጥ የከተታቸውን ሰዎች እንደኔ ይቀሰቅሳቸው ይሆናል የሚል ተስፋ አለኝ፡፡

እንዘጭ!-እምቦጭ! የኢትዮጵያ ጉዞ በሚለው መጽሐፌ የሚከተለውን ብዬ ነበር፤

 

የማድፈጥ ጉዳት

ማድፈጥ አንድ ክፉ ነገርን ያስከትላል፤ማድፈጥ የሚያተኩረው ቂም ላይ ነው፤ ማድፈጥ የሚያተኩረው በበቀል ላይ ነው፤ ማድፈጥ የሚያተኩረው ባለፈው ላይ ነው፤ ወደኋላ እያዩ ወደፊት መሄድ አይቻልም፤ስለዚህም አንድ የግፈኛ ሥርዓትን ጥሎ ለሌላ የግፈኛ ሥርዓት ሁኔታውን አመቻችቶ መተው የወደፊቱንም ያለፈው አምሳያ ማድረግ ይሆናል፤ የግፈኛውን ሥርዓት ቁንጮ ማውረድና ሥራቱን ማውረድ አንድ አይደለም፤ ዛሬም የፖሊቲካ ፓርቲዎች የተባሉትን ዘመናዊ ቅርጽ የያዙ ድርጅቶችን ብንመለከት ለግፈኛነት የሚፎካከሩ ናቸው፤ ቢያንስ ደርግን አይተናል፤ ኢሕአፓንና መኢሶንን አይተናል፤ ሻቢያን አይተናል፤ ወያኔን አይተናል፤ እስከዛሬ ድረስ በኢትዮጵያ ውስጥ ምንም ዓይነት የሥርዓት ለውጥ አልተደረገም፡፡ …

… ማድፈጥ መንቀልን እንጂ መትከልን አያውቅም፤ ቀኑ ደርሶ አምባው ከፈረሰ በኋላ በዋናው ግፈኛ መውደቅ ሁሉም አንጀቱ ይርሳል፤ ዋናው ዓላማ በቀል ስለሆነ የግፈኛው መውደቅ ለአብዛኛው ሕዝብ ዓላማውን አሳክቶለታል፤ ስለዚህም ሰላማዊው ሰው በደስታ ወደቤቱ ይመለሳል፤ ጉልበተኞች ከሎሌዎቻቸው ጋር ሆነው ይፋለሙና አዲስ ግፈኛ ይሰየማል፤ ግፉም ይቀጥላል፤ ማድፈጥም ይቀጥላል፡፡

 

መናገር የምንወደደውን ያህል ማንበብን እንጠላለን፤ ስንት ምሁራን አንብበውታል? ስንት ምሁራን በሀሳቡ ተወያይተውበታል? (በቅርቡ አንዳርጋቸው በጉዳዩ ያሰበበት የሚመስል ነገር ሰምቻለሁ፤) ተማርንም አልተማርንም፣ በየፈረንጅ አገሩ በአሽከርነት ኖርንም፣ መሬት እየቆፈርን በገጠር መንደር ውስጥ ኖርንም ሳናስብ መናገር፣ ፊደል ካወቅንም ሳናስብ መጻፍ ይቀናናል፤ ዱሮ የወንዜ ልጅ ስንባባል የነበርነው ዛሬ አቆልቁለን የጎሣዬ ልጅ መበባልና መቆራቆዝ ጀምረናል፤ ቁልቁል መውረድ እንጂ ወደላይ መውጣት የተከለከልን ይመስላል፡፡

ካለንበት ማጥ በጊዜ ለመውጣት የምንሻ ከሆነ ያለን አማራጭ አንድ ብቻ ነው፤ ዓቢይን ከነግሳንግሱ ደግፈን ሀሳቡን ማንገሥ ይበጃል፤ ዓቢይን ማዳከም አዳዲሶቹን ጉልበተኞች ማጠናከር ነው፤ እዚህ ላይ አንድ አውነት ነጥለን ማየት ያስፈልጋል፤ ዓቢይ ከአዲሶቹ ጉልበተኞች ጋር ተቃቅፎም ባይሆን እጅ-ለእጅ ተያይዞ የቆመ ይመስላል፤ ዓቢይን ከአዲሶቹ ጉልበተኞች መለየት እንዴት ለይተን እንወቀው? እንዴት የዓቢይን ጓደኞች አዳክመን እሱን እናጠንክረው? የፖሊቲካ ቡድኖች ያስቡበት!

ዓቢይ በጣም ጠንክሮ እንዲወጣ ካልተደረገ ሌላው አማራጭ እውን ካልሆነ ጉልበተኞች ተደባድበው አሸናፊው የሥልጣን ወንበሩን ይይዛል፤ ሁለት አደጋዎች ፊትለፊት ገጥመውናል፤ አንዱ አደጋ በጉልበተኞቹ መሀከል የሚደረገው ውጊያ በብዙ ሰላማዊ ዜጎች ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ያደርሳል፤ ሁለተኛው አደጋ አሸናፊው ጉልበተኛ መንበረ ሥልጣኑን ከያዘ በኋላ ሌላ የመከራ ዘመን ውስጥ እንገባለን፤ ከዚያ ይሰውረን!

Filed in: Amharic