>

ኦዴፓ መለስ ዜናዊ ቀምሞ ያስቀመጠለትን  መርዝ ለመድፋት መጀገን ይኖርበታል!!! (ያሬድ ጥበቡ)

ኦዴፓ መለስ ዜናዊ ቀምሞ ያስቀመጠለትን  መርዝ ለመድፋት መጀገን ይኖርበታል!!!
 
ያሬድ ጥበቡ
ኦዴፓ የኦነግን አጀንዳ ለመንጠቅ ሲሟሟት ይታያል። ይህም ቢያንስ በደቡቡና በመሃል ሃገሩ ኢትዮጵያዊ ዘንድ የስጋት ምንጭ ሆኗል። የኦነግን አጀንዳ ለመቀማት ከመሯሯጥ  በራሱ እምነቶች ላይ ፀንቶ በመቆም የሚያገኘውን ውሱን የኦሮሞዎች ድጋፍ ይዞ የሌሎች ኢትዮጵያውያንን ድጋፍ በመጨመር ሃገራዊ ምርጫውን ለማሸነፍ ቢሰራ…
የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) 29ኛ ዓመት ልደቱን ለማክበር በተደረገው ስብሰባ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያደረጉት ንግግር ቅንጭብጫቢው ተዘግቧል። በመጀመሪያ ኦዴፓ ለ29ኛ ልደት በአሉ በመድረሱ እንኳን አደረሰህ ማለት እወዳለሁ። የኦዴፓ መሥራች የሆኑትን አብዛኛውን አባላት ከኤርትራ የምርኮኛ ህይወት አውጥቼ ኢህዴን ውስጥ ለ7 ዓመታት እንዲታገሉ በማመቻቸት የአንበሳውን ድርሻ የተጫወትኩ በመሆኑ አሻራዬም ያለበት ድርጅት በመሆኑ እንኳን አደረሳችሁ ማለት ተገቢ መስሎ ይሰማኛል። በሚቀጥለው ዓመት ኦዴፓ 30ኛ ዓመቱን ሲያከብር በክብር እንግድነት ይጠራኛል ብዬ ለማሰብ እወዳለሁ።
ስለ 29ኛው የኦዴፓ ዓመት በአል ከተነገረው ዜና ጋር ተያይዞ የድርጅቱ አመራር የሁለት ቀን ስብሰባ እንደሚያደርግ ተዘግቧል። ይህ ስብሰባ የረፈደ ቢሆንም መካሄዱ እጅግ ወቅታዊ ነው ። በግሌ ከስብሰባው የምጠብቃቸው፣
1ኛ) ኦዴፓ ያሳየውን የመዋጥና የመጥቅለል ዝንባሌ ያስከተላቸውንና ወደፊትም የሚያስከትላቸውን ጦሶች በመገምገም፣ ኢህአዴግ ውስጥና መንግስታዊ አመራሩ ውስጥ ያለውን ሚና ወይም ድርሻ በተመለከተ ከኦሮሞ ህዝብ ቁመና ጋር የተመጣጠነ መሆን እንደሚገባው መቀበልና፣ በ2007 የህዝብ ቆጠራ ላይ ተመሥርቶ የኦዴፓ ድርሻ በሁሉም እርከኖች ደረጃ ከ32% ያልዘለለ ማድረግ ፍትሃዊና የእኩልነት መርህ የሚጠይቀው መሆኑን መቀበል። አሁን ተራው የኛ ነው ከሚል ፀረ ዴሞክራሲያዊ ዝንባሌ መቆጠብ፣
2) የታከለ ኡማ ሹመት የጠቅላይ ሚኒስትሩ ብሎም የኦዴፓ የህገወጥነት ጅማሮ ፣ (ወይም ፈረንጆቹ ኦሪጂናል ሲን የሚሉት) መሆኑን ተቀብሎ ተገቢውን እርማት ለማድረግ መጀገን። አዲስ አበባ ከእቅፏ በወጡ መሪዎች መተዳደር የዴሞክራሲ እሳቤ መሰረትና የህገመንግስቱም ድንጋጌ በመሆኑ፣ ኦዴፓ ራሱን ለህግ የበላይነት ተገዢ የማድረግ አስተሳሰቡን አፅንቶ የሚወጣበት ስብሰባ እንዲሆን፣
3) በአቶ ለማ መገርሳና አዲሱ አረጋ የተነገሩትና ህዝብ ጆሮ የደረሱት መረጃዎችን ታሳቢ በማድረግ፣ ኦዴፓ ከህዝብ ጀርባ የሚያውጠነጥናቸው ሴራዎች እንደማይኖሩትና፣ በግልፅና በህዝብ አደባባይ ተከራክሮ ለመርታትም ሆነ ለመረታት ዝግጁ መሆኑን ማረጋገጥ ።
4) የኦሮሞ ቄሮ ወደማይሟላ አጉል ተስፋ በመነዳት ሌሎች ደክመው ባፈሩት ሃብት ለመክበር በመነሳሳት ላይ ያለውን ስሜት ለመቆጣጠርና ሃብት ጥሮ ግሮ በድካም የሚገኝ እንጂ የሌላውን ባለሃብት  የድካም ውጤት በመዝረፍ ሊገኝ እንደማይችል በስፋት ለማስተማር ኦዴፓ በግንባር ቀደምነት መሰማራት እንደሚገባው መወሰን፣ ለዚህም ባለፉት አራት አመታት ኦሮሞ ያልሆኑ ኢትዮጵያውያን ባለሃብቶች እንዲዘጉ የተገደዷቸውን ቢዝነሶች የሚከፍቱበትን ሁኔታ ማመቻቸት፣ ከተቻለም ለደረሰባቸው ዝርፊያና እንግልት የሚገባቸውን ካሳ መስጠት፣
5)ለዓመታት ከልጆቻቸው አፍ እየነጠቁ ለኮንዶሚንየም ግዢ ጥሪት ያጠራቀሙ ኢትዮጵያውያን በሎተሪ ያገኙዋቸውን ቤቶች እንዲረከቡ ማድረግ። እነዚህ ቤቶች የተሰሩባቸው መሬቶች በየትኛው አስተዳደር ሥር ታክስ ይደረጉ የሚለው መፍትሄ እስኪያገኝ ድረስ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ስር በተቋቋመ ጊዜያዊ ኮሚቴ ሥር እንዲተዳደር ማድረግ ። መንግስት ተገቢ ክፍያ ሳይፈፅም አፈናቀላቸው ለሚባሉት ገበሬዎች ያፈናቀለው መንግስታዊ አካል ተገቢውን ክፍያ እንዲፈፅም መመሪያ መስጠት። በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚያድጉ ከተሞች የግድ የአዲስ አበባን መስፋፋት የሚያመጡ ሳይሆን ከተሞቹ የኦሮሞ ክልል ከተሞች ሆነው ማደግ እንደሚችሉ መቀበል፣
6) የኦሮሚያ ክልል የሥርአተ አልበኝነት መፈንጫ መሆን ከሁሉም በላይ እየጎዳ ያለው ኦሮሞዎችን በመሆኑ ፣ ህግና ሥርአትን ማስጠበቅ የክልል አመራሩና የመሪው ፓርቲ ሃላፊነት መሆኑን ተቀብሎ በተጨማሪም፣ በጌዶዎ ህዝብ ላይ ለደረሰው ግፍና ሰቆቃ አመራሩና ፓርቲው ሃላፊነት በመውሰድ ይቅርታ መጠየቅ፣
7) የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማ ከአዲስ አበባ እንዲወጣና ኦሮሞው ባህሉን፣ ቋንቋውን፣ ትውፊቱን ያለምንም ተፅእኖና ያላስፈላጊ ውጥረትና ውድድር ማድረግ የሚችልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት እንደ ጅማ ወይም ነቀምት ያሉ ከተሞችን በመዲናነት ለመምረጥ መጀገን ያስፈልግ ይመሰለኛል። የኦሮሚያ ክልል ዋና ከተማን አዲስ አበባ ላይ መደረብ፣ መለስ ዜናዊ በምርጫ 97 ብሽቀቱ ወቅት በዝረራ ያሸነፈውን የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት ለመቅጣት የቀመመው መርዝ በመሆኑ፣ ኦዴፓ ይህን መርዝ ለመድፋት መጀገን ይኖርበት ይመስለኛል።
8) ኦዴፓን ከሌሎቹ የኦሮሞ ብሄርተኞች ይለየው የነበረው በኢትዮጵያ ሃገረመንግስት ቀጣይነት ላይ የነበረው ፅኑ አቋም ነበር። አሁን ከምርጫ 2012 ጋር በተያያዘና የኦነግ ወደሃገርቤት መግባት በክልሉ ከፈጠረው ተሰሚነት ችግር በመነጨ ኦዴፓ የኦነግን አጀንዳ ለመንጠቅ ሲሟሟት ይታያል። ይህም ቢያንስ በደቡቡና በመሃል ሃገሩ ኢትዮጵያዊ ዘንድ የስጋት ምንጭ ሆኗል። የኦነግን አጀንዳ ለመቀማት ከመሯሯጥ፣ ኦዴፓ በራሱ እምነቶች ላይ ፀንቶ በመቆም የሚያገኘውን ውሱን የኦሮሞዎች ድጋፍ ይዞ የሌሎች ኢትዮጵያውያንን ድጋፍ በመጨመር ሃገራዊ ምርጫውን ለማሸነፍ ቢሰራና እጣው መሸነፍ ከሆነም ሽንፈትን በፀጋ ለመቀበልም መዘጋጀት የተሻለውና ዴሞክራሲያዊ ጉዞው የግድ የሚለው ይመስለኛል። የፖለቲካ ምስቅልቅሉንም የሚፈጥረው የ2012 ምርጫ መዳረስ በመሆኑም፣ እንኳንስ ምርጫ፣ ዘፋኞች እንኳ አዲስ ስራዎቻቸውን ለማድረስ የማይችሉባቸው ክልሎች በሰፈኑበት ሁኔታ ምርጫው ሊደረግ እንደማይቻል ተቀብሎና፣ የለውጥ አመራሩ ተቀባይነት ማሽቆልቆል ያደረሰውን የፖለቲካ ድቀት በመቀበል፣ ከተደራጁት ሃገራዊ ሃይሎች የተውጣጣ የሽግግር ምክርቤት እንዲመሠረት በማድረግ በዶ/ር አቢይ አመራር ዙሪያ አዲስ ሃገር አቀፍ የፖለቲካ አመራር እንዲፈጠር ቁርጠኛ አቋም መውሰድ፣
9) ኦሮሞ ቁመናው ትልቅ ነው ፣ ከዴሞክራሲያዊትና ኢትዮጵያዊት አዲስ አበባ ጋር ጎን ለጎን መቆም ይችላል ። አዲስ አበባን የኢትዮጵያ ብሄርተኝነት መናኸርያ አድርጎ መተው ለኦሮሞው ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የጎሳ ብሄርተኝነቶች ጠቃሚ ነው። አዲስ አበባ እምብርት ሆና ሁሉንም ማገናኘት፣ ማዋሃድ ነው ታሪክ የጣለባት አደራ ። ኦዴፓ ይህን አምኖ መቀበልና የአዲስ አበባን ህዝብ ሉአላዊነት (ህይወቱን ባፈተተው መንገድ የመምራት መብቱን) መቀበል አለበት፣ ይህንን በአሁኑ የአመራር ስብሰባ ወቅት አፅንኦት ሰጥቶ ሊያሰምረበት ይገባል። በቃ! አዲስ አበባ የነዋሪዎቿ ናት ብሎ መወሰን ለምን ይከብዳል?
10) ኦዴፓ በክልሉ ምሁራንና የፖለቲካ መሪዎች የሚፈጠሩ በሬ ወለደ ትርክቶችንና ህዝብን ከህዝብ የሚያለያዩ ንግግሮች የሚያርምበት ጠንካራ የኮሙኒኬሽን ቢሮ መመስረት ይገባዋል። በአቶ በቀለ ገርባ የተነገረውን ዓይነት ዘረኛ አስተሳሰብ (ከሌላ ብሄረሰብ አትዋለድ፣ አትገበያይ ወዘተ)፣ የጃዋር 43 ሰዎች ከቡራዩ ግድያ በፊት በአዲስ አበባ ተገድለዋል በሬ ወለደ ክፋት፣ የለገጣፎና ሱሉልታ ከንቲባዎች ያሳዩት ጭካኔና ዘር ተኮር ጥፋት ለማድረግ የመሻት ዝንባሌ ወዘተ ወዘተ ኦዴፓ ፈጥኖ ሊቆጣጠራቸው የሚገባቸው ጉዳዮች ይመስሉኛል። በተለይ በአዲስ አበባና ዙሪያው እንዲሁም በሸዋ በአጠቃላይ የሚመድባቸው የፓርቲና የክልል መንግስት ካድሬዎችና ሠራተኞች ከአካባቢው ህዝብ አብራክ የወጡና፣ ማንነታቸውን ህዝቡ የሚያውቃቸው ከሩቅ ከባሌ ወይም አርሲ የመጡ አክራሪ ብሄርተኞች ባይሆኑ የሚጠቀመው ኦዴፓ ራሱ ነው ብዬ መምከር እወዳለሁ። አላህ ቀናውን ያሳያችሁ!
Filed in: Amharic