>
5:18 pm - Monday June 16, 8138

"ልጓም አልቦው የኬኛ ፖለቲካ የት ያደርሰናል?!?" (መስከረም አበራ)


“ልጓም አልቦው የኬኛ ፖለቲካ የት ያደርሰናል?!?”
መስከረም አበራ
ብዙ ያልተነገረለት ግፍ የተከሰተው በቡርጅና በኮይራ ህዝቦች ላይ ነው፡፡ እነዚህ የደቡብ ህዝቦች ከኦሮሚያ ክልል ጋር ስለሚጎራበቱ በአገረማርያ (ቡሌ ሆራ) እና አጎራባች የኦሮሚያ መሬቶችም ይኖራሉ፡፡ መሬታችንን ለቃችሁ ውጡ እየተባሉ መንገላታት ከጀመሩ አንድ አመት አልፏቸዋል። በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ ቡርጅና ኮይራዎች፣ ባለመሬት ነኝ ባዮቹ ካድሬዎች የፈለጉትን ቢያደርጓቸው አቤት የሚሉበት አካል የለም፡፡ አንድ ከአካባቢው የመጣ፣ ኦሮሞ መሆኑን፣ ግን በድርጊቱ በጣም እንደሚያዝን የነገረኝ ልጅ፤ “የሃገር ባለቤት ነን” በሚሉ የኦሮሞ ጎረምሶች አራት ጌዲኦዎች ታርደው ተጥለው በአይኑ እንዳየ እየዘገነነው አጫውቶኛል!!!

ህወሃት በአምሳሉ ጠፍጥፎ ሰርቶ እስትንፋስ “እፍ” ያለባቸው የኢህአዴግ እህት ድርጅቶች ካድሬዎች፣ የእውቀት ራስ ህወሃት ብቻ ይመስላቸዋል፤ እርሱ  ከሄደበት መንገድ ውጭም ፖለቲካ የሚዘወር አይመስላቸውም። የኢትዮጵያ ህዝብ ወዝውዞ ወዝውዞ ያዛለውን ፈጣሪ ጌታቸውን ህወሃትን ገፍትረው ለመጣል የደፈሩት የህዝብን ክንድ ተማምነው ነበር፡፡ ህወሃት ከወደቀ በኋላ ስልጣን ላይ የተሰየመው ኦዴፓ፤ ጌታው ህወሃት አይንህ ላፈር የተባለበትን ነገር ሁሉ እየደገመ ያለው፣ ከህወሃት ውጭ አስተማሪና  ንባብ፣  ባጠቃላይ “ትምህርት ቤት” ስለማያውቅ ነው፡፡
ብዙ ህዝብ እንወክላለን የሚሉትን የኦህዴድ ካድሬዎችን ጨምሮ፣ ሁሉንም የኢህአዴግ ድርጅት ሰዎች ሲዘውር የኖረውን ህወሃት፤ እንደ እውቀት ጥግ ሲያዩት ለኖሩት ለአገልጋዮቹ ሲያስተምር የኖረው፣ አንዴ ስልጣን ላይ ከተቀመጡ፣ እንዴት “ይሉኝታ ቢስ፣ ብልሹ ዘረኛ” መሆን እንደሚቻል ነው፡፡ በህወሃት እግር ስር ቁጭ ብለው ዘረኝነት፣ እብሪት፣ ሃሰት፣ ሸርና ዘረፋ ሲማሩ ከነበሩት አንዱ (ኦዴፓ) በለስ ቀንቶት ስልጣን ላይ ሲወጣ፣ እየደገመ ያለው፣ ብቸኛው መምህሩ ህወሃት፣ ሲያደርግ የኖረውን ነው፡፡
የተለየ ነገር ቢኖር፣ ኦዴፓ የእበልጣለሁ ባይነቱን ስሜት፣ እንደ ህወሃት ጊዜ ወስዶ፣ ረጋ ባለ መንገድ ማስኬድ  አለመቻሉ ነው፡፡ የኦዴፓ ለበላይነት መራወጥ ከፍተኛ ፖለቲካዊ መንቀዥቀዥ የታየበት፣ በይሉኝታ ቢስነቱም ህወሃትን ሊያስናፍቅ የሚቃጣው ነው፡፡ ይህ ኦዴፓን በአራስ ቤት እንደሚሞት ህፃን እድሜውን ሊያሳጥር የሚችለው አካሄድ፣ ሁሉን ነገር ለእኔ በሚለው በዚህ ፅሁፍ ሁኔታ፣ “የኬኛ ፖለቲካ” እያልኩ በምገልፀው እጅግ ብልሃት በጎደለው አካሄዱ ይታጀባል፡፡ እየጎመራ የመጣው የኬኛ ፖለቲካ አዝማሚያ፣ ለሁሉም ዜጋ እጅግ አደገኛ ነገር ይዞ ስለሚመጣ፣ መገለጫዎቹን መመርመሩ፣ አስፈላጊ ነውና ወደዛው ልለፍ፡፡

የ”ባንክ እና ታንክ” ቁጥጥር
የኦህዴድ መምህር ህወሃት፣ ለ27 ዓመታት የኢትዮጵያን ሁለመና በመሀል እጁ ይዞ የኖረው፣ በክላሹና ከህዝብ በሚዘርፈው ገንዘብ ነበር፡፡ ከህወሃት ውጭ ዓለምም፣ አስተማሪም፣ንባብም የሌላቸው የኦህዴድ ካድሬዎችም፤ በለስላሳ ምላሳቸው የሚሉትን ብለው ህዝቡን ወከክ ካደረጉ በኋላ መንግስታቸው የፀና ሲመስላቸው ያደረጉት፣ ባንኩንና ታንኩን መቆጣጠር ነው። ህወሃት ኤፈርትን የመሰለ የዘረፋ ኢምፓየር የገነባው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን እየዘረፈ ነበር። የአሁኑ ንጉስ ኦዴፓም ተመሳሳዩን ለማድረግ የጎጡን ሰዎች ከአዋሽ ባንክ አምጥቶ በንግድ ባንክ ቁንጮ የአስፈፃሚነት ቦታዎች ከኮለኮለ እነሆ አንድ  ወር ተጠጋው፡፡
ባንኩን መቆጣጠር የገዥውን ጎጥ ሰዎች እየመረጡ ቱጃር ለማድረግ አመች ነገር ነው። ዘመድ ሰብሰብ ብሎ ባለስልጣን በሆነበት ባንክ፣ ያለማስያዣም ቢሆን የብድር አገልግሎት ይቀላጠፋል፣ በንግድ መሃል ኪሳራ ከመጣም ክፈሉ የሚል ግዳጅ የለም፤ የተበላሸ ብድር ተብሎ እዳው ወደ ኢትዮጵያ ህዝብ ይዞራል። የዘመድ በየባንኩ መኮልኮል የሚበጀው የራስን ጎጥ  ለመጥቀም ብቻ አይደለም፤ “የትምክህተኛን” ወይም የሌላን ዘር አድጋለሁ ባይ ነጋዴ ለማቀጨጭም ነው፡፡ ሁሌም በልዩ ሁኔታ ተጠቃሚ ካለ፣ በልዩ ሁኔታ ተጎጂ አለ። የራስን ጎጥ በልዩ ሁኔታ ተጠቃሚ፣ ሌሎችን የበይ ተመልካች ማድረግ ደግሞ ለጎጥ ፖለቲከኛ ትልቁ ስኬቱ ነው!
ኦዴፓ እንደ ዝንጀሮ ልጅ (የዝንጀሮ ጎረምሳ ማደጉን የሚያረጋግጠው እግሩን ከአባቱ እግር ጋር ሲለካ ነው ከሚለው አባባል ጋር በሚዛመድ መልኩ) እድገቱን የሚለካው እግሩን በህወሃት ዱካ እየለካ ለመሆኑ ማስረጃው በሃገር መከላከያ ሰራዊት ውስጥ የጎጡን ሰዎች የሰገሰገበት እጅግ አደገኛ አካሄድ ነው፡፡ በዚህ ላይ የኦሮሚያ ልዩ ሃይል ዋና ማዘዣ አዲስ አበባ  እንዲከትም አዲሱ ጌታ ኦህዴድ አዟል፡፡ ይህን ተከትሎ ሶስት ሺህ አዳዲስ የኦሮሚያ ልዩ ሃይል ፖሊሶችም አዲስ አበባ እንዲከትሙ ተደርጓል፡፡ ከዚህ የምንረዳው፣ የኬኛ ፖለቲካ የተንተራሰው የፈጠራ ታሪክንና የህገ-መንግስት ተረክን ብቻ ሳይሆን የወታደር ጉልበትንም ደጀን እንዳደረገ፣ በታንክም እንደሚታገዝ ነው፡፡
የለውጥ አመራሮች- የንቅል ካድሬዎች
ኦህዴድ ከህወሃት የተለየ ለመምሰል በሚሞክርበት ዘመን፣ ፓርቲው “የለማ ቡድን” የተባሉ የለውጥ አመራሮችን መፍጠሩን ሲያወራ ከርሟል፡፡ እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን ሲገልጡ ደግሞ የለገጣፎዋ አረመኔ አፈናቃይ ወ/ሮ ሃቢባ ሲራጅን፣ ግራ የገባቸውን ተፈናቃዮች ሰብስባ ስትመፃደቅ የሰነበተችዋን የክልሉን ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወ/ሮ ጠይባ አህመድን፣ ከጎኗ ተሰይሞ በሰው ቁስል እንጨት ሲሰድ የከረመውን አቶ አዲሱ አረጋን አይነት ሰዎች ናቸው፡፡ ሌላዋ ግልፅ ዘረኛና እብሪተኛ የለውጥ አመራር ተብዬ ደግሞ “በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ባላፈናቅል፣ ጣቴ ነው አንገቴ ይቆረጥ” ስትል በአደባባይ የምትናገር፣ ወ/ሮ ሮዛ የተባለችው የሱሉልታ ከንቲባ ነች፡፡ ይህች ሴትዮ ቤታቸው እንደሚፈርስ ተነግሯቸው ሰማይ ምድር የዞረባቸውን ሰዎች ሰብስባ፣ የኦሮሞ ቤት ተቀባ ማለት ይፈርሳል ማለት እንዳልሆነና ኦሮሞዎች የባዕዳንን ጦርነት መዋጋታቸውን እንዲያቆሙ ኮራ ብላ በአደባባይ የምትናገር ናዚ ነች፡፡ እነዚህ የለውጥ አመራር የተባሉ ሰዎች የሚያስፈፅሙት፣ ዐቢይ እና ለማ በሌሉበት፣ ብቻቸውን ያቀዱትን ዕቅድ እንዳልሆነ ግልፅ ነው፡፡
እነዚህ አደገኛ የዘረኝነት አዝማሚያ የተሸከሙ የኦህዴድ የለውጥ አመራር ተብዬዎች፣ ህወሃት ከትግራይ ገጠራማ አካባቢዎች አምጥቶ አዲስ አበባ ይሰገስጋቸው የነበሩ፣ ህወሃት ካዘዛቸው ምንም ከማድረግ ወደ ኋላ የማይሉ፣ በተለምዶ ንቅል ካድሬ የሚባሉትን አይነት ናቸው፡፡ እንደ ህወሃት ንቅል ካድሬዎች ሁሉ የኦህዴድ የለውጥ አመራር ተብዬዎች፣ ከሚመሩትና ከሚያፈናቅሉት ህዝብ ጋር አንዳች የቆየ ትስስር የሌላቸው፣ ከኦሮሚያ ሌላ አካባቢዎች መጥተው የተሾሙ እንደሆኑ ነው ተጎጂዎች የሚናገሩት፡፡ እነዚህ ንቅል የለውጥ አመራሮች ከሌላ የኦሮሚያ ቦታ (ምናልባትም ገጠራማ ቦታዎች) መጥተው አዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ከተሞችን እንዲመሩ የተደረገው፣ የከተሜን ከዘር ትስስር የራቀ አኗኗር ስለማይረዱ፣ በማፈናቀሉ ላይ ወደ ኋላ የማይሉ መሆናቸው ስለተፈለገ ነው፡፡ ለዚህ ማስረጃው ምክትል ርዕሰ መስተዳድሯ ወ/ሮ ጠይባ ሃሰን፣ አቶ አዲሱ አረጋን አስከትላ፣ ለገጣፎ ተገኝታ፣ ወ/ሮ ሃቢባ ያደረገችው አረመኔያዊ ማፈናቀል እንዴት ህጋዊ እንደሆነ ለተጎጂዎቹ ለራሳቸው ልታስረዳ የተሟሟተችበት መንገድ ነው፡፡
እንደዚህ ከላይኛው አመራር ጥብቅና የሚቆምላቸው ንቅል የለውጥ አመራሮች፣ የከተማ ሰው እንዴት እንደሚኖር የማያውቁ፣ ጥሩ ፖለቲከኛ ማለት ጭፍን ዘረኛ የሚመስላቸው፣ ብልጣብልጦቹ አለቆቻቸው የኬኛ ፖለቲካን የመሰለ አደገኛ መርዝ ጭነው ፈተው የለቀቋቸው የእውቀት ድሆች ናቸው። ብልጦቹ የላይኞቹ አመራሮች ደግሞ የሚያምን ሞኝ ካገኙ፣ ይህን የሚያደርጉት ከነሱ ቁጥጥር ውጭ የወጡ አክራሪ ዘረኞች እንደሆኑ ይናገራሉ። በዚህ መንገድ ከኦሮሙማ አላማቸውም ሳይናጠቡ፣ ከህዝብ ድጋፍም ሳይጎድሉ ለመጓዝ ይሞክራሉ። ይህ እስከ የት እንደሚያስኬዳቸው የሚታይ ይሆናል፡፡
ኢትዮጵያን ከኦሮሚያ ማስወጣት፤ ኦሮሚያን ወደ ኢትዮጵያ ማስገባት
የኦህዴድ ንቅል የለውጥ አመራሮች፣ የኦሮሙማ አጀንዳቸውን የሚያሳኩበት የኬኛ ፖለቲካ ዋና አላማው፣ ኦሮሚያን የኦሮሞዎች ብቻ ማድረግ ነው፡፡ ኦሮሚያ የኦሮሞዎች ብቻ የምትሆነው ደግሞ በለገጣፎና በሱሉልታ እንደተደረገው፣ ዘር እየለዩ ኦሮሞ ያልሆነውን ህዝብ አፈናቅሎ፣ ከኦሮሚያ ምድር በማስወጣት ነው፡፡ መፈናቀሉ ዘር የለየ እንደሆነ የለገጣፎዋ ወ/ሮ ሃቢባም ሆነች የሱሉልታዋ ወ/ሮ ሮዛ በገዛ አንደበታቸው የተናገሩት ነው፡፡ አሁን በዚህ ሰዓት ደግሞ በአርሲና በባሌ የተለያዩ ቦታዎች፣ ኦሮሞ ያልሆኑ ሰዎች በተለይ አማሮች ሃገራቸውን ለቀውላቸው እንዲወጡ የሚያሳስብና የሚያስፈራራ ወረቀት በየ”ባዕዳኑ” በር ላይ እየተለጠፈ እንደሆነ እማኞች እየተናገሩ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ከአርሲና ባሌ እንዲወጡ የተጠየቁት እንደ ሱሉልታና ለገጣፎዎች ህገወጥ ቤት ሰርታችኋል የሚል አስመሳይ ምክንያት እንኳን ሳይነገራቸው ነው፡፡ ከዚህ የምንረዳው የኬኛ ፖለቲካ መዳረሻው፣ ኦሮሚያን ከኢትዮጵያ ማፅዳት እንደሆነ ነው፡፡
“ኦሮሚያ የኦሮሞ ነች” ብሎ ሰፊና ለም ክልልን ለኬኛ ፖለቲከኞች ብቻ የሸለመው የህወሃት ህገ-መንግስ፤ ይህ ክልል ኦሮሞ ወደ ኢትዮጵያ ከመፍለሱ በፊት ህዝብ እንደነበረበት ለኬኛ ፖለቲከኞች አላስረዳቸውም፡፡ ከህወሃት የሚያልፍ እውቀት ያለ የማይመስላቸው የኬኛ ፖለቲከኞች ደግሞ “ኦሮሚያ የኦሮሞ ነች” የሚለውን የህወሃት ተረክ ንጥር ሃቅ፣ የማይጠየቅ እውነት አድርገው ተቀብለው፣ ሃገርን እግር በራስ የሚያደርግ ስህተት እየሰሩ ነው፡፡ አሮሚያን ለኦሮሞ ብቻ የሚሉት የኬኛ ፖለቲከኞች፤ በአንድ በኩል፣ ኢትዮጵያን ከኦሮሚያ እስከ ማስወጣት የደረሰ የቂል ሙከራ ሲያደርጉ፣ በሌላ በኩል ኦሮሚያን ኢትዮጵያ ላይ ለማንሰራፋት የፌደራል ስልጣኑን ወረውታል፡፡ ከሲቪል እስከ ወታደራዊ ስልጣን፤ ከሚዲያ እስከ የፍትህ አካላት፣ የፌደራል መንግስቱ ስልጣን በእጃቸው ነው። የመንግስት ሚዲያው ኦህዴዶች ለኦሮሙማ አላማቸው የማይፈልጉትን አጀንዳ የሚያራምድ ሁነት አይዘግብም፤ ለምሳሌ የአዲስ አበባ ህዝብ በባልደራስ ተሰብስቦ ዘረኝነትና ስልጣን ተጋግዘው ካመጡበት አደጋ ራሱን ለመከላከል የሚያደርገውን ትግል መንግስት የሚቆጣጠራቸው ሚዲያዎች በስህተት እንኳን አልዘገቡም፡፡ ኦህዴድ ህገ-መንግስቱን ጥሶ በማያስተዳድረው ግዛት ውስጥ ያለችው አዲስ አበባ ከተማ፣ የግል ንብረቴ ነች የሚል ህገ-ወጥ መግለጫ ሲያወጣ፣ ጠቅላይ አቃቤ ህግ በወንጀል ያልጠየቀው፣ መስሪያ ቤቱ  በኦህዴድ ስለሚዘወር ነው፡፡
የኬኛ ፖለቲካ መዘዘዞች
ከላይ የተጠቀሱ እና ባለፈው ሳምንት ለመጠቆም የሞከርኳቸውን አስቻይ ሁኔታዎችን ተጠቅሞ፣ ክፉኛ እየሰገረ ያለው የኬኛ ፖለቲካ ፈረስ፣ ልጓም ካልገባለት በርካታ መዘዞችን ይዞ የሚመጣ ነገር ነው፡፡ እነዚህ መዘዞች የወዲያው (Immediate) እና የረዥም ጊዜ (Long term)ተብለው በሰፊው ለሁለት ሊከፈሉ ይችላሉ። የኬኛ ፖለቲካ የወዲያው ጥፋቶች መታየት ጀምረዋል፡፡ ከነዚህ ጥፋቶች አንዱ የህዝቦች መሞት፣መፈናቀል፣ መዘረፍ፣ ፍትህ ማጣት ነው።
የጌዲኦ ተፈናቃይ ህዝቦች ስቃይ፣ የለገጣፎ ተፈናቃዮች፣ በሱሉልታ መፈናቀል የተደገሰላቸው በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች፣ በቄለም ወለጋ የሚኖሩ አማሮች፣ በአርሲና ባሌ በስጋት የሚኖሩ ኦሮሞ ያልሆኑ ህዝቦች፣ ስጋትና እንግልት አንዱ ምክንያት  የኬኛ ፖለቲካ መዘዝ ነው፡፡ የኬኛ ፖለቲካ ብዙ ያልተነገረለት ግፍ የተከሰተው በቡርጅና በኮይራ ህዝቦች ላይ ነው፡፡ እነዚህ የደቡብ ህዝቦች ከኦሮሚያ ክልል ጋር ስለሚጎራበቱ በአገረማርያ (ቡሌ ሆራ) እና አጎራባች የኦሮሚያ መሬቶችም ይኖራሉ፡፡ በተለይ በጤፍ አምራችነታቸው፣ በአጠቃላይ በጠንካራ አራሽነታቸው ይታወቃሉ፡፡ በዚህ ምክንያት መሬታችንን ለቃችሁ ውጡ እየተባሉ መንገላታት ከጀመሩ አንድ አመት አልፏቸዋል። ከአንድ አመት በላይ መንገድ ተዘግቶባቸው ለቅንጦት ቀርቶ ቢታመሙ፣ ወላድ ምጥ ቢይዛት ሆስፒታል የሚደርሱበት መንገድ የላቸውም፡፡ በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ ቡርጅና ኮይራዎች፣ ባለመሬት ነኝ ባዮቹ ካድሬዎች የፈለጉትን ቢያደርጓቸው አቤት የሚሉበት አካል የለም፡፡ አንድ ከአካባቢው የመጣ፣ ኦሮሞ መሆኑን፣ ግን በድርጊቱ በጣም እንደሚያዝን የነገረኝ ልጅ፤ ይህን ግፍ  አጫውቶኛል፡፡ አራት ጌዲኦዎች ታርደው ተጥለው በአይኑ እንዳየ እየዘገነነው ነግሮኛል፡፡ “የሃገር ባለቤት ነን” ያሉ የኦሮሞ ጎረምሶች፣ በቀን በብርሃን የቡርጅዎች ቤት ጣራ ላይ ወጥተው፣ ቆርቆሮ ነቅለው ሲወስዱ፣ ባለቤቶቹ ቡርጅዎች ቆመው ከማየት ውጭ አማራጭ እንደሌላቸው፤ ይህንንም ሲያደርጉ እንዳየ እያዘነ ነግሮኛል፡፡ ይሄ ቡርጅ፣ ኮይራ፣ ጌዲኦ ላይ ለምን ተደረገ ብሎ መጠየቅ አንድ ነገር ሆኖ በቡርጅ፣ ኮይራና ጌዲኦ ተወስኖ ይቀራል ብሎ ማሰብ ግን ሞኝነት ነው፡፡ ዝም ከተባለ ነገ አዲስ አበባ ይመጣል፤ እየመጣም ነው፡፡
ይህ የህዝቦች መፈናቀል፣ የባለ ጊዜ ነኝ ባዮች ስርዓት አልበኝነት በራሱ እጅግ አደገኛ ነገር ሆኖ ሳለ፣ ለሌሎች ክልሎች ጎረምሶችም አርአያነትን ሊያመጣ ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ በተጨባጭ በደቡብ ክልል ዋና ከተማ በአዋሳ፣ በአማራ ክልል ዋና ከተማ ባህርዳር የታየ ነው፡፡ ባለ ጊዜ ነኝ ባይ ስርዓት አልበኛ ምንም ሲደረግ ያላየ የሌላ ክልል ጎረምሳም፣ ዘሩን የበላይ ለማድረግ “ሌሎች” በሚላቸው ላይ ተመሳሳዩን እያደረገ ሲሄድ፣ ሃገራችንን መልሰን ላናገኛት እንችላለን፡፡ ነገሩን ከሃገር መፍረስ በመለስ እንየው ከተባለም፣ ሃገሪቱን ለከፋ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ቀውስ ይዳርጋታል፡፡ ሲንፏቀቅ የኖረው ኢኮኖሚያችን ጨርሶ እንዲሞት ያደርጋል፡፡ የኢኮኖሚ ችግር ደግሞ ዘረኝነት የለኮሰውን የፖለቲካ እሳት ይብስ ያነደዋል፤ ስርዓት አልበኝነቱን ያጎነዋል። ይህ ሁሉ ተደማምሮ በሃገር ተስፋ መቁረጡን ያባብሳል፡፡ ስደት መፍትሄ ይሆናል፤ የባህር እራት መሆኑ ከነበረው ብሶ ይቀጥላል፡፡ ኢትዮጵያዊነት የሚኖር ከሆነም፣ እንደ ውሻ በየቦታው ወድቆ ከመቅረት፣ በየባዕድ ሃገር በረሃ ከማለቅ ውርደት ጋር ተጋምዶ ይቀጥላል፡፡
በኬኛ ፖለቲካ ምክንያት በህዝብና በመንግስት መሃል ወርዶ የነበረው እርቅ ይከስማል፤ ጠብና ክርክር ከአንድ አመት እረፍት በኋላ ወደ ቦታው ይመለሳል፤ እየተመለሰም ነው፡፡ በዚህ ሳቢያ ከዲያስፖራው ይመጣ የነበረው የውጭ ምንዛሬ ይመናመናል፤ እንደ ቀድሞው በዘመቻ የሚታገድበት ጊዜም ሩቅ አይመስለኝም፡፡ ሃገር ውስጥ ያለው ዜጋ ስራውን እንዳያከናውን የፖለቲካ አለመረጋጋቱ እግር ብረት ሆኖ ይቀይደዋል፡፡ የውጭ ምንዛሬ እጥረቱ ያገሪቱን ኢኮኖሚ ከድጥ ወደ ማጥ ይከተዋል፡፡ ይህ የኬኛ ፖለቲካ የወዲያው ተፅዕኖ  የሚያመጣው ተራዛሚ ውጤት ይሆናል። ይህ ተራዛሚ ውጤት ሃገሪቱን መልሶ ወደ አለመተማመን ፖለቲካ፣ ወደ ተስፋ መቁረጥና በኋላቀር ኢ-ዲሞክራሲያዊ ሁኔታ ወደ መመራት ልማዷ ይከታታል፡፡ ተከባብሮ ተማምኖ መኖር ይጠፋል፡፡ መብለጥን እንጂ እኩልነትን እንደ መፍትሄ የማያየው የዘር ፖለቲካ፣ መጨረሻው ሃገር ማፍረስ ነው፡፡ በሰለጠነ ዘመን፣ በነቃ ህዝብ ላይ የበላይ ሆኖ መኖርን ማሰብ፣ በልብ ሌላ ይዞ በአፍ ሌላ እያወሩ ሰውን ለማሞኘት የሚደረግ የሞኝ ሩጫ፣ ሄዶ ሄዶ ኢትዮጵያን እንደ ዩጎዝላቪያ “ነበረች” ወደ ምትባል ተረት ሊቀይራት ይችላል፡፡
የኬኛ ፖለቲከኞች ሁሉን ለእኔ በማለታቸው የገፉት ይህን ሁሉ ስለማያውቁ አይደለም። ይልቅስ የያዛቸው የዘረኝነት አባዜ ኢትዮጵያ  ፈርሳ ኦሮሚያ ልታብብ እንደምትችል ስለሚነግራቸው ነው፡፡ ይህ እጅግ ስህተት ቢሆንም ተገፍቶበታል፡፡ ልጓም ያልገባለት ምኞታቸው፣ የኢትዮጵያዊነት አንድያ አምባ የሆነችውን አዲስ አበባን የአንድ ጎጥ ንብረት ለማድረግ እስከ መሞከር ሄዷል። ይህ ሳይታፈርበት በመግለጫ እስከ መነገር ደርሷል፡፡ የኬኛ ፖለቲካ በአዲስ አበባ ላይ ያለውን አላማ እንዲያሳካና ከተማዋን እንዲቆጣጠር መፍቀድ ለማንም ኢትዮጵያዊ የሚሆንለት ነገር አይደለም፡፡ አዲስ አበባን የመሰለች ኢትዮጵያዊነት ምልክት ለመታደግ ሰመራም፣ ጅጅጋም፣ ባህርዳርም፣ ድሬዳዋም፣ አርባምንጭም፣ ሆሳዕናም፣ ወላይታ ሶዶም፣ ዱረሜም፣ አሶሳም፣ ደብረማርቆስም ሩቅ አይደሉም፡፡ በሰለጠነ ዘመን የሃገር ሩቅ የለም! “በቅርብ ያለሁ እኔ ነኝና አርፋችሁ ተቀመጡ” የሚለው ቂልነት የማያጣው ሃሳብ፤ ይልቅስ ከተማዋን የእልቂት አምባ ያደርጋታል፡፡
አዲስ አበባ ስትታመስ የሚናጣው ብዙ ነው፡፡ አዲስ አበባችን ከኒውዮርክና ጄኔቭ ቀጥላ የአለም አቀፍ ድርጅቶች መዲና በመሆን ሶስተኛዋ ዓለም አቀፍ ከተማ ነች፡፡ ይህ ክብራችን ነበር! ከሁሉም በላይ አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና ነች፤ ይህ የሆነው እኛ በዘር መባላቱ አዳርሶን በሰራነው ስራ አይደለም- ነጋ በጠባ የምንረግማቸው አባቶቻችን ሞተው ባመጡልን ክብር የተገኘ እንጂ! የኬኛ ፖለቲካ ዝቅታ፣ እንዲህ ላለው ለአዲስ አበባ ዓለማቀፋዊ ግዝፈት የማይመጥን፣ የኦሮሙማ ጠባብ ጥብቆ ሊያለብስ የሚንገታገት ነው፡፡ ግዙፏ፣ አለማቀፏ አዲስ አበባ፤ በዚህ ጠባብ ጥብቆ ለመግባት ትልቅነቷ አይፈቅድላትም፡፡ በጠባቡ ጥብቆው እንድትገባ የሚደረገው አሽቆልቋይ ትግል፤ አዲስ አበባን እጅግ ያውካታል፤መረጋጋቷን ይነጥቃታል፡፡ ባልተረጋጋ ከተማ ለመኖር የሚፈቅድ ዓለም አቀፍ ተቋም ደግሞ አይኖርም፡፡ ሁሉም አንድ አንድ አንድ  እያለ በኬኛ ፖለቲካ የምትታመሰውን አዲስ አበባን እየለቀቀ ይሄዳል፡፡ ይሄኔ የአፍሪካ መዲናነት ምን እንደሆነ ጠንቅቀው የሚያውቁ፣ ይህን ክብር ለማግኘት ሌት ተቀን ሲሰሩ የኖሩ የአፍሪካ ሃገራት፣ መባላታችንን ጠቅሰው፣ የአፍሪካ መዲናነት ወደሚመጥነው ከተማ እንዲያቀና ይከራከራሉ፡፡ ያኔ ምን እንደምናወራ አላውቅም! የሜንጫና የዱላ ትርኢት በሚታይበት፣ ጦርነት በሚታወጅበት ከተማ መኖር አለባችሁ ብሎ ማስገደድ ይቻላል? ላስገድድ ቢባልስ ማን ይሰማል? ስለዚህ የኬኛ ፖለቲካ በዚህ ከቀጠለ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫነታችንን ሊነጥቀን ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ ታሪካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ስነ-ልቦናዊ ውርደት ያመጣል፡፡ ከዚህ ውርደት ለመዳን ኦህዴድ ሃይ መባል አለበት፡፡ እንዴት ለሚለው ሌላ ቀጠሮ ልያዝ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ከላይ የቀረበው ጽሁፍ፣ የጸሃፊዋን ሃሳብ  ብቻ የሚያንጸባርቅ መሆኑን ልንገልጽ እንወዳለን፡፡
Filed in: Amharic