>

የጦርነት አምሮታችንን ለመወጣት!!! (ደረጀ ደስታ)

የጦርነት አምሮታችንን ለመወጣት!!!
ደረጀ ደስታ

ደቡብ ኮሪያ ላይ በአጋርነት ለተዋጉ ኢትዮጵያውያን፣ ቼንቸዮን በተሰኘ ሥፍራ፣ የተሠራ የመታሰቢያ አዳራሽ ነው። እንደ ሙዚየምም ሆኖ ኢትዮጵያም ራሷን ታስተዋውቅበታለች።

አንዳንዴ እንዲህ እሚያንቀለቅለን የጦርነት አምሮታችንን ለመወጣት፣ ችግር ካለበት አንዳንድ አገር ሄደን በአጋርነት ብንዋጋ ሳይሻል አይቀርም። ቢያንስ ሁላችንም እምንኮራበት የጋራ መታሰቢያ ይቆምልናል። አገራችን ውስጥ ግን – ወንድም ወንድሙን ወግቶም ሆነ በወንድሙ ተወግቶ የድልና የበቀል፣ የአርበኝነትና የሰማዕት ሐውልት ከመትከል፣ አበባና እህል ማብቀል በተሻለን ነበር። ወይም ያስመኛል።
ኮሪያን ማንሳቴ እለውና እልበት መንገድ ባጣ “ምሳሌ ስጠኝ እንጂ ምሳሌ አታድርገኝ” የሚለው ተረት ትዝ ብሎኝ ነው። እንጂማ እዚያ ድረስ መሄዴ ወድጄ አይደለም ነድጄ ነው። የአባቴ እና እናቴ ወገኖች በየፊናቸው እሚተክሉት የሁለት፣ ምናልባትም የሶስትና የአራት ቤት ሐውልት ከወዲሁ እየታየኝ ነው።
 እሚያጨራርስ ጦርነት፣ በባንዲራው ብዛት ያስታውቃል። ያውም እንኳን ገድለው ፣ ቆጥረው እማይጨርሱት ዘርና ማንዘርዘር፣ በሚተረተርባት አገር፣ ጦርነት ኪሳራ ነው። ብለነው ብለነው ሲያቅተን፣ ተመልሰን መታረቃችን ላይቀር፣ ከወዲሁ ብንስማማ ምን ነበረበት?
Filed in: Amharic