>
5:13 pm - Monday April 18, 2507

ልዩ መግለጫ! የዜጎችን ሕይዎት በግፍ የቀጠፉ ፅንፈኞች ለፍትህ ይቅረቡ! (Global Alliance)

Urgent Press Release

Global Alliance for the Rights of Ethiopians (GARE) PO Box 1836, Rancho Cordova, CA 95741 Telephone: (877)746 -4384 www.GlobalAlliancefortheRightsofEthiopians.org
info@defendethiopians.org

All Lives Have Equal Value

 

 

 

                                                                     ልዩ መግለጫ

 

                             የዜጎችን ሕይዎት በግፍ የቀጠፉ ፅንፈኞች ለፍትህ ይቅረቡ!

 

ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያዊያን መብት ከተቋቋመበት የዛሬ ስድስት ዓመት ጀምሮ በተከታታይና ባለው አቅም መሰረት ብሄር፤ ኃይማኖት፤ የፖለቲካ ዝንባሌ፤ ጾታ ወይንም እድሜ ሳይለይ በአገር ቤትና በውጭ ለሚኖሩ ለኢትዮጵያዊያን ወገኖቹ በያሉበት ለሚደርስባቸው ግፍ፤ በደልና ችግር ያልተቆጠበ ጥረት ሲያካሄድ ቆይቷል። በተለያዩ ወቅቶች በተከሰቱ አሰቃቂ ሁኔታዎች ላይ መግለጫዎችን አውጥቷል።

ዛሬም በሰሜን ሸዋ በሚኖሩ ንጹህ ኢትዮጵያዊያን ላይ የተፈጸመውን ግፍ፤ በደልና እልቂት በተመለከተ ይህን መግለጫ አውጥቷል።

ከድርጅታችን ዋና ተግባሮች መካከል ትኩረት ሰጥተንባቸው የቆዩት ስራዎች ከወገኖቻችን ገንዘብ ሰብስቦ ሰብአዊ የገንዘብ እርዳታ ( Humanitarian Assistance) ለተጎዱ ወገኖቻችን በአስቸኳይና አስተማማኝ በሆነ መንገድ እንዲደርሳቸው ማድረግ፤ ለወገኖቻችን አቤቱታዎችን ለሚመለከታቸው የአገር ውስጥና የውጭ አካላት ማቅረብ፤ በሕግና በሌላ በባለሞያዎች የተደገፈ እርዳታ ለሚመለከታቸው ግለሰቦች ግጋፍ እንዲያገኙ ማመቻቸት፤ እርቅና ሰላም፤ ብሄራዊ መግባባትና ሌሎች የአቅም ግንባታ ስራዎች እንዲሰሩ ሁኔታዎችን ማመቻቸትና በዘላቂነት ከቤታቸውና ከቀያቸው የተፈናቀሉትን ወገኖቻችን ራሳቸውን እንዲችሉ ከሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ አገልግሎት ሰጭ ድርጅቶችና ከመንግሥት ተቋማት ጋር ሆኖ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይገኙበታል።

ድርጅታችን በተቻለው መጠን ዛሬ በሰሜን ሸዋ በልዩ ልዩ ቦታዎች ለሞቱትና ለቆሰሉት ቤተሰቦችም ተመሳሳይ ድጋፍ ለመስጠት የወሰነ መሆኑን ለደጋፊዎቻችንና ለኢትዮጵያ ሕዝብ እናስታውቃለን።

በአሁኑ ወቅት ድርጅታችንን እጅግ በጣም ያሳሰበው፤ ያስጨነቀውና ድምጹን በመግለጫ እንዲያሰማ ያስገደደው ሁኔታ በሰሜን ሸዋ በሚገኙ ከተሞችና መንደሮች፤ በንጹህ ወገኖቻችን ላይ ከቅዳሜ መጋቢት 28, 2011 ጀምሮ የተካሄደው እልቂት ነው። በሩዋንዳ የተከሰተውን የዜጎች የብሄር ተኮር እልቂት (Genocide) ሃያ አምስተኛ ዓመት እያስታወስን የጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ተምሳሌት በሆነችው ኢትዮጵያ የብሄር ተኮር እልቂት ሲካሄድ ማየታችን የኢትዮጵያ የፖለቲካና የአስተዳደር ሁኔታ ከፌደራልና ከክልል ባለሥልጣናት አቅም ውጭ መውጣቱን ያሳስበናል።

የጭካኔውን ጥልቀትና ስፋት ስንገመግመው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የዓለም ሕዝብ ቢሰማው የሚዘገንና የሚያሳፍር ድርጊት ነው። አጥፊዎቹ ከፍተኛ መሳሪያ ተጠቅመው፤ መሳሪያውን የተሸከሙ ተሽከርካሪዎችን ይዘው፤ አልሞ ተኳሽዎች፤ የወታደር ልብስ የለበሱ ልዩ ኃይሎች ኢላማ ያደረጓቸው የንጹህ ኢትዮጵያዊያንን ቤቶችና ንብረቶችን፤ የኢትዮጵያ ተዋህዶ ክርስትና ቤተከርስቲያኖችን ሲሆን፤ ንጹህ ሰርቶ አደር ነዋሪዎቹ በገፍ፤ በከባድ መሳሪያ፤ በጥይትና በቦምብ ተገድለዋል፤ ቆስለዋል፤ ቤትና ንብረታቸው ተደፍሮ ተዘርፏል። ነዋሪዎች ከቤታቸው እንዲሸሹ ተገደዋል። ይህ ግፍና በደል የደረሰባቸው ኢትዮጵያዊያን “ለመሆኑ መንግሥት አለ ወይ?” ብለው መጠየቃቸው ሕዝብን እያነጋገረ ነው።

ይዘቱ የተለያየ ቢሆንም፤ በንጹህ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን ላይ የሚካሄደው ግፍና በደል በቡራዩ፤ በጌድዮ፤ በጉጅ፤ በጎንደር፤ በለገጣፎ፤ በደሴና በሌሎች አካባቢዎች ተከስተዋል።

ኢትዮጵያ በሰላም ከቤት ወጥቶ በሰላም ለመመለስ ብርቅ የሆነባት አገር መሆኗ በጣም ያሳፍረናል። ግራ ያጋባል። ምን አይነት ሁኔታ ተፈጥሮ፤ ማን ተገን ሆኖ ነው እልቂቱ የተካሄደው? የዚህ አይነት አይን ያወጣ፤ ብሄርንና ኃይማኖትን ኢላማ ያደረገ ሽብርተኛነትና ጀሃዲስትነት ሊካሄድ የቻለው በምን ምክንያት ነው? ይህን ለመመለስ አንችልም።

በእኛ የአጭር ጊዜ ምርምርና ዘገባ መሰረት ግን፤ ይህ አደጋ ሕዝብ በራሱ ሕዝብ ላይ ያካሄደው እልቂት አይደለም።

ድርጅታችን ይህን በአገራችን ታሪክ ውስጥ ታይቶና ተሰምቶ የማይታወቅ ኢ-ሰብአዊ፤ የሚዘገንን፤ ጭካኔን፤ እብሪተኛነትን፤ ዘረኝነትን፤ ጠባብ ብሄርተኝነትን፤ ጽንፈኛነትን፤ ሽብርተኛነትንና ጅሃዲስትነት የሚያንጸባርቅ ድርጊት ሙሉ በሙሉ እናወግዛለን።

የዛሬይቱ ኢትዮጵያ የሚያስታውሰን የመን ወደ ውድቀት ከመሸጋገሯ በፊት የሆነውን ሁኔታ ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት በአስቸኳይ የችግሮቹን መሰረት (Systemic, Sttructural and Root Causes) ለመቅረፍ ካልቻለ ሁኔታው እየተባባሰ እንደሚሄድ እንገምታለን።

የዚህ አይነቱና ሌላ ተመሳሳይ ኢ-ሰብአዊ ድርጊት እንዳይደገም ጥሪ እናደርጋለን። በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ እልቂቱን ያመቻቹት፤ ሽፋን የሰጡቱና ያካሄዱት ግለሰቦች፤ ልዩ ኃሎችና ድርጅቶች ሳይውል ሳያድር ተይዘው በሃላፊነት በሕግ እንዲጠየቁ የኢትዮጵያን የክልልና የፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናት እናሳስባለን።

ኢትዮጵያ ሃገራችን ሰላማዊና ዲሞክራሳዊ ለውጥ እያካሄደች በምትገኝበት በአሁኑ ወቅት ይህን የመሰለ የእብሪተኞችና የጀሃዲስቶች እልቂት መካሄዱ ለኢትዮጵያ 110 ሚሊየን ሕዝብና ለአገሪቱ ሕልውና አስጊ መሆኑን እየጠቆምን፤ የዜጎች ደህንነት፤ ሰብአዊና ዲሞክራሳዊ መብት፤ ሰላምና እርጋታ በአስቸኳይ ከፍተኛ ትኩረት እንዲሰጣቸው እንጠይቃለን።

በዚህ አጋጣሚ ዛሬም ሆን ከዚህ በፊት በየአካባቢው ያልተቆጠበ ጥረት ላደረጉት ሁሉ ከፍተኛ ምስጋና እናቀርባለን። ዛሬም እንደ ትላንቱ ለወገኖቻችን እንድረስላቸው ለሚሉትና ለሌሎች ጥሪ የምናደርገው በያላችሁበት የገንዘብ መሰብሰብ ጥረቱን እንድትቀጥሉበት፤ ያልጀመራችሁ እንድትጀምሩና ላልሰሙት እንድታሰሙ አደራ እንላለን።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

የኢትዮጵያ ሕዝብ ብሄራዊ አንድነት ይለምልም!

ከአክብሮትና ከሰላምታ ጋር

ታማኝ በየነ፤ ፕሬዝደንት ከታላቅ አክብሮት ጋር

Filed in: Amharic