>

የዶ/ር አቢይ መንግስት አቢይ ችግር?!? ( አፈንዲ ሙተቂ)

የዶ/ር አቢይ መንግስት አቢይ ችግር?!?
አፈንዲ ሙተቂ
የዚህ መንግስት ዐቢይ ችግር በህዝብ የተመረጠ መንግስት በምርጫ እስኪተካው ድረስ ሀገሪቷን ወደ ዲሞክራሲያዊ ምዕራፍ ለማሸጋገር የተመሠረተ የባለ አደራ መንግስት መሆኑን መዘንጋቱ ነው። ይህ መንግስት የተመረጠው በኢህአዴግ ምክር ቤት ምርጫ እንጂ ኢትዮጵያዊያን በተሳተፉበት ህዝባዊ ምርጫ አይደለም።  የዚህ መንግስት አጣዳፊ ስራዎች መሆን የነበሩባቸው
1 ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የሚያስፈልጉ ተቋማትን መገንባት
2 የሀገሪቷን የዲሞክራሲ ጉዞ ሰንገው የያዙ ህጎችና መሻርና ማሻሻል
3 ፓርቲና መንግስትን ሙሉ በሙሉ መለያየት (ይህ ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። እስከ አሁኗ ሰዓት ድረስ በድርጅት ጽ/ቤት የተመደቡ ሰዎች እንደ መንግስት ሰራተኛ ደመወዝ እየተከፈላቸው ነው። እንዲህ ዓይነቱ አሰራር ከማዕከል እስከ ወረዳ ድረስ ስሩን ሰዷል። ይህ ዐይን ያወጣ ወንጀል ነው)።
4 በመንግስት ጫና የተመሠረቱ ህዝባዊ ማህበሮችን (ለምሳሌ ኦልማ፣ የወጣቶች ማህበር፣ የሴቶች ማህበር) ከመንግስት ተፅእኖ ነፃ ማድረግ
5 የዳኝነትና የፍትሕ ስርዓቱን ከመንግስት ተፅእኖ ነፃ ማድረግ
6 የምርጫ ህጉንና የምርጫ ስርዓቱን ማሻሻል
7 የጸጥታ አካላት ህጋዊነትን በተላበሰ ሁኔታ ህዝቡን እንዲያገለግሉ ማድረግ
8 ያለፉት ስርዓቶች በረጩት መርዝ ሳቢያ በተቋሰሉ ህዝቦች መካከል እርቀ ሰላምን መፍጠር
9 ህዝብን ሲገድሉ፣ ሲዘርፉ፣ ሲገርፉና ሲያፈናቅሉ የኖሩ ባለስልጣናትንና የፀጥታ አካላትን ለፍርድ ማቅረብ
10 ተፎካካሪ ፓርቲዎች በሁሉም ስፍራ በነፃነት የሚንቀሳቀሱበትን ሁኔታ ማመቻቸት
11 በህዝባዊ ትግሉ ሳቢያ ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን ማቋቋም
12 ህገ ወጥ ታጣቂዎች በክልሎችና ድንበር አቅራቢያ በሚኖሩ ህዝቦች ላይ የሚፈፅሙትን ጥቃት ማስቆም
13 ወዘተ
—-
ባለፈው አንድ ዓመት እንዳየነው ከሆነ የዶክተር አቢይ መንግስት እነዚህን ትልልቅ ተግባራት መስራቱን ዘንግቷል። ከእነርሱ ይልቅ ለጊዜያዊ ታይታና ጭብጨባ ብቻ የሚመቹ ስራዎችን ማጧጧፉን ቀጥሎበታል። ውጤቱ ግን የትም የሚያስኬድ አልሆነም። በተቃራኒው ከሁለቱ ታላላቅ ብሄሮቻችን (ኦሮሞና አማራ) በወጡ ታጋዮችና ወጣቶች መካከል ተፈጥሮ የነበረውን የትግል አንድነት ድምጥማጡን አጥፍቶታል። በነሐሴ መጀመሪያ ላይ OMN በሚሊኒየም አዳራሽ ባዘጋጀው ዝግጅት ላይ የተገኙት ተወዳጁ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ንግግር ሲያደርጉ ህዝቡ “ይደገም! ይደገም! ይደገም” እያለ ነበር ንግግራቸውን የተከታተለው። አሁን ግን ያ ሁሉ ተረት ሆኖ ቀርቷል።
እስቲ ሁለት ጊዜ የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችን እያፈረሱ ማዋቀር ምን ይባላል? የአዲስ አበባ የወንዞች ተፋሰስ ግንባታ እራት ስነ ስርዓትስ ምንድነው? “ኦነግን ትጥቅ ማስፈታት ቀዳሚ ስራዬ ነው” እያሉ በእርሱ ላይ ብቻ አምስት ወር መፍጀትስ? የማስተር ፕላኑ ጣጣ ሳይፈታ ኮንዶሚኒየም ለማከፋፈል መሞከርስ? የድንበርና የማንነት ኮሚሽን የተባለ አጨቃጫቂ መስራ ቤት አቋቁሞ ለንትርክ ህዝቡን መጋበዝስ? ተቃዋሚ ፓርቲዎች ራሳቸውን ችለው በህዝቡ ውስጥ በመንቀሳቀስ መዋቅራቸውን እንዲያደራጁ እንደመደገፍ በየጊዜው ከፓርቲዎች ጋር ኮንፈረንስ መቀመጥስ?
ይህ መንግስት በዲፕሎማሲው ዘርፍ ጥሩ ስራ ሰርቷል። በሌላው ዘርፍ ግን እስከዚህም ነው። ለዚህ ዋነኛው ምክንያቱ ደግሞ አንድ የባለ አደራ መንግስት መስራት ያለባቸውን ዋነኛ ስራዎች መዘንጋቱ ነው። ስለዚህ ወደ መነሻው ተመልሶ በተቀሩት ወራት ውጤታማ ስራ እንዲሰራ በአክብሮት እንጠይቃለን።
በሌላ በኩል ህብረተሰቡም ለትንሽ ከትልቁ ጉዳይ ሁሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲያነጋግረው መጨቅጨቁ ተገቢ አይደለም። የሃይማኖት መማክርት ጉባኤ፣ የወጣት ማህበራት ምክር ቤት፣ የቢዝነስ ማህበረሰብ በየጊዜው ከጠቅላዩ ጋር ስብሰባ መጥራታቸው መንግስት ከላይ በተገለፁት ስራዎች ላይ እንዳያተኩር አድርገውታል። ይህ ልማድ ከዚህ በኋላ መቀነስ አለበት። እንደዚሁም ደግሞ አክቲቪስት ተብዬዎች ከላይ የተጠቀሱት ዐቢይ ስራዎች እንዲፈፀሙ መጠየቁን ትተው በየቀኑ “እስክንድር ነጋ፣ ባልደራስ፣ ፊንፊኔ” የሚል የቸከ ፖለቲካ ላይ ሙዝዝ በማለት ተወዳጅነትን ለማትረፍ የሚሞክሩበትን አካሄድ ቢቀይሩት ይሻላቸዋል።
Filed in: Amharic