>
5:13 pm - Friday April 19, 0813

የአብይ አህመድ አስተዳደር የአንድ ዓመት ጉዞና ፈተናዎቹ (አበጋዝ ወንድሙ)

የአብይ አህመድ አስተዳደር የአንድ ዓመት ጉዞና ፈተናዎቹ

አበጋዝ ወንድሙ

ከአስራ ሶስት ወራት በፊት ማንም ባልጠበቀውና ባላሰበው መንገድ ኢትዮጵያ የለውጥ ተስፋ የታየበት ጉዞ ጀምራለች። ይሄን ለውጥ ደግሞ ልዩ የሚያደርገው ፣ የለውጡ ተዋንያን ኢትዮጵያን ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት አምባገነናዊ ስርዓት ገንብቶ መከራዋን ሲያበላት ከነበረው ኢህአዴግ ጉያ ውስጥ የወጡ አባላት መሆናቸው ነው።

ይሄም በመሆኑ ሀገራችን የምታስተናግደው ለውጥ ምን ዓይነት ለውጥ ነው? ለውጡስ ምን ያህል ድረስ
የሚዘልቅ ነው? ለአመታት የተከማቹትን የህዝብ ጥያቄዎችስ በበቂ ሁኔታ ሊመልስ ይችላል ወይ… ወዘተ የሚሉ
በርካታ ጥያቄዎችም በወቅቱ የተነሱ ጥያቄዎች ነበሩ።

ራሱን የለውጥ ሃይል መሪ አድርጎ የሚያየው የአብይ አህመድ አስተዳደር እነሆ አንድ ዓመት ሞልቶታልና ስልጣን
ላይ ሲወጣ ከነበሩ ጥያቄዎች አንጻር እንዴት ሊገመገም ይገባል በሚል ዳሰሳ ማድረግ የሚቻልበት ጊዜ
ነው።የአንድ አመቱን የስራ ይዘትና የለውጡን ሂደት አስመልክቶም በርካታ ሰዎች የሚመስላቸውን ግምገማ
ያካሄዱ ቢሆንም ፣ በኔ እይታ አብዛኛዎቹ የተካሄዱት ግምግማዎች ክፍተት አላቸው ብዬ በማመን የበኩሌን
ምልከታ ላቀርብ ወደድኩ ።

የዛሬ ዓመት አብይ አህመድ የለውጥ ሃይሉ መሪ ሆኖ ብቅ ማለት ፣ በተወሰኑ ክፍሎች አምላክ ኢትዮጵያን
ለመታደግ ከሰማይ የላከው እስከሚል ጥግ ድረስ ሲንቆለጳጰስ የነበረውን ያህል ፣ ዘንድሮ ደግሞ በአንዳንድ
ወገኖች ‘አፉ ቅቤ ልቡ ጩቤ’ ሆኖ ዓመት ሙሉ ድብቅ አጀንዳ ይዞ ሲያሞኘንና ሲያታልለን ከርሟል እስከመባል
ደርሷል ።

ከዚያ መለስ ሲል ደግሞ ተቀባይነቱ እየቀነሰ ወይንም እያሽቆለቆለ ነው የሚሉ፣ ሆኖም ይሄ ድምዳሜ መቼና የት
በተደረግ ጥናት የተገኘ ግኝት እንደሆነ በማይገልጹ ወገኖች የሚሰማ ሲሆን፣ ከእድሜና የስራ ልምድ የተገኘ
አስተዋይነት ሳይሆን ድፍረት ብቻ ያላቸው ደግሞ ለሀገር የሚበጀው አሁኑኑ ስራውን ቢለቅ ነው እስከማለትም
የደረሱ አሉ።

በተቃራኒው ወገን ደግሞ ጥፋት ወይንም ስህተት መስራቱን ከነጭራሹ የሚክዱና፣ አብይን አይነኬ አድርገው ደግ
ደጉን ብቻ መመልከት ከሚሹ፣ እስከ ስህተትና ጥፋት መስራቱን አምነውና ተቀብለው ሲያበቁ ደግሞ ፣ የአብይን
አስተዳደር በአሁኑ ጊዜ መንቀፍ ፣ ለውጡን ማደናቀፍ በመሆኑ ዝምታ መመረጥ አለበት የሚል የሞኝ ፈሊጥ
የሚያራምዱ ወገኞችም አሉ።

አስከፊው የህወሃት/ኢህአዴግ የ 27 ዓመት አገዛዝ ዜጎችን አስመርሮ ፣ ዜጎችም፣ ግፉ ከሚሸከሙት በላይ
በመሆኑ ስድስት አመታት ያህል፣ በኢትዮጵያ ሙስሊሞች ትግል ተጀምሮ ፣ በኮንሶ ፣ በኦሮሚያ ብሎም በአማራ
ክልል የተካሄዱት ትግሎች፣ መላ ሀገሪቱን አጥለቅልቀው አገዛዙን ማንገዳገዳቸውን እንደማንቂያ ደወል
በመጠቀም፣ የለማ ቡድን የሚባለው ስብስብ፣የዛሬ አመት በኢህአዴግ ውስጥ ተደራጅቶ፣ ህዝባዊ እንቢተኝነቱን
እንደ ምርኩዝ በመጠቀም፣ ድርጅቱን በበላይነት የሚያሽከረክረውን ህወሃትን ገፍትሮ አብይ አህመድን ለስልጣን
ሊያበቃ ችሏል።

የለማ ቡድንም ሆነ አብይ ኢህአዴጋውያን መሆናቸውን ላፍታም እንኳን ያልረሳው ህዝብ ፣ በኢህአዴግ ውስጥም
ቢሆን የህወሃት የበላይነት መከርከምን ፣ ለሃገር፣ በራሱ እንደ በጎ ኩነት በመቁጠር የተደረገውን የአስተዳደር
ለውጥ በመልካም ጎኑ እንዲመለከተውና የተስፋ ጭላንጭል እንዲያይበት አድርጓል።

ከዚህም በላይ ደግሞ ፣መጋቢት 18 የኢህአዴግ ሊቀመንበር ሆኖ የተመረጠው አብይ አህመድ ፣ በድርጅቱ
የተለምዶ አሰራር የጠቅላይ ምኒስትር እንዲሆን በመወሰኑ፣ ፓርላማ ቀርቦ ሹመቱ በጸደቀለት ቀን ባደረገው
መሳጭ፣ የድርጅቱን ስህተት ተቀብሎ፣ የኢትዮጵያን ህዝብ ይቅርታ የጠየቀ ፣ ለ እርምት የተዘጋጀ፣ አስታራቂና
ጋባዥ ንግግሩ የአብዛኛውን የኢትዮጵያ ህዝብ ቀልብ መሳብ ከመቻሉም በላይ፣ በቀጣይም ሊያደርግ ላሰባቸው
ተግባራት ትልቅ ህዝባዊ የድጋፍ ምንጭ የሚሆን ስንቅ ጭምርም ያገኘበት ወቅት ነበር።

በሀገራችን ባለፈው ዓመት የተከናወኑ እጅግ በርካታ በጎ ነገሮች ፣ ማለትም በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ፣ የፖለቲካ
እስረኞች መፈታት፣ በግፍ የታሰሩ ጋዜጠኞችና ሌሎችም መፈታታቸው፣ በስደት የነበሩ ተቃዋሚዎች ወደ ሀገራቸው

ገብተው በሰላማዊ መንገድ ትግላቸውን እንዲያካሂዱ መጋበዝ… ወዘተ እና በተቋማዊ ደረጃ ልዩ ልዩ መስሪያ
ቤቶች ላይ የተካሄዱ ማሻሻያዎች፣ አፋኝ ህጎችን ለማስተካከል የተወሰዱ እርምጃዎች፣ በዋናነት ደግሞ እጅግ ጠቦ፣
መኖሩ አጠራጣሪ የነበረውን የፖለቲካ ምህዳር ማስፋት፣ ከጎረቤት ኤርትራ ጋር የበጎ ግንኙነት ጅምር… ወዘተ
ማናችንም በዚህ እጅግ አጭር ጊዜ ውስጥ ዕውን ይሆናሉ ብለን ከጠበቅናቸው በላይ የነበሩ እርምጃዎች
እንደነበሩ መቀበል ይኖርብናል ።

እነዚህን በጎ ነገሮች መቀበል ማለት ግን የተሰሩ ስህተቶች አልነበሩም፣ እነዚህም ማስተካከያና እርምት
እንዲደረግባቸው መንግስት ላይ ጫና ከማድረግ መቆጠብ አለብን ማለት እናዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል። ዋናው
ጉዳይ የአመቱን ተግባራት ስንገመግም ሚዛናዊ የመሆን ሃላፊነት እንዳለብን መገንዘብ ነው።

በዚህ ግምገማችን ላይ መዘንጋት የሌለበን የ አብይ የአንድ ዓመት የአስተዳደር ዘመን የሚለካውና የሚገመገመው
፣ ማናችንም በምንፈጥረው የተለየ መስፈርት ሳይሆን ፣ አብይ ስልጣኑን ሲረከብ በገባው ቃልና ፣ ቃሉን
ተግባራዊ ለማድረግ የወሰዳቸው እርምጃዎች ከቃሉ ጋር ምን ያህል እንደሚጣጣሙ በማስላት እንጂ ፣ እኛ አብይ
ያደርገዋል ብለን ከጠበቅነው ወይንም ማድረግ ነበረበት ብለን ከምናስበው በመነሳት ከሚለው ሊሆን አይገባም።
አብይ ፓርላማው ሹመቱን ባጸደቀበት ቀን ከሀይለማርያም እጅ ህገመንግስቱ የሰፈረበትን ማህደር ተቀብሎና
ከትከሻው ከፍ አድርጎ በማንሳት ለፓርላማ አባላቱ ሲያሳይና ቃል ኪዳኑንም የፈጸመው፣ በስራ ላይ ላለው
ህገመንግስት ታማኝነቱን በመግለጽና ለተግባራዊነቱም ጠንክሮ እንደሚሰራ በመናገር ጭምር እንደነበር
ማስታወሱም ፣ በየስፍራው ጎልተው የሚታዩ ወቀሳዎችን ሚዛናዊነት ለማየት ይረዳል።

ይሄንን ከላይ የተጠቀሰውን ታሳቢ ማድረግም ‘ክልሎችን አስካሁን ለምን አላፈረሰም ወይንም ማፍረስ ነበረበት
ወይንም አለበት፣ ህገመንግስቱን አሽቀንጥሮ ጥሎ ሌላ አዲስ ህገመንግስት መረቀቅ ይኖርብርታል…. ወዘተ’
ጥያቄዎች በአሁኑ ወቅት ስፍራ እንደሌላቸው እንድንገነዘብ ይረዳል።

ክልላዊ አደረጃጀት ለሀገራችን አይበጅም ፣ መለወጥም አለበት፣ ህገመንግስቱም መቀየር ይኖርበታል ብለው
የሚያስቡ ወገኖች ያላቸው አማራጭ ተደራጅተውና ህዝብን አሳምነው መጪውን ምርጫ በማሸነፍ፣ የመንግስት
ስልጣን ከተረከቡ በዃላ የሚከውኑት ተግባር እንጅ ፣ የኢህአዴጉ ሊቀ መንበር አብይ በአዋጅ እንዲያደርገው
የሚጠብቁት ሊሆን አይችልም ብቻ ሳይሆን፣ የሱም ሆነ የድርጅቱ ፍላጎት ነውም ለማለት እንኳን አስቸጋሪ ነው።
የአመቱን ጉዞ አስመልክቶ አንዳንድ ችግሮች የፍትህ ስርዓቱን አስመልክቶ ፣ የገፍ እስር ባይኖርም፣ከእንግዲህ ሰው አስሮ ማስረጃ መፈለግ ሳይሆን ፣ ማስረጃ ከተሰበሰበ በዃላ ፍርድ እንመሰርታለን የተባለው ቃል በተደጋጋሚ ተግባራዊ አለመሆን፣ ለወጣቱ ይሄ ነው የሚባል የስራ እድል ፈጠራ አለመታየቱ ፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መዳከም፣ ግልጽነት የጎደለው የስራ አመዳደብ (በአጭር ጊዜ ውስጥ ሹም ሽር ማካሄድ ፣ በሥራ ልምድና ብቃት ሳይሆን ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ባላቸው ገጽታ
ወይንም ተሰሚነት አላቸው ከሚል በመነሳት በሚመስል መልኩ የሚሾሙ ሹሞች) ፣ ፖሊስን ጨምሮ የጸጥታ
አካላትና በርካታ የመንግስት መስሪያ ቤት ሃላፊዎች የሚያሳዩት ዳተኝነት… ወዘተ ባለፈው ዓመት የታዩ ግልጽ
ጉድለቶች ነበሩ።

ከዚህ በተጨማሪ፣በውጭ ይኖሩ የነበሩ ተቃዋሚዎች ሃገር ገብተው በሰላማዊ መንገድ ትግላቸውን እንዲያካሂዱ
መንገዱን ማመቻቸት ተገቢ የነበረ ቢሆንም፣ ቅጥ ያጣው አቀባበልና አላስፈላጊ ጋጋታ፣ በሀገር ቤት የነበረውን
ህዝባዊ ትግሉን አስመልክቶ የረባ አስተዋጽኦ ያላደረጉ ሁሉ እብጠት እንዲሰማቸው ያደረገ ብቻ ሳይሆን የሹም ዶሮ
ነን እስከ ማለትም አድርሷቸዋል ። (መንግስት አስካሁን ግልጽ ባለማድረጉም ለነዚህ ግለሰቦችና ቡድኖች የሆቴል
ምግብና ጥበቃ ምን ያህል ወጭ እንደጠየቀ የምናውቀውም የለም ብቻ ሳይሆን ፣ እስካሁን ቀጥሎም ከሆነ ግን
በአፋጣኝ ተቋርጦ የእስከዛሬውም ወጭ ለህዝብ ይፋ መሆን ይኖርበታል። )

በርካታ ሊስተካከሉ የሚገባቸው መሰል ችግሮች ቢኖሩም ፣ በኔ እምነት የአብይ አስተዳደር ትልቅ ድክመት
የህዝብን ሰላምና መረጋገት በሚመለክት ያሳየው ደካማ አካሄድ ነው ። ይሄ ሰላምና መረጋጋት በአንዳንድ
የሀገራችን ክፍል ( በተለይ ምዕራብ ወለጋና ጉጂ ዞን) የተደራጁና በኦነግ ስምና አርማ የሚንቀሳቀሱ

አንጃዎች(አዲስ አበባ ያለው አመራር አንዳንዶቹን የኔ አይደሉም ሲል ፣ ሌሎቹ ደግሞ አመራሩን አንቀበለውም
በራሳችን ነው የምንቀሳቀስ የሚሉ) በሰላማዊ ህዝብ ላይ የሚያደርጉት ጥቃት፣ ሌሎች የተደራጁ ቡድኖች
ወይንም የመንደር ወሮበሎች ዜጎችን ከቀዬአቸው ማፈናቀል፣ ማሰደድ ለረሃብና ችግር መዳረግ፣በየስፍራው ያሉ
የመንደር ወሮበሎች በተቃውሞ ሰልፍ ስም እህልና መሰል ቁሳቁሶች ከአንድ ክልል ወደ ሌላ እንዳይጓጓዝ ለቀናት
ወይንም ሳምንታት፣ አንዳንድ ስፍራ ለወራትም ጭምር መንገድ መዝጋት፣ ብሎም ለህዝብ ለማደል በሚል ዘረፋ
ማካሄድን ያጠቃልላል።

እርግጥ ነው ፣ ከ 1.5 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ወገኖቻችን አብይ ስልጣን ላይ ከመውጣቱ በፊት ተፈናቅለው የነበረ
ቢሆንም ያንኑ ያህል ወገኖች ደግሞ ባለፈው አመት መፈናቀል ዕጣ ፈንታቸው እንዲሆን ተገደዋል። በሚሊዮኖች
የሚቆጠሩ ወገኖች በእንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ መሆን በቶሎ መቋጫ ካልተገኘለት ፣ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር፣
ልማትና እድገት ይቅርና ለሀገር ህልውና ትልቅ አደጋ ሊሆን ይችላል። ይሄም በመሆኑ መንግስት ችግሩን ማደባበስ፣
ይባስ ብሎም አላየንም ወይንም አልሰማንም ማለት ሳይሆን፣ ነገ ዛሬ ሳይል በቁርጠኝነት ቅድሚያ ሰጥቶት ትልቅ
ርብርቦሽና ክትትል ተደርጎ አስፈላጊውን እርምጃ በመውሰድ እንዲከስም ማድረግ ያለበት ጉዳይ ነው።

ይሄን መሰል አለመረጋጋቶች በተወሰነ ደረጃ የአስተዳደር ለውጥ በሚካሄድበት ወቅት በሚኖረው ክፍተት ወይንም
ነገሮች እስኪረጋጉ የሚያጋጥሙ ቢሆንም፣ በኛ ሀገር የሚሆን ያለው ግን ሆን ብሎ የተቀነባበረ ፣ መንግስት
የሚጠበቅበትን ተግባር ከማከናወን ይልቅ፣ እንደ እሳት አደጋ ተከላካይ በየቦታው የሚጭሩትን እሳት ለማጥፋት
እንዲሯሯጥ በማድረግ ከህዝብ አግኝቶት የነበረውን ተቀባይነት ለማሳጣት እንደሆነ ግልጽ ነው።

በኔ ግምት በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የሚካሄዱት እነዚህ አለመረጋጋቶች ቆስቋሾችና አቀጣጣዮች በኢህአዴግ
መዋቅር ውስጥ ያሉና ከቀበሌ እስከ ወረዳና ክልል የተደራጁ ፣ የለማ ቡድን የለውጥ ኃይል ሆኖ ብቅ ማለትና የ
አብይ ጠቅላይ ሚንስቴር ሆኖ መሾም ስልጣናቸውን የነጠቃቸው ወይንም ስልጣናችንን እናጣለን ብለው
የገመቱና የሰጉ ቡድኖች ተቀናጅተው የሚያካሂዱት ይመስለኛል።

ይሄም በመሆኑ ጽዳት ከቤት ነውና የሚጀምረው በመዋቅሩ ውስጥ ተሰግስገው ፣ እንደከዚህ ቀደሙ ህዝብን
በማሰቃየትና በማንገላታት የተሰማሩትን ፣ህዝብ ለለውጥ ይዞት የነበረውን ተስፋ በማጨለም ላይ ያሉ አባላት
ጠርጎ ማውጣት፣ በፍጥነት መካሄድ ይኖርበታል።

ህዝብ ላይ እንዲህ ያለ መጠነ ሰፊ ጥቃት ከመድረሱ በፊት ነቅቶ መከላከል የመንግስት ሃላፊነት ሲሆን ፣ ከሆነም
በዃላ ሳይባባስ ህዝብን ከጉዳት መከላከል በትዕግስት ስም የሚታለፍ ወይንም ቸል የሚባል ሊሆን አይገባም ፣
ህዝብ በመንግስት ላይ ያለውን ዕምነት ይሸረሽራልና !

የአብይ አስተዳድር ያለፈው ዓመት ጉዞ ለሀገራችን በርካታ መልካም ነገሮችን ያጎናጸፈ በመሆኑ ሊመሰገን
የሚገባው ሲሆን፣ በቀጣይ ዓመት ደግሞ የሰራቸው ጉልህ ስህተቶች ላይ እርምት በማድረግ፣ መልካም ነገሮችን
ማጎልበቱን ቀጥሎ በዋናነት ግን የተናጋውን የህዝብ ሰላምና መረጋጋትን አስመልክቶ ቁርጠኛ እርምጃዎች
በመውሰድ የዜጎችን ሰላም በማስጠበቅ፣ የዛሬ ዓመት የፈነጠቀው የተስፋ ጭላንጭል የበለጠ ብሩህ አንዲሆን
የሚያስችሉ ተግባራት ላይ አትኩሮት ሰጥቶ ሊንቀሳቀስ ይገባዋል።

Filed in: Amharic