>

የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት( ባልደራስ) ጋዜጣዊ መግለጫ:- የጋጥ ወጦች ድርጊት ትግላችንን እንድናጠናክር ያደርገናል እንጂ አያስቆመንም!!!

የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት( ባልደራስ) ጋዜጣዊ መግለጫ

 

የጋጥ ወጦች ድርጊት ትግላችንን እንድናጠናክር ያደርገናል እንጂ አያስቆመንም!!!

  የአዲስ አበባ በለአደራ ምክር ቤት ከህዝብ የተሰጠውን ተልዕኮ ለማስፈፀም ላለፉት 35 ቀናት ደፋ ቀና እያለ ይገኛል፡፡ በዚህ ጊዜ 3  ህዝባዊ ስብሰባዎችና አንድ ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት ሞክሮ፣ ሁሉም በአዲስ አበባ መስተዳድር ተፅዕኖ ተደርጎባቸው፣ ሁለቱን ለመሰረዝ ተገዷል፡፡
አንዱ ጋዜጣዊ መግለጫም ቢሆን፣ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅም መልኩ ክልከላ ተደርጎበታል፡፡
ይህ ሁሉ መንግስታዊ ህገ ወጥነት አግባብ እንዳልሆነ፣ የምክር ቤቱ ሰብሳቢና ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ በተገናኙበት ጊዜ ተማምነውዋል፤ በቀጣይነትም፣ መስተዳድሩ ከህገ ወጥ ተግባራቱ ተቆጥቦ ህዝባዊ ስብሰባዎች ያለምንም ተፅዕኖ እንዲደረጉ ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር፡፡
ይህ ስምምነት ሰኞ ዕለት ተደርሶ፣ በማግስቱ፣ ማክሰኞ፣ ለመስተዳድሩ በገባ ደብዳቤ፣ በቀጣዩ ቅዳሜ ሚያዚያ 5/2011 ዓ.ም በ24/መገናኛ በሚገኘው ኮከብ አዳራሽ የቦሌና አቃቂ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ህዝባዊ ስብሰባ ለማድረግ እቅድ መያዙን፣ ለዚህም የፖሊስ ጥበቃ እንዲደረግ ተጠይቋል፡፡  ሆኖም፣ እስከ ዓርብ ድረስ የመስተዳድሩ ምላሽ በመጥፋቱ፣ ለራሳቸው ለምክትል ከንቲባው በቴክስት እንዲያውቁት  ተደርጓል፡፡  በመጨረሻም፣ ዓርብ ዕለት በተሰጠ የቃል ምላሽ፣ በህጉ መሰረት ስብሰባ ለማድረግ እንደ ማይከለከል፣ የፖሊስ ጥበቃ ለማድረግ ግን መስተዳድሩ ፈቃደኛ አለመሆኑ ተገልጿል፡፡
በዚህ ተስፋ ባለመቁረጥ፣ ስብሰባውን በራሳችን ኃይል እያስጠበቅን ለማከናወን ወስነን በቦታው ላይ የተገኘን ቢሆንም፣ ስብሰባው ከመጀመሩ በፊት በመኪና ተጭነው የመጡ ኦሮምኛ ተናጋሪ ወጣቶች፣ በቡድን በቡድን ተደራጅተው በአካባቢው ከመሰማራታቸውም በላይ፣ ወደ ስብሰባው አዳራሽ በመምጣት ሁከት ለመቀስቀስ ሞክረዋል፡፡ ይህንን ለፖሊስ ብናሳውቅም፣ በመጨረሻ ላይ፣ “ጥበቃ አይደረግላችሁም” የሚል እጅግ አሳፋሪና ኃላፊነት የጎደለው ምላሽ ተሰጥቶናል፡፡ በዚህ የጋጥ ወጦች ስልት ስብሰባ እንዳናደርግ በእጅ አዙር ጋሪጣ ተደቅኖብን፣ ራሳችንን ለመከላከል በቂ ኃይል ቢኖረንም፣  የህዝብ ደህንነትንና የሀገረን ሰላም በማስቀደም ስብሰባውን ሰርዘናል፡፡
እንደዚህ ዓይነቱ ጋጥ ወጥ አካሄድ፣ በባለአንጣነት እየተፈረጀ ላለው ለአዲስ አበባ ህዝብ ብቻ ሳይሆን፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለተጀመረው የዲሞክራሲ ሽግግር አደገኛ በመሆኑ፣ አስቸኳይ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድ አጥበቀን እንጠይቃለን፡፡
ማሳሰቢያ
የማስተካከያው እርምጃ ቢወሰድም ባይወሰድም ግን፣ ሰላማዊ ትግላችን ከመቼውም ጊዜ በላይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ለወዳጆቻችንም ሆነ ለተቀናቃኞቻችን ማሳሰብ እንወዳለን፡፡ ቁርጠኝነታችንንም በቀጣይነት በምንወስዳቸው ሰላማዊ የተግባር እርምጃዎች እናሳያለን፡፡
የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት
Filed in: Amharic