>
5:13 pm - Thursday April 19, 4903

የለማ መገርሳን ቁጣ (ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም)


የለማ መገርሳን ቁጣ

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም

አንዳንድ ሰዎች እንደፖሊቲከኛ ትርኢት አይተውታል፤ ያለቀሱም አጋጥመውኛል፤ እኔ እንባዬ ጠብ አላለም አንጂ በዓይኔ ላይ አቅርሮ ነበር፤ ይህ ሁኔታ እጅግም አያስደንቅም፤ ኢትዮጵያውያን ስሜታውያን ነን፤ የኔም እንባ ተንጠልጥሎ የቀረበት ምክንያት አእምሮዬ ጥያቄዎችን አጎረፈልኝ፡፡

በተደጋጋሚ የሰማኋቸውን ልግለጽ፡

• ለማ መገርሳ ብዙ ሺህ ኦሮሞዎችን በአዲስ አበባ አስፍሯል፤
• በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኦሮሞዎች የአዲስ አበባ መታወቂያ እየተሰቸጣው ነው፤
• ኦሮሞዎች እየተመረጡ ኮንዶሚኒየም (ቤት) ተሰጣቸው፤

እንድንግባባ በትክክል ሦስቱም ድርጊቶች መሆን ወይም አለመሆናቸው አንድ ነገር ነው፤ በኢትዮጵያ ዜጋዎች መሀከል በጎሣ ልዩነት የተነሣ አድልዎ መፈጸሙ ሌላ ነገር ነው፤ ሰዎችን ከቦታ ወደቦታ ማዘዋወሩ ብቻውን ወንጀል ሊሆን አይችልም፤ በተለያዩ ምክንያቶች በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመንም፣ በደርግ ዘመንም ተደርጓል፤ አሁን ተደረገ ለተባለው ምክንያቱ ሌላ ሳይሆን በጎሠኛነት ላይ ለተመሠረተ ምርጫ መዘጋጀት ነው፤እንዲህ ከሆነ የኢትዮጵያን ፖሊቲካ ብቻ ሳይሆን ጨዋነታችንንም የሚያራቁት ድርጊት ነው፤ ግን ድርጊቱ መፈጸሙን ወይም አለመፈጸሙን በትክክል አናውቅም፤ ድርጊቱ ቢፈጸምም እውነተኛውን ምክንያት አናውቅም፤ በዚህ ምክንያት ነው ለማ መገርሳን ማስተባበል አስቸጋሪ የሚሆነው፤ ለማስተባበል የሞከሩ ብዙ ሰዎች አሉ፤ ነገር ግን በእኔ አስተያየት ከአሉባልታ የወጡ አይመስለኝም፡፡

አንድ ሰው በተለይ ዙሪያውን የተከበበበትን ጋሬጣ ሁሉ በጣጥሶ፣ የወያኔን ጭካኔ ተጋፍጦ፣ በአደባባይ በስብሰባ ላይ ለወያኔ ባለሥልጣኖች ልካቸውን የነገራቸውና የሀያ ሰባት ዓመቱን አፈና የደረመሰው ሰው እንደዚህ ምርር ብሎት ሲናገር ያሳዝናል፤ በጣም ያሳዝናል፤ የወያኔ ባለሥልጣኖችን ልብ አፍርሶ፣ ሐሞታቸውን አፍስሶ ፊታቸውን ጥቀርሻ ያለበሰው ሰው ሲያዝን ያሳዝናል፤ በስብሰባው ላይ ሲናገር ያስደሰተኝ በኢትዮጵያዊነቱ ነው እንጂ በኦሮሞነቱ አልነበረም፤ ሲያዝንም ያሳዘነኝ በኢትዮጵያዊነቱ ነው፤ በወያኔ ስብሰባ ላይ ሲናገርም ሆነ አሁን አዝኖ ሲናገር እሱንና እኔን ያያዘን ትልቁ የኢትዮጵያዊነት ገመድ ነው፤ ሁለቱንም ጊዜ የተሰማኝ ኢትዮጵያዊነቱ ነው፤ ከተሳሰርንበት ገመድ ወጥቼ ከምጠራጠረው ገመዱ ውስጥ ሆኜ አምኜው ብሳሳት ይሻለኛል፡፡

አጼ ኃይለ ሥላሴን ከዙፋናቸው ያወረዳቸው ማነው? የራሳቸው ሎሌዎች ናቸው፤ ሎሌዎቹ ራሳቸውን ነጻ አወጡና ጌቶች ሆኑ! ዓቢይና ለማም የወያኔ ሎሌዎች ነበሩ፤ ዛሬ ጌቶች ሆነዋል? አዝማሚያው የለም አልልም! የኢትዮጵያ ሕዝብ በሆነውና ባልሆነው እልል እያለና እያጨበጨበ ባለሥልጣኖችን ያባልጋል፤ ዓቢይ በእስክንድር ላይ የወረወረው ዛቻ ይህንን የሚያመለክት ነው፤ የእስክንድር ስሕተት እንዳለ ሆኖ፤ መሣሪያ የያዘ ሰው መሣሪያ በሌለው ላይ ጉልበተኛነቱን ሲያውጅ ዴሞክራሲ ዘሩ ይጠፋል፤ ዓቢይ ያየውን አደጋ እኔም አይቼዋለሁ፤ ጉልበት ያለው የተሻለ ዘዴ ለመፈለግ ጊዜውም ዝንባሌውም የለውም፤ ሕግ፣ ማንንም የማይምር ሕግና ልብ ብሎ የሚታዘብ ሕዝብ ሲኖር ጉልበት ዋጋ አይኖረውም::
ዓቢይና ለማ በአማርኛ ሲናገሩ የምንሰማው ጠንካራ ኢትዮጵያዊነት በኦሮምኛ ሲናገሩ በእኔው ድንቁርና ምክንያት አልሰማምና አስተያየት መስጠት አልችልም፤ ነገር ግን ስገምተው የሚወክሉትን ሰብአ ኦሮምያ ለማስደሰት ሲሞክሩ ኢትዮጵያዊነትና ኦሮሞነት ቢደባለቁ አያስገርምም፤

Filed in: Amharic