>

የሹመቱ ቀን!!! (ደረጀ ደስታ)

የሹመቱ ቀን!!!
ደረጀ ደስታ
* ደብረጽዮን ዘመኑ የለውጥ ነው፣ ኦቦ ለማንም ይቅናቸው አሉ።
* ጅዋር ደብረጽዮን ጥሩ ተናግረዋል አለ።
* የብአዴን ሰዎችም ኦቦ ሽመልስን እንኳን አደረሰህ አሉ።
* ሰዎቹ ሁሉ አብረው ስቀው ተሳስቀው ታዩ።
* ጋሽ በቀለ ገርባም ያማረ ነገር አወሩ።
* ገዱም የእንግሊዝኛ ፈተና ተሰጣቸው። በዚህም ፈገግ ተሰኙ።
ሁሉም ትንፋሽ እየወሰደ ይመስላል። እኛም ከነገር ትንፋሽ ወስደን እንዲህ አሰብን-
በሹመቱ ያው ወጣቶች በዝተዋል። ትኩስ ኃይል እና ዘመናዊነት በመሆኑ በጣም ደስ እሚል ነገር ነው። እድሜም ልምድ ነውና ምራቅ የዋጠ ነገር ያላመጠም ቢደባለቅ ይጠቅማል። የጎለመሰው ሁሉ ለጎረመሰው ይልቀቅ አይባልም። ቢሆንም ቢሆንም ወጣትነት ብቻውን እድሜ እንጂ አስተሳሰብ ወይም ዘመናዊነት አይደለም። የሸመገለ ሁሉ እዚያው የተቸከለ ከዘመን የተነቀለ ነው ማለትም አይደለም። ከአረጀ ካፈጀው፣ አገርና ሰው ከፈጀው፣ የብሔር ፖለቲካ ብቻ ተሰናክሎ የቀረ ወጣትም እኮ ይኖራል። ፊደል ትቶ ዘር እየቆጠረ እዚያው የቀረ ወጣትና ሽማግሌም ሞልቷል። ቴክኖሎጂው ክደረሰበት፣ ዓለም አንድ ከሆነበት፣ ዘመናዊ አስተሳሰብ፣ አገርን ለመቀላቀል እሚታገል ከሁለቱም ወገን አለ። እውቀት የገባው ሰላም የጠማው ሽማግሌም ሆነ ወጣትም ይኖራል። ስለዚህ ማን ምን ያስባል እንጂ፣ ዘር ከልጓም ይስባል፣ እድሜም ከነገር ይጥላል ማለት ልክ አይደለም። ውጭውን አይቶ ውስጡን ማድነቅ ወይም ማዋደቅ አይጠቅምም። ያለፈው አልፏል ማለት ካልተጀመረ መጪው አይመጣም። የሰዎችን ማንነት እድሜና ውጫዊ ቁመና ትተን ብቃትና ችሎታ መመልከት እንጀምር። ካልቻሉ እሚወርዱበትን ከበረቱ እሚበረቱበትን ማሰብ ይጠቅማል። ለፖለቲካው ግን መደራጀትና መወያየት መቋረጥ የሌለበት ነገር መሆኑን አለመዘንጋት ነው። ነገር ሁሉ እሚበላሸው እሱ እየተዘነጋ ይመስለኛል። ስለጉዳዮች ስለፖሊሲዎች ስለ መንግሥቱ፣ ስለ ህገመግንስቱ፣ ስለ ኢኮኖሚው፣ ጤናና ትምህርቱ ብሎም ስለ መደራጀቱ መወያየት ያስፈልጋል። ይህን የማድረግ “ምርጫ” አለን።  ምርጫ የሌለን ምርጫውን ስለማንጠቀምበት ነው። የኛ የሹመት ቀን የምርጫው እለት መሆኑን እናስብ። በነገራችን ላይ፣ እሱ ነገር እንዴት ሆነ?
Filed in: Amharic