>
11:27 am - Wednesday November 30, 2022

የመፅሃፍ ዳሰሳ:- ርእስ፡ አባ ጃዊ ጎቤ፤ አባ ድፈን መሳፍንት - ክፍል ሁለት (በሰሎሞን ዳውድ አራጌ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ፤

ርእስ፡ አባ ጃዊ ጎቤ፤ አባ ድፈን መሳፍንት
ደራሲ፡ ጌቱ ሙጨ
የታተመበት ዓመት፡ 2011
የገፅ ብዛት፡ 200

ክፍል ሁለት

ሰሎሞን ዳውድ አራጌ
ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ፤ እንግሊዝኛ ቋንቋና
ስነፅሁፍ ትም/ት ክፍል መምህር

 

ታሪክ ቀያሪዋ ሐምሌ 05/2008 ዓ.ም ስንቃኛት!

ወያኔ መራሹ የኮማንዶ ቡድን በተለያዩ ግዜያት በቀላሉ ይፈፅመው እንደነበረው የለመደች ጦጣ … ይሉት ፈሊጥ ተከትሎ የወልቃይት ሕዝቦች ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ አባላትን ጎንደር ገብቶ አንጠልጥሎ ለመውሰድ በልበ ሙሉነት አፋኝ ቡድን ላከ፤ ቡድኑም የተወሰኑ የኮሚቴው አባላትን በክልሉ ፖሊስ አጋዥነት በመዳፉ ውስጥ አስገባ፤ ነገር ግን ሁለት እጅግ ተፈላጊ ሰዎች ይቀሩታል እነሱም አቶ ጎይቶም ሕርስቀይ እና ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ ነበረ፡፡ የመጀመሪያው ሰው ቀድሞ ሸሽቶ ነበርና አልተገኛቸውም፤ ስለዚህ ይኸው አፋኝ ቡድን በዚያው ውድቅት የአንድ ወንድ ሰው ቤት አንኳኳ፤ ታዳኙ ማነህ ሲል ጠየቀ፤ ክፈት እኔ ነኝ ሲል የንቀት ምላሽ የሰጠውንም የአፋኝ ወገን ድምፅ ኮ/ሉ ጠንቅቆ የሚያውቀው የአንድ ትግራዋይ ቀደምት የስራ ባልደረባው የሆኑት ኮ/ል ሐለፎም ናቸው፡፡ የሌሎቹ መታን ቀድሞ መረጃው የደረሳቸው ኮ/ል ደመቀ ሲነጋ በብርሃን ብትመጡ የሚል ምላሽ ቢሰጥም አልተሳካም፤ ነገሩ ቁርጥ ነው፤ ይሀኔ ልጆቻቸውና ባለቤታቸውን ጥግ ጥግ አስይዘው ለፍልሚያ ራሳቸውን እያዘጋጁ በህግ አምላክ ቢሉም ሕግ የማይገዛው ቡድን ነውና አልተመለሰም፡፡ ይሄኔ ነበር ለወዳጅ ዘመድ መታፈናቸውን በስልክ አሳውቀው፤ መሳሪያቸውን አቀባብለው በተጠንቀቅ ቆሙ፡፡

የመጀመሪያዋን ጥይት ተኮሰ፤ አጥራቸውን ዘሎ የገባ አንድ የማፋያ ቡድን አባል በጥይት መትቶ ጣለ፡፡ በዚህ የተበሳጨው አፋኝ ቡድን በኮ/ሉ ቤት ላይ የቦንብና ተኩስ እሩምታውን አወረዱበት፡፡ ምቹ ቦታ ይዘው የሚጠባበቁት ኮ/ል በተደጋጋሚ የልጆቻቸውና ባለቤታቸውን ስሞች እየጠሩ ባስቀመጧቸው ቦታ መፅናታቸውን እየተከታተሉ ደፈጣቸውን ቀጠሉ፡፡
በዚህም ወቅት አቶ አዛኔና አቶ ዮሃንስ ተደዋውለው ኮ/ል ቤት ቢደርሱም አፋኝ ቡድኑ አታስፈልጉም ብሎ ይመልሳቸዋል፤ በመኪናቸውም ፈጥነው ወደ ቤታቸው ሄደው መሳሪያ ታጥአው ሰጠኝ ባብልን ከታጋዩ ጎራ ጨምረው ትግሉን ተቀላቀሉ፡፡ ሰጠኝ ባብል ትግሉን የተቀላቀለው ከ200 – 250 የሚደርሱ ታጣቂዎቹን ይዞ ነበር፡፡ አፋኙ ቡድን በኮ/ሉ ቤት ላይ ተደጋጋሚ ተኩስና የፈንጅ ጥቃት ሰነዘረ፡፡ የጎንደር ከተማ ሰው ጆሮም ደረሰና ምንድን ነው ነገሩ ብሎ ቢጠይቅ ሃይለኛ ሽፍታ ገብቶ ነው የሚል የተሳሳተ ዜና ነዝተው ኮ/ሉን ከእጃቸው የማስገባት ስራን ገፉበት፡፡ በኋላም የኮ/ል ስልክ ላይ ጥሪ ተሰማ፤ የደጀኔ ማሩ ስልክ ነበር፤ እየመጣሁ ነው እጅህን እንዳትሰጥ፤ ለመሆኑ መሳሪያ አለህ፤ የከፋ ነገር ከመጣም ዕጅህን እንዳትሰጥ ባለህ ታገልና አንዷን ጥይት ለራህ ታደርጋለህ አለው፡፡ ይህ ጀግና በቦታው እንደደረሰ የጠላትን አሰላለፍ ጠይቆ በእጅ ቦንብ ፈጃቸው፤ በመሃል ግን ሰጠኝ ባብል ተሰዋ፡፡

የሰጠኝ ባብል መሰዋት ጉዳዩን አከፋው እነ ሲሳይ ታከለ፣ እነ ሻንቆ ሽባበው፣ እነ ብርሃን አቡሃይ … በርካቶች ትጥቅ ያለው በትጥቁ የሌለው ጀሌውን አስከትሎ ገባ፤ በዚህኛው ወገን ጥቂቶች ተሰው፤ አፋኙን ቡድን ለወሬ ነጋሪ ሳይስቀሩ ፈጇቸው፡፡ የጎንደር ወጣትም ተሳታፊ ሆነ፤ ጉዳዩ በግልፅ እንደደረሰው መንገድ በመዝጋት፣ ለታጋዮቹ ስንቅ በማቀበል፣ ጥይት በማሰራጨት፣ የአፋኝ ቡድኑን መኪኖች በማጋየት፣ አምሳያ ተላላኪዎችና ሰላዮችን በማስጠንቀቅና ርምጃ በመውሰድ፤ የአካባቢው እንስቶችም ሰንቅ ማቀበል፣ ቁስለኛ ማከም፣ ሙት ከተገኘም አስከሬን በማግለል በእንስት ታጋይ ንግስት ይርጋ ፊታዉራሪነት ህብረታቸውን ገለፁ፤ የትግሉም ደጀንነታቸውን አሳዩ፡፡

በመጨረሻም ለወንበዴው ቡድን ድል ስትርቀው የታወቀው የመንግስት ጣልቃ ገብነት ደርሶ ከች ይልና የክልሉ ፖሊስ ከአርበኞች ጋር ተደራደረ፤ ለሕዋሓት መራሹ ፌደራል መንግስት ይሰጥ የሚል ጥያቄ ቀረበ፤ አርበኞች ይህ እንዳሆን ጥብቅ ማሳሰቢያ በመስጠታቸው በጎንደር አንገረብ ማረሚያ ቤት ጠባቂ ተመድቦለት እንዲቀመጥ ተደረገ፡፡ ሌላኛው ወሳኝ ቀን በሐምሌ 05 እና 06/ 2008 ለተሰው ጀግኖች የድጋፍ ሰልፍ ለማድረግ ሐምሌ 24/2008 ጥሪ ታላለፈ፡፡ ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ ታሪካዊ ሰልፍም ተደረገ፡፡ በወቅቱ በሰልፈኞች ላይ ይገጥም ይሆናል ተብሎ የተሰጋው የአገዛዙ በትር ቢሆንም አርበኞቹ በከተማዋ ዙሪያ ሰባት ሽህ በሚደርስ ታጣቂ መከበቧን አሳወቁ፤ ቅንጣት ሙከራም ሳይደረግ አለፈ፡፡ እናም ሕዝቡ በሰላም ፍቅርን ሲሰብክ፣ የመላ ሃገሪቱን እንከኖች የሚያስተጋቡ መልክቶች ይዞ አደባባይ ወጣ፡፡

ሐምሌ 29/2008 ዓ.ም ደግሞ ሌላው ውጥረት ይኸውም የኮ/ሉ የፍርድ ቤት ውሎ ሲሆን መንግስት እንወስዳለን፤ ህዝቡ ወይ ፍንክች የአባ ቢላዋ ልጅ ብለው ውጥረት ሰፈነ፡፡ የከተማ ነውጥ ተከተለ፤ መንገዶች ተዘጉ፣ በአባ ጃዊም መንደር ቁርጥ ጥትዕዛዝ ተላለፈ አርማጭሆ ና ሳንጃ ሙሉ በሙሉ መንገድ ተዘጋ፤ አባይ ማዶዎች ተቀላቀሉ፤ ባህር ዳር ላይ መተላለፊያ ተዘጋ፤ አንገረብ ኬላ ተጣለ፤ አባ ጃዊና ዳኘው ማሩ ዘንድ ሁሉም ታጥቆ ለፍልሚያ ተዘጋጀ፤ 1400 ስንዱ ታጣቂ አለሁ አለ፡፡ የጎንደር በርሃዎች በጎበዝ አለቃዎችና እምቢ ባይ ነፍጠኞች ቁጥጥር ስር ዋሉ፤ የሙሴ ባምብ አርበኞችም የመንግስት ሃይል መድረሻ አሳጥተው፤ መሳሪያ ነጥቀው 600 የሚሆኑ ጀሌዎች ባለትጥቅ አደረጉ፡፡ ይህ ሃይል በእነ ሰጠኝ ባብል እና ሲሳይ ታከለ ቀብር ለት ተገናኝቶ ትግሉን በቃለ ምህላ ያፀና ታማኝ ስብስብ ነበር፡፡

የሃይል ሚዛኑን መቋቋም ያቃተው መንግስት ተብየው ወንበዴ ቡድን መሃላ ተማምሎ መቆሚያ መቀመጫ ያሳጣው ነፃነት ናፋቂው ነፍጠኛ በሙሉ ሆኖ ሳለ፤ ሽምግልና የላከው ግን ወደ አባ ጃዊ ዘንድ ብቻ ነበር፡፡ ይህንም በቀላሉ ያልተመለከተው አባ ጃዊ ይህ ምን አይነት ተንኮልና ሴራ በእርሱ ላይ አንዲያስከትልበት ጠንቅቆ ቢያውቅም እስኪ ይሁን ብሎ መንገዱን ከዘጋው አንዲት እንጨት አነሳና ወደ ጥግ አስቀመጠ፤ እርሱን ተከትሎም ወጣቱ የተዘጉ መንገዶችን በሙሉ ከፈተ፡፡ ከዚያን ግዜ ጀምሮ አባ ጃዊ ትንኮሳ እየሸተተው ከሙሴ ባምብ አርበኞች ጋር በአንድነት ካምፕ ገብቶ መሸገ፤ ከጓዶቹም ጋር መከረ፤ ወደ ሁለተኛው የግል ካምፑ መዛወር እንዳባቸው ቁርጥ ውሳኔ አደረጉ፡፡

አዋጅ ወቃለ-ምህላ ለሐምሌ 05 /2008 ዓ.ም

በዚች ሰበበኛ ቀን ሁለት ጀግኖች ተሰው፤ እነሱም ሰጠኝ ባብልና ሲሳይ ታከለ ነበሩ፡፡ ታዲያ ቀኗ ማርሽ ቀያሪ ናትና 300 ሚደርሱ አርበኞች ተሰባሰቡ ቃለ ምሕላ በታላላቆቹና ምራቅ በዋጡት አርበኞች ጎቤ መልኬና ጌጤ አዳል ውሳኔ ተላለፈ፡፡ የምህላ ቃሉም እነሆ፤ “ሳንጃ ኪዳነ ምህረት ትታዘባችሁ! የሰጠኝ ባብል አጥንት እሾህ ሆኖ ይውጋችሁ! አበራ ጊዎርጊስ ይታዘባችሁ! የሲሳይ ታከለ አጥንት እሾህ ሆኖ ይውጋችሁ!” እነሆ ሰጠኝ በሚያምናት ኪዳነ ምህረት ቅጥር ግቢ ከመቃብሩ ግርጌ አይኑ ሳይፈስ፣ አካሉ ሳይፈርስ፣ በመሃላ ተሳስረን መስቀለ ክርስቶስ መትተን፣ የሞተለትን ዓላማ ከግብ ሳናደርስ ወደ ቤታችን ላንመለስ ቃል ገብተናልና ትግላችን ይቀጥል! ልቦናችን ከሃብት ንብረታችን ይነቀል፤ እያለ ሁሉም በየሸንተረሩ መሰሉን ሰብስቦ ወደ ትግሉ ክተት እንዲል ታወጀ፡፡

አባ ጃዊ ጎቤ መልኬ ድሕረ ሐምሌ 05/2008

ከአባ ጃዊ ጋር ከቄስ በመስቀል ተለማምጦ ነገሩን ለማገብ የሞከረው መንግስት ተብየ ቡድን ቂሙን አጠናክሮ አባ ጃዊን ማሰድድ ያዘ፤ እርሱም የዋዛ አልነበረምና ቀድሞ ሽምግልና ሲላክበት ነገሩን ተረድቶት ነበርና ስልጠና ለአዲስ ተመልማዮች ማዘጋጀት፣ ስንቅና ጥይት ማሟላት ስራንተያይዞታል፤ በዚህ መሃ አዲስ ዓመትን ከቤተሰቡ ዘንድ ለማክበር ወደ ሳንጃ ወረደ፤ መስከረም 01/2009 ከወትሮው በተለየ በዱካክና በትካዜ ተሞልቶ ያሳለፈው አባ ጃዊ መረጃ ሲደርሰው በዓል በማያውቀው በሰው በላው ወንበዴ ቡድን በጥብቅ ተፈላጊ ዝርዝር ውስጥ ስሙን ሰፍሮ እየታደነ መሆኑን ነበር ታማኝ የትግል ጓዱ አርበኛ ጌጤ አዳል የነገረው፡፡ እናም ዕለቱን መረጃው እንደደረሰው አርባ ጎራሹን ከሽጉጡ ጋር ታጥቆ እርሱም በተራው ሊታፈኑ ይችላሉ ያላቸውን ጓደኞቹ ዘንድ ደዋውሎ አሳውቆ ቤቱን ጥሎ ወጣ፡፡

አባ ጃዊ ወደ ውጅባ ገስግሶ ሄዶ ለትግል አጋሮቹ የፍልሚያውን ርግጠኝነት አስረድቶ እነ ሙሃቤ በለጠ፣ ሞላጃው ሙላው፣ ቃቁ አወቀ፣ ደሳለኝ አዱኛና የአጋየ ጦር ከጎኑ አሰልፎ በርሃ ገባ፡፡ መከላከያ ሰራዊቱን ከወረዳ ካቢኔ አባላቶች መረጃ እየወሰደ ሰላዮች ይልክበት ጀመር፤ አርበኞችም ቁርጥ መሆኑን ሲረዱ ጥቃት ይሰነዝሩ ጀመር፤ አርበኛ አበራ ጎባው ድረስ ሄደው ገጠሙ፤ በፍልሚውም በርካታ የመንግስት ወታደሮች ከረገፉ በኋላ አርበኛ አበራ ጎባው ወደቀ፡፡ የአርበኛ ጎባው ድል መደረግ የወገን ዕጅ እንዳለበት በቁርጠኝነት የተረዱት ሌሎች የትግሉ አባላት ቦታ ቀይረው ይበልጥ ዝግጅት ጀመሩ፤ ያን ተከትሎም መንግስት ስጋቱ በማመሉና የታጋዮቹን አደገኛነት በመረዳቱ 13 ኦራል ሰራዊት በቦታው አሰፈረ፡፡ ይህም ሰራዊት አባ ጃዊን አላማው አድርጎ ተነስቷልና ቤቱና ካምፑ ድረስ በመሄድ ቤተሰቡ ላይ ምርመራ፣ መከራና ስቃይ አፀኑባቸው፤ 200 ያህል ወታደር አባ ጃዊ ወጀድ ድረስ ተጠጋ እንስሳቶቹን ፈጁ፤ “ደመና” ሲል የሚጠራውን በሬውን በጥይት ግንባሩን ፈርክሰው ልቡን በሃዘን ሊያደሙት ሞከሩ፡፡

በዚህ ግዜ የአባ ጃዊ መደፈር የነደደው የአካባቢው ኮበሌ ከሰራዊቱ ጋር ገጥሞ፤ መድረሻ አሳጣቸው፤ አካባቢውን በአስከሬናቸው ሞላው፤ ግድ የሌለው መንግስት የድሃ ልጅን ለውጊያ ይማግዳል፤ እኒህ የተበሳጩ የአርማጭሆ ሳተናዎች ደግሞ በጥይት ይቆሉት ይዘዋል፤ የደም አበያ ወረደ፤ ሞት ረከሰ፤ ከእልህ አስጨራሹ ትግል በኋላ እነ አርበኛ ሙሐቤ (ነብሮ)፣ ደሳለኝ፣ ሞላጃውና ቃቁ ወደቁ፡፡ አጥቅቶ መገልበጥ ይከተል የነበረው የአርበኞቹ ቡድን በቀን 18/ ህዳር ወር 2009 ዓ.ም ወደ ጃኖራ ጉዞዋቸውን ለማድረግ ተስማምተው፤ አንዳቸውም የጃኖራን አቋራጭ መንገድ በማያውቁበት ሁኔታ የእግር ጉዞ ጀመሩ፤ ሕዳር 21 /2009 ከአርበኛ አባ ድፈን መሳፍንት ተስፋ ቀየ ሎሚዮ ቅርና አምባ ኪዳነ ምህረት ደረሰው ተገናኙ፤ አቀባበልም አድርጎ ተቀበላቸው፡፡

የአርበኛ አባ ጃዊ ጎቤ መልኬ ፍፃሜ ዳርዳርታ;

ታህሳስ 08/2009 ዓ.ም ርጉም ዕለት ክንደ ብርቱና ጠርጣራውን ጀግና በደካማ ጎኑ ዘመድ ወዳድነቱ ጠገግ ታኮ አንድ እንግዳ ሰው ትግሉን ልቀላቀል ብሎ ተጠጋው ታዋቂና ሃገሪቾው ይኸ ሰው በክፉ በደጉ የአባ ጃዊ ወሮታ የተደረገለት ሰው ስለነበርና በወቅቱ ሙሉ ትጥቅ የያዘ በመሆኑ ማንም ሳያንገራግር አንዲቀላቀል ፈቃድ አገኘ፡፡ ወገናችን ያሉት ይህ ሰው ለሽንት በገባ በወጣ ቁጥር ይደዋወል ነበርና ለተደጋጋሚ ሶስትና አራት ድንገተኛ አፈናና ከበባ ዳረጋቸው፡፡ አይበገሬዎቹ የአባ ጃዊ ሰዎች ግን አፋኞቹን አፈር ድሜ እየቀላቀሉ ጥሰው ሲወጡ፤ ወደ ሌላ ቦታ ሲቀጥሉ ከባዱና መጨረሻው አፋና ግን ታህሳስ 11 ለ12 ሌሊት 7 ሰዓት ገደማ በድጋሜ ተከበቡ፤ እጅግ መራራ ትግል አድርገው አባ ጃዊንም ለጥቂት ከሞት አትርፈው፤ ከበባውን ሰብረው ወጡ፤ ይሁን አንጅ አባ ጃዊ ክፉኛ ቆስሎ ነበር፡፡ ውጊያው የበረታባቸው አባ ጃዊና ጓደኞቹ በሌት ብርሃን ታግዘው ሌላ የማረፊያ ቦታ መረጡ፤ በትግሉ ብቸኛ እንስት አርበኛ የነበረችውን መቅደስ ንግሩን ሙሴ ባምብን ቆርጣ ወደ ጎንደር እንድትሄድ ብሎም ትግሎ እንዲበቃት ቁርጥ ውሳኔ ላይ ደረሱ፡፡

አባ ጃዊ ቁስሉ እስኪሽር ድረስ ከሌሎች አርበኞቹ ዘንድ ቆላ ወገራ ረፍት አደረገ፤ ነገርግን ሐምሌ 05 ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ ሲከበብ ያቋረጠው የዓይኑ ሕመም ጠናበት፡፡ ቁስሉ እያገገመ ሳለ ድንገት ባልተጠበቀ ሁኔታ አሁንም ወታደር ከበበው፤ የመጣውንም ወታደር ተቋቁመው ሰብረው ወጡ፡፡ ዘመድ የሻተው አባ ጃዊ በተደጋጋሚ ጥቃትና ውጊያ ክንዱ እየዛለ፤ ሕመም እየባሰበት ቢመጣ ዘመድ የተባለውን የትግሉ እንግዳ ሰው ሲቀላቀለው ከአንድ ብርቱ … ብሎ ነበር፤ የአባ ጃዊ አርበኞች ግን ሰውየውን በጥርጣሬ ተሞልተው ወደ ትልልቅ ሰዎች ደወሉ፤ ማንም የተለየ ነገር የነገራቸው የለም፤ ይልቁንም የተረጋገጠላቸው ዝምድናው ብቻ ነበር፡፡ ውሎ አድሮም አዲሱ ሰው ከመጠባበቂያ ጠብመንጃ ክምችት መሃል አንዱ ተሰጠውና ህመሙን እያስታመመ፣ የትግል ስልት እያወጣ የነበረውን ከአባ ጃዊ ጎን እንዲሰለፍ ተደረገ፡፡ በዚህ ወቅት አባ ጃዊ ከኪሱ 2000 ብር ብቻ ቀርታዋለች፤ በየካቲት 19/2009 ዘመድ ጥየቃ ብሎ ወጥቶ ከሌሎች ሰዎች ጋር ተገናኝቶ የተመለሰው እንግዳ ሰው፤ በነገታው ተመልሶ ሲቀላቀል፤ ሁሉም የአርበኛ አባላት መኖሩን ደውሎ አረጋግጦ እዚያው በፍጥነት ደረሰ፡፡ እንደደረሰም ሲጋራ ግዛልኝ ብሎ አባ ጃዊን ይጠይቃዋል፤ አባ ጃዊም በርከት አድርጎ አስገዛለት፡፡

 

ክፍል አንድን ካላነበባች ሁ። የመፅሃፍ ዳሰሳ:- ርእስ፡ አባ ጃዊ ጎቤ፤ አባ ድፈን መሳፍንት – (በሰሎሞን ዳውድ አራጌ ከጎንደር ዩኒቨርሲቲ፤

ጸሃፊውን ለማግኘት tadilafiker143@yahoo.com 

 

Filed in: Amharic