>

የቀስት ሞት ብዙ ነገር ያሳያል -የገዳዩን አረመኔነት ፣የዘር ፖለቲካችንን ክርፋት፣ የወደፊታችንን አስፈሪነት!!! (መስከረም አበራ)

የቀስት ሞት ብዙ ነገር ያሳያል -የገዳዩን አረመኔነት ፣የዘር ፖለቲካችንን ክርፋት፣ የወደፊታችንን አስፈሪነት!!!
መስከረም አበራ
ወደ ኋላ የሚያንደረድረን የዘር ፖለቲካችን በጥይት ከመግደል ወደ ጦር እና ቀስት ግድያ ወስዶናል። ከቀስት ሞት በአንፃሩ የጥይት ሞት የተሻለም “ዘመናዊም” ነው። የቀስት ሞት ብዙ ነገር ያሳያል -የገዳዩን አረመኔነት ፣የዘር ፖለቲካችንን ክርፋት፣የወደፊታችንን አስፈሪነት፣ከሰው ደረጃ የመውረዳችንን ቁልቁለት ወዘተ ።
ከሁሉ በላይ የዘር ፖለቲካ ጉዞው ወደ ኋላ ወደ ጦር እና ቀስት ዘመን እንደሆነ አመላካች ነው። ልቦናችን ወደ ኋላ እየነጎደ፣ አረመኔነታችን እየባሰ እንዴት ዘመኑን መመጠን ይቻለናል?በየት አልፈን ሰው የደረሰበት እንደርሳለን?እንዴት ሆነን በምን ቀዳዳ አምልጠን ከብሄር ብሄረሰብነት ወደ ሰውነት ከፍታ እናድጋለን?ሰው ስንሆን ብቻ ሌላውም እንደ እኛው ክፉ ሊሆንበት የማይገባ ክቡር የሰው ፍጡር እንደሆነ እናምናለን።
 ብሄር ብሄረሰብ ስንሆን ነው የሌላውን ክቡርነት የምንክደው ፨ክደን ቀስት ሰንጥቆት ያልፍ ዘንድ የተገባ በአወቃቀሩ ከእኛ ያነሰ ፍጡር መስሎ የሚሰማን። ሰው መሆን ብቻ ርህራሄ በልቦናችን ያሳድራል።በሌላው ጫማ ገብቶ የማሰብ ማስተዋል ይሰጣል ፨ሰው መሆን ብቻ እኔስ ብሆን ቀስት ያለፈብኝ ፣በልስልስ የህፃን ገላው የቀስት ብረት ያለፈው ልጄስ ቢሆን ያስብላል። ዘራዊነት ከሰውነት የትየለሌ ቁልቁለት ላይ ያለ ፣ፊት ከሰጡት ማስተዋልን የሚቀማ ወደ አውሬነት የሚነዳ አደገኛ ህመም ነው። የሩዋንዳ ሁቱዎችሰው መሆናቸውን እየተው ሲሄዱ የቱትሲዎችን ሰውነት በረሮነት ቀይረው ማሰብ ጀመሩ። ከዛ በገጀራ አናቱን የሚሰነጥቁት ቱትሲ በረሮ አንጅ ሰው አልነበረም ለነሱ።
 የሌላውን ሰውነት የሚያስረሳን የዘረኝነት ቅመም መጀመሪያ ራሳችንን ከሰውነት ደረጃ አውርዶ ብሄር ብሄረሰብ ካደረገን በኋላ ነው። ከዛ በኋላ ሲኦል ወለል እንደሌለው ሁሉ የእኛ ዝቅጠትም ማቆሚያ አይኖረውም-ሩዋንዳ ምስክር ነች!ያኔ ትምህርታችን አይረዳንም፣ከሰውነት ወርደን ዘራዊ ማንነት ስንላበስ “ሃይ” ያላለን ትምህርታችን ቁልቁለቱን ከተያያዝነው በኋላ ይበልጥ ወደታች ይነዳን ይሆናል እንጅ ወደ ከፍታ አያመጣንም።ዋናው ነገር ዝቅታውን አለመጀመር ነው፣ከተጀመረ ማብቂያው እያደር የሚወርድ አዘቅት ነው።
ከዚህ ለመዳን ከሰውነት ከፍታ አለመውረድ ነው። ከሰውነት ካልወረድን በእኛ ላይ ቢደረግ የማንወደውን በሌላ ሰው ላይ አናደርግም። የዚህ ማገሩ ፖለቲካችንን ከዘራዊነት ዝቅታ  ወደ እሴታዊነት ከፍታ መሳብ ነው፨ አሁን አሁን በጣም እየሳበኝ የመጣው ፖለቲከኛ አቶ ሙስጠፋ ዑመር በቅርቡ በብሄራዊ ቲያትር ተገኝቶ ስለ እሴት መር ፖለቲካ መድህንነት  እና ስለ ርዕዮተ-ዓለም ፖለቲካ ጠባጫሪነት   የተናገረው ነገር የምለውን በደንብ ይገልፀዋል። የዘር ፖለቲካ ርዕዮት ደግሞ ስስት፣ጥላቻ ፣በሃገር ልጅ ወንድም ላይ ቀስት እስከ መወርወር የደረሰ ዝቅጠት ነው።
 አሳዛኙ ነገር የዘር ፖለቲካ የሚሰራው ጥፋት ላርምህ ቢሉት የማይሆን መሆኑ ነው። የዘር ፖለቲካ ምርቱ ውሻ የሚዞረው የሬሳ ክምር፣በወንድም ሬሳ የጠነባ ቀዬ፣ ዘረኛ ገዳይ ከገደለ በኋላ ፀፀትን ታቅፎ የሚኖርበት የጨፈገገ ስነ-ልቦና ፣የተሰበረ ቅስም ነው። ያኔ ያጋደለው መሬት፣ያጣላው ስልጣን ሁሉ ትርጉም አልቦ ኦና ይሆናል።የሰው ደም የፈሰሰበት ምድር አስጨናቂ የሙት መንፈስ እንጅ አስደሳች ነገር የለውም! ለፀፀት አንሩጥ ፤ ለስብራት አንቸኩል።
Filed in: Amharic