>
6:12 am - Wednesday December 7, 2022

እወክለዋለሁ ከሚለው ህዝብ ባለደም የሆነው ብአዴን!!! (አቻምየለህ ታምሩ)

እወክለዋለሁ  ከሚለው ህዝብ ባለደም የሆነው ብአዴን!!!
አቻምየለህ ታምሩ
ሁለተኛው የአለም ጦርነት እንደተጀመረ ፈረንሳይ በጀርመን ስትሸነፍ አዶልፍ ሒትለር ፈረንሳይን በቀጥታ ለመግዛት እንዲያስችለው ተቀማጭነቱ ቪቼ በሚባለው የፈረንሳይ ከተማ ውስጥ የሆነና ፈረንሳይን እንወክላለን ብለው ለናዚ ያደሩ ፈረንሳውያንን አደራጅቶ የጀርመን እንደራሴ የሆነ የባንዶች መንግሥት አቋቁሞ ነበር።
አፍቃሪ ሒትለር በሆኑት ፈረንሳውያን የተቋቋመው ለናዚ ባደሩ የፈረንሳይ ባንዶች የተቋቋመው የእንደራሴ መንግሥት የቪቼ መንግሥት[Régime de Vichy] ይባላል። የዚህ የፈረንሳይ ባንዶች መንግሥት መሪና የሒትለር የፈረንሳይ እንደራሴ  የነበረው  ወዶ ገብ ፊሊፕ ፔታን የሚባል ፈረንሳዊ ማርሻል ነበር። ማርሻል ፊሊፕ ፔታን ምንም እንኳ በአንደኛው የአለም ጦርነት የፈረንሳይን ጦር እየመራ ለአገሩ የተዋጋ ሰው ቢሆንም በሁለተኛው የአለም ጦርነት ግን አገሩን ከድቶ የሒትለር እንደራሴ መሆን በርካታ የፈረንሳይ አርበኞችን በናዚ ወታደሮች አስጨፍጭፏል።
ሁለተኛው የአለም ጦርነት ከተጠናቀቀ በኋላ ግን የአርበኞቹ የነ ቻርለስ ደጎል መንግሥት ድል ስላደረገ አዲሱ የአርበኞች መንግሥት ቀዳሚ ተግባሩን ያደረገው የባንዶቹን የቪቼ መንግሥት አመራሮችና አገልጋዮች አንድም ሳይቀሩ እያሳደዱ ለፍርድ በማቅረብ ፈረንሳይን ከናዚ ባንዶች ማጽዳት ነበር። በዚህ ፈረንሳይን ከናዚ ርዝራዦች የማጽዳት ዘመቻ የአርበኞቹ የነ ቻርለስ ደጎል መንግሥት ለናዚ ወታደሮች በሴተኛ አዳሪነትና በተራ የጥበቃ ስራ ከሰሩ እስከ ቪቼ መንግሥት መሪ ማርሻል ፊሊፕ ፔታን ድረስ ያሉትን ለናዚ ፓርቲ የሚጠቅም ተግባር የፈጸሙ የፈረንሳይ ባንዶችን ሁሉ ያለ ምህረት ከያሉበት አገር አንገታቸውን እያነቀ ችሎት ፊት በማረቅብ በአገር ክዳት ወንጀል ከሶ አስፈረደባቸው። በኔ ንባብ በአውሮፓ የፍርድ ታሪክ የቪቼ መንግሥት አባላትን ለመፋረድ የተከፈተውን ያህል ሰፊና ብዙ መዝገብ የወጣው የፍርድ ሂደት የለም።
በአርበኞቹ ችችሎት የባንዶች መንግሥት መሪ የነበረው ማርሻል ፊሊፕ ፔታን በፈጸመው የአገር ክዳት የሞት ቅጣት ተፈረደበት። ሆኖም ግን ሰውየው እድሜው የገፋ በመሆኑና በአንደኛው የአለም ጦርነት ፈረንሳይን እየመራ ለአገሩ በመዋጋቱ እንደውለታ ተቆጥሮለት የቅጣት አስተያየት ሊደረግለት በመቻሉ ቅጣቱ ወደ እድሜ ልክ እስራት ተቃሎለት ቀሪ ዘመኑን በፈረንሳይ እስር ቤት ውስጥ ብቻውን ታስሮ እስከ ሕይወቱ በእስር ተቀጥቷል። ከሱ መንግሥት ጋር ያገለገሉ ሌሎች ባንዶችም በፈጸሙት የአገር ክዳት ወንጀል ያለ ምህረትና ርሕራሔ ተጠያቂ ተደርገው ፈረንሳይ ከባንዶች ልትጸዳ ችላለች።
ብአዴን እንደ ድርጅት አዶልፍ ሒትለር ፈረንሳይን ወርሮ በእንደራሴ ለመግዛት የፈረንሳይ ባንዶችን አሰባስቦ እንዳቋቋመው የቪቼ መንግሥት አይነት ሕወሓት ኢትዮጵያን ሲወር አማራን እንደራሱ አድርጎ እንዲገዛለት የፈጠረውና መቀመጫውን ባሕር ዳር ያደረገ  የባንዳ አማሮችና የአማራ ጠሎች ነውረኛ ድርጅት ነው። ሆኖም ግን አማራ እንደ ቻርለስ ደጎል አይነት አርበኛ ባለመውለዱ ሕወሓት ኢትዮጵያን ሲወር በእንደራሴነት ያቋቋመው ብአዴን ባላደራዎች የወራው ሕወሓት እንደራሴዎች ሆነው ፖሊሲውን ሲያስፈጽሙ በኖሩበት የአገር ክህደት ወንጀል ሳይጠየቁና ለፍርድ ሳይቀርቡ ዛሬም ላይ በግፍ ስልጣናቸው ላይ ጸንተው ተደላድለው በአማራው ላይ ይፈራረቁበታል።
ማርሻል ፊሊፕ ፔታን የናዚ መንግሥትን ተቀብሎ ሲያስፈጽም የኖረው የአዶልፍ ሒትለርን ፖሊሲ ነበር። ፋሽስት ጥሊያን ጀምሮት የተወውን ኢትዮጵያን በጎሳና በቋንቋ የመከፋፈል አባዜ የተከተሉት የመንፈስ ወራሾቻቸውና የፋሽስት ጥሊያን አገልጋይ ባንዶች ልጆች የሆኑት ፋሽስት ወያኔዎች ከጎጃም ወስደው «ቤንሻንጉል ጉሙዝ» የተባለው ክልል ሲፈጥሩ ዋናው ፈራሚዎቹ ብአዴዎች ነበሩ። ትናንትና ጎጃም የነበረው መተከል ዛሬ እድሜ ለብአዴን አማራ የሚታረድበት ቆራ ሆኗል።
ብአዴን እንደ ድርጅት የተመሰረተው የአማራን ጥቅም ለማስጠበቅ ሳይሆን ሕወሓት ኢትዮጵያን ሲወር ወዶ ገብ በመሆን የሕወሓትን ፍላጎት በአማራ መካከል ለማስፈጸም ነው። በሌላ አነጋገር ብአዴን ናዚ ፈረንሳይን ወርሮ እንዳቋቋመው የቪቼ መንግሥት ሁሉ ሕወሓት ኢትዮጵያን ሲወር አማራውን በእንደራሴነት ለመግዛት ያቋቋመው የባንዶች ድርጅት ነው። የቪቼ መንግሥት ለናዚ የሰጠውን ሁሉ ጥቅም ብአዴንም ለሕወሓት ሰጥቷል።
ኢትዮጵያን የአማራ መታረጃ ቄራ ያደረገው ሕገ አራዊት ሲጸድቅ ብአዴን ቀዳሚ ፈራሚ ነበር። ከዚያም በኋላ አማራ ባለፉት ሀያ ሰባት ዓመታት በሕግ የዜግነት መብቱን እንዲያጣና እንደፋሲካ ዶሮ እንዲታረድ ሲደረግ ከሥርዓቱ ባላባት ከፋሽስት ወያኔ በላይ ያስፈጽም የነበረው ብአዴን የሚባለው
የሕወሓት ባንዶች ድርጅት ነው። ብአዴን ይህንን ተግባሩን ዛሬም ስሙንና ጌታውን ለውጦ አጠናክሮ ቀጥሎበታል። ለዚህ አብነት ማቅረብ እችላለሁ።
አምባቸው መኮንን የሚባለው የዐቢይ አሕመድ አሽከር ባለፈው ሳምንት አምቦ ላይ ባደረገው ንግግር ኦሮምያ የሚባለው ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለው ልዩ ጥቅም ሳይሸራረፍ እንዲከበር እንደሚታገል ተናግሯል። ልዩ ጥቅም የሚባለው የአፓርታይድ እሳቤ መሰረቱ አማራና የተቀረውን አዲስ አበቤ የአዲስ አበባ መጤና ሰፋሪ አድርጎ በማሳነስ አገር አልባ የማድረግ ዘረኛነት ነው።
እንግዲህ! አምባቸው መኮንን ኦሮምያ የሚባለው ክልል በአዲስ አበባ ላይ ያለው ልዩ ጥቅም ሳይሸራረፍ እንዲከበር የሚጋገለው አማራንና የተቀረውን አዲስ አበቤ ነው ማለት ነው። አምባቸውና የወንጀል ባልደረቦቹ ደልቷቸውና ተዘባነው የሚኖሩት የአማራ ገበሬ በሚከፍለው ግብር ቢሆኑም አምቦ ላይ በአንደበቱ እንደተናገረው እነሱ ግን የሚታገሉት ለአማራ ሳይሆን አማራን ነው። ለዚህም ነው ብአዴን ዛሬም ድረስ የአማራ ባለደም የሚሆነው። አማራ ያልተወከለበት ሕገ መንግሥት ሳይሸራረፍ እንዲከበር የሚሰራ፤ አብዛኛው ኗሪ አማራ የሆነበት አዲስ አበባ ከተማ ኦሮምያ ለሚባለው ክልል ልዩ ጥቅም እንዲሰጥ የሚታገል ድርጅት መቼም የሚታገለው አማራን እንጂ ለአማራ ነው ብሎ የሚያስብ የዋህ የሚኖር አይለስለኝም።
አንዳንድ የዋሆች «አምባቸውን መኮንን ወጣት የሆነ የብአዴን መሪ ስለሆነ ለአማራ ሕዝብ በመታገል ለውጥ ሊያመጣ ይችላል» ሲሉ እመለከታለሁ። እነዚህ ሰዎች የሰውየውን ታሪክ አፈናልገው ለማወቅ ባይችሉ እንኳ እሱ ስለ ራሱ ሕይዎት የተናገረውን አለመስማታቸው ያስገርማል። አምባቸው ራሱ እንደተናገረው ሕወሓትን የተቀላቀለው ገና ጫካ ሳሉ ነው። በሌላ አነጋገር አምባቸው ልክ እንደ ገዱ አንዳርጋቸው ፋሽስት ወያኔን የተቀላቀለው ጫካ ሲሆን፤ ሕወሓት በጎንደርና ጎጃም፤ በወሎና ሸዋ አልፎ ከበረሀ ወደ ቤተ መንግሥት ሲመጣ አምባቸው መንገድ እየመራ አብሯቸው የመጣ «ነባር» ታጋያቸው ነበር።
አማራ እንደ ቻርለስ ደጎል አይነት አርበኛ ባለመፍጠሩ ኢትዮጵያን የወረረውንና አማራን ሲያጠቃ የኖረውን ሕወሓትን በእንደራሴነት ለሀያ ሰባት ዓመታትን በባንዳነአት ሲያገለግል የኖረው ብአዴን ጌታው ፋሽስት ወያኔ መቀሌ ሲመሽግ እሱ ግን ኦሕዴድ ለሚባል ጌታ አድሮ የዐቢይ አሕመድን አገዛዝ ጉዳይ ፈጻሚ በመሆን የቪቼ መንግሥት ለናዚ ሒትለር የሰጠውን አይነት አገልግሎት ለኦሕዴድ እየሰጠ ይገኛል።
አማራ እነ ቻርለስ ደጎል እንዳደረጉት እንወክለዋለን ብለው በመሰየም ጠላት ያደረጉትን ድርጅቶች ፍላጎት ያለ ገደብ በላዩ ላይ ሲያስፈጽሙ የኖሩ ባንዶች ድርጅት የሆነውን ብአዴንን እንደ ቪቼ መንግሥት እያሳደደ አንድ ባንድ እስካልተፋረዳቸው ድረስ ስርየት አያገኝም። እንደ አባቶቹ አርበኞች በየጎበዝ አርበኛው ተደራጅቶ አማራን ጠላት ያደረጉትን ድርጅቶች ዓላማ በአማራው ላይ የሚያስፈጽሙት ብአዴኖች አንድ ባንድ እስካልተፋረደ ድረስ አማራ ማኅበረሰባዊ እረፍት አያገኝም። አማራን ሲገድል የኖረ፣ ሲያሳድድ የባጀ፣ የቀስት መለማመጃ ያደረገው ወንጀለኛ ድርጅት ሁሉ የብአዴን ወዳጅ ነው።
ቀንደኛዎቹ የአማራ ጠላቶች የሆኑት ወያኔዎቹ በረከት ሰምዖንና ታደሰ ካሳ እንዳይከሰሱ እስከመጨረሻው ድረስ የተከራከሩት የለውጥ ኃይል የተባሉቱ ገዱ አንዳርጋቸው፣ አምባቸው መኮንንና ደመቀ መኮንን ነበሩ። ታምራት ላይኔም እንደነገረን ምንም እንኳ ፋሽስት ወያኔ ጫካ የወረደው ወልቃይትን፣ ጠገዴን፣ ጠለምትን፣ ሁመራን ፣ራያ አላማጣን፣ ወዘተን በመውረስ የትግራይ አካል ለማድረግ ቢሆንም እነዚህ አካባቢዎች በኦፊሴል ወደ ትግራይ ክልል የተካለሉት ግን የያኔው ኢሕዴን የትናንቱ ብአዴን ያሁሉ አዴፓ በ1983 ክረምት በጎንደር ከተማ ባካሄደው ጉባኤ የትግራይ መሆናቸውን ከፈረመ በኋላ ነበር። ታምራት እንደመሰከተው ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምት፣ ሁመራ፣ አላማጣ፣ ወዘተ… የትግራይ እንደሆኑ በኢሕዴን ጉባኤ ወረቀት ያቀረበው በወቅቱ የኢሕዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና ኢሕዴንን ወክሎ የሽግግር መንግሥት ተብዮው ምክር ቤት አባል የነበረው የገነት ዘውዴ የአክስት ልጅ ነውረኛው ዳዊት ዮሀንስ ነበር። የዳዊትን ወረቀት ተከትሎ ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጠለምት ፣ ሁመራ ራያና አላማጣ ወደ ትግራይ እንዲካለሉ ኢሕዴን በሙሉ ድምጽ ወሰነ። ባጭሩ በአማራ ላይ ሲፈጸሙ የኖሩትና የተፈጸሙት ወንጀሎች ሁሉ ቀድመው የሚጸድቁት በብአዴን ፊርማና ማኅተም ነው።
የአማራ ኅልውና የሚረጋገጠው በተፈጸሙበት ወንጀሎች ሁሉ በቀዳሚነት ፊርማውና ማኅተሙን ሲያሳርፍ የኖረው አማራን ጠላት ያደረጉ ድርጅቶች እንደራሴው ብአዴንና ልክኪ ያላቸው አባላቱ ሁሉ አንድ ባንድ በመብራት እየተለቀሙ ለፈጸሙት የአገር ክዳት ወንጀል እንደ ቪቼ መንግሥት ባልደረቦች ለፍርድ ሲቀርቡና የእጃቸው ሲያገኙ ብቻ ነው። የአማራ እውነተኛ ትግል ከግብ የሚደርሰው አገር የገነቡት እነ ቻርለ ደጎል የአገርና የመንግሥት ባለቤት ለመሆን የተከተሉትን የአርበኛነት ተጋድሎ በመከተል ብቻ ነው።
ከዚህ ውጭ የሕገ አራዊቱ ባላደራና ጠባቂ የሆነው ብአዴን ትናንትን ጎጃም በነበረው መተከል ውስጥ አማራ ባለፉት ሀያ ሰባት ዓመታት ሙሉ በቀስት እየተገደለ ሕይዎቱን የሚያጣበትን ዘግናኝ ሽብር መሰረታዊ ምክንያት ሕገ መንግሥቱ ነው ቢል ጌቶቹ እነ ዐቢይ ስለሚቆጡበት ሕገ አራዊቱ የወለደውን ሽብር የጎጂ ልማድ ውጤት እንደሆነ አድርጎ በማቅረብ አማራን ጠላት ላደረጉት ሁሉ ለሺያጭ ከማቅረብ የማይመለስ የባንዶች ድርጅት መሆኑን እኔ ከደመደምሁ ቆይቻለሁ። እንድግመዋለሁ የፈረንሳይ አርበኞች እነ ቻርለስ ደጎል ፈረንሳይን ከባንዶቹ ከነ ፊሊፕ ፔታን የባንዳ መንግሥት ባላደራዎች እንዳጸዱት ሁሉ አማራም የጠላቶቹ እንደራሴዎች የሆኑትን ነውረኞቹን ብአዴኖችን አንድ ባንድ እያሳደደ እስካልተፋረዳቸውና ለፈጸሙት የአገር ክህደት ወንጀል ተጠያቂ እስካላደረጋቸው ድረስ ስርየት ሊያገኝ አይችልም።
Filed in: Amharic