>

የረባ ትምርት  እና የረባ ስራ የሌለው ዜጋ በብሄር ቀርቶ ፤በመላኣክት ስምም ቢደራጅ ከማውደም አይመለስም! (በእውቀቱ ስዩም)

የረባ ትምርት  እና የረባ ስራ የሌለው ዜጋ በብሄር ቀርቶ ፤በመላኣክት ስምም ቢደራጅ ከማውደም አይመለስም!
በእውቀቱ ስዩም
አንዳንድ ሰዎች ‘ የብሄር ፖለቲካ በህግ ይታገድልን ሲሉ’ እሰማለሁ፤ የብሄር ፖለቲካ አይጥመኝም፤ባገራችን ወትሮ የሚታየው መከራ ምንጮች አንዱ ያልተገራ የብሄር ፖለቲካ እንደሆነም አምናለሁ፤ ያም ሆኖ ዜጎች በቁዋንቁዋና በዘመድ የመደራጀታቸውን  መብት መግፈፍ ሰላምና ደስታ  ያመጣል ብየ አላስብም፤ብጤውን መርጦ መቡዋደን የሰው ባህርይ ነው፤ በየጊዜው ልዩ ማንነት  መፍጠር፤ ልዩ መለዮ ማበጀት፤ ድንበር ማስመር የሰው ባህርይ ነው፤ አባቶች አድርገውታል! ልጆቻችንም ይቀጥሉታል! በብሄር  እንኩዋ ባይኖር  ሰዎች በሃይማኖትና በስፖርት ሰበብ እየተቡዋደኑ ሊተቃቀፉም ሆነ ሊተናነቁበት የሚችሉበት እድል ሞልቱዋል፤ ሰዎች በብሄር መቡዋደናቸው በራሱ  ችግር  አይመስለኝም፤ ችግሩ የብሄር ቡድናቸውን የክፋት መሳርያ ሲያደርጉት ነው፤ እኔ ስጋ የማይመገቡ  ሰዎች ማህበር ከተቁዋቁዋመ  አባል መሆን እፈልጋለሁ፤አንድ ቀን ወፈፍ አርጎኝ፤ካዛንቺስ ወርጄ፤  የዮናስ ጨርጨር ስጋ ቤትን ላቃጥለው እስካላልሁ ድረስ የኢትዮጵያ ችግር ልሆን አልችልም፤
እና እቴዋ! የብሄር ፖለቲካን አበቃቀሉን ተረጂው፤ከልኩ እንዳያልፍ አድርገሽ ግሪው፤ብትፈልጊ  አብጠልጥ ይው፤ግን ላግደው ብለሽ ስትነሺ የበለጠ ታባልጊዋለሽ!የበለጠም ታከሪዋለሽ!
በበኩሌ ፤የብሄር ፖለቲካ በዚህ ዘመን የምናየውን ለከት የለሽ ክፋት መሳርያ የሆነው በሁለት መራዦች ምክንያት ይመስለኛል ፤ቦዘንና የሾቀ የትምርት ስርአት!
ቦዘን
ብዙ ወጣት ስራ የለውም፤ መሬት የለውም፤ ሰንደቅ አላማ እንጂ የኑሮ አላማ የለውም፤ አፍላ እድሜውን ያባከነበት ትምርት መሰል ነገር ስራ እንዲፈጥር የሚያስችል አቅም አላስታጠቀውም፤  ዛሬ ብዙ ወጣት ሰርቼ ያልፍልኛል ከሚል ሀሳብ ይልቅ ፤ ምርኮ በመሰብሰብ ተስፋ ተጠምዱዋል፤ ችጋርና ርሀብ ፖለቲካውን ይዘውረዋል፤ የተራበ ህዝብ መሪውን ይበላል ይላል ኦቦ መረራ ጉዲና! እኔ ይመስለኝም! መሪዎች ምናቸው ሞኝ ነው?! ራሳቸውን የተራበ ህዝብ  መንጋጋ የማይደርስበት ቦታ ማስቀመጥ ይችሉበታል፤  ይልቅስ የተራበ ህዝብ ጎረቤቱን ሊበላ ይችላል፤  በቀድሞ ዘመን አንድ የመንደር ጉልበተኛ ተነስቶ ጥቂት ጭፍራ ሰብስቦ ጎረቤት ግዛት ይወር ነበር፤  ከተወረረው አገር የሚገኘው የምርኮ እቃ ለመቀራመት ያሰቡ ወጣቶች  በጉልበታሙ ሰውየ ስር ለመሰለፍ አያቅማሙም ነበር፤እንዲሁም፤ ዛሬ፤ የብሄር ፖለቲካ ፤ የዚያኛውን ብሄር ሀብት ወርሼ ያልፍልኛል የሚል ህልም ያደረባቸውን ወጣቶች ይማርካል፤
የትምርት ስራቱ ፈርሶ ይሰራ!
ያገራችን የትምርት  ስርአቱ ቡትቶ ነው፤ ምንም አይነት ችሎታ፤ ምንም አይነት የኑሮ መላ ለዜጋው አያስታጥቅም፤ ችሎታ የሌለው ሰው ደግሞ ያገር  ሸክም ብቻ አይደለም፤ ለርሻ በታጨ መሬት ላይ እንደተቀበረ ፈንጅ ነው፤ትምርት ቤቶች ልጆችን ሰብስቦ ከማቆየት ያለፈ ፋይዳ የላቸውም፤ መንግስት አገራችን ያልታደለችውን  ነዳጅ ከመፈለግ ሲማስን ከሚኖር፤ የዜጎችን የተዳፈነ አቅም ቆፍሮ ቢያወጣ ይጠቅመናል! ይህን ማድረግ የሚችለው ቡትቶውን የትምርት ስርአት ወዲያ ጥሎ ፤በተግባራዊ ትምርት ስርአት በመተካት ነው፤የትምርታችንን ሹቀት ለመግለጥ አንድ ነገር ላንሳ፤ዳግማይ ምኒልክት  የተማረ አናጢ ስላልነበራቸው ቤተመንግስታቸውን ያሰሩት በውጭ አገር ግንበኞች ነበር፤ዛሬም ቤተመንግስቱ ሲታደስ አናጢዎች የውጭ አገር ባለሙያዎች መሆናቸውን አይተናል! አይተንም በግብዳው አፍረናል!
የሰናይ ምግባር  ችግር ይነሳል ፤ መዋደድን መከባበርን ለልጆቻችን እንዲያስተምሩልን  የሃይማኖት ጌቶችን ማስቸገር የለብንም፤ የሃይማኖት ጌቶች  ጊዜ የላቸውም፤ በሽቀላ ፤በቅዱስ ዘይት ሽያጭ እና ጋኔንን በቃለመጠይቅ እና በካራቲ በማባረር ተጠምደዋል! ትውልድን በሰናይምግባር  ማሰልጠን የትምህርትቤት  እዳ ነው፤ ልጆች ትሩፋት ቢሰሩ  ምድራዊ ሽልማት ፤ክፋት ቢሰሩ  ምድራዊ ቅጣት እንደሚጠብቃቸው እያስረዱ መቅረፅ የዘመናይ ትምርት ድርሻ ነው፤
ስጠቀልለው፤
የረባ ትምርት  እና የረባ ስራ የሌለው ዜጋ በብሄር ቀርቶ ፤በመላኣክት ስም ቢደራጅ ከማውደም አይመለስም!
Filed in: Amharic