>
10:38 am - Tuesday July 5, 2022

የኢትዮጵያ ጠላቶች ፍጻሜ !!!  (ዘመድኩን በቀለ) 

የኢትዮጵያ ጠላቶች ፍጻሜ !!!
  ዘመድኩን በቀለ 
★ የሱዳኑ አልበሽርም መጨረሻ በድንጋይና በአሸዋ መደብደብ ሆነ!
★ የኢትዮጵያም ጦር በዘር፣ በጎሳ ባያደራጁት ኖሮ ተዐምር እናይ ነበረ። ነገ ግን አይቀርም። ኢትዮጵያ የራሷ መከላከያ ሠራዊት ይኖራታል። ትግሬም፣ ዐማራም፣ ኦሮሞም የማያዘው ሠራዊት ይኖራታል። የኢትዮጵያ ሠራዊት በጭንቅ፣ በምጥ ይወለዳል። የህዝብ ሠራዊት ይወለዳል። ዜጋ የማያርድ ሠራዊት ይወለዳል። ይሄን እንደ ትንቢት መዝግቡልኝ። ይኸው ነው። 
ህወሓቶች፣ ብአዴኖች፣ ኦህዴዶች፣ ደኢህዴኖች ሆይ የእናንተንም መጨረሻችሁን እነሆ በፊልም ተመልከቱት። የቀን ጉዳይ፣ የጊዜ ጉዳይ ብቻ ነው። አከተመ። 
•••
የኢትዮጵያ ጠላቶች አመድም፣ አሸዋም፣ አፈርም ይቅማሉ። አፈርደቼም ይበላሉ። ወላ ህወሓት፣ ኦህዴድ፣ ደኢህዴን፣ ብአዴን ገና ዋጋችሁን ሳታገኙማ አይቀርም። የጊዜ ጉዳይ ብቻ ነው። በረከትና ክንፈ ዳኘው ብቻ አይደሉም ተጠያቂዎቹ። ኢህአዴግ የሚባል ፓርቲ በሙሉ መጨረሻው የአልበሽር መንገድ ነው።
•••
ይህ ቪድዮ የሚያሳየን ባለፈው ወር በዳቦ ጭማሪ ሰበብ ከሱዳን ገዢነቱ የወረደው፣ የኢትዮጵያችንም ቀንደኛ ጠላት የሀገር አፍራሹ ወያኔም የልብ ወዳጅ የነበረው አምባገነኑ የሱዳኑ መሪ አልበሽርና የእሱ ካቢኔ የነበሩት በሙሉ እንደ ከብት፣ እንደላምና ፍየል በአይሱዙ ተጭነው ወደ ዘብጥያ ሲወርዱ የሚያሳይ ቪድዮ ነው። ያ ሁሉ ክብር በደቂቃ ውስጥ እንደ ጉም ሲቦንን የሚያሳይ ቪድዮ ነው። መቼም ይሄን የአልበሽር ፍጻሜ የመቀሌዎቹ ጉዶችና ሰልፈኞች እነ አጅሬ ህወሓትም ጭምር ቁጭ ብለው እንደሚያዩ ተስፋ አደርጋለሁ። አይዟችሁ ጊዜው ስላልደረሰ ነው እንጂ እናንተም መቀሌ አክሱም ሆቴል ተደብቃችሁ አትቀሩም። ቀን ይመጣል። የእግዚአብሔር ቀን ይመጣል። ኢትዮጵያን በዘር አባልታችሁማ እናንተ ሳትበሉ አትቀሩም። ራሱ የትግራይ ህዝብ አውጥቶ ይበላችኋል። ቱ ምን አለ ዘመዴ በሉኝ።
•••
በሱዳን የግፍ ጽዋው ሲሞላ እንዲህ ሆነ። እግዚአብሔር ሲጣላህ አርጩሜ አይቆርጥም። ዱላና ጨፈቃ ክላሽና መትረየስም አይዝም። እግዚአብሔር ሲጣላህ ምክንያት ነው የሚፈልግልህ። ከዚያ የማይነቃነቅ ከሚመስለው ዙፋንህ በማይገመት መንገድ ፈንግሎ ጥሎህ እንደ ናቡከደነጾር እንደከብት ሳር ያስግጥሃል። እንደ ፈርኦን አባብሎ ወድዶ ከነ ሠራዊትህ ቀይ ባህርን በላይህ ላይ ይከድንብሃል። አዎ የግፍ ጽዋው ሲሞላ እግዚአብሔር ምክንያት አበጅቶ በቀላሉ እፍ ብሎ ያጠፋሃል።
•••
የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴን የ40 ዓመት ዘውድ ገርስሶ የጣለው በነዳጅ ላይ የተጨመረ 5 ሳንቲም ነው። እሱ ምክንያት ነው። በእነ መንግሥቱ ነዋይ የመንግሥት ግልበጣ ያልተሳካውን በተማሪ ጩኸት የንጉሠ ነገሥቱ ዘውድ ተገረሰሰ። በጩኸት። ቀጥሎ የመጣው ደርግ ነበር። በአፍሪካ እኔ ነኝ ያለ ጦር ነበረው። የግፍ ጽዋው ሲሞላ ግን ትምህርት ጠል የሆኑ አንድ ዐማራና ሰባት የትግሬ ጎሮምሶችን ደደቢት በረሃ አስገብቶ በሰባራ ሽጉጥ ድራሹን አጠፋው። ደርጎችም እንደ ጢስ በነው ጠፉ። ታሪክም ሆነው ቀሩ።
•••
ትምህርት ጠሏ ወያኔ፣ ፀረ ኢትዮጵያዋ ወያኔ፣ ዘራፊና ከፋፋይዋ ወያኔም ያለፉትን 27 ዓመታት በዘር፣ በሃይማኖት፣ በጎሳ ስታቧድነን ከርማ፣ ሀገር ስትዘርፍ፣ ብሔር ከብሔር ስታባላ ከርማ እንዴት ትጠፋለች ሲባል በመጨረሻም የግፍ ጽዋው ሲሞላ ዐይናችን እያየ በቀን በፀሐይ ድራሽ አባታቸው ጠፍቶ አረፈው። መጀመሪያ ሰማይና ምድርን በወስፌ ካልሰፋሁ ሞቼ እገኛለሁ ባዩን መለስ ዜናዊን አበበ ገላው በተባለ ጋዜጠኛ ጩኸት በመብረቅ የተመታ ያህል አስደንግጦ ገደለው። መለስ እንደ ኢያሪኮ በጩኸት ፈረሰ። አፍንጫው ጥግ በደረሰ ትእቢት፣ ማንአለብኝነት ጉራውን ቸርችሮ ሲደነፋ የነበረን አምባገነን በአንድ ሰው ጩኸት ቅስሙን ሰብሮ አስወገደው። ይሄን ከእግዚአብሔር በቀር ማንም ማድረግ አይችልም።
•••
ከመለስ ሞት በኋላ ህወሓት ኃይለማርያም ደሳለኝን መናጆ አድርጋ አልሞት ባይ ተጋዳይ ሆነች። ብዙ ዐማሮችንና ኦሮሞዎችን፣ ሱማሌዎችና ኮንሶዎችንም በጅምላ ፈጀች። እንቡር እንቡር አለች። ፋኖ በነፍጡ አናፈጣት። ኦሮሞ በዱላው ሆ እያለ መንገድ በመዝጋት ትንፋሿን አሳጠራት። በመኪናና በታንክ የገባችበትን አዲስ አበባን በአውሮፕላን ተሳፍራ ወደ መቀሌ ነካችው።
•••
እነ ስብሃት ነጋ፣ አባይ ፀሐዬም እነሆ ሂልተንና ሸራተን ከናፈቃቸው አንድ ዓመት ተቆጠረ። 
•••
የቀረው እንደ አሰልጣኛቸው፣ እንደመከታቸው፣ የኢትዮጵያው ጠላት እንደ ሱዳኑ አልበሽር ፍርዳቸውን ማግኘት ነው። እሱ ደግሞ ኢህአዴግ የሚባል ነቀርሳ እያለ አይታሰብም። ለዚህ ነው አሁን መቐለ ላይ ተሰብስበው የሚደነፉት። ለዚህ ነው እስከአሁን የብዙዎች ደም በኢትዮጵያ የሚፈሰሰው።
•••
አቢይ አህመድና ለማ መገርሳ ወያኔ ህወሓት ጡጦ አጥብቶ፣ ዳይፐር ቀይሮ ያሳደጋቸው ልጆቹ ናቸው። ሁለቱም የኢትዮጵያን ህዝብ ሲገድሉ ሲያስገድሉ የነበሩ የህወሓት አገልጋዮች ናቸው። አቢይ ስልክ እየጠለፈ ንፁሐንን ሲያስር፣ ሲያኮላሽ ለነበረው ጌታቸው አሰፋ የሚታረዱ ዜጎችን አቅራቢ ነበረ። በሜክአፕ እንዲህ እምር ብሎ ሞዴላ ሞዴል መስሎ ሲሰብከን ደነዘዝን እንጂ አብይም በብዙዎች ውድመት ነገ ተጠያቂ ነው። ለብዙዎች የኦሮሞ ልጆች በኦነግ ስም መታረድ ኃላፊው ኦቦ ለማ መገርሳ ነው። ዛሬ ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው ምናምን ስላለ የንፁሐንን ደም እግዚአብሔር ከእጁ ሳይቀበለው እንደሁ አይቀርም። ወርቅነህ ገበየሁ በ1997 ዓም ምርጫውን ተከትሎ ለፈሰሰው የንጹሐን ደም ዋነኛው ተጠያቂ ሰው ነው። ኃይለማርያም ደሳለኝ በጎንደርና በባህር ዳር ጎዳናዎች በመትረየስና በእስናይፐር ላለቁት ዐማሮች ገና መች ፍርዱን አገኘና?
•••
እናም እነ አብይ አህመድ መንገድ ጠራጊዎች ናቸው። ነገ ይጠየቋታል። አብይ አህመድን ወዳጄ ዲን ዳንኤል ክብረት አጠገቡ ሆኖ ስብከት ስላስጠናው ከመጠየቅ አይድንም። [ ስለ ዳንኤል ክብረት በሌላ ጊዜ በሰፊው እመለስበታለሁ። ለጊዜው ግን እንደ ሸንኮራ እየመጠጡት መሆኑን ሳልነግረው ግን አላልፍም። ሰዎቹ አንተን የፈለጉህ ለመላቸው ነው። ነግሬሃለሁ በጊዜ አምልጥ። ኢንጂነር ስመኘውን አስታውስ። ነግሬሃለሁ ዳኒ። የምትወዱት ምከሩት፣ አልቅሱለትም። አከተመ። ] ዛሬ እንደ ቅጠል ለሚረግፉት ዜጎች ዋነኛው ተጠያቂ አቢይ አህመድና ለማ መገርሳ ናቸው። የጊዜ ጉዳይ እንጂ እግዚአብሔር እንዴት ጉድ እንደሚሠራቸው ዕድሜ ሰጥቶን ለመመልከት ያብቃን።
•••
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ጠላቶችና የኢትዮጵያውያንን ደም በከንቱ ያፈሰሱ፣ እንዲፈስም ያደረጉ ሁሉ ይዋረዱዋታል። እንደ አልበሽር፣ እንደ ጋዳፊ፣ እንደ ሙባረክ ይዋረዷታል። እንደ ሶሪያ፣ እንደ የመን፣ እንደ ሊቢያ በቁማቸው ይፈርሷታል። ይሄ የማይቀር ሃቅ ነው። ክርስቲያኖች በመጽሐፍ ቅዱስ እስላሞች በቁርዓናቸው ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን የነካ ከምድረ ገፅ ይጠፋሉ የሚል ሃቅ መዝግበው አስቀርተዋል። ኢትዮጵያን የነካ ይጠፋል። የጊዜ ጉዳይ ብቻ ነው።
•••
ሻሎም !  ሰላም !
ሚያዝያ 23/2011 ዓም
ከራየን ወንዝ ዳር።
Filed in: Amharic