>
5:13 pm - Saturday April 18, 7587

የዶክተር ነጋሶ ጊዳዳን ህይወት በደራሲ ዳንኤል ተፈራ አንደበት!!! (በዘላለም ግዛው)

የዶክተር ነጋሶ ጊዳዳን ህይወት በደራሲ ዳንኤል ተፈራ አንደበት!!!
በዘላለም ግዛው
የዶክተር ነጋሶ ጊዳዳን ህይወት የሚተርከው “የነጋሶ መንገድ”ና የተለያዩ መጻሕፍት ደራሲው ዳንኤል ተፈራ፤ የዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ሰብዕና በሁለት ዋና ዋና ነገሮች የተገነባ መሆኑን ይናገራል፡፡ ከትንሽ ነገር ተነስተው ውጣ ውረድን በማለፍ ርዕሰ ብሄር የደረሱበትን ስኬት በቀዳሚነት በማንሳት ይጀምርና በኃላፊነት ዘመናቸው አገራቸውን ማገልገላቸውንና ብዙ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ይጠቅሳል፡፡

አስከትሎም፤ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ ተሳትፏቸውን ያነሳል፡፡ እስከ ህይወታቸው ፍጻሜ ነገሮች ሳይጋጩባቸው ማህበራዊ ጉዳዮችን እየከወኑ ከሰው ጋር ያላቸውን ተግባቦት ጠብቀው ያሳለፏቸውን ሁኔታዎች ያስታውሳል፡፡

እንደ እርሱ ማብራሪያ፤ የፖለቲካ አቋማቸው ለረጅም ዓመታት አብሯቸው ኖሯል፡፡ በዋናነት መነሳት የሚገባውም የመሀል ፖለቲካ አራማጅነታቸው ነው፡፡ የመሀል ፖለቲካ ብሄርን መሰረት ያደረገና ለራስ ብሄረሰብ ጠበቃ በመሆን መደራጀት፤ ሌላው ደግሞ ኢትዮጵያዊነት ነው የሚያዋጣው የሚል ስሜት የያዘ ነው፡፡

ሁለቱ የፖለቲካ ዘውጎች በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ አንዱ አሸናፊ ሌላው ተሸናፊ ሆነው ሲታገሉ ከተማሪዎች ንቅናቄ ጀምሮ 50 ዓመታት አልፈዋል፡፡ በእነዚህ ሂደቶች የዶክተር ነጋሶን አካሄድ ስናይ የመሀል ፖለቲካ አራማጅነትን ይከተሉ እንደነበረ እንረዳለን፡፡

አንድ ሰው የወጣበትን ማህበረሰብ ስርዓት፤ ባህልና ወግ ማክበር፤ መቆጨትና መቆርቆር ይችላል የሚለው ደራሲ ዳንኤል፤ ለኢትዮጵያዊነት ግን መዋጮ ሊኖረው ይገባል፤ ሁለቱ አይጣሉም ማስታረቅ ይቻላል የሚል አቋም ነበራቸው ሲል ይጠቁማል፡፡ ኦሮሞነትና ኢትዮጵያዊነት፣ አማራነትና ኢትዮጵያዊነት፣ ጋምቤላነትና ኢትዮጵያዊነት አይጣሉም፣ ሁለቱን ማስታረቅ ይቻላል፣ የመሃል መንገድም አላቸው የሚል ፖለቲካ የሚያራምዱ ነበሩ ሲልም ያስታውሳል፡፡

ዶክተር ነጋሶ ካለፉበት የፖለቲካ መንገድ የአንድነት ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራርነታቸውን እናስታውሳለን የሚለው ደራሲ ዳንኤል፤ አንድነት ተፎካካሪ አገር አቀፍ ፓርቲ ሆኖ በግለሰብ መብት የሚያምን ነበረ ሲል ያስታውሳል፡፡ በፓርቲው ውስጥ አመራር እንደነበሩም ይጠቁማል፡፡

ቀድሞም የኦህዴድ ፓርቲ አመራር እንደነበሩና ፓርቲው የኦሮሞን ህዝብ ብቻ ማዕከል አድርጎ እንደተቋቋመም ይጠቅሳል፡፡ በፓርቲዎቹ አመራርነታቸው በብሄር ውግንና ሳይወሰኑ “ማዋጣት ይቻላል” የሚል አቋም አራማጅ እንደነበሩም ይናገራል፡፡ በኢትዮጵያዊነትም መሄድ ይቻላል የሚል እሳቤ እንዳላቸው ያሳያል፤ ሁለቱም ሳያስቸግራቸው መምራት ችለዋል ባይ ነው፡፡

እኔ እስከማውቀው ድረስ ከኢትዮጵያዊነት ጋር ተጣልተው አያውቁም፤ ኢትዮጵያዊነት መሆን ካለበት ብሄረሰቦች ያላቸውን ባህል፤ ወግና ቋንቋ የማሳደግና የማበልጸግ መብቱና ተቋማዊ ድጋፉ ሊደረግላቸው ይገባል የሚል አመለካከት ነበራቸው የሚለው ደራሲ ዳንኤል፤ “የሃመር ሰው ሆኖ የሀመርን ባህል የሚጠብቅ ከሆነ ጥሩ ኢትዮጵያዊ መሆን ይችላል፡፡ እንዲህ አይነቱ ለአገር ጌጥ ነው የሚሆነው” የሚል አመለካከት አራማጅ ነበሩ ይላል፡፡

ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ተቋማት አስፈላጊ ናቸው፡፡ ከህገ መንግስቱ አርቃቂዎችና እንዲጸድቅ ተሳትፎ ካደረጉ ሰዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ህገ መንግስቱ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አንድ መሰረት ይሆናል የሚል እሳቤ ነበረ፡፡ ግን ህዝቡ የሚመኘውንና የሚፈልገውን አላሳካም፡፡ በሂደቱ ግን የራሳቸውን ሚና ካበረከቱ ሰዎች በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ ይላል፡፡

የብዙሃን ፍላጎት ካለበት ህገ መንግስቱ መሻሻል አለበት የሚል አቋም ያንጸባርቁ ነበር፡፡ ህገ መንግስቱ በሚሻሻልበት ሁኔታም መጽሃፍ በመጻፍ ላይ ነበሩ፡ ፡ በተለያዩ መድረኮችም ይህንን ሃሳብ በማንጸባረቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ መጽሀፉ ከአንድ ዓመት በፊት ተጽፎ ቢጠናቀቅም ለውጡ ነገሮች በፍጥነት እንዲቀያየሩ አድርጓል። በጽሀፉ የተገለጹ አንዳንድ መደምደሚያዎች መስተካከል ይገባቸዋል ሲል ይጠቁማል፡፡

የታጠቁና በውጭ አገር የነበሩ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አገር ውስጥ መግባት አለባቸው የሚል አቋም እንደነበራቸውና አገር ውስጥ መግባት የሚችሉበትን ሁኔታ በመጽሃፋቸው በቅደም ተከተል ዘርዝረው እንደነበረም ምሳሌ በማንሳት ያስረዳል፡፡ ይህና መሰል ጉዳዮች መስተካከል ይኖርባቸዋል፡፡ ቤተሰቦቻቸው እነዚህን ሁኔታዎች ከግምት በማስገባት እንዲስተካከሉ በማድረግ ለኢትዮጵያ ህዝብ ያወጡታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ ይላል፡፡

በህገ መንግስቱ ላይ በርካታ ምሁራንና ልሂቃን የሚያነሱት ብዙ አጨቃጫቂ ነገሮች አሉበት በማለት የሚያስታውሰው ደራሲ ዳንኤል፤ ህገ መንግስቱ የብሄር ብሄረሰቦችን መብት ለማክበር፣ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታን ለማፋጠን እንደመነሻ ጥሩ ነው፡ ፡ መጀመሪያም ይተግበር ቢባልም ግን ትልቅ ፈተና የነበረው ህገ መንግስቱ አለመከበሩ እንደሆነ ያነሱ እንደነበር ያስታውሳል፡፡

የመሰብሰብ፣ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት አይከበሩም ነበር፡፡ ዜጎች በአመለካከታቸውና በአስተያየታቸው ጭቆናና በደል ይደርስባቸዋል የሚል ቅሬታም ያሰሙ እንደነበረ ያስታውሳል፡፡

ከለውጡ በኋላም እየሰፋና እያደገ ያለውን የማህበረሰቡን ፍላጎት መሰረት በማድረግ ህገ መንግስቱ በሚሻሻልባቸው መንገዶች ዙሪያ ጥናት እንደሰሩም ያነሳል፡፡ ከማርቀቅ እስከ ማጽደቅ፤ ቀጥሎም ክፍተቶችን እስከማሻሻል ጥረት ማድረጋቸውንም ነው የሚጠቁመው፤ እርሳቸው በልዩነት ከሚገለጹበት መካከል ርዕሰ ብሄር ደርሰውም ያላቸውን የፖለቲካ ልዩነት ለመግለጽ አለመገደባቸው ነው የሚለው ደራሲ ዳንኤል፤ በስልጣን ዘመናቸው ቁስ ለመሰብሰብ የሚጓጉ አልነበሩም ይላል፡ ፡

ጥቅማቸው እንደ ርዕሰ ብሄር ሳይጠበቅላቸው መኖራቸውን፣ ህክምና እስከማጣት፣ መኖሪያ ቤት እስከመከልከል የደረሰ ሸርና ደባ እንደተፈጸመባቸውም ይገልጻል፡፡

ያመኑበትን ዓላማ ማስቀደም የዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ብቸኛ መገለጫ ነው፡፡ ንጹህ፣ ቀና እና አስተዋይ ሰው ነበሩ፡፡ ይህ ለብዙ ፖለቲከኞች ይከብዳል፡፡ እርሳቸው ከፍ ብለው ኖረዋል ቀጥለውም እንደማንኛውም ሰው ሆነው ኖረዋል፡፡ ከፍታውንም ዝቅታውንም አይተው ያለፉ ናቸው በማለት ከህይወት ገጻቸው አካፍሏል፡፡

በ76 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ዶክተር ነጋሶ የሁለት ሴትና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነበሩ፡፡

Filed in: Amharic