>

“አማራ ነው! አማራ ነው!”እያለ ጮኸ!  (ቅዱስ መሀሉ)

“አማራ ነው! አማራ ነው!”እያለ ጮኸ! 
ቅዱስ መሀሉ
በ1991ዓ/ም ለተወሰኑ ቀናት ወደ ምስራቅ ሃረርጌ ሂርና ሂጄ ነበር። የመጀመሪያ ቀን ከመኪና ወርጄ አንድ ዛፍ ስር ቆሜ ሳለ አንድ ሰው ገንዘብ ለመነኝ። ምን እንደሚፈልግ ዘመዴን ወደመኪናው ዞሬ ስጠይቀው “ረቢሴ ያኬኒ” አለው። ሄደ። ምን ማለት እንደሆንም ነገረኝ። በከተማው ትናንትም ሆነ ዛሬ ‘ትልቅ’ የሚባለው ሰው (በርግጥም ነው!) ወደቤቱ ጋብዞን ለመሄድ መልክተኛ ልኮ እየጠበቅነው ነው። እሱ እስኪደርስ ወዲያና ወዲህ እያልኩ አካባቢውን እቃናለሁ።አሁንም የሆነ ሰውየ ሳንቲም ጠየቀኝ። ኪሴ ውስጥ ሳንቲም እየፈለግሁ ሳለ የሆነ ሰው ከርቀት ሆኖ እየጮኸ የሆነ ነገር አለ። ዞሬ አየሁት። የሚጮኸው ለሚለምነኝ ልጅ ነው። “አማራ ነው፤አማራ ነው፤አማራ ነው።” አለ። ዘመዴን ጠየቅሁት። እዚያ ሆኖ አማራ መሆኔን እንዴት አወቀ። ከማንም ጋር ደግሞ እያወራሁ አልነበረም አልኩት። አንገቴ ላይ ያለውን ማተብ አሳየኝ። እዚህ አካባቢ አማራ ማለት ክርስቲያን ነው።”ኦሮሞም ሆነ ትግሬ ወይም ጉራጌ ብትሆን አንገትህ ላይ ማተብ እስካለ ድረስ አንተ ለነሱ አማራ ነህ። አንዳንዴ ግጭት ሲከሰትም አንተ እና እኔ እንደምናስበው አይመርጡም። አንገቱ ላይ ገመድ ያለው ሁሉ ለአማራ ነው። ሲገድሉም እንደዚያው ነው። እኛ እንኳ አብረን ኖረናል እንተዋወቃለን።” አለኝ። ፈራኋቸው።
ፕሮፌሰር መስፍን በጥናት ደረስኩበት ብለው “አማራ የለም፤አማራ ማለት ክርስቲያን ማለት ነው።” ያሉት እንግዲህ ይሄን ነው። ይህ ደግሞ በውስን አካባቢ እና በአንድ ሃይፖቴሲስ መነሻ ወደ ውስን ግብ የሚያደርስ እንጅ “አማራ የለም” ብሎ ከአካዳሚክ ተቋሙ እና የአካዳሚክ ቋንቋ ውጭ መገለጽ የማይችል ጥናት ነው። የፕሮፌሰር መስፍን ጥናት ለፐብሊክ የተደረገ አልነበረም። ለፐብሊክ ሲገለጽም ቋንቋው እና አጠቃቀሙ ፐብሊኩ ሊረዳው በሚችል ቋንቋ ወይም ለፖለቲካ መሳሪያ ሊውል በሚችል መንገድ መሆን አልነበረበትም። ስህተቱም ያን ማድረግ እንጅ ጥናቱ አይደለም። የጥናቱ ውጤት እኮ ይህ እኔ ያጋጠመኝ እውነታ ነው። አርሲ ውስጥ እኮ ዛሬም ኦሮሞዎቹ እርስ በርስ እስላሙን “ጋላ” ክርስቲያኑን “አማራ” እያሉ ነው የሚጠሩት። ሁሉም ግን ኦሮሞዎች ናቸው። ይህም አባባል ውስን ቦታ እና አካባቢ ያለን ልማድ የሚገልጥ እንጅ “ኦሮሞ ማለት እስላም ነው።” የሚል የጅምላ ስም አይደለም።  አማራ ማለት ክርስቲያን ማለት ነው እንደሚለው ሁሉ ኦሮሞ ማለትም  እስላም ነው ማለት አይደለም። የሆነ ሆኖ ፕሮ መስፍን የደረሱበት ጥናት እዚህ እዚህ ቦታ እና አካባቢ “አማራ ማለት ክርስቲያን ነው።” እንጅ “አማራ የለም” አይልም።
የእሳቸው የምርምር ጥናት አካዳሚክ ነው። ስለዚህ በየትም ሃገር አካዳሚክ ጥናት ለፖለቲካ ዓላማ ወይም ኢላማ ተደርጎ በትምህርት ተቋም ውስጥ አይሰራም። ከተሰራም ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም። ይህን ለማረጋገጥ ሌላ ምስክር አልጠራም። የራሴን ቴሲስ ዲፌንስ ሳደርግ ዓላማውን ከጻፍኩት ውጭ የፖለቲካም ግብ እንዳለው በመጥቀሴ በጀርመን የሚገኝ አንድ ዩኒቨርስቲ አካዳሚክ ቦርድ ቴሲሱን ውድቅ በማድረግ እና ቀድሞ የተሰጠኝን 98ከመቶ ውጤት ሰርዞ ድጋሚ አዲስ ቴሲስ በሌላ ከኢትዮጵያ ጋር በማይገናኝ ርእስ(በአሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት የንግድ ግንኙነት እና ተያያዥ ጉዳዮች) ላይ እንድጽፍ አድርጎኛል። አስቡት!
Filed in: Amharic