>

የአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ ሚያዚያ 29 2011 ያደረገውን ጠቅላላ ጉባኤ አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ 


የአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ ሚያዚያ 29 2011 ያደረገውን ጠቅላላ ጉባኤ አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ
 
ሚያዚያ 29 2011
አርበኞች ግንቦት 7 ሰላማዊና ህጋዊ ትግል ለመጀመር ከወሰነ ጀመሮ ከሁሉም ነገር ቅድሚያ ሰጥቶ የተንቀሳቀሰው በህዝብና በሃገር ላይ ያሰፈሰፈውን አደጋ ህዝብን በማሳተፍ መቋቋም የሚችል አንድ ጠንካራ ሃገራዊ ፓርቲ በመመስረቱ ተግባር ላይ ነው። ንቅናቄው በማህበራዊ ፊትህና በዜግነት ፖለቲካ ላይ ጽኑ እምነት ካላቸው ድርጅቶች ጋር ተነጋግሮ ለአንድ ትልቅ ሃገራዊ ፓርቲ መመስረት ስምምነት ላይ የደረሰው ሰላማዊና ህጋዊ ትግል ለማድረግ ወስኖ ወደ ሃገር ቤት በገባ በመጀመሪያው ወር ውስጥ ነው። በወቅቱ ከንቅናቄው ጋር ሌሎች ድርጅቶች ያደረጉት ስምምነት አዲሱ ፓርቲ በሚያዚያ ወር ምስረታው ተጠናቆ በፍጥነት እንቅስቃሴ እንዲጀምር ነበር።  ይህን ትልቅና አጣዳፊ አጀንዳና ሌሎች ተዛማጅነት ያላቸውን ጉዳዮች ላይ ውሳኔ ለመስጠት አግ7 ሚያዚያ 29 ቀን በአዲስ አበባ ከተማ ከመላው ኢትዮጵያና ከሌሎች የአለማችን ክፍሎች የተሰበሰቡ አባላቱ በተገኙበት ጠቅላላ ጉባኤ በማድርግ የሚከተሉትን ውሳኔዎችን በማሳለፍ ጉባኤው በስኬት ተጠናቋል።
1. ንቅናቄው ሰላማዊና ህጋዊ ትግል ለማድረግ ወደ ሃገር ቤት ከገባበት ጊዜ ጀመሮ ራሱን ወደ ፓርቲነት ለመቀየር ያከናወናቸውን ተግባራት በመገመገም፣  እራሱን ወደ ላቀ ሃገራዊ ፓርቲ ለመቀየር ከሌሎች ድርጅቶች ጋር የገባውን ስምምነት ተግባራዊ ለማድረግ እንዲችል፣ ራሱን አክስሞ በግንቦት 1 እና 2 በተጠራው በሰባት ድርጅቶች ውህድት የሚፈጠረው አዲስ ፓርቲ አካል እንዲሆን ወሳኔ አሳለፏል። ውሳኔው በ 243 ድጋፍ፣ በ18 ተቃውሞና በ14 ድመጸ ተአቅቦ አልፏል።
2. ከኤርትራ በረሃ የተመልሱ የሰራዊትና ከእስር የተፈቱ  አባልቱን፣  እንዲሁም በሃገር ውስጥ ነፍጥ አንስተው ሲታገሉ የነበሩ ታጋዮቹን የመልሶ ማቋቋሙን ስራ አዲስ የሚመሰረተው ፓርቲ በሃላፊነት እንደሚረከበው፣  ይህም ወሳኔ የአዲሱ ፓርቲ መስራች ድርጅቶች መሪዎች ቀድመው የተስማሙበት ጉዳይ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ይህንን የመልሶ ማቋቋም ስራ እስካሁን በሃላፊነት ሲከታተል የነበረው የአግ7 ጸሃፊ በሃላፊነት እንዲከታተሉ የቀረበውን የወሳኔ ሃስብ በሙሉ ድምጽ ጉባኤው አሳልፎታል። ከዚህ ውሳኔ ጋር ጉባኤው ለሰራዊቱ አባላትና ሰራዊቱ ትልእኮ ሰጥቷቸው በጠላት እጅ ወደቀው በእስር ሲማቅቁ ለነበሩ አባላት የተለያዩ ፍላጎቶች ወጪ መሸፈኛ እንዲሆን 3000000 ሶሰት ሚሊዮን ብር በአደራ እንዲቀመጥ ወስኗል። ይህ ገንዝብ የመልሶ ማቋቋም ኮሚሽን ለማይሸፍናቸው አላባሳትን ለመሳሰሉ ነገሮች ወጪ የሚሆን ይሆናል።
3. በኤርትራ ምድር የተሰው 65 የቀድሞ የአርበኞች ግንባር አባላትና ግንባሩ ከግንቦት 7 ጋር ከተዋሃደ ቦኋላ በአደጋና በህመም የተሰው 3 አባልትን በድምሩ የ68 ታጋዮችን አጽም ከኤርትራ አጓጉዞ፣ በሃገር ወስጥ ለግዳጅ ተሰማርተው ከተሰው የስራዊት አባላት አጽም ጋር በአንድ ቦታ እንዲያርፍና በቦታው የመታሰቢያ ሃውልት ለመስራት የሚሆን ወጪ  1000000 አንድ ሚሊዩን ብር በአደራ እንዲቀመጥ ወስኗል።
4. ህጻናት ልጆቻቸውንና ተጧሪ ቤተሰቦቻቸውን ትተው ትግሉን ከተቀላቀሉ ቦኋላ ለተሰው የታጋዮች ቤተሰብ ለማገዝ 500000 ብር በአደራ ተያዞ በአስቸኳይ እንዲከፋፈል ወስኗል።
5. የንቅናቄውን ሃብትና ንብረት በሚመልከት፣
5.1. ጉባኤ  በአደራና እዲያዝ ከወሰነው ገንዝብ የሚተርፈው የንቅናቄው ገንዘብ በሙሉ አዲስ ለሚመሰረተው ፓርቲ እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል።
5.2. የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥንን (ኢሳት) በተመለከተ
• የኢትዮጵያ ህዝብ በወያኔ አፋኝ ስርአት የሚደርስበትን የመረጃ አፈና ለመበጣጠስና በኢትዮጵያ ወስጥ ለዴሞክራሲ የሚደረገውን ትግል ለማገዝ የግንቦት ንቅናቄ ኢሳትን ማቋቋሙን ለመጀመሪያ ጊዜ በጉባኤና በአደባባይ ግልጽ በማድረግ፣ የኢሳት ባለቤትነት ጉዳይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት እንዲያገኝ በማሰብ፣ ኢሳት ከተመሰረተ ጀምሮ አብዛኛውን የገንዘብ፣ የመረጃና የቴክኒክ ድጋፍ ሲያገኝ የነበረው ከህዝብ መሆንን በመገንዘብ፣ ሲያገለግልም የነበረው የኢትዮጵያ ህዝብ አይናና ጆሮ ሆኖ ስለነበር፣ የወደፊቱ የሚሻሻለው የሃገሪቱ የሚድያ ህግ በሚፈቅደው አዲስ አሰራር መሰረት የኢሳት ባላቤት የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲሆን፣ ተቋሙም አትራፊ ያልሆነ ማህበራዊ ድርጅት ሆኖ እንዲመዘገብ፤
• ኢሳት ሲያገለግላቸው የኖሩትን የሃገሪቱን ዜጎች በሙሉ የሚወክል ስፋትና ስብጥር ያለው ቦርድና የማህበር አባላት ያሉት ሃገራዊ ተቋም ሆኖ በኢትዮጵያ ውስጥ እንዲደራጅ፣
• ይህን የሽግግር ስራ በወቅቱ ኢሳትን የሚያስተዳድሩ የቦርድ አባላት ከግቡ እንዲያደርሱት፣
• ይህን ተቋም አዲሱ ፓርቲ በባለቤትነት የሚወረሰው ተቋም ስለማይሆን፣ ንቅናቄው ሲፈርስ የጉቤውን ውሳኔ በባለቤትነትና በበላይነት የሚያስፈጽም አካል ክፍተት እንዳይኖረው በማሰብ፣ አሁን ያለው የኢሳት ቦርድ የጀመረውን የማሸጋገር ስራ ተከታትሎ የሚያስፈጽም ኮሚቴ መኖር አስፈላጊነቱን በማመን፣ አዲሱ ፓርቲም  በማያውቀው ጉዳይ ሃላፊነት ውስጥ ገብቶ ችግር ላይ እንዳይወድቅ በመስጋት፣ የሚቋቋመው ኮሚቴ አባላት ኢሳትን ከምስረታው ጀምሮ የሚያውቁት፣  ኢሳትን ነጻና ገለልተኛ ተቋም ለማድርግ የሚያስችል አቅም ብቃትና የመርህ ጥብቅነት ያላቸው  ሊሆኑ ይገባል በሚል እሳቤ፣ አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን፣ አቶ መአዛህ ታፈሰን፣ አቶ ሲሳይ አጌናንና አቶ ፋሲል የኔአለምን የኮሚቴው አባላት ሆነው እንዲሰሩ ጉባኤው በሙሉ ድምጽ ወስኗል።
5.3. ነጻነት አሳታሚዎችን በተመለከተ
• ነጻነት አሳታሚ የራሱ እሴት የሌለው፣ ስራው መጽሃፍ በማሳተም ለንቅናቄው የገንዘብ ግቢ ማሰባሰብ መሆኑን ግልጽ በማድረግ፣ ነጻነት አሳታሚዎች ሙሉ በሙሉ የአዲሱ ፓርቲ ንብረት ሆኖ እንዲተላለፍ፣
• በወቅቱ ነጻነት አሳታሚዎች የጀመራቸውን ስራዎች ማስፈጸሚያ የሚሆን ገንዘብ ሁሌም ሲደረግ እንደነበረው በንቅናቄው እጅ ካለው ገንዝብ እንዲመደብለት፣
• ከእነዚህ ስራዎች የሚሰበስበውን ማናቸውንም ገቢ ተጠያቂነትና ግለጽነት ባላው መንገድ ለአዲሱ ፓርቲ ገቢ እንዲያደርግ፣
• የነጻነትን አሳታሚዎች ልምድና ኤክስፕርቲዝ በመጠቀም አዲሱ ፓርቲ አሳታሚ ብቻ ሳይሆን ራሱ የህትመት ስራ ውሰጥ መሳተፉ ከፍተኛ ድርጅታዊ ጥቅም እንደሚኖረው በማሳሰብ፣ ከላይ የቀረቡትን ከነጻነት አሳታሚ ድርጅት ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የውሳኔ ሃሳቦች ጉባኤው በሙሉ ድምጽ አሳልፏል።
በመጨረሻም ጉባኤው፣ “ሰው በጠፋባት ወቅት ሰው ሆነው ለተገኙ ሃገር ወዳድ የንቅንቄው አባላትና ደጋፊዎች በንቅናቄው ስም ያዘጋጀውን የእውቅና ሰነድ ይፋ በማድረግና ከአግ7 ጋር በመሆን በአዲስ አበባ ከተማ ከግ 1 እስከ ግንቦት 2 በሚደረገው ሃገራዊ ስብሰባ ላይ አዲስ ፓርቲ ለመመሰረት ራሳቸውን ካከስሙ የቀድሞ ስደስት ድርጅቶች ሊቃነመናብርት የእንኳን ደስ ያላቹሁ መልእክት በማዳመጥ በከፍተኛ ስሜትና ስኬት ተጠናቋል።
ዘላለማዊ ክብር፣ ለዜጎች ነጻነት ለወደቁ ሰማእታቶቻችን
ኢትዮጵያ በጀግኞች ልጆቿ ታፈራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!  
የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ የመጨረሻው ጠቅላላ ጉባኤ
አዲስ አበባ
Filed in: Amharic