>

"  ሰ   ው   የ   ው  "   !   ?   !   ? (አሰፋ ሃይሉ)

”  ሰ   ው   የ   ው  ”   !   ?   !   ?
አሰፋ ሃይሉ
 ስላሳሰቡኝ የሰውየው ጉዳዮች በጥቂቱ . . . !
በድኅረ “ሪፎርሟ” ኢትዮጵያ ውስጥ – ከእርሱ በቀር – ከሁሉም የህዝብ መነጋገሪያ አጀንዳዎች በላይ ስሙ ገንኖ መነጋገሪያ የሆነ ማንም የለም። የቀድሞ የብሔራዊ ደኅንነት ዋና ዳይሬክተር – አይተ ጌ ታ ቸ ው  ፡  አ ሰ ፋ  ።
በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የግጭትና መፈናቀል ዜናዎች በተከታታይ ይወጣሉ። ይደመጣሉ። መሣሪያ ያማዘዙ የመከላከያ ሠራዊትና የአሸማቂ ኃይሎች ውጊያ ትኩስ ዜና ሆኖ ተደምጧል። የመፈናቀል፣ የዝርፊያ፣ የሞትም ሆነ የመቁሰል፣ የሰው ሠራሽም ይሁን የተፈጥሮ አደጋ – ሁሉም ከህወኀት የመሪነት መፈናቀል ክስተት በኋላ – በኢትዮጵያ ሠማይ ሥር ሆነዋል። ተከስተዋል። ነገር ግን ማናቸውም ዜናዎች የዚህን ሰው ያህል የአነጋጋሪነት አቅም ኖሯቸው አልታዩም።
ስለሆነም ነገሩን ሎጂካል ሆነን (በተጠየቅ አመክንዮ) ካሰብነው – እንደ ዜጋ – ራሳችንን – አንዳንድ ቁልፍ ጥያቄዎችን ለመጠየቅ እንገደዳለን፦
1ኛ/ ይህን ሰው ከሁሉም የቀድሞ የሀገሪቱ አድራጊ-ፈጣሪ ቱባ ባለሥልጣናት ሁሉ በተለየ አኳኋን፣ አሁንም ከነሥልጣናቸው፣ ከነጠብመንጃቸውና ከነተፅዕኗቸው ጋር በክብር ከሚገኙት እልፍ የህወኀትም ሆነ የሀገሪቱ የሲቪል፣ የመከላከያና የደኅንነት ሹማምንቶች ሁሉ መሐል በተናጠል ተለይቶ – የዚህ ሰው እጅ መያዝና አለመያዝ አጀንዳ – ከሀገሪቱ ሌሎች አሳሳቢ አጀንዳዎች ሁሉ በላይ ልቆ – ቁጥር-አንድ የሀገሪቱ ተፈላጊ ሰው ያደረገው አንዳች ከሁሉም የተለየ እጅግ ታላቅ ኃጥያት ወይም ምክንያት ኖሮበት ተገኝቶ ነው ማለት ነው?? – መሆን አለበት። There must be sth behind all this!
2ኛ/ ምናልባት . . . ይህ ሰው በቅድመ-ሪፎርሟ ህወኀታዊት-ኢህአዴጋዊት ኢትዮጵያ የ27 ዓመታት ዘመነ-ሥልጣን ወቅት (ወይም ቢያንስ… ከቀድሞው የህወኀት የደኅንነት ሹም ክንፈ ሞት ማግስት ባሉት 17 ዓመታት ወቅት) በሀገሪቱ በሞላ ለተፈፀሙት የግፍ ግድያዎች፣ እስሮች፣ ስቃዮች፣ ድብደባዎች፣ ማንገላታቶች፣ ዝርፊያዎች፣ አፈናዎችና ሌሎች ለቁጥር የሚያታክቱ ሰብዓዊ በደሎችና የግፍ ተግባራት ሁሉ – ለእነዚያ ግፎች ሁሉ – ተጠያቂው – ይሄው አንድ እና አንድ ግለሰብ ብቻ ነው ማለት ነው?? ሌሎቹ የሥርዓቱ ትዕዛዝ ሰጪዎችስ፣ መሪዎችስ፣ አቀናባሪዎችስ፣ አውራጆች፣ ተኳሾችና አስተኳሾችስ??? – በዚህ አንድ ኀጥዕ ሰው መያዝ ወይም ውንጀላ የተነሳ – ከእርሱ ጋር በተመሣሣይ የታሪክ ምዕራፍ ከሠሯቸው የክፋት ሥራዎች ሁሉ እንደ ጲላጦስ እጃቸውን ታጥበው ከደሙ-ንፁህ ሆነው በብፅዕና እንዲወጡ ያስችላቸዋል ማለት ነው?? – I don’t think so!
3ኛ/ ስለዚህ ይሄ ሰውዬ (“ሰውየው!”) በድኅረ-ኢህዴጋዊ-“ሪፎርሙ” ዘመን – ቁጥር-አንድ የሀገሪቱ ተፈላጊ ሰው፣ እና (ቢያንስ) የሀገሪቱ ቁጥር-አንድ አጓጊ መነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ የወጣበት አንዳች የተለየ ከሰውየው ላይ የሚፈለግ ነገር አለ ማለት ነው?? – I think so!
4ኛ/ ሰውየው እየታደነ ያለበት ቁልፉ ምክንያት – እና እርሱን ያስመሸገው የህወኀት ወግ-አጥባቂ አመራርና ሠራዊት አባላት በተደጋጋሚ እንደታየው እርሱን ከምሰጥ “ገመድ-ባንገቴ!” ብለው በደጀንነት የቆሙት – የሰውየው ፈላጊዎችም ሆነ የሰውየው ደባቂዎች – ሁለቱም – ሥርዓቱ ከፈጠራቸው አድራጊ-ፈጣሪ ሰዎች ሁሉ መሐል ለይተው ይህን ሰው እንደ ዕንቁ የቆጠሩበት ምክንያት – ምናልባት ሰውየው ፈፀማቸው በሚባሉ ድርጊቶች የተነሣ ሳይሆን – ላለፉት 17 ዓመታት በሰውየው እጅ ውስጥ በገቡ እና አሁንም ሰውየው ተሸክሟቸው በሚገኙት የሥርዓቱ ባለሥልጣናትና ምንደኞች ጥብቅ ሚስጥሮች የተነሣ ይሆን???
/ማለትም… ሰውየው በሥርዓቱ ውስጥ የፈፀማቸውን የፈፀመው ከመላው የሥርዓቱ ቁንጮዎችና መናጆዎች ጋር እጅና ጓንት ሆኖ ስለነበር ብቻውን ይሄን ያየነውን ያክል የእርሱ መያዝ በተለየ pivotal agendae ተደርጎ መነጋገሪያ አይሆንም ነበር የሚል ግምት አለኝ። ከሆነ ደግሞ ሰውየው እየተፈለገም፣ እየተከለለም ያለው – ከሌሎች ጋር ሆኖ ከሠራው ሥራ ይበልጡን – ሰውየው በግሉ በተሸከማቸው የሀገሪቱ (እና/ወይም የባለሥልጣናቱ) ዕንቁ መረጃዎች የተነሳ መሆን አለበት።/
5ኛ/ ይህ ከሆነ ደግሞ ዕንቁውን (ወይም እንቁላሉን) የምትጥለው ዶሮ በዝንጋኤና ሰዶ-ማሳደድ – አሊያም ዕንቁላሎቹን በመፍራት – በአራጆች እጅ እንዳትገባ – ታላቅ ሥጋት ሊያድርብን ይገባል።
/በእርግጥ – ይሄ ጉዳይ – በዋሺንግተን ወይ በሞስኮ አሊያም በለንደን ተከስቶ ቢሆን ኖሮ… አንድ በህይወት ያለ የቀድሞ የስለላ (የደኅንነት) ዳይሬክተራቸው – አድራሻውን ሳያሳውቅ ለ24 ሰዓታት ከተሰወረ – ጉዳዩ በሚመለከታቸው የሀገሪቱ የደኅንነት፣ የፖሊስና የሲቪል ተቋማት አማካይነት እጅግ-አስቸኳይ እና እጅግ-መጠነሰፊ ፍለጋ (search) እንዲካሄድ ይደረጋል። ያ ምላሽ ካላስገኘ ለወዳጅ ሀገራት የመረጃ ደኅንነት ተቋማት ሁሉ እና እንደ ኢንተርፖል ላሉ ዓለማቀፍ ተቋማት መረጃው ተሰራጭቶ አድራሻው ወይም መቼቱና ደህንነቱ እንዲታወቅ ፈጣን ጥረት ይደረጋል።
/ምክንያቱም ሰውየው የተሸከመው የሀገሪቱን አንኳር ምስጢር ነውና። ያ መረጃ ጠላት እጅ ቢገባ የሀገሪቱ የደኅንነትና የመንግሥት መዋቅር፣ ሰነዶች፣ የምስጢር ኮዶች፣ የመረጃ ምንጮች፣ እና ሌሎች ሀገሪቱ በጥልቅ ካዝና እንዲቀበሩላት የምትፈልጋቸው መረጃዎቿ ሁሉ ለአደባባይ ተስጣጥተው ለአላፊ አግዳሚው እርቃኗን ቀረች ማለት ስለሚሆን ነው።
/ለዚሁም ነው – ሰውዬአቸውን በአስቸኳይ ካለበት ፈልገው፣ አፈላልገው በእግር በፈረስ የሚያገኙት። በነገራችን ላይ – እናክልበት ከተባለም – ብዙው ሰው እንደሚያውቀው – በብዙ ሀገራት ዘንድ – የሀገር ደኅንነት ሹማምንት ሌላ ቀርቶ በወንጀል ተጠርጥረው ወይም በተከፈተባቸው ምርመራ ሳቢያ ከአክቲቭ ዲዩቲ ተገልለው በቁም እስር እንዲውሉ ሲደረጉም ሆነ ተፈርዶባቸው ወደልዩ እስር ጣቢያዎች ሲላኩ – አንዳንዶቹም ከፍርዳቸውም በኋላ – እስከ ህልፈተ ህይወታቸው በመንግሥት የፀጥታ መሥሪያቤት ከፍተኛ ጥበቃ እየደተረገላቸው የሚቆዩትም በዚሁ የቁልፍ ሀገራዊ  መረጃ ቋትነታቸው የተነሳ ነው።/
6ኛ/ ስለዚህ በመጨረሻ እንደ አንድ ለሀገር ተቆርቋሪ ዜጋ ሁለት ለሀገሬ ሰው ማስተላለፍ የምፈልገጋቸው ዋነኛ መልዕክቶች አሉኝ፦
@ አንደኛ ነገር.. ከላይ በጠቀስኳቸው አመክንዮአዊ ምክንያቶች የኢትዮጵያ መንግሥት “ሰውየውን” ያለበትን ለማመላከትና ለማግኘት ከእንግዲህ ወዲያ ምንም ጊዜ ማባከንና ቸልተኝነት ማሳየት እንደሌለበት ግላዊ ምክሬን ለመለገስ፤
@ሁለተኛ ደግሞ… የሰውየው መያዝ (መሰጠት) ጉዳይ ሀገርን ጦር የሚያማዝዝ አሊያም አይቀሬ ክስተት የመሆኑን ቁርጥ ከወዲሁ የተገነዘቡ አጥፍቶ-ጠፊ የሸፍጥ ኃይሎች “የፍፃሜው መጀመሪያ” (the beginning of the end!) ነው ከሚል ተጠየቃዊ ድምዳሜ በመነሳት የሰውየውን ህይወት አደጋ ውስጥ ሊጨምሩ የሚችሉበት ዕድል እጅግ ሰፊ በመሆኑ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የሀገሬ አካላት እንደ አንድ ዜጋ ስለ ሰውየው ደኅንነት ያደረብኝን ሥጋት በኃላፊነት ስሜት ለማስተላለፍ።
መልዕክቴ ይኸው ነው። ጨርሼያለሁ። አመሠግናለሁ።
ፈጣሪ ኢትዮጵያን – እና ኢትዮጵያውያንን ሁሉ – በጥበቡ አብዝቶ ይባርክ!
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!
Filed in: Amharic