>

ሞኝን ሁለት ጊዜ እባብ ነደፈው....!!! (ዳንኤል ክብረት)

ሞኝን ሁለት ጊዜ እባብ ነደፈው….!!!
ዳንኤል ክብረት
ዘረኝነት፣ መከፋፈል፣ ጦረኝነት፣ ግጭትና መፈናቀል መቆም የነበረባቸው የዛሬ ሃያ ዓመት ነበር፡፡ ፍቅር፣ ይቅርታና አብሮ መኖር መተከል የነበረባቸውት የዛሬ ሃያ ዓመት ነበር፡፡ አልሆነም፡፡ ግን ዛሬም አልረፈደም!!! 
–‘
‹ዛፍን ለመትከል ምርጡ ጊዜ የዛሬ ሃያ ዓመት ነበር፡፡ ሁለተኛው ምርጥ ጊዜ ደግሞ ዛሬ ነው› ይላሉ ቻይናዎች፡፡ ከሃያ ዓመት በፊት ቢተከል ኖሮ ዛፉ ዛሬ አድጎ ለፍሬ ይበቃ ነበር፡፡ አልሆነም፡፡ ላለፈ ክረምት ቤት አይሠራም፡፡ ዛሬ የዛሬ ሃያ ዓመት የዛፉን ፍሬ ለመብላት ከፈለግንዛፉን ዛሬ እንትከለው፡፡  ዛሬ የምንሰቃይባቸው ዘረኝነት፣ መከፋፈል፣ ጦረኝነት፣ ግጭትና መፈናቀል መቆም የነበረባቸው የዛሬ ሃያ ዓመት ነበር፡፡ ፍቅር፣ ይቅርታና አብሮ መኖር መተከል የነበረባቸውት የዛሬ ሃያ ዓመት ነበር፡፡ አልሆነም፡፡ በዛፎቹ ፋንታ ሰርዶ በቅሎ እጅ ከወርች አሥሮናል፡፡ ዋርካ በሌለበት እንቧጮ ዛፍ ሆኖ መከራ እናያለን፡፡ ‹መተውም መዝራት ነው› ይላል ያገሬ ገበሬ፡፡ አንድን መሬት አልዘራንበትም ማለት የፈለገ ይብቀልበት ብለን ትተነዋል ማለታችን ነው፡፡ እኛም መዝራት የነበረብንን ሳንዘራ፣ መትከል የነበረብንንም ሳንተክል ሀገሩን ወፍ እንዲዘራበት ተውነው፡፡ በምትኩ ‹ጸራዊ በሌሊት መጥቶ እንክርዳዱን ዘርቶ ሄደ፡፡›
ዛፉን መትከል የነበረብን የመጀመሪያው ምርጥ ጊዜ አልፏል፡፡ አሁን ትካዜው፣ ቁዘማውና ንዴቱ አይጠቅምም፤ ጨጓራና ራስ ከመላጥ ውጭ፡፡ ሽሚያው መሆን ያለበት ሁለተኛው ምርጥ ጊዜ እንዳያልፍ ነው፡፡ እርሱም አሁን ነው፡፡ ጉንዳን መከር እንዲመጣ ስትጸልይ ያያት ዝንጀሮ ‹መከር ቢደርስ ለሰው እንጂ ለአንቺ ምን ያደርግልሻል?› ቢላት ‹ሞኝ፤ ሰውም ያጭዳል ጉንዳንም ይሰበስባል፤ ዋናው መከሩ ይምጣ› አለቺው ይባላል፡፡ ዋናው መከር መምጣቱ ነው፡፡ የምንፈልገውን ማድረግ የኛ ድርሻ ነው፡፡ ለሀገርና ለወገን እንዲጠቅም አድርጎ መኸሩን መሰብሰብ የኛ ፋንታ ነው፡፡ እየደጋገሙ መሸወድና እየደጋገሙ ማልቀስ አመላችን ሆኗል፡፡ ትናንትን ከመርገም እንውጣና የተሻለ ዛሬና የሚናፈቅ ነገ እንገንባ፡፡ ትናንትን በመውቀስ ትናንትን ማሸነፍ አይቻልም፡፡ ትናንትን ለማሸነፍ የተሻለው ብልሃት ዛሬን በተሻለ መሥራት ነው፡፡ ‹ አንድ ጊዜ ሳያይ፣ ሁለተኛ ሲያሳይ› ይባላል፡፡
Filed in: Amharic